Print this page
Saturday, 14 March 2020 12:09

“ጤናማነት ለራስ” የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማንቂያ ንቅናቄ ተጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  “ያገባናል” የበጐ አድራጐት ድርጅት ከ“ሻዴም ሚዲያና ኮሙኒኬሽን” ጋር በመተባበር በ46ቱም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የሚተገበር “ጤናማነት ለራስ” የተሰኘ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የማንቂያ ንቅናቄ ሀሙስ መጋቢት 3 ቀን 2012 ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል፡፡
በይፋ በተጀመረበት ሰዓት የ ያገባኛል በጐ አድራጐት ማህበር መስራችና ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መስታወት ስሜ እና የሻዴም ሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ሄኖክ ይርጋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ወጣት ለምክንያት እንጂ ለስሜት አይሞትም” በሚል መርህ በየዩኒቨርስቲው በመንቀሳቀስ ወጣቶች በትምህርት ላይ እያሉ ማድረግ ስለሚገባቸው የጤና የትምህርትና የተግባቦት ሁኔታ እንዲሁም ተመርቀው ሲወጡ ስለሚገጥሟቸው ፈርጀ ብዙ የህይወት መስመሮች በማስተማርና በማንቃት በአካልም ሆነ በስነ ልቦና ጤናማ የትምህርት ቆይታ እንዲኖራቸው ድጋፍ ያደርጋል፡፡
የተለያዩ አነቃቂ ንግግር አድራጊዎችን አርቲስቶችን በሱስ ውስጥ ኖረው ነፃ የወጡ ባለተሞክሮዎችን በየዩኒቨርስቲው ይዘው በመጓዝ ተሞክሮና ልምድ እንደሚያካፍሉም ዋና ሥራ አስኪያጆቹ ተናግረዋል፡፡
“ያገባናል የበጐ አድራጐት ማህበር በ2004 የተቋቋመ ሲሆን ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ በተለይ ወጣቱን ማዕከል በማድረግ በርካታ ስራዎችን የሰራ ሲሆን ባለፈው ዓመት በወላይታ ሶዶ፣ ጅግጅጋ፣ ጋምቤላ፣ ኮተቤ ሜትሮፖሊታንና በአርሲ ዩኒቨርስቲዎች በመጓዝ ተማሪዎች ከግጭትና ከብጥብጥ ራሳቸውን አቅበው የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲወጡ በማስተማር በኩል ያስመዘገቡትን አመርቂ ውጤት የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ለታዳሚ አቅርበዋል፡፡
 “ጤናማነት ለራስ” የተሰኘውና ትላንት በይፋ የተጀመረው ይህ እንቅስቃሴ ከከፍተኛ ትምህርትና ሳይንስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሚተገበርና በሶስት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡  

Read 2968 times
Administrator

Latest from Administrator