Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 07 July 2012 09:16

“የኦርኬስትራ መሪ ባንዱን ሲመራ ጀርባውን ለህዝቡ መስጠት ግዴታው ነው!” (የዚምባቤዎች ተረት)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ ሰው ለአንድ ወዳጁ እንዲህ ይለዋል፡-

“ለማንም እንዳትነግር፤ አንድ ምስጥር እነግርሃለሁ”

“ለማንም አልነግርም፡፡ ያንተ ምስጥር’ኮ የኔ ሚስጥር ነው” ይላል ወዳጁ፡፡

“ማልልኝ” ይለዋል፡፡

እሺ ብሎ ይምላል ወዳጅ፡፡

ከዚያም ጓደኝየው፤

“የአለቃችንን ቤት ያቃጠልኩት እኔ ነኝ! ግን ማንም አያውቅም!”

“ለምን አቃጠልከው?”

“የሚሰሩትን ግፍ አጥተኸው ነው? ዋጋቸውን ያግኙ ብዬ ልበቀላቸው ነው ቤታቸውን ያጋየሁላቸው! ካሰብኩት ቆይቻለሁ፡፡ ከርሜ ከርሜ ዘንድሮ ጨከንኩ! ግን አደራ ለማንም እንዳትነግርብኝ!” ይላል፡፡

ወዳጁም፤ “እንዲህ ያለ የሚያሳቅልህን አይነት ሚስጥርማ ትንፍሽ አልልም” ይላል፡፡

ጓደኝነታቸው እንደቀጠለ ነው፡፡ ሆኖም በየነጋ ሲገናኙ ወዳጅየው

“ዛሬ ቁርስ አልበላሁም” ይላል፡፡

ጓደኝየውም ሚስጥሩን እንዲጠብቅለት በማሰብ፤

“ምን ችግር አለ? እኔ እከፍላለሁ ብላ” ይለዋል፡፡

ሌላ ቀን ደግሞ ይመጣና

“ዛሬ ምሳ አልበላሁም” ይላል ወዳጅ፡፡

ጓደኝየውም፤ “ምን ችግር አለ እኔ እከፍላለሁ ብላ” ይላል፡፡

ሌላ ቀን፤ “ሲጋራ ግዛልኝ?” ይለዋል፡፡

ፓኬት ሲጋራ ገዝቶ ይሰጠዋል፡፡

እያደር የወዳጁ ፍላጐት እየበረከተ ጓደኝየው መክፈል እየሰለቸው መጣ!

“ዛሬ የለኝም” እንዳይለው ሚስጥሬን ቢያባክንስ የሚል ስጋት አለበት፡፡ ሁልጊዜ እንዳይከፍለው ወጪው በዛበት፡፡ ግራ እየገባው መጣ፡፡

በመጨረሻ አንድ ሃሳብ መጣለት፡፡

“እንዲህ ሁልጊዜ እየተሰቀቅሁ ከምኖር ለምን ለአለቃዬ እውነቱን ተናግሬ የመጣው አይመጣም!” አለ፡፡

እንዳሰበው በቀጥታ ወደ አለቃው ሄዶ፡-

“ጌታዬ አንድ ጉዳይ ነበረኝ” አለ

“የምን ጉዳይ” አሉ አለቅየው፡፡

“ቤትዎን ያቃጠልኩት እኔ ነኝ፡፡ እውነቱን ተናግሬ ያረጉኝን ያርጉኝ? ብዬ አስቤበት ነው የመጣሁት!”

አለቅየው ነገሩን አወጡ አወረዱና፤

“አይዞህ እውነተኛ ሰው በመሆንህ ነው መጥተህ የነገርከኝና ምሬሃለሁ - ሂድ!” ብለው አሰናበቱት!

ወዳጅ እንደልማዱ በነጋታው መጥቶ፤

“ገንዘብ ያስፈልገኛል” ይላል፡፡

“የለኝም” ይላል ጓደኛ፡፡

“እንዲህ ከተጨካከንማ የማረገውን አውቃለሁ”

“የፈለከውን አድርግ”

ወዳጅ ወደ አለቃው ይሄድና ቤታቸውን ማን እንዳቃጠለ ይነግራቸዋል፡፡ አለቅየውም፤

“እስከዛሬ የት ነበርክ!? ዋናው ባለጉዳይ እውነቱን ከነገረኝ ወዲህ መጥተህ በሁለት ቢላ ልትበላ! ወራዳ! ከዛሬ ጀምሮ ዐይንህን እንዳላይ!” ብለው አባረሩት፡፡

***

እውነቱን መናገር ከብዙ ጣጣ ያወጣል! እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ሲሰቀቁ ከመኖር ያድናል፡፡ በሁለት ቢላ ከሚበላ ይሰውረን! በጥቅም ከታወረ ወዳጅ ያድነን! ቀን ጠብቆ ካርድ ከሚያወጣ ጠላት ራሳችንን እንጠብቅ! ወዳጅና ጠላትን መለየት የነገር ሁሉ ቀዳሚ ትምህርት ነው! ከሀሰተኛ ወዳጅ እውነተኛ ጠላት ይሻላል ይባላል፡፡ ማንነቱ የታወቀን ጠላት ቢያንስ መሸሽ ይቻላል፡፡ አሊያም በምን አይነት ዘዴ አብሮ መኖር እንደሚቻል መዘየድ ይቻላል፡፡ ካልሆነም ተዘጋጅቶ መጋፈጥ ይቻላል! ሀገራችን አያሌ ወዳጅና ጠላቶችን አይታለች - የተማሩም ያልተማሩም፡፡ አምባገነኖችም ለቀቅተኞችም፡፡ አድር-ባዮችም ሀሳዊ-ዴሞክራቶችም፡፡ አፍአዊዎችም ልባሞችም! ከሁሉም የጐዷት አስመሳዮቹ ናቸው፡፡ በህዝብ ስም የሚነግዱት ናቸው፡፡ አፈ-ቅቤ ልበ-ጩቤ የሆኑቱ ናቸው፡፡ የሚገነቡ መስለው የሚሸረሽሩ፣ የሚያለሙ መስለው የሚቦረቡሩ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ የሚባሉቱ ናቸው፡፡ ሰብቀኛውን ከሀቀኛው፣ አስብቶ አራጁን ከእውነተኛ ተቆርቋሪው ካልለየን የነግ አበሳችን የትየለሌ ነው! They shout at most against the vices they themselves are guilty of ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ እንደምንለው ነው!

ያቺ ሚስትህ ወለደች ወይ? ቢለው ማንን ወንድ ብላ አለ አሉ፡፡ ሙስናው፤ ግፉ፣ ኢዲሞክራሲያዊነቱ ሳያንስ ንቀቱና ዐይን-አውጣነቱም የዚያኑ ያህል ነው፡፡ ዘርፎና በዝብዞ የልማት ሰው መምሰል ከተዐብዮውም ይልቅ አደባባይን መድፈሩ ይገርማል፡፡ እንደፋሽን ሁሉ ከላይ እስከታች አንድ አይነት ቃላት ማነብነብ ተለምዷል! አስቀድሞ የተጠና የሚመስል ንግግር ይዞ መቅረብ እንደ ሀቀኝነት ተቆጥሯል፡፡ አገርና ህዝብን ለመምራት የመሪነት ሚና ምን እንደሆነ ማወቅን ይጠይቃል፡፡ የጨዋታውን ህግና ሥርዓት አበጥሮ መረዳትን ይጠይቃል፡፡ ብዙሃኑ ምን ይለኛል በሚል የመሪነትን ተግባርና ግዴታ ቸል ልንል አይገባም፡፡ ዚምባቡዌአውያን “የኦርኬስትራ መሪ ባንዱን ሲመራ ጀርባውን ለህዝቡ መስጠት ግዴታው ነው” የሚሉት ለዚህ ነው!

 

 

Read 3129 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 09:18

Latest from