Saturday, 21 March 2020 12:40

ኢትዮጵያ የቶኪዮ 2020 ዝግጅቷን ቀጥላለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    - ከመጋቢት 9 ጀምሮ ወደ ስፖርተኞች ካምፕ/ አምባሣደር ሆቴል ኦሎምፒያኖች እንዲገቡ ጥሪ ተደርጓል
    - አትሌቶቻችንን በድል እንደምንቀበል በድል መሸኘት አለብን - የተከበሩ አባዱላ ገመዳ
    - በቶኪዮ ኦሎምፒክ ተዘጋጅተን ነው መቅረት እንጂ ተዘናግተን መቅረት የለብንም- ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ (የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት)
    - በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ዙሪያ እየከፈልንም ቢሆን እንሠራለን - ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ
    - በቶኪዮ ኦሎምፒክ በብቃት ተዘጋጅተን የሚገባንን ውጤት ማግኘት አለብን - አትሌት ገ/እግዚብሔር


            የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለ2020 ቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚያደርገውን ዝግጅት በብቃት እያከናወነ መሆኑን ገለፀ፡፡ ኮሚቴው ትናንት በአምባሳደር ሆቴል የሰጠው መግለጫ በ5 አንኳር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡  
ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው 11 አባላት ያሉት ሲሆን፤ በመግለጫው ላይ ሰብሳቢው የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ፤ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልጊዮርጊስ፤ ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ አትሌት ገ/አግዚአብሔር ገብረማርያም ተገኝተዋል፡፡  የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ህክምና ኮሚቴ አባላት የሆኑ ዶክተሮች እና የስነምግብ ባለሙያም በመግለጫው ላይ በመገኘት ለቶኪዮ ኦሎምፒክ በየኃላፊነት ድርሻቸው ያደረጉትን ዝግጅት አብራርተዋል፡፡ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ከመጋቢት 9 ጀምሮ ለቶኪዮ ኦሎምፒክ የተመረጡ ኦሎምፒያኖች ወደ ስፖርተኞች ካምፕ እንዲገቡ ጥሪ አድርጓል:: ኮሚቴው የስፖርተኞች ካምፑ አምባሳደር ሆቴል እንደሆነም አሳውቋል፡፡
የብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አባዱላ “ከጀግኖች ሯጮች፣ ከህክምና እና የስነ ምግብ ባለሙያዎች እና ከኦሎምፒክ ኮሚቴው ጋር መግለጫ መስጠታችን በላቀ ዝግጅት ላይ መሆናችንን ያመለክታል፡፡” ነው ያሉት፡፡ “በኦሎምፒክ ተሳትፏችን የውድድር መስኮችንን ለማብዛት እና ህብረተሰብን ለማሳተፍ ዕቅድ አዘጋጅተናል፡፡  የቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅታችን ለቀጣይ ኦሎምፒኮች መሠረት የምንጥልበት ይሆናል፡፡ የኦሎምፒክ የስፖርተኞች ማብቂያ የሚሆን ማዕከል ለመገንባት እየሰራን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እስከ 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለመስጠትና ለማሰባሰብ ቃል ገብተዋል:: ስለዚህም የመጨረሻውን ስራዎች እንቀጥላለን፡፡ የሚቆም ምንም ነገር የለም:: አትሌቶቻችን በድል እንደምንቀበል በድል መሸኘት እንፈልጋለን፡፡
የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞቻችን በተያዘላቸው ፕሮግራም ይቀጥላሉ፡፡ በማለትም አቶ አባዱላ ገመዳ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ከIOC ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ ከሰሞኑ መሰብሰባቸውን አንስተው፤ ባወጣው መግለጫ የኮረና ወረርሽኝ ዓለምን እየጐዳ ቢሆንም ኦሎምፒክ በታሪክ በችግር ወቅት ያለፈባቸው ምዕራፎች በምሳሌነት  ጠቅሰው፤ የዓለም ኦሎምፒክ ቀን መከበር የተጀመረው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ቶኪዮ 2020 እንደማይቋረጥ ወስኗል፡፡ የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ አባል አገራትም በፊርማቸው አጽድቀዋታል፡፡ ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ተዘጋጅተን ነው መቅረት ያለብን እንጂ ተዘናግተን መቅረት የለብንም፡፡” በማለት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ተናግረዋል፡፡  
“በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ዙሪያ እየከፈልንም ቢሆን እንሠራለን፡፡ ክፍያ ብናገኝም እንኳን በአትሌቶች ውጤት ነው” ያለው በብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የሆነው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ፤ “በኦሎምፒክ ዝግጅት መጓተት አያስፈልግም፤ ቶኪዮ ላይ መካሄዱ አይቀርም፡፡ ኦሎምፒክ የሚካሄድበትን ወቅት በምንም መልኩ መሰረዝ ሆነ ጊዜውን ማሸጋሸግ አይቻልም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ መዘጋጀት አለብን፡፡ አትሌቶች ከውድድር ውጭ በመሆናቸው ወደ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ያስፈልጋል፡፡” በማለትም የኦሎምፒክ ቡድኑ ወደ ስፖርተኞች ካምፕ መጠራት ወሳኝ እንደሆነ አብራርቷል፡፡ “በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በመላው ዓለም በርካታ የስፖርት ውድድሮች ተሰርዘዋል:: አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ገቢ የሚያስገኙ በመሆናቸው አትሌቶች ይጐዳሉ፡፡ ለኦሎምፒክ በሚደረግ ዝግጅት ሞራላቸውን ማነሳሳት እንፈልጋለን:: አትሌቶች በጋራ ሰብስበናቸው ከወረርሽኙ መጠበቅ ይቻላል፡፡ ለኦሎምፒኩ በብቃት ተዘጋጅተን ውድድሩ ቢሰረዝ ጥሩ ነው” ብሏል ሻለቃ ኃይሌ፡፡
“የቶኪዮ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ልዩ ምዕራፍ አለው፡፡ የሚገባንን ውጤት ማግኘት አለብን፡፡ የኦሎምፒክ ስፖርተኞች በሚያርፉበት ሆቴል ከወቅታዊ የኮረና ወረርሽኝ በተያያዘ ስጋት አይኖርባቸውም:: በሆቴል ቆይታቸው ሁሉንም በተለይ ለእነሱ ብቻ እንዲወሰን እናደርጋለን:: ሬስቶራንት፣ ጅምናዚዬም፣ የሊፍት አገልግሎት ለኦሎምፒክ ቡድኑ ለብቻው ተዘጋጅቷል፡፡” ብሎ የተናገረው ደግሞ የብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ዋና ፀሐፊ ገብረእግዚአብሔር ገ/ማርያም ነው:: “ሁላችንም ዓይኖቻንችን ወደ ቶኪዮ ማዞር ይኖርብናል፡፡ በዓለም ዙሪያ ሌሎች የስፖርት ውድድሮች እንደተሰረዙት ሁሉ ኦሎምፒክም ይቋረጣል ማለት አይደለም:: ከ90 በላይ አትሌቶችን ተሰብስበው ወደ ስፖርተኞች ካምፕ አምባሳደር ሆቴል እንዲገቡ ነው፡፡ ይህም የኦሎምፒኩን ቡድን በቅርበት በመከታተልና ወረርሽኙን በመቆጣጠር ለመሥራት የተሻለ መንገድ ነው፡፡ ሆቴል ሲገቡ የጋራ ጤንነታቸው በልዩ ክትትል  ይጠበቃል፡፡ ሲልም አትሌት ገ/እግዚአብሔር ሃሳቡን ገልጿል፡፡
በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ዝግጅት እንደ ጥንካሬ የሚነሳው 9 ዶክተሮችና የህክምና ባለሙያዎች መሰባሰባቸው ነው:: ዶ/ር ቃልኪዳን የህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢ ስትሆን፤ በመግለጫው ላይ እንዳብራሩት አምባሳደር ሆቴል ለኦሎምፒክ ቡድኑ ማረፊያ ሆኖ ሲመረጥ የህክምና ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት በጥልቀት መክረውበታል:: አምባሳደር  ሆቴል ሙሉ ለሙሉ ብሉክ ዲ ህንጻውን ዘግቶ ሰጥቶናል፡፡ የኦሎምፒክ ቡድኑ በሚጠቀምባቸው የሆቴል አካባቢዎች የፀረ ተዋህስያን ርጭት ስራ ይከናወናል” ብለዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው አጭር ማብራሪያ የሰጠችው የስነ ምግብ ባለሙያዋ ኤደን በማረፊያው ሆቴል ምርጫ ከኮሚቴው ጋር መሠራትን አንስታ፤ አምባሳደር ሆቴል ለኦሎምፒክ የሚያስፈልጉ የምግብ ዝግጅቶች፤ አዳዲስ መጨመር ያለባቸው ነገሮች እና የአመጋገብ ስርዓትን የተቃና ለማድረግ ከአምባሳደር ሆቴል ጋር በቅርበት እየሰራን እንገኛለን ብላለች፡፡ ከስፖርት ጉዳት ጋር በተያያዘ የሚያስፈልገውን አመጋገብ እና በቶሎ ለማገገም የሚያግዙት አመጋገቦች ጥናት አድርገንባቸው ከስፖርተኞች ጋር ለመሥራት ሙሉ ዝግጅት አድርገናል ብላለች የሥነ ምግብ ባለሙያዋ፡፡   

Read 1310 times