Saturday, 21 March 2020 13:02

የሁለት አፎች ተረክ

Written by  ከቃል ኪዳን
Rate this item
(7 votes)


           አፋፉ ላይ ያለዉ በጅብ ቆዳ የተሠራዉ ቤት፤ በጭነት ጎብጠዉ ወደ ገበያ የሚሄዱትን አህዮች ኮቴ በሰማ ቁጥር፤ በቁጭት ያንጎራጉራል፡፡
‹‹የአፈር አፍ ትልቁ፤
የአፈር ሆድ ትልቁ
ይለስኑህ ገቡ እየጨፈለቁ››፡፡
የጅብ አራጁ ሰዉዬ ልጅ በራፉ ላይ በጅብ ሠርዲን ጣሳና በሲሚንቶ ያበጀዉን ክብደት ከፍ፣ ዝቅ እያደረገ፤ በአጠገቡ ፊቷን አቦካዶ ተለቅልቃ ወደ መደብር የምትሄደዉን ጎረቤቱን እያየ ምራቁን ዋጠ፡፡ አቦካዶ በዳቦ ነብሱ ነዉ፡፡ የቤቱ የመጨረሻ ልጅ ሆነ እንጂ፤ ለታናሺየዉ ብኩርናዉን በአቦካዶ በዳቦ ከመሸጥ አይመለሰም ነበር፡፡
ልጁ የጎረቤቱን እንደ ላዛኛ ቅባት የሚተፉ እንቡጥ ከንፈሮችን ትቶ፤ ፊቷን አልጌ የወረሰዉ፣ ድንጋይ ያስመሰለዉን አቦካዶ እያየ ምራቁን ዉጦ ጨረሰዉ፡፡ ምራቁን ሲዉጥ ከፍ ዝቅ የምትለዉ ማንቁርቱ፤ ከሚያነሳዉ ክብደት ምት ጋር ስለገጠመች፤ ክብደቱን የሚያነሳዉ ክንዱ ላይ አይጥ ለማዉጣት ሳይሆን፤ ጉሮሮዉ ላይ እንቅርት ለማዉጣት አስመሰለበት፡፡
ድንገት እንድ ያልመጣ የሚመስል ጎረምሳ መጥቶ ልጁ ፊት ቆመ፡፡ ወዲያዉ ያላወራ በሚያስመስለዉ ድምጽ አንዳች ነገር ዘበዘበና ጥያቄ የማይመስል ጥያቄ ጠየቀዉ:: ልጁ ያነሳዉን ክብደት አስቀመጠና በደረቀ አፉ ታሪክ ለመንገር፤ ወሬ ማዳመቂያ ሣቅ ለመሣቅ ሞከረ፡፡ ከደረቀዉ አፉ የሚወጣዉ የተንኮሻኮሸ የሣቅ ድምጽ ግን ለራሱም ደስ ስላለዉ እቤት ገብቶ አንድ ጣሳ ዉሃ አንደቅድቆ ተመለሰ፡፡ አፍ ሁለት፡- በአንድ ጣሳ ዉሃ የራሰዉ ጉሮሮዉ መለስለሱን ባቋረጠዉ ሣቅ ከሞከረ በኋላ ባልንጀራዉ ለጠየቀዉ ጥያቄ መልስ መስጠት ጀመረ፡፡
‹‹መጋዘን የመጣዉን ዕቃ አዉርደን እንደጨረሰን፣ ሰዓቱ ስለሄደ ሳንተጣጠብ፤ ‹ሶሲ› ጋር ምሳችንን በልተን፤ ከሰማኒ ጫታችን ገዝተን፣ ወደ ባህታዊ ሠፈር (የሠፈሩ ወጣት ሁሉ ጸጉሩ የተገመደ ስለሆነ ለሠፈሩ የተሰጠዉ ስያሜ ነዉ) ሄድን:: መቼም እሱ እንግዳ ተቀባይ ነዉ ብለን ሁልጊዜ ባዶ እጃችንን መሄድ የለብንም፡፡ በዛ ላይ ሰዓቱ ስለሄደ፤ ገና ቤቱ ሄደን እሱ ጫት እስኪልክ ድረስ አፍጥጦ መጠበቁ ይከብዳል፡፡ ኖሮንም ሳይኖረንም የእሱን እጅ እየጠበቅን፤ በእሱ ሰዓት እየቃምን…›› ንግግሩን ገረዘዉ፡፡
‹‹ቆይ ማን ማን ነበራችሁ ግን?›› ጓደኝየዉ ጠየቀ፡፡
‹‹ሁላችንም ነበርን፡፡ እኔ፣ ‹ስሞኪ›፣ ኪያ፣ ማስ፣ ክብዴ ኧ…ሳንቾና አብዱ ነበርን (ሁላችንም ካለ፣ የሁሉንም ማንነት ምን አዘረዘረዉ?)፡፡ እቤቱ ስንደርስ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም (ሥሙ አብርሐም ነዉ፤ ግን እንዳብርሐም በጣም ደግ ስለሆነ ነዉ እንደዛ ብለዉ የሚጠሩት) በዛ ሰዓት እንደሚያደርገዉ እቤቱን እየጠረገ ደረስን:: እንደተለመደዉ አብርሐማዊ ፈገግታዉን ለገሰን፡፡ ከእነ አቧራችን እንደመጣን ስላወቀ ቤቱን መጥረጉን አቁሞ፤ በሩ ላይ ያከማቸዉን ቆሻሻ እንኳን አፍሶ ሳያወጣ፤ ወደ ውስጥ አስገባን፡፡ ከዛም….››
አቦካዶ ግርፏ ጎረቤቱ ተመልሳ ስትመጣ ወሬዉን አቁሞ ዓይኖቹን እያቁለጨለጨ መቋመጥ ጀመረ፡፡ ጓደኛዉ ወሬዉ መቋረጡንና የልጁ ዓይኖች ከእሱ ዓይኖች ላይ ተነቅለዉ ወደ መንገዱ መሄዳቸዉን ሲረዳ፤ ዓይኖቹ የጓደኛዉን ዓይኖች ዱካ ተከትለዉ ሄደዉ፣ ጉዳዩን እንዲያጣሩ ላካቸዉ፡፡
ልጅቱን አንደኛዉ ፊቷ ላይ የተመረገዉን አቦካዶ፤ ሌላኛዉ ደግሞ ከፊቷ ላይ እየቀለጠ ወደ አፏ በሚሠርገዉ አቦካዶ የዳበረዉ ዳሌዋን ተከትለዉ በድፍርስ ዓይኖቻቸዉ ሸኟት፡፡ የአየር መንገድ ‹ቴክኒሽያን› የነበሩት አባቷ፤ ከ‹ፎከር› ገላ ላይ ገፈዉ የሠሩትን፤ የአየር መንገዱ አርማ ያለበትን የግቢ መዝግያ ገፍታ ስትገባ፣ የጅብ አራጁ ልጅ፤
‹‹ከዛ…›› ብሎ ወሬዉን ሊቀጥል አወጀ:: ጓደኛዉ የልጅቱ ፊት ላይ የተመረገዉን አቦካዶ አብሮት እንዲበላ አልፈለገም፡፡
‹‹ከዛ ወደ ዉስጥ ገብተን ማስ ሹፌር ሆና ፏ ማለት ጀመርን፡፡››
‹‹እሺ ከዛስ?››
ጓደኝዬዉ ተመልሻለሁ ለማለት ያህል፤ ንግግሩን ያልገታዉን ጓደኛዉን ጠየቀ:: በልቡ ግን ልጅቱ አዙሪት አግኝቷት፤ አፈር ልሳ፤ ከቀልቧ እስክትመለስ ድረስ ሠፈሩን ስታካልል ብትዉልና ባጠገባቸዉ አሥሬ እየተመላለሰች፤ በዓይኖቹ ቢያላምጣት ተመኘ፡፡
‹‹ከዛም ምን ልበልህ? እጣኑ፣ ሰንደሉ…በቃ ቤቱ እፍንፍን አለ፡፡ የእጣኑና የሰንደሉ ጭስ፤ ቤቱ ጣርያ ሥር ደመና እየሠራ፤ ጨዋታና ሣቅ ይዘንብ ጀመር፡፡››
ጓደኝየዉ የቤቱን ድባብ በዓይነ ህሊናዉ ሥሎ ሳይሆን ድሮ አእምሮ ዉስጥ የነበረዉን ሥዕል አደማምቆ፣ በጓደኞቹ ቀና፡፡ አዲስ ሙሽራ እህቱን ጥየቃ ሄዶ የበላዉ ቅልጥም፤ እርም ሆኖበት ሆዱ ዉስጥ ተገላበጠ፡፡
‹‹እሺ ምን ተፈጠረ? እሱን ንገረኝ!›› የሚያስቀናዉን ነገር ከእዚህ በላይ መስማት አልፈለገም፡፡  
‹‹እሱማ…ያ ልማደኛ ስሞኪ ምርቅን ሲል እንደ ቡዳ መድኃኒት አንገቱ ላይ አንጠልጥሎ የሚዞረዉን፤ ‹ኽርብ› አዉጥቶ ጠበረረና ለኮሰ፡፡ ሀሉም አሪፍ ‹ሙድ› ላይ ስለነበረ ማንም ተዉ ሊለዉ አልቻለም፡፡ ብታይ እኮ ድባቡ...!››
‹‹የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ዝም አለ?›› አቋረጠዉ፡፡
 በጊዜዉ የነበረዉን ድባብ አስመልክቶ የሚያስቀናዉን ነገር መስማት አልፈለገም፡፡
 ‹‹ለነገሩ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም እስከሆነ ድረስ ምንም ማለት የለበትም::›› ለእራሱ ጥያቄ እራሱ መልስ ሰጠ፡፡ ዋናዉ ጉዳይ መልሱን ከየት አገኘሁ ሳይሆን ‹ድባቡ፣ ድባቡ› እያለ የሚዘበዝበዉን ጓደኛዉን ማናጠቡ ነዉ፡፡
‹‹ትክክል ብለሀል! የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም እንግዶቹን መናገር የለበትም!››
‹‹እሺ ከዛስ?›› ጠየቀ ጓደኛ (እስኪ ይሄንንም ጥያቄ እራሱ ይመልስ!)፡፡
‹‹ከዛማ ሁላችንም ጭሱ ሲደርሰን ቤቱ ሣቅ በሣቅ ሆነ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም እራሱ መሣቅ ጀመረ፡፡ ኪያ ከመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ጎን ነበር የተቀመጠዉ፡፡››
‹‹እሱ ʻባክሁ ሁሌም እሮጦ ከእሱ ጎን ነዉ የሚቀመጠዉ፡፡ የሆነ ‹ሳራ ነኝ› ምናምን ጭዌ መጫወት ይፈልጋል፡፡›› ተሣሣቁ፡፡
‹‹ከዛ ከስሞኪ ተቀብሎ እሱም ማጨሰ ጀመረ፡፡ እንደዉም እምቢ አለዉ እንጂ አጭስ ምናምን ብሎ ሁላ ለመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ጋብዞት ነበር፡፡››
‹‹ማሽቋለጥማ አንደኛ እኮ ናት!››
‹‹ከዛ አብርሽዬ በእጄ ይዤ አላጨስም እንዳላለች ሁሉ ስሞኪ የሚተፋዉን ጭስ ስትምግ ቆይታ፤ ድንገት ተነስታ ቀጥ ብላ ቆመች፡፡ ድንግጥ አልን፡፡ ከዛ በሣቅ ወደቅን፡፡ ድንገት ‹ሁላችሁም ከድንኳኔ ዉጡ!› አለን:: በአንዴ ከመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐምነት ወደ ‹ጀስት› አብርሐምነት ተቀየረች፡፡
‹‹‹አንተ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ነህ:: የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ግቡ እንጂ ዉጡ አይልም!› አልሁት፡፡ ‹አዎ! የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ‹ዌልካም› እንጂ ‹ዌልጎ› አይልም› ሲል እስሞኪ ተደረበ፡፡ ‹ነኝ እንዴ?› ሲል ጠየቀን፡፡ ‹አዎ!› ስንል ሁላችንም በአንድ ድምጽ መለስንለት፡፡ ትንሽ ሲያስብ ቆይቶ ‹እሺ እኔስ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ልሁን ግን ድንኳኔስ? እሷስ የመጽሐፍ ቅዱሷ ድንኳን ናት ወይ?› ሲል እንባ እየተናነቀዉ ጠየቀ፡፡ ምን እንደምንመልስ ግራ ተጋብተን ዝም አለን፡፡ እሱ ግን ቀጠለ፡-
‹እሺ እኔስ ልሁን ግን ለእናንተ ቡና እየቀቀለች የምታመላልሰዉ እህቴስ ማናት?› ብሎ አፈጠጠ፡፡ ‹ሳራ ናት› አለዉ አብዱ:: ማስ አብዱን ገላመጠዉ፡፡ ‹ምነዉ ምን አጠፋሁ?› ብሎ ጠየቀ አብዱ፡፡ ‹ሳራ የአብርሐም ሚስት እንጂ እህት አይደለችም:: የአብርሐምና ሳራ ታሪክ እኮ እናንተም ጋ፤ እኛም ጋ አለ፡፡› ማስ ተቆጣ፡፡
‹እስኪ የድንኳኔን ወለል ተመልከቱት!› አለን የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም:: ‹ተመለከትነዉ ምን ሆነ?› አልነዉ በአንድነት:: ‹እስኪ እላዩ ላይ የረበበዉን ቆሻሻችሁን ተመልከቱት!፡፡ ምን እዳ አለበትና ነዉ የእናንተ ገንዳ የሚሆነዉ?› ተራ በተራ ተመለከተን፡፡
‹የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም እኛ ባንመጣም እኮ ቤቱ መቆሸሹ አይቀርም:: ከእግር በታች የተፈጠረ ነገር መቆሸሹ አይቀሬ ነዉ፡፡ ምናልባት ዛሬ ባይቆሸሽ ነዉ፡፡ ነገ ተነግወዲያ ግን የሚራመድበት ባይኖርም በርሮ መጥቶ፤ በቀዳዳ ሾልኮ፤ የሚያርፍበት ጉድፍ አያጣም!› አለዉ እስሞኪ፡፡ ሁላችንም አንገታችንን በመስማማት ነቀነቅን፡፡ ትንሽ ሲያስብ ቆየና፡
‹እሺ ድንኳኔ የቱን ይመርጣል? በርሮ መጥቶ የሚያርፍበትን ወይስ ረግጦ የሚያቆሽሸዉን?› ተራ በተራ ተመለከተን:: ከዛም ከት ብሎ ሣቀና ‹እኔ እናንተን መረጥሁ፤ ድንኳኔስ ማንን መረጠ?› አለ ድምጹን ከፍ አድርጎ፡፡ ከዛም እየተንገዳገደ በሩን ከፍቶ ወጣ፡፡
‹ድንኳንህ አንተ የመረጥከዉን መምረጥ አለበት፡፡ ለዛ እኮ ነዉ ድንኳንህ የተባለዉ፡፡ አለበለዚያማ ድንኳን ብቻ ነበር የሚባለዉ::› አልነዉ በአንድ ድምጽ፡፡ እሱ ግን ወጥቶ ሄዶ ነበር፡፡ ማስ፤
‹እንግዲህ ድንኳኑ አለን፤ ሌላ አብርሐም ጠፍጥፈን መሥራት ሊኖርብን ነዉ፡፡› ሲል ተናገረ፡፡ የአንዱ አብርሐም ድንኳን ለሌላኛዉ አብርሐም ድንኳን መሆን ይቻል አይቻል ግን ማንም እርግጠኛ ስላልሆነ ሁላችንም ዝም አልን፡፡ ደግሞስ ድንኳኑ ካለን አብርሐም ያስፈልገናል እንዴ? ስንል አሰብን፡፡››
‹‹ከዛ እንዴት ሆነ?››
‹‹በዝምታ እንደተዋጥን ጫታችንን ጨርሰን ስንወጣ፣ አብርሐም ዉጪ ቁጭ በሎ ነበር፡፡ ቻዎም አላልነዉም፡፡ እንደዚህ እንዲሆን አልነበረም የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ያደረግነዉ፡፡›› ጓደኝየዉ በመስማማት አንገቱን ነቀነቀ:: ከዚያም ሁለቱ ጓደኛሞች፣ ኪያን ትንሽ ሲያብጠለጥሉት ቆዩና ሌላ ጨዋታ ጀመሩ፡፡
ቤቱ በራፍ ላይ ተቀምጦ የጠዋት ጸሐይ የሚሞቀዉ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም፣ ፊት ለፊቱ የቆመችዉ የግራዋ ዛፍ ላይ ዓይኖቹን ተክሏል፡፡ ማንኛዉም ተክል የማደግ እድል ከተሰጠዉ ዛፍ መሆኑ አይቀርም የሚል እምነት፤ ካመናቸዉ ሌሎች ነገሮች በታች፤ በልቡ ላይ ተከተበ:: የግራዋዉ ዛፍ ላይ ያለቸዉ ወፍ ግን ፊቷን አኮፋትራበታለች፡፡ ‹ትናንትና ምን ብዬ አስቀይምያት ይሆን?› ሲል እራሱን ጠየቀ:: መልስ ግን የለም፡፡ መልሱን አገኝ ብሎ የትናንት ዉሎዉን ለእራሱ ማዉጋት ጀመረ::
አፍ አንድ፡- ‹‹ድንኳኔን እያጸዳሁ ሳለ እንግዶቼ ቀለባቸዉን ብብታቸዉ ሥር ወሽቀዉ ሲመጡ ተመለከትሁ::›› ወሬዉን እንደጀመረ የግራዋዉ ዛፍ ላይ ያለችዉ ወፍ ሚጢጢ ጆሮዋን አቆመች፡፡ ‹በሹክሹክታ እያወራሁ እንዴት ልትሰማኝ ቻለች?› ሲል በግርምት እራሱን ጠየቀ:: ወፊቱ ወሬኛ የተባለች ያህል ተሰምቷት፤ አፍራ ፊቷን ከመንደሩ በላይ ወዳለዉ አህዮች ወደሚመላለሱበት ዳገት አዞረች:: ዓይኖቿ ዳገቱን ከመርገጣቸዉ በፊት ግን የጅብ አራጁ በር ላይ የጅብ አራጁ ልጅና ዓይነ ድፍርሱ ጓደኛዉ አፍ ለአፍ ገጥመዉ ሲያወሩ ተመለከተች፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ወሬዉን ሲቀጥል፣ ፊቷን ሳትመልስ ጆሮዎቿን በአትኩሮቷ ወጥራ ተከለች፡፡
‹‹እንግዶቼ አቧራ ለብሰዉ ነበር፡፡ የድንኳኔን ወለል ተጨማሪ የደረቁ ዘንባባ እጆች ቢዳብሱት ከእንግዶቼ አካል በላይ እንደሚጠራና እንግዶቼን ሊያሳቅቅ እንደሚችል አስቤ ወለሉን መጥረጌን ትቼ፤ እንግዶቼን ወደ ዉስጥ አስገባኋቸዉና እንደተለመደዉ ስምንት አጎዛዎቼን አዉጥቼ አነጠፍሁላቸዉ (ሰባት ከሆነማ አብርሐም እንጂ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ሊሆን አይችልም ነበር)፡፡
እንግዶቼ ወደ ድንኳኑ ገብተዉ እንደተቀመጡ አገልግላቸዉን ፈቱ፡፡ አገልግላቸዉ የብብታቸዉን ጠረን ቀስሞ የጎረምሳ እንጀራ እላዩ ላይ ጋግሯል፡፡ ተነስቼ እጣኑንም፣ ሰንደሉንም አጫጭሼ እንጀራዉን መቁረጥ ጀመርን (የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም እንዴት ተጸይፎ አልበላም ይላል?)
ሀድራዉ ደራ፡፡ ጨዋታዉ ደመቀ፡፡ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔርን ስልጣን የማያዉቁ አፎች፤ ርዕሰ ብሔሩ አምባሳደር ከመቀበልና ከመሸኘት ዉጪ ለአገሪቱ ምንም ሥራ እየሠሩ አይደሉም ሲሉ ወቀሱ፡፡ ሌሎች አፎች ‹‹ምን እሳቸዉ ብቻ!›› ሲሉ ሌሎች ባለስልጣናትን ያለ ቦታቸዉ እየከተቱ ችሎት ፊት አቆሟቸዉ፡፡
ኪያ አጠገቤ ተቀምጦ እዉነተኛዉ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም በዚህ ዘመን ቢኖር እንኳን ሊያደርግ የሚያዳግተዉን ነገር እያደረግሁ እንደሆነና በላዔ ሰብ፤ ከእኔ በኋላ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ፤ እንዴት አብርሐምን መሆን እንደሚቻል በደንብ ይረዳ እንደነበረ…ኧ…እና ደግሞ ከገባበት ችግር ዉስጥ ከመግባት ይተርፍ እንደነበር ሲነግረኝ ቆየ፡፡
በዚሁ ሁሉ ሁካታ መሀል ድንገት ስሞኪ አንገቱ ላይ ያንጠለጠለዉን የዝሆን ጥርስ የመሰለ የአንገት ጌጥ አዉልቆ፤ አሽከርክሮ ከፈተዉና ከኪሱ ወረቀት አዉጥቶ ትንባሆ የመሰለ ነገር አፍስሶበት ጠቅልሎ ለኮሰዉ:: ወድያዉ ቤቱ ልዩ ጠረን ባለዉ ጭስ ታፈነ:: ኪያ ወሬዉን ትቶ ዓይኖቹን ስሞኪ ላይ ተከለ፡፡ የኪያን ዝምታ ተንተርሼ እኔም ጫቴን በሰላም መቃም ጀመርኩ፡፡››
ወፊቱ በወሬዉ ተመስጣ ከግራዋዉ ዛፍ ላይ ዘላ ወርዳ የወለሞ ተክል ላይ አረፈች፡፡ ከዛም ዓይኖቿን በወለሞዉ ቅጠል ጠራርጋ ፊት ለፊቱ በራ መጥታ ቆመች፡፡ ምናልባት ወፎች እንደ ሰዉ ዓይናቸዉን በጨዉ ሳይሆን በወለሞ አጥበዉ ነዉ ይሉኝታቸዉን አራግፈዉ የሚጥሉት፡፡
‹‹ድንገት ዓይኖቼ እያዩ የእጣኑ፣ የሰንደሉና ከስሞኪ አፍ የሚግተለተለዉ ጭስ የቀደምትነትና የባለቤትነት ጥያቄ አንስተዉ ድንኳኔን የጦር አዉድማ አደረጉት፡፡ ምን እንዳጣላቸዉ ግራ ገባኝ፡፡ ‹ቆይ ሰንደሉና እጣኑ እስካሁን ለምን አልተጣሉም ነበር? ወይስ እንግዳዉ ጭስ ሲከሰት እጥረት ተከሰተ? እጥረት ከሆነስ የዘር ማንዘራቸዉን ስም እየጠሩ አየሩ የእኔ ነዉ ከሚሉ፤ ለምን ጠበበኝ ብለዉ አይንፈራገጡም?› ስል ልመልሳቸዉ በማልችላቸዉ ጥያቄዎች ተወጠርኩ፡፡ ድንገት ኪያ ተነስቶ አፍንጫ ላፍንጫ ገጥመዉ ሊጣሉ ኮሽታ የሚጠብቁትን ጭሶች በሞላላ ጭንቅላቱ እየጠረገ ሄዶ ከስሞኪ የሚያጨሰዉን ተቀብሎት መጣ፡፡ ሲመለስ የተረፉትን ጭሶች ጠራርጎ አጠፋቸዉ፡፡ እኔም ጥያቄዉ በለሌለበት፤ መልሱን ማሰብ ትቼ ወደ ጫቴ ተመለስሁ፡፡ ሌሎቹ ክርክራቸዉን ትተዉ በረባዉ ባረባዉ መሣሣቅ ጀምረዋል፡፡ እኔም አሣሣቃቸዉ አሥቆኝ ወደ ሣቁ ድግስ ተቀላቀልኩ፡፡ ሣቄ ግን ከጉንጭ በታች ስለነበረ አእምሮዬ እንዲህ አሰበ፡-
‹‹እንዴት?›› አለች ወፊቱ፡፡ ወፊቱ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ጫማ ጋ ደርሳለች፡፡ በጠዋቱ ጸሀይ የወፊቱ ገላም፤ ጫማዉም ያብረቀርቃሉ (እንኳን ኪያ አላየ! ይሄኔ አብርሐምን ወደ ራሱ ጫማ እንዲያይ እያዘዘ ‹ተመልከት ጫማህን፤ የእዉነተኛዉ አብርሐም የጠፍር ጫማ፤ ያንተን ጫማ ግማሽ ያህል እንኳን አላብረቀረቀም፡፡ ተመልከታት ደግሞ ወፊቱን! ከሰለሞን በላይ ያማረ የለበሰችዉ ወፊት እንኳን ልብስዋ ያንተን ጫማ ያህል አላማረም!› እያለ ያደርቀዉ ነበር)፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ወፊቱን በዓይኖቹ ገረፍ አድርጓት፤
‹‹ሁላችንም ከማይረባዉ ክርክራችን በኋላ ወይ ደግሞ ክርክራችን መሀል ላይ ገትተን እንዲህ በእንቶ ፈንቶዉ ከት ብለን ብንስቅ ብዬ አሰብኩ!›› ሲል ለወፊቱ መለሰላት፡፡ ወፊቱ በመስማማት እራሷን ነቀነቀች፡፡
‹‹ኪያ እስሞኪ ጠቅልሎ ያበጀዉን ጭስ አንድ ሁለቴ ምጎ አሳለና ለአፍታ ተመስጦ ቆይቶ እንካ ብሎ ጋበዘኝ፡፡ እምቢ አልኩት (አብርሐም አልሰጥም አይልም እንጂ አልቀበልም ማለት ግን ይችላል!)፡፡ ከዛ ሳልተክዝ፤ በላዔ ሰብም ቢሆን እንደጸደቀና ዋናው ነገር መጽደቁ እንደሆነ ነግሮ ሊያረጋጋኝ ሞከረ፡፡ ነገር ግን ቀድሞኝ እራሱ ተረጋጋ፡፡ ያጎረሰኝን ጉርሻ የዋጠብኝ ያህል ተሰማኝ፡፡
ከኪያ አፍ የሚወጣዉ ጭስ በአፌና በስርኔ እየገባ እንደ ጉንዳን ወረረኝ፡፡ ንጹህና የጠራ መስሎ ይሰማኝ የነበረዉ ዉስጤ፤ ግድግዳዉና ወለሉ፤ ከልቤ የሚመዘዙ ሕብረ ቀለማት፤ ዉስብስብ ድር ሲያደሩበት ተሰማኝ፡፡ ዉስጤ ይቆሽሽ ወይ ይጽዳ፤ ግራ ተጋባሁ፡፡
ዓይኖቼን ከዉስጤ ነቅዬ ለእንግዶቼ ብዬ የተከልኩትን ድንኳኔን ተመለከትኩት:: ጸድቶ የነበረዉን ወለል፤ ከእንግዶቼ ላይ እንደፎረፎር የረገፈዉ አቧራ ወደነበረበት መልሶታል፡፡ ዘንጦ ወጥቶ፤ ጓደኞቹ ገፍትረዉ ጥለዉት እንዳቆሸሹት ህጻን፣ ድንኳኔ አሳዘነችኝ፡፡ ሁሌም ቢሆን እንግዶቼን እንጂ ድንኳኔን አስቤ አላዉቅም ነበር፡፡ በእራሷ ስትቦርቅ ወድቃ ቆሽሻ ቢሆን እሺ!
ድንገት ተነሳሁና ‹ሁላችሁም ዉጡ!› ስል አንባረቅሁ ድንኳኑ እረጭ አለ፡፡ ጸጥታዉን ተከትሎ አንድ ጥያቄ ወደ አእምሮዬ መጣ:: ወሬዉን ገታ አድርጎ ወፊቱን ተመለከተ፡፡ ወፊቱ ለወሬዉ የጓጓች ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐምን ‹‹የምን ጥያቄ?›› ስትል አልጠየቀችዉም፡፡ ትንሽ ጠበቃትና ወሬዉን ቀጠለ፤
‹‹‹እኔ እንግዶች መቀበል እንደምፈልገዉ፤ ድንኳኔ እንግዶችን መቀበል ትፈልጋለች ወይ? የሚል ጥያቄ አእምሮዬን ጠቅ አደረገዉ፡፡ መልሱን ላሰላስል ስል ጥያቄዉን መመለስ እንደማልችል ተገለጸልኝ፡፡ ‹ቆይ ስለ ድንኳኔ እኔ እንዴት ልመልስ እችላለሁ?› ስል አሰብኩ፡፡ ወዲያዉ ግን ሸራዉን ቀድጄና አበጅቼ ድንኳን ያደረግሁት እኔ እንደሆንኩና ድንኳን በማድረግ፣ የድንኳንነት ግብር የሰጠሁት እኔ እንደሆንሁ አሰብኩ፡፡ ሸራ፤ ድንኳን ከሆነ በኋላ እንግዳ አልቀበልም ማለት አይቻልም ብዬ እራሴን አረጋጋሁ::›› ወፊቱ በፈገግታ ተሞልታ እራሷን በመስማማት ነቀነቀች፡፡
‹‹ችግሩ ግን ሌላ ጥያቄ ደግሞ ወደ አእምሮዬ መጣ (ወፊቱ ‹አይ አብርሐም! እኔ ደግሞ እንግዳ ብቻ የምትቀበል መስሎኝ፤ ለካ የጥያቄም እንግዳ ትቀበላለህ፡፡ ለነገሩ ‹ሞዴልህም› ጠያቂ ነበር፡፡ እሱ ጥያቄዉን ተቀብሎ ባያስተናግድ ኖሮ አምላኩን ፈልጎ አግኝቶ አይባረክም ነበር› ብላ ሳታስብ አልቀረችም፡፡)
‹‹ቆይ እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ!›› የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም ወፊቱ ላይ አፈጠጠ፡፡ ወፊቱ ወደ ኋላ ራመድ፣ ራመድ ብላ ከጫማዉ ፈቀቅ አለች፡፡ ኮቴዋ ‹በል፣ በል እዛዉ እራስህን ቻል!› የሚል ድምጽ አወጣ፡፡
‹‹ቆይ የድንኳኑ ህልዉና ዉሉ ያለዉ የቱ ጋር ነዉ? ሸራዉ ተቀዶ፣ ከተሰፋ በኋላ ነዉ? ወይስ ክሮች እየተወሳሰቡ ሸራዉ የተበጀ ጊዜ ነዉ? ወይስ ክሮቹን ለማበጀት…››
ወፊቱ የነገሩ መጨረሻ እንደሚያሳብዳት አስባ ፊቷን አዙራ ወደ ሰማይ ተተኮስች፡፡ ነገር ግን ካሰበችዉ ሳትደርስ አንድ ጭልፊት አሞራ ቀልቧት ተፈተለከ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ አብርሐም አምላክ!Read 2493 times