Saturday, 04 April 2020 11:31

በጎ ልቦችን ያብዛልን!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

   “ስሙኝማ…መቸም ዘንድሮ አየሩን የሞላው የፈጠራ ወሬ ለጉድ ነው፡፡ እናላችሁ… ልክ ክረምት፣ በጋ እንደምንላቸው ወቅቶች ‘የሀሰት ወሬ ወቅት’ ላይ ያለን ነው የሚመስለው፡፡ ከምንም ጊዜ በላይ እውነትንና እውነትን ብቻ በምንፈልግበት ጊዜ፣ ይሄ ሁሉ የሀሰት ወሬ አለ አይደል… ጥሩ አይደለም፡፡-- “
       
                    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ለአስተማሪዎች ክብር አለኝ፡፡ እዚህ ታክሲ ውስጥ የሚሳፈር አስተማሪ መታወቂያውን አሳይቶ በነጻ መሄድ ይችላል::” አንድ ሚኒባስ ታክሲ ውሰጥ የተለጠፈች ማስታወቂያ ነች፡፡ እንደ ብዙዎች የከተማችን ባለ ታክሲዎች ባህሪይ ከሆነ ይህ አስገራሚ ነገር ነው፡፡  ትርፍ ለማግኘት “እስቲ ጎንበስ፣ ጎንበስ በሉ!” ብለው ትከሻችን ላይ ለመጫን ምንም የማይቀራቸው ባለ ታክሲዎች በበዙበት እንደዚህ አይነት ወጣት ማግኘት ደስ አይልም! የምር ግን… ይሄኔ እዛ ውስጥ ከተሳፈርነው መሀል በሆዳችን “ይሄ ደግሞ የማን ልወደድ ባይ ነው! ጉረኛ!” ምናምን ብለን ያሽሟጠጥነው አንጠፋም፡፡
በአሁኑ የከፋ ጊዜ እንኳን፣ ሀገር እንዲህ ጭንቅ ላይ በሆነበት ጊዜ እንኳን፣ “ትርፍ እንዳትጭኑ!” የሚል መመሪያ ከተላለፈ በኋላ እንኳን፣ አሁንም በ“ጠጋ በሉ” ሊያጭቁን የሚሞክሩ መኖራቸው ግርም እኮ ነው የሚለው፡፡ “የአሁኑ የህይወት ጉዳይ ነው፣” ሲባሉ እንዴት ነው የሰሙት:: በየሀገራቱ እየደረሰ ያለውን እያዩ እንዴት ነው እንደ ሰው ነቃ ማለት ያቃታቸው:: በነገራችን ላይ የህግ ማስከበር አካላትም ህግን ለማስከበር የልብ ልብ የሚሰጥ የማባበልና የ“ኸረ እባካችሁ!” ተማጽኖ አይነት አካሄዳቸውን ትተው፣ የማያዳግም የሚባል አይነት እርምጃ የመውሰጃ ጊዜ ላይ ያሉ ይመስለናል! በተወሰኑ ህግ አፍራሾች የተነሳ ህጉን አክብረው የሚሠሩት የእንጀራ ገመድ መበጠስ የለበትም፡፡
አስተማሪዎችን “በነጻ እወስዳለሁ” ያለው ወጣት ባለ ታክሲ እኮ ገንዘብ ተርፎት አይደለም፡፡ እንደ ማናችንም ከቀን ቀን፣ ከወር ወር የእሱን እጅ የሚጠብቁ የቤተሰብ አባላት ይኖሩታል፡፡ የእሱ ኪስ ባዶ ከዋለ የእነሱ ሆድም ባዶ የሚያድር በስሩ ያሉ ሰዎች ይኖሩታል፡፡ እንደ ማናችንም በተለይ የምግብ ነክ ነገሮች ዋጋ ጣራ ሲነካ የእሱንም ኑሮ ያናጋዋል፡፡ እንደ ብዙዎቻችንም ብር በብር ሆኖ “የገንዘብ ችግር ደህና ሰንብት፣” የሚባልበት ኑሮ ለመኖር ይመኛል፡፡
ግን ደግሞ ሰብአዊነቱ ከሁሉም ነገር በለጠበት፡፡ የሌሎቹ አይነት ‘ብልጥነት’ ስለጎደለው አይደለም፡፡ እሱም… “ጠጋ በሉ!” እያለ ሰዉን ሰርዲን ማድረግ አቅቶት አይደለም፡፡ 
እናላችሁ…አሁን ከምንጊዜም በላይ ሰብአዊነትና እርስ በእርስ መተሳሰቢያ፣ መደጋገፊያ ጊዜ ላይ ነን፡፡ አሁን ከምንም ጊዜ በላይ የአንዳችን ህልውና በሌላኛችን ድርጊቶች ላይ የወደቀበት ጊዜ ላይ ነን፡፡
ስሙኝማ…መቸም ዘንድሮ አየሩን የሞላው የፈጠራ ወሬ ለጉድ ነው፡፡ እናላችሁ… ልክ ክረምት፣ በጋ እንደምንላቸው ወቅቶች ‘የሀሰት ወሬ ወቅት’ ላይ ያለን ነው የሚመስለው፡፡ ከምንም ጊዜ በላይ እውነትንና እውነትን ብቻ በምንፈልግበት ጊዜ፣ ይሄ ሁሉ የሀሰት ወሬ አለ አይደል… ጥሩ አይደለም፡፡
ስሙኝማ…ቁጥራችን ቀላል ለማይባል፣ ውሸት የህይወታችን አካል የሆነ ነው የመሰለው፤ልክ እንደ ወረደ ፎቶሾፕ ምናምን በፕሮግራምነት የተጫነብን ነው የመሰለው::
“ስማ፣ እንትና የምትባለው ልጅ ምን እንደሆነች ታውቃለህ?”
“ምን እንደሆነች ማለት…”
“ከአንጀትህ ነው! ምን እንደሆነች አታውቅም ማለት ነው?”
“ይልቅስ ሰስፔንሱን ተወውና የምትነግረኝ ካለ ንገረኝ፡፡ ምን ሆነች ነው የምትለኝ?”
“አጅሪትማ ምን ትሆናለች፡፡ የአዲሱ ሥራ አስኪያጅ ገርል ነች አሉ…”
“በቃ ይኸው ነው?”
“አይገባህም እንዴ! ሰውየው እኮ ሰባት ነው ስምንት ልጅ አለው፡፡”
እናማ… ግራ ይገባችኋል፡፡ እናንተ በእሷና በሥራ አስኪያጁም ይሁን በእሷና በመዝገብ ቤት ሀላፊው መሀል ምን ይኑር ምን ‘የሚኮነስራችሁ’ ነገር የለ! ለምን ያነካካችኋል! በኋላ እኮ ለሌሎቹ ይህንኑ ወሬ ያወራና ማመሳከሪያ ልትሆኑ ትችላላችሁ፡፡ “እሱን ብትጠይቁት ይነግራችኋል፣” ይልና በማግስቱ ሌላኛው ይመጣና…አለ አይደል…የ‘ሰበር ዜናው’ ምንጭ እናንተ የሆናችሁ ይመስል.. “ስማ አጅሬዋ የአለቃችን ቺክ ነች የሚባለው እውነት ነው?” ሊላችሁ ሁሉ ይችላል፡፡ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡  
“እና ይሄን ለእኔ የምትነግረኝ ለምንድነው… እኔ ምን አገባኝ?”
“ለምን አያገባህም! የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ አይደለህም እንዴ!”
ጉድ እኮ ነው! እመኑኛ ከሳምንት በኋላ ‘ሰበር ዜናው’ እናንተ ትሆናላችሁ፡፡
“አጅሬውን ተጠንቀቁት…”
”ለምን… ምን አደረገ?“
“የሥራ አስኪያጁ ስፓይ ነው፡፡”
“አትለኝም! እኔም እኮ ድሮም እንዲህ አቀርቅሮ ሰው በጭንቅላቱ እያየ ሲሄድ አይጥመኝም ነበር፡፡ ለካስ ሥራውን ሲሠራ ነበር!”
‘አለቀላችሁ’ ማለት ነው፡፡ ከዛ በኋላ ደራሲዎች ‘አጽመ ታሪክ’ እንደሚሉት አይነት ታሪኩ እየተለዋወጠ መአት አይነት መልክ ይሰጣችኋል፡፡ (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“ጆሮ ጠቢ” ከሚለው ቃል ይልቅ “ሰላይ” የምትለዋ ቃል የሆነ ‘ክላስ’ ነገር ያላት አትመስልም! አሀ…ጄምስ ቦንድም ‘ስፓይ’ ነበራ!)
እኔ የምለው… በዚህ ዘመን…እንዲህ አይነት “እከሊት የእከሌ እንትኑ ነች፣” “እከሌ የእከሊት እንትኗ ነው፣” አይነት ነገሮች አቅመ አዳምን ካለፉ በሰነበቱ ሰዎች ሲወራ አይደብርም! ስንት የሚወራ ነገር ባለበት! ወደው ከገቡበት የራሳቸው ጉዳይ ነዋ!
ስሙኝማ… ቆይቶ ሌላው ይመጣላችኋል::
“ስማ፣ የጓደኛችንን ጉድ ሰማህ አይደል!” ‘ጓደኛ’ የተባለው መጀመሪያ ላይ ወሬውን ያወራላችሁ ሰው ነው፡፡ መቼም ወግ ነውና ትጠይቃላችሁ…
“ምን ሆነ፣ ደህና አይደለም እንዴ!”
“ምን ደህና ይሆናል! ይኸው እንትናን ቢላት፣ ቢላት እምቢ ብላው ኮረንቲ ሊጨብጥ ምንም አልቀረው፡፡ ‘እንትና’ ያላት ደግሞ የሥራ አስኪያጁ እንትናዬ የተባለችው ነች፡፡ እናማ… የወሬ ቅብብሎሹ ቡድን አባል ከሆናችሁ መልሳችሁ ምን ይሆን መሰላችሁ…
“አትለኝም! ለካስ እየዞረ ስሟን የሚያጠፋው ለዚህ ነው!” ትሉና ትንሽ ትመርቁለታላችሁ… “እሱ ግን ያለ ሊጉ ፕሬሚየር ሊግ ምን ያንጠራራዋል!” ግን ምን ይኮነስራችኋል! ስለዚህ እንደነገሩ… “ነው እንዴ…” ብላችሁ ልታልፉ ትሞክራላችሁ:: ወሬ ነጋሪው ደግሞ ‘ሰበር ዜናውን’ ያመጣላችሁ እንዲህ አይነት መልስ እንድትሰጡት አይደለም፡፡ እናማ ጥቂት ቀን ቆይቶ በ‘ጓደኛ’ ቦታ የእናንተ ስም ይተካል፡፡
“እሷን አገኛለሁ ብሎ የምትኖርበት ሰፈር ሌሊት አስራ አንድ ሰዓት ነው የሚሄደው አሉ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… (ምናለ…ጸሀይዋ ትንሽ ከፍ እስክትል ቢጠብቅ!) አስቸጋሪ ነው፡፡
ደግሞላችሁ…ለሰዎች የሌላቸውን ለመልአክትነት የሚያሳጭ ባህሪ የመስጠት ነገር አለላችሁ፡፡ የመሥሪያ ቤቱን የወረቀት ፍጆታ በሆነ ባልሆነው ለሠራተኞቹ ማስጠንቀቂያ በመጻፍ የሚጨርሰውን ሰው…አለ አይደል… “እንዴት አይነት ለሰው የሚጨነቅ፣ የመጨረሻ ታጋሽ ሰው መሰለህ!” ይባላል፡፡ ‘ቲራቲሩ’ በሌለበት ጭብጫቦ!
የምር ግን ዘንድሮ በባዶ የምናጨበጭብ በዛን፡፡ በሆነ ባልሆነው መዳፋችንን የምናሳሳ በዛን፡፡ ግን እኮ የሚጨበጨብለትም ለጊዜው ደስ ያለው ይምሰል እንጂ መታዘቡ አይቀርም፡፡ እውነቱን አያጣውማ!  ጭብጨባችን የስትራቴጂ እንጂ የእምነት ጉዳይ ያለመሆኑን ያውቀዋላ! “አጅሬዎቹ ነገ ደግሞ ለባለ ጊዜ ማጨብጨባቸው አይቀርም፡፡” ለሁለቱም፣ ለሶስቱም ወገኖች እኮ በእኩል የምናጨበጭብ ሆነናል፡፡
እናላችሁ… ከላይ የጠቀስነው “አስተማሪዎችን በነጻ እወስዳለሁ” ያለው አይነት ዜጎች በብዛት ያስፈልጉናል፡፡ መጪዎቹ ጊዜያት በራስ ወዳድነትና በ“እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፣” አስተሳሰብ የሚታለፉ አይደሉም፡፡ የምር እኮ…አለ አይደል…ይሄ  ሁሉ “እከሌ እንዲህ አድርጎ…” “እከሊት እንዲህ ሠርታ…” ምናምን አይነት ነገሮች የሚበዙት መተሳሰቡ ስለሌለ ነው:: ለዛኛው ሰው ስም፣ ለዛኛው ሰው ህልውና ካለመጨነቅ የሚመጣ ነው፡፡
በጎ ልቦችን ያብዛልን!
ደህና ሰንበቱልኝማ!


Read 1399 times