Saturday, 04 April 2020 12:03

ደራሽ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

እየጮህኩ ነበር የነቃሁት፡፡ “ሃሎ ሃሎ!..” ጩኸቷ ነቅቼ እንኳን ይሰማኛል፤ “ለምንድን ነው ለእኔ ያልደወልሽልኝ? ወንድሜን አፍነሽ ልትገይው ነው?” አባባሏ ከነቃሁ በኋላም እንኳን ይሰማኛል፡፡ ቁጣዋ የሚያስበረግግ ነው፡፡ “ለምን? ለምን….?” የመረረ ጥያቄዋ ያስጨንቃል፡፡ እንዴት ግን? ቢቸግረኝ እራሴን ጠየቅሁ፡፡
“የፈጣሪ ያለህ! ደወልኩላት እንዴ?” በድንጋጤ ወንድሜን አሰብኩ፡፡ አድርጌው ከሆነ ይገለኛል፡፡ ቆይ ለማን ለማን ነበር የደወልኩት? ማሰብ ጀመርኩ፡፡ የመጀመሪያው የሱው አለቃ ነበሩ፣ የጋራዡ ባለቤት፡፡
“ተይ እንጂ! እንደሱ ተባለ ደግሞ? እንዴት ያሳዝናል?... ም…ን መጥፎ ቀን ላይ ሆነብን እኮ!... በአሁኑ ሰዓት… ምን ሥራ አለ ብለሽ ነው?.. በዚህ ላይ ግብሩ ምንጥሱ እያሉ… አይ አይ! እኔስ ምንም ገንዘብ የለኝም…! በይ እስቲ አግዚአብሔር ይርዳሽ! እሱንም ይማርህ…” እኔው በደወልኩት ሊጠይቁት ሲሞክሩ ዘጋሁት፡፡ አናደውኛል፡፡ በሳቸው ተስፋ ጥዬ ነበር፤ ይወዱትና ያደንቁት እንደነበር አውቃለሁ፡፡ እሱም በሙሉ ጉልበቱ አገልግሏቸዋል፡፡ ቀጣዩ የራሴ አለቃ ናቸው፡፡ የሱፐር ማርኬቱ ባለቤት፡፡ ከባድ ቢሆንም ከእነሱ የተሻለ ሰው አናውቅም፡፡
“አለሽ እንዴ አንቺ?! ደህና ነሽ፣ ወንድምሽ አልተሻለውም?” በመጀመሪያ ፈቃድ ላስጨምር ስለመሰላቸው ዘና ባለ ድምጽ ነበር የተናገሩት፡፡ ምን እንደተፈጠረና ወደፊት ተሰርቶ የሚከፈል ብር እያፈላለግሁ እንደሆነ ሲያውቁ ግን፣ ድምፃቸውን በአንዴ ለወጡት፡፡ ድሮም ዝም ብዬ ነው! የት ያውቁኝና! በራሴ እየተበሳጨሁ ተሰናብቼ ስልኩን ዘጋሁ፡፡
“ያ ማዶ መንደር እንካ በእንካ ነው
 ጤፌን አውጥቼ ብሰልቅ ምነው” አለች ሴትየዋ፡፡
“…አሄሄ… ‘እናት ባዳ ሆነች’ አሉ! አሁን አንቺም እንደማያውቅ? እኔ እራሴ ስንት ችግር ላይ እንደከረምኩ.. በዚህ ላይ ገበያው ራሱ እንደ ዓይን ጠፍቷል፡፡ ከየት ይመጣል?.....” ብዙ ተስፋ የጣልንበት የናጠጠ ነጋዴ የሚባለው አጎታችን እንኳን እንዲህ ነበር ያሰናበተኝ፡፡ ወደ እህቴ ስደውል ግን በፍፁም ትዝ አይለኝም፡፡ ታዲያ እንዴት ድምጿን? ግራ እየገባኝ ስልኬን መፈለግ ጀመርኩ፡፡ አልጋው ላይ ተደፍቼ ነበር የተኛሁት፡፡ ስልኬን ከማግኘቴ በፊት ግን የቴዲ አስተኛኘት አስበርግጎ አስነሳኝ:: ሙሉ ለሙሉ በጀርባው ተዘርግቶ ነበር፡፡ በቆምኩበት ሰውነቴ የሟሟ መሰለኝ፡፡
“እንዴ ምንድነው? ቴድዬ! ቴዲ!” በድንጋጤ ጮህኩበት፡፡ እንዲህ ሲተኛ አልወድም፡፡ እንኳን እሱ በስጋት ላይ ያለው ጤነኛም ያስፈራኛል፡፡
“አ አንቺ፣ ደ--ደህና ነኝ! ት--ትንሽ ጎኔን ላሳርፈው ብዬ ነው? ተኝ ስልሽ እኮ እምቢ አልሽኝ፡፡” ድክም ባለ ድምጽ እየተናገረ፣ እግሩ ላይ የወደቀ ስልኬን በዓይኑ ሊየሳየኝ ሞከረ፡፡
“አይሆንም! አይሆንም! እባክህ እንደሱ አትተኛ! እንዳይጎረብጥህ አንሶላውን እደርብልሃለሁ” ተንደርድሬ ሻንጣ ከፈትኩና አንሶላ አውጥቼ ተመለስኩ፡፡
“ኡፍ! ኡፍ! ምን አይነቷ ልጅ ነሽ! አንሶላ አይደለም ችግሩ አንቺ! ብዙ ስተኛበት ጎኔን እያመመኝ ነው” እየተማረረ ተገላበጠ:: በዚህ ሁኔታ አይቼው ሰላም ልሆን አልችልም:: ይህ ደግሞ የእሱን ችግር እንዳልረዳው ያግደኛል፡፡
የእሱን ንጭንጭ ችላ ብዬ ስልኬን አንስቼ አየሁት፡፡ የእህቴን ቁጥር አልደወልኩም:: እና እንዴት ሰማኋት? በአግራሞት ዙሪያዬን ቃኘሁ፡፡ የተለየ ነገር አልነበረም:: ቢሆንም አጋጣሚው ሰዓቱ መርፈዱን ነግሮኛል፡፡ የጠዋቷ ፀሃይ ፍንትው ብላ በመስኮት ገብታለች፡፡ ለማንኛውም አሁን ቀሪ ሙከራዬን ማድረግ አለብኝ፡፡ ስልክ የመዘገብኩባቸውን ወረቀቶች ስብስቤ ይዤ ተነሳሁ፡፡ ከመኝታ ቤት ከመውጣቴ በፊት ግን የወንድሜን ሁኔታ ማረጋገጥ ይኖርብኛል፡፡ ልብሱን የማስተካክል መስዬ ቀርቤ አየሁት፡፡ ዓይኑን ገልጦ በግድ ፈገግ አለ፡፡ እሱም ለምን በየደቂቃው ከአጠገቡ እንደምሽከረከር ያውቅብኛል፡፡ ለዚህ ነው የማይሰማውን ደህንነት ሊያሳየኝ የሚጥረው፡፡
“እኔ እምልህ! ለእህት ተብያችን ልደውልላት እንዴ?” አልኩት፤ድምጼን አለስልሼ፡፡ በህልሜ የተናገረችው ነገር ከአዕምሮዬ አልወጣ ብሎኛል፡፡ በድንጋጤ አትኩሮ አስተዋለኝና፤
“ለማን? ለመንጠቆ!?” አለኝ፤ ያለ የሌለ ሃይሉን አጠራቅሞ እየጮኸ፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ገንዘብ አያያዟ ለየት ያለ ስለነበር ‘መንጠቆ’ ቤተሰቡ ያወጣላት ቅጽል ስሟ ነው፡፡ ድሮ ካየነው የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የተወሰደ የገፀ ባህሪ ስም ነበር፡፡ ከህመሙ ላይ ብስጭት የጨመርኩበት ስለመሰለኝ ደነገጥኩ፡፡ ቢሆንም መመለስ ነበረብኝ፡፡
“እና ሌላ እህት አለን እንዴ?” አልኩት፤ ልስልስ ብዬ፡፡
“እሷን እንደ እህት መቁጠር የጀመርሽው ከመቼ ወዲህ ነው? ወይስ ሰልችተሽኛል? እዚህ አስተኝተሽ ለምን ገንዘብ ታባክኛለሽ? ወስደሽ አታስቀብሪኝና አትገላለይም? እንድ…” ትንፋሽ አጥሮት አቋረጠ፡፡ ይሄም ለእሷ ያሰባሰበው አቅም ነው፡፡ ጥላቻው የሌለውን አቅም ይፈጥርለታል፡፡
ይህን ምግባሯን የሰሩት አባቴና ጓደኛው ይመስሉኛል፡፡ ከአባባ ጋር ተንጠልጥላ መውጣት ትወዳለች፡፡ እሱም ገንዘብ አያያዙ እንደሷው ነው፡፡ ዕቅዱ በእኔና ብሩኬ ላይ ስላልሰራለት እሷን ከጅምሩ ኮትኩቷታል፡፡ ምን ያህል ገንዘብ ለምን እንደሚያስፈልጋት ማቀድና መቆጠብ  የጀመረችው ገና በልጅነቷ ነው፡፡ ለእሷ ብቻ የገንዘብ ሳጥን ተገዝቶላት የሚሰጣትን የኪስ ገንዘብ እየቀነሰች ታጠራቅም ነበር፡፡ አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላት እናቴ በስሟ የባንክ ቡክ ከፈተችላት፡፡ እሷና ቁጠባ ቁርኝታቸው እንዲህ ነው፡፡
እኔና ቴዲ ደግሞ በሁሉም ነገር ከእሷ ተቃራኒዎች ነን፡፡ ይህ ተቃርኖ በጣም የከረረው ግን ከወላጆቻችን ሞት በኋላ ነበር፡፡ እናታችን ስትሞት በሁለታችን አምርራ አዘነች፡፡ በእናንተ ጥፋት ነው እናቴ ሳትታከም የሞተችው ባይ ናት፡፡ የአባታችን  በአደጋ መሞት፣ እናታችንን በሽተኛ አድርጓት ቆይቶ ነበር፡፡ ሃዘን ስላደከማት መተዳደሪያችን የሆነውን ሱፐር ማርኬት ለቴዲ አስረከበችው፡፡ አስራ ሁለተኛን ያለ ውጤት ጨርሶ አሸሸ ገዳሜ ላይ ነበር:: አጋጣሚውን ተጠቅሞ ጨፈረበት፤ ተዝናናበት! እኔ ግን ብዙውን ስለተጋራሁት እንደ ሳባ አላከረርኩም፡፡ ቢሆንም ብስጭቷ ገብቶኛል፡፡ አምላክ የወሰነውን ቀን መለወጥ ባይቻልም፣ እናታችን ጥሩ ህክምና ብታገኝ… ቀለቧን እንኳ ያጠራቀመቻትን እያወጣች ታማርጣት የነበረችው እሷው ነበረች፡፡
“ምን እያልክ ነው! አብደሃል እንዴ? እሷስ ብትሆን ይህን ያህል አውሬ ናት? ወንድሟን አውጥታችሁ ከእነ ነፍሱ ቅበሩ የምትል?” ሰውነቴ እየተንዘፈዘፈ ጮህኩ፡፡ ታናሻችን ናት፡፡ ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም የሚል እሳቤዋ ካላስወቀሳት በስተቀር፣ ሌላ ክፋቷን አላስታውስም፡፡
“እና ሰው ስለሆነች ነው ከእናታችን ቤት አውጥታ የጣለችን?” እንደገና በጩኸት ተናገረ፡፡ መናደዱ እየጨመረ መምጣቱ ስላሳሰበኝ ዝም አልኩት፡፡ የወላጆቻችን ቤት በእሷ ይፋ ጥያቄ ይሸጥ እንጂ ሃሳቡን ያመጣው እሱ ነበር፡፡
“ለእናንተ መተዳደሪያ ታክሲ ገዝቼላችኋለሁ፤ በተረፈው ውጭ ልሂድና እናንተንም እወስዳችኋለሁ!” ሲል ለእኔ አማክሮኝ ነበር፡፡ እሷ እንዴት እንደሰማች ግን አላውቅም፡፡ በወቅቱ ገና የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ ወደ ት/ቤትና ወደ መኝታ ክፍሏ ስትወጣና ስትገባ ከማየት በስተቀር እናታችን ከሞተች ወዲህ አናግራን አታውቅም፡፡ ሁኔታችን አስፈርቷት ይሁን፣ ነገሩን ደርሳበት አላውቅም፡፡ ብቻ ቤቱ ተሸጦ ድርሻዬ ካልተሰጠኝ ብላ ከሰሰች፡፡ ከዛ ውሳኔ በኋላ ነበር ከዘመድ መዝገብ ላይ የሰረዝናት፡፡ ከአመታት በኋላ ቤቱን መልሳ እንደገዛችው ብንሰማም እግራችን ወደዛ አልረገጠም፡፡ ዛሬ ግን ድምጿን በህልሜ ሰማኋት፡፡ ከሃያ ምናምን ዓመት በኋላ፡፡ እርግጥ ነው የመመረቋንም ሆነ፣ ጥሩ ሥራ የመያዟን እንዲሁም ጎን ለጎን የከፈተችውን ንግድ  ጭምር ሰምተናል፡፡
“እሽ ተወው በቃ! አንተ ካልፈለግህ አልደውልላትም” እንደ ህፃን እያባበልኩ ልብሱን አስተካክዬለት ስወጣ፣
“መደወል ሳይሆን አታስቢው! እሷን ልጅ ሳላይ ነው መሞት የምፈልገው፡፡ ይልቅ ለቀሩት ወገኖቻችንና ሞክሪ፡፡ እየተቆጣ ተናግሮ ሽፍን ብሎ ተኛ፡፡ እንዲህ ሲሆን ባዶነት ነው የሚሰማኝ፡፡ እሱን ካጣሁ እውነትም የባዶ ባዶ ነኝ፡፡ ቢቸግረኝ ወደ አልጋዬ ተመልሼ እንዲቀናኝ መፀለይ ጀመርኩ፡፡ ያቋረጠኝ የስልኬ ጩኸት ነበር:: አንዱ ቆጭቶት ሊረዳኝ የደወለ መስሎኝ በርግጌ አየሁት፡፡ ለማመን የሚከብድ ነው:: እሷ ናት፣ በድንጋጤ እየተርበተበትኩ የሚጮኸውን ስልክ ይዤ ወደ ወንድሜ ክፍል ገባሁና፤
“ክርስቶስን! የእናቴን ቀን ይስጠኝ! እመነኝ! መድሃኒያለምን! እውነቴን ነው! እኔ አልደወልኩላትም! እየው እራሷ!..” መሃላዬን እየደረደርኩ የሚጮኸውን ስልክ አሳየሁት::  ጨነቀኝ! እንዲያ እያስጠነቀቀኝ ደወለች፤ ብሎ ካሰበ እያመመውም ቢሆን ወጥቶ ሊሄድ ይችላል፡፡
“አላምንሽም! እስቲ ድምጹን ጨምሪና አንሽው!” አለ በተራዬ የተናገረውን ማመን አቅቶኝ አፈጠጥኩበት፡፡ ዝጊው ይለኛል ብዬ ነበር የጠበቅሁት፡፡
“እኮ አንሽዋ! ምን አስፈራሽ! አልደወልኩም አላልሽም?” በቁጣ አፈጠጠብኝ፡፡
“ሃ ሃ ሃሎ!” አልኩ እየተንቀጠቀጥኩ:: ከሃያ ምናም አመት በኋላ የታናሽ እህቴ ድምፅ ወደ ጆሮዬ ገባ፡፡
“ሄሎ እንደምን አለሽ ታባ! ሳባ ነኝ!” ቴዲ በግድ ቀና ብሎ እያዳመጠ ነው፡፡ “ደ-- ደ-- ደህና ነኝ! ደህና ነሽ” አልኩ፤ለዚህም እንዳይከፋው እሱን እሱን እያየሁ፡፡ ለእሱ ብዬ እንጂ እኔ ከሳባ ቂም አልነበረኝም፡፡ የራሷን የህይወት ዘይቤ ነው የተከተለችው:: ይህ ደግሞ ሰው አድርጓታል፡፡
“ደህና ነኝ ታባ፤ በእናታችን አጥንት ይዤሻለሁ እንዳትዋሽኝ! አንድ ነገር ልጠይቅሽ ነው፡፡ ወንድም ጋሼ አለ?” አለች፤ እምባ እየተናነቃት፡፡
“አዎ! እንዴ ምን እያልሽ ነው! ምን ሆነሻል?” ሞቱን እሷ የምታመጣው ይመስል በድንጋጤ ጮህኩባት፡፡
“እና ለምንድን ነው ደጋግሜ በህልሜ እያየሁት ያለሁት! እባክሽ ስለፈጠረሽ የእውነትሽን ንገሪኝ! ይግባሽ እሽ ለእኔም እኮ የእናቴ ልጅ ነው?” ጩኸቷ ብቻ ሳይሆን ለቅሶዋ በገሃድ መሰማት ጀምረ፡፡
“አላውቅልህም ልነግራት ነው!” የስልኩን ድምጽ አፍኜ፣ እያለቀስኩ ወንድሜ ላይ ጮህኩበት፡፡ ለካስ እሱም እያለቀሰ ኖሯል:: ምንም ሳይናገር እየተንሰቀሰቀ ፊቱን ሸፈነ:: ያፈንኩትን ስልክ ለቅቄ፣ እያለቀሰች ላለችው እህቴ እያለቀስኩ ወንድሜ ጉበቱ ተበጣጥሳ ከማለቋ በፊት ካልተቀየረች በቅርቡ እንደሚሞት እንደተነገረን በጭካኔ አረዳኋት:: ጮሃ ስልኩን ስትጥለው ይሰማኛል:: ከዚያ በኋላ ያናገረኝ ሌላ ሰው ነበር፡፡ እሱም አድራሻችንን ብቻ ወስዶ ዘጋ፡፡ የት እንደምትሰራና እንደምትኖር አላውቅም፡፡ ቤታችንን ትግዛው እንጂ እንደማትኖርበት ሰምቻለሁ፡፡ አደራረሷ ግን ጎረቤት የነበረች አስመስሏታል፡፡
“ለምንድን ነው ያልደወልሽልኝ?” የመጀመሪያ ጥያቄዋ ነበር፡፡ በህልሜ የሰማሁትን ተመሳሳይ ጥያቄ እያሰብኩ ዝም ስላልኩ እሷ ቀጠለች፡፡
“እናንተ ገንዘብ ለምን እንደሚውል አታውቁም፤ እና እኔን ልትወቅሱ አትችሉም:: እናንተ የልግስና ትርጉም ስለተዛባባችሁ፣ እኔን ክፉ አድርጋችሁ መራቅ የለባችሁም፡፡ ቆይ ገንዘብ እቆጥባለሁ ማለት ለአንድ ወንድሜ አልደርስም ማለት ነው? የእናቴ እያንገበገበኝ ወንድሜን ሸፍነሽ ትገይው?....” ለቅሶዋ፣ ጩኸቷ ቀጥሏል፡፡ እኔ ግን የምናገርበት አፍ አላገኘሁም፡፡ በዝምታ የምታደርገውንም፣ የምትናገረውንም መቀበል ጀመርኩ፡፡ ለጊዜው ሃገር ውስጥ አለ ከሚባል ሆስፒታል ነው ያደረሰችው፡፡ ለሌላውም ግን አልቆየችም፡፡
ምኑን ከምን እንዳሳካችው አላውቅም:: ሁሉንም አስጨርሳ ወደ ውጭ የላከችን በቀናቶች ወስጥ ነበር፡፡ እድሜ ዘመኗን ካጠራቀመችው በላይ የሆነ ብር ከመ/ቤቷ ተበድራ እንደጨመረች ሰምቻለሁ፡፡ ቤቱን ግን ደግማ አልሸጠችውም፡፡
ለዶክተሮቹ ሳይቀር አስጊ የተባለለት ሕክምና እንኳን ቅንነቷን አይቶ ነው መሰለኝ በማይታመን ስኬት ተጠናቀቀ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አገግሞ ወደ ሃገራችን ተመለስን፡፡
“እሽ አሁን እንዴት ነው የማያት? አውቃ የተወለደችውን እህቴን ለምን እንደኔ ብኩን አልሆነሽም ብዬ ደጋግሜ ጎድቻታለሁ? ከኋላችን ተወልዳ ገንዘብን እንዴት መጠቀም እንዳለብን ልታስተምረኝ በሞከረች፣ ደጋግሜ አሸማቀቅኳት፡፡ እኔ ሽጬ ልበትነው የነበረውን ቤት ቀድማ አውቃ ባተረፈች ብቻዋን ተሰቃይታ እንድታድግ ፈረድኩባት፡፡ እሽ አሁን እንዴት ብዬ ነው የማያት? ለምን እንድሞት አልተውሽኝም?...”
ሳባ ገንዘቧን፤ እኔ አካሌን ለግሼ ወንድማችንን ከሞት ማትረፍ ብንችልም፤ ከፀፀት ግን ማዳን አልቻልንም፡፡ በተለይ የተሳፈርንበት አውሮፕላን የአዲስ አበባን አየር መቅዘፍ ሲጀምር የእሱ ስቃይ ጨመረ:: እሷ ወዳና ፈቅዳ ያደረገችው በመሆኑ እንዳይፀፀት ብመክረውም ሊሰማኝ አልቻለም፡፡ በጥላቻ ርቋት የከረመውን ያህል በተቃራኒው አይኗን ለማየት ፈራ፡፡
እሷ ደግሞ ቅጣቱን ለማባስ የፈለገች ይመስል፣ ለበሽተኛ የሚያስፈልጉ ነገሮችን አሟልታ አየር ማረፍያ  እየጠበቀችን ነበር:: ቆሞ እየተራመደ ስታየው፣ እያለቀሰች መጥታ ተጠመጠመችበት፡፡
“እግዚአብሔር ደግ ነው፤ ሁለታችሁንም በሰላም አመጣልኝ፤ አንችም አስግተሽኝ ነበር:: አካልን ያህል ነገር ሰጥተሽ ስላተረፍሽው አመሰግናለሁ፡፡” እምባዋን እያፈሰሰች፣ እኔም ላይ መጥታ ተጠመጠመችብኝ፡፡


Read 2379 times