Saturday, 07 July 2012 10:03

የጥበብ ሀይል ከታዳሚ ይመነጫል

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

“አለም የተቀመጠችው (የታዘለችው) በአንድ ትልቅ ኤሊ ጀርባ ላይ ነው” አለ አንዱ ሰውዬ፤ አፈታሪኩን ተመርኩዞ/ተውሶ፡፡

“አለምን በጀርባዋ ያስቀመጠችውስ ኤሊ ምን ላይ ነው የተቀመጠችው?” ተብሎ እንደሚጠየቅ አልጠበቀም፡፡

“በሌላ ኤሊ ላይ!“

“ሌላኛዋ ኤሊስ በምን ላይ ተቀመጠች?” በጥያቄ ተከታተለው፤ አጥብቆ መርማሪው

“በቃ…እስከ ታች ድረስ ኤሊ ብቻ ነው!” ብሎ ፍርጥም አለበት፡፡

…ለማንኛውም አሁን የተቀመጠችበት ታውቋል፡፡ ለመቀመጥ ማስመቀጫ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ በስነ ስበት ህግ ተንሳፍፋ ተቀምጣለች፡፡ ተንሳፍፋ የተቀመጠችው አለም… እኛን ደግሞ መሬት አስረግጣ እያኖረችን ነው፡፡

ህልም የሚመስል ነገር አለው፤ በተንሳፋፊ ህዋ ላይ ተረጋግተን የመቀመጣችን ነገር፡፡

ዛሬ መፃፍ የፈለግሁት ስለ ህልም ነው፡፡ ስለ ህልም እና ከህልም ጋር ብዙ ቁርኝት ስላለው ጥበብ፡፡ ….እያወራሁ ያለሁት በነቃ አእምሮ ስለምናየው ህልም እንደሆነ ግልጽ ይሁንልኝ፡፡ …ተኝተን የምናየው ህልም ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ነው፡፡ አንዳንዶች ተተኝቶ የሚታይ ህልም የፈጣሪ መልዕክት ነው፤ ይላሉ፡፡ እንደ አባባላቸው ከሆነ… “ተነቅቶ የሚታይ ህልም ደግሞ የሰው ልጅ ፀሎት ነው” ብዬ ብጨምርበት… ከአባባላቸው አኳያ ብዙ ስህተት የሰራሁ አይመስለኝም፡፡

በቀን… በነቃው አእምሮ ስለሚታየው ህልም ተጨባጭ መመሰያ ያስፈልገኛል በዓይናችሁ አተኩራችሁ ከፊት ለፊታችሁ በግማሽ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አንድ ህንፃን እየተመለከታችሁ ነው፤ እንበል፡፡

በነቃው አእምሮ የሚያየው አይን (የብረቱ) …ማየት የሚችልበት የርቀት መጠን አለው፡፡ ፎቁን እንጂ በፎቁ መስኮት አልፎ ማየት አይችልም፡፡ ማየት ስለተሳነው፤ ከመስኮቱ ባሻገር እየተካሄደ ያለ ምንም ነገር የለም ማለት ግን አይደለም፡፡ ሳያዩ ማመን በህልም/ጥበብ አለም ብፁእነት ሳይሆን ጤነኝነት ነው፡፡ ማየት የማይችሉ… የጥበብ ድንቁርና ያለባቸው ሊኖሩ ይችላል፡፡ ህልም የማየት አቅም የሚሰጥ ክኒን ካለ… ቢውጡ ይመከራል፡፡

እንግዲህ ህልመኛው ይህንን ፎቅ ሲመለከት፣ ከፎቅነቱ ባሻገር ከመስኮቱ ጀርባ ስለሚካሄደው ነገር ማለም ከቻለ ያለመበት አይኑ የጥበብ ነው፡፡ ከማለም አልፎ፤ ስለ ህልሙ በተጨባጭ (በቅርጽ እና ይዘት አዋድዶ) መግለጽ ከቻለ፤ ህልመኛው ጥበበኛ ሆኗል፡፡ በነቃው አእምሮ የታለመ ህልም፣ በእንቅልፍ ወይንም ያልነቃ አእምሮ ላሉት አይሆንም፡፡ ፕሌቶ “man made dreams for those that are awake” ያለውም ሊገባን የሚችለው በዚህ አተያይ ብቻ ነው፡፡

እሩቅ ካለው ፎቅ መስኮት ባሻገር ያለውን (ህልም የማየት አቅምን በመጠቀም) የተገለፀ ህልም፤ እውነት ወይንም ውሸት መሆኑ ሊያሳስበን አይችልም፡፡ በዜና ላይ የተዘገበ ተጨባጭ ክስተትን በምንመዝንበት ሚዛን ከሆነ የለካነው… ህልም ሁሉ ውሸት ነው፡፡ የህልምን ውሸት ወደ ዜና (ዘጋቢ) እውነት ለመለወጥ አንዳንዴ የሳይንስ መግለጫ እንደ መሳሪያ ሊያገለግል ይችላል፡፡

ለምሳሌ፤ አጉልቶ የሚያሳይ የጦር ሜዳ መነጽር አይናችን ላይ ብንደቅን፤ ከመስኮቱ ባሻገር የሚካሄደው ነገር ወለል ብሎ ሊታይ በእርግጥም ይችላል፡፡ በዚህ መልክ ህልም ወደ ተጨባጩ እውነታ ገብቶ ሲደባለቅ፤ በአገልግሎት የህይወት ቋንቋ የተፈታ ህልም ይባላል፡፡

ህልምን ለመፍታት ህይወት ወይንም ሳይንስ እንደሚያስፈልገው፤ ህልምን ለመግለጽ ደግሞ ጥበብ ግዴታ ነው፡፡ ሁሉም ጥበብ ህልም (Illusion) ከመሆን ባሻገር…ህልሙ የሚገልፀው ነገር እና የተገለፀበት ቦይ (የመፍሰሻ መንገድ) አለው፤ ህልምን የመግለጫ አውታሮች ተብለው ይጠራሉ፡፡ ስዕል፣ ስነጽሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ግጥም፣ ቅርፃ ቅርጽ፣ ስነ - ህንፀ …ወዘተ፡፡ …ህልም በተጨባጩ ቋንቋ በነቃው አእምሮ ስለሚገለጽ “ሆን ተብሎ” የተከወነ Deliberate ነው፡፡

የጥበብን ህልም ለመፀነስ የሚደረግ ሙከራ ከባድ የሚሆነው… ምናልባት፤ ህልምን ለማርገዝ (ወይንም ራሳችንን ለማስረገዝ) የምንሞክረው በአካል አማካኝነት ስለሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይንም የህልም አገር ገፀ በረከቶችን …ገንዘብ በምንጨምርበት ኪሶቻችን ለመጨመር ስለምንፍጨረጨር ሊሆን ይችላል፡፡

H.G. wells እንደሚከተለው ይለናል፡- “The forces of our minds are clumsy things, and crush the truth a little in the course of taking hold of it”

የአእምሮአችን ጡንቾች ጨምላቃ ነገሮች ናቸው፤ አንዳንዴ እውነትን ለመጨበጥ በሚያደርጉት ሂደት ትንሽ ሊጨፈልቁት ይችላሉ፤ ነው፡፡ እንግዲህ የፈጠራ ህልምን ለሃሳቡ ለማስረገዝ ሲሞክርም የሚያደርሰው “Clumsyfication” አለ ለማለት ይመስላል፡፡ ብዙዎች ግን፤ ህልም እንደ እለት ተለት የአካል አለም የወሲባዊ ተራክቦ ፅንስ ማርገዙን ቀላል አድርገው ነው የሚገልፁት፤ ለእነሱ እንደውም የማዋለዱ ሂደት ነው ከባድ…፡፡…የተፀነሰው ሃሳብ በደም ፍሰት ሳይሞት እንዲወለድ ማድረጉ ላይ ነው አሳሩ፡፡

አንዴ ከተወለደ በኋላ ራሱን ችሏል ይባላል፡፡ አሳዳጊ አይፈልግም፡፡ ጥበብ ከህልም የሚለየው፤ በጥበበኛው የተወለደ መሆኑ ላይ ሲሆን፤ ከህይወት የሚለየው ደግሞ አሳዳጊ አለመፈለጉ ላይ ነው፡፡

የሰው ልጅ የህልም አቅም አለው፡፡ የህልም አቅም አለው ብቻ ሳይሆን…ቅድም ባወራነው አፈ ታሪክ ላይ ምድርን የተሸከመው ትልቁ ኤሊ… አሊውም በሌላ ኤሊዎች ጀርባ ላይ ተደራርቦ እንደሆነው ሁሉ፤ የሰው ልጅም ህልውና ተቀጣጥሎ የተሸመነው ከህልሙ ነው፡፡ ፈጠራ በሙሉ የህልም ውጤት ነው፤ ከጥበብ እስከ ሳይንስ፤ ከተስፋ እስከ ስልጣኔ፣ ከእምነት እስከ መንግስተ እግዜር… ጊዜ ራሱ ከህልም የተፈጠረ በሂደት እና በሳይንስ የማጉያ መነጽር የተቀመረ ህልም ነው፡፡ ራዕይም ለተጨባጩ ህይወት መሻሻል ሲባል የታለመ የህልም አይነት ነው፡፡ ህልሙ ታልሞ የሚቀር ወይንም ህልሙ እውነታን የመቀየር አቅም ያለው ሊሆን ይችላል፡፡

ህልም ለጥበብ መሰረታዊ ንጥረ ነገር ቢሆንም፤ ህልም ሁሉ ግን ጥበብ ይሆናል፤ ማለት አይደለም፡፡ ለህልም አለም እውን የሆነ ነገር ለጥበብ አለም እውነት ላይሆን ይችላል፡፡ ለጥበብ እውነታ (Art reality) እውነት የሆነ ነገር ደግሞ… ለህይወት እውነታ ህልም ወይንም ቅዠት ሊሆን ይችላል፡፡

በህልም አለም (Sub consciousness)  የተፈጠሩ ፍጥረታት በስዕል ሸራ ላይ ወይንም በሆሄያት ግዛት ህያው ሆነው ለማኖር አይቻልም፡፡ የህልም አለም ከልካይ የለበትም፡፡ ስፋቱም መጠን የለሽ… ህዋ ነው፡፡ የቃላት ወይንም የሸራ ስዕል አለም ግን ውስን ነው፡፡

ወሰን የለሹን በውስን መጥኖ ለማስቀመጥ ምርጫ ያስፈልጋል፡፡ ምርጫ የመወሰኛ ዘዴ ብቻ ሳይሆን ራሱም ውስን ነው፡፡ ሰው ሆነን በስፋት የማለም አቅም ቢኖረንም፤ ያለምነውን ወደ ጥበብ ለማምጣት የመምረጫ አማራጮቻችን ግን ውስን ናቸው፡፡

ይኼንን ውስን የመምረጫ አማራጭ ተጠቅሞ ከተለመደው ውስጥ ያልተለመደ….ከተሰለቸው Subject ተነስቶ ያልተለመደውንም መፍጠር መቻል ዋናው የጥበብ እውነታ እውነትነትን ማረጋገጫ መንገድ ነው፡፡

ይህ መመዘኛ “ውበት” ተብሎ በተለምዶ የሚጠራው ነው፡፡ የትላንቷ ጨረቃ በትላንቱ ገለፃ ከተፃፈች ወይንም በከርሞው አማራጭ ከተሳለች፤ ገለፃው የተደገመ በመሆኑ ግኝቱ እንዳልተፈጠረ ይቆጠራል፡፡ አንድ ህይወት አስመስሎ በአካል የሚወልድ ማህፀን (በመንታ መልክ ካልሆነ) እንደሌለው…የጥበብ ፈጠራም ሲደገም…ውበት ሳይሆን ኑሮ ሆኗል፡፡ ህይወት ስል፡- ማህበረሰቡ፣ የጥበቡ ተቀባይ … ጥበብ በሚፈጥረው ውበት አማካኝነት የራሱን ህልም የማየት አቅም የሚቀሰቅሰው ታዳሚ ማለቴ ነው፡፡

… በጥበብ አማካኝነት የሚገኙ ከራስ በላይ የሚያንሳፍፉ ስሜቶች (aesthetic experience) … ከጥበበኛው፣ ከጥበብ እና ከታዳሚው ህብረት ውጭ እንደ እየራሳቸው ውበት ሊሆኑ/ሊፈጥሩ አይችሉም፡፡

የደራሲው ህልም ወደ ድርሰት፤ መሬት በረገጡ ቃላት፣ ህግን በተከተለ ቅንብር እንደሚፈጠረው …የተፈጠረው ድርሰት … ወደ አንባቢ ተመልሶ ካልገባ፤ የውበት ሙሉ ማዕረጉን አይዝም፡፡ ምክንያቱም፤ የጥበብ ስራ የሚያፈልቀው ሀይል የሚመነጨው ከተቀባዩ (ከታዳሚው) እንጂ፤ ከራሱ ከጥበቡ ባለመሆኑ ነው፡፡ … ስዕሉን ስሎ ከሚያቃጥለው አርቲስት እና ስዕሉን አልሞ ሳይቀባ ከቀረው … ሁለቱም እማኝ ስለሌላቸው … ተራ ሰዎች ናቸው፡፡ ሁሉም ተራ ሰው የህልም አቅም አለው፡፡ …ጥበብ ውበትን የመመልከቻ መስኮትን ይሰጣል እንጂ ራሱ የመመልከት አቅም የለውም፡፡ ተመልካች የውበትን ህልም ያለ አመልካች (ጥበበኛ) እና መመልከቻ (ጥበብ) ለመቀበል አይችልም፡፡ The work of Art does not provide current, like an electricity company, but merely the installations, the current has to be generated by the consumer. ከሴት ልጅ መልክ፣ ቁመና፣ ጠባይ … ላይ የሚታይ ውበት … በተመልካቹ የተሰጣት እንጂ ራሷ ብቻዋን የምታሟላው አይደለም፡፡ … ብቻዋን ያለ አድናቂ በራሷ የቀን ህልም ውስጥ እንደታየች ቅዠት ናትና፡፡

 

 

Read 3058 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 10:19