Saturday, 11 April 2020 14:27

‘ፎርጀሪ’ እና የእኛ ነገር

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

    “ስሙኝማ…የፎርጀሪ ነገር ካነሳን አይቀር ስንት ዓይነት ፎርጂድ አለላችሁ መሰላችሁ! እንደውም እኮ ዘንድሮ አሱ ነው ያስቸገረን፡፡ ፈላስፋውም፣ አዳኙም፣ ጀግናውም በዛብን እኮ! ልክ ነዋ…ትናንት ያልነበረ ፈላስፋነት፣ ትናንት ያልነበረ አዳኝነት፣ ትናንት ያልነበረ ጀግንነት…አለ አይደል… እንዴት ነው በአንድ ሌሊት ሊሰፍርብን የሚችለው!”
     
               እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንደምንም እያቃሰታችሁም፣ እያማረራችሁም ለስንት ወር ያጠራቀማችኋትን የሆነች … አለ አይደል…ሦስት ዜሮ ወዳላት ድፍኗ ‘ሺ’ ልትጠጋ ምንም የማይቀራት ብር ትይዙና ሱሪ ሸመታ ገበያ ትወጣላችሁ፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ሌክሰስ መኪና እጅ በእጅ ሊገዛ የወጣውም፣ ነጠላ ጫማ በዱቤ ልንገዛ የወጣነውም እኩል “ገበያ ወጡ” ነው የምንባለው፣ አይደል! (በዚች፣ በዚች እንኳን ‘እኩል’ እንሁን እንጂ!)
እናላችሁ፣ ከሰው ለመመሳሰል እያለፋችሁ፣ እያገደማችሁ በባዶ ኪስ ብቅ ወደ ምትሉበት ሞል ትሄዳላችሁ:: ስሙኝማ…እግረ መንገድ፣ እነኚህ ‘ሞል’ የሚባሉ ነገሮች እዚህም እዛም ያሉት በጣም አይመሳሰሉባችሁም! አሀ…ልክ ነዋ፣ ከውጭ ወደ ውስጥ ስትገቡ ነው እንጂ አንዴ ውስጥ ከገባችሁ በኋላ ነገርዬው ሁሉ ከመመሳሰሉ የተነሳ “ጠዋት ስዞርበት ያረፈድኩበት ሞል ነው እንዴ ደግሜ የመጣሁት” ባያሰኝ ነው! ከሌሎች የሚለየው ምንም ነገር የለማ! እንደውም …የ‘ቪዥን’ ጉዳይ እያጭበረበረን ካልሆነ በስተቀር በየሱቁ የሚያስተናግዱን ወጣቶች ሁሉ እኮ እዛኛው ሞል ካሉት ጋር የመቶ በመቶ መንትዮች ሊመስሉ ምንም አይቀራቸው፡፡
ደግሞላችሁ…ስንት ከገበያና ከግብይት ጋር የተያያዙ ቃላት እያሉ ‘ሞል’ የሚሏት ነገር ሰርስራ ገብታ ቋንቋችን ሆነች አይደል! ሀሳብ ለማቅረብ ያህል፣ ለምሳሌ ‘ምን አለሽ ተራ በቦሌ’ ወይም ‘ምናምን በረንዳ በሳሪስ’ አይነት ነገር የማይባሉሳ! እናላችሁ ለሽለላ ኪስ ውስጥ የገባ የሚመስለው እጅ ብሮቹ በሆነ ተአምር ‘እንዳይተኑ’ ግጥም እንዳደረገ አንዱ ቡቲክ ‘ዘው’ ትላላችሁ፡፡ (‘ዘው’ በማለትና በ‘መግባት’ መካከል ልዩነት ያለ ስለመሰለን ነው፡፡ እነሱ ‘ይገባሉ፣’ እኛ ‘ዘው’ እንላለን…ፉልስቶፕ! ለምን ይዋሻል… አንዱ ጫማ የእኛ የሙሉ ቤተሰብ የስድስት ወር የቤት ወጪ የሆነበት ቡቲክ ስንገባ (ይቅርታ፣ ‘ዘው ስንል’) ትከሻችን ላይ የሚከብደን ነገር እንዳለ ልብ ይባልልንማ፡፡) እናማ…አንዱን የሚያውቃችሁን  ሰው ብቻ ሳይሆን አላፊ አግዳሚውን ኢምፕሬስ ያደርጋል የምትሉትን ሱሪ አገላብጣችሁ ታያላችሁ፡፡ በሆዳችሁ… “ናይን ሀንድረድ ምናምን ብር ይሆናል” እያላችሁ ዋጋ ትጠይቃላችሁ…
“እህት፣ ይሄ ሱሪ ስንት ነው?”
“ሦስት መቶ ሀምሳ ብር፡፡”
‘ምን! የትናንት ወዲያዋ ‘ቁንዲፍቱ’ አሁንም ከሲስተሜ አልወጣችም! እሷ ቁንዲፍቱ እኮ ለሌላ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያነት እንደ ጥሬ እቃ ነገር ተጠጥታ (ቂ…ቂ…ቂ…) በማግስቱ ወይ የመስማት ሀይል ታዳክማለች፤ ወይ ጉልበት ታዳክማለች! (ለነገሩ ሁሉም ‘መድሀኒት’… አለ አይደል… ‘ሳይድኢፌክት’ የሚሉት ነገር  አለው ይባል የለ!) ለነገሩ አሁን፣ አሁን እንዲህ ህዝቡ ሁሉ እየተረባረበ ሊሸምታት፡፡
ስሙኝማ… የፎርጀሪ ነገር ካነሳን አይቀር ስንት ዓይነት ፎርጂድ አለላችሁ መሰላችሁ! እንደውም እኮ ዘንድሮ አሱ ነው ያስቸገረን፡፡ ፈላስፋውም፣ አዳኙም፣ ጀግናውም በዛብን እኮ! ልክ ነዋ…ትናንት ያልነበረ ፈላስፋነት፣ ትናንት ያልነበረ አዳኝነት፣ ትናንት ያልነበረ ጀግንነት…አለ አይደል… እንዴት ነው በአንድ ሌሊት ሊሰፍርብን የሚችለው!
ማታ ቤታችሁ ሀገር ጤና ብላችሁ (ቢሆንም፣ ባይሆንም) ዓይናችሁን ቲቪ ላይ ተክላችኋል፡፡ መቼም ዘንድሮ በአንዱ ወይም በሌላው ቲቪ ጣቢያ ያልታየ ሰው መቼም የለም፡፡ “አንኳኩ ይከፈትላችኋል” ለቲቪ ጣቢያዎች ነው የሚሠራው፡፡ እናላችሁ “አሁን ይቺ ዜና አንባቢ መሆኗ ነው!” “ይሄኛው ደግሞ እ…እ…ማለት የሚያበዛው አንደኛውን አቃስቶ ጨርሶ አይመጣም እንዴ!” ምናምን እያላችሁ ይህንንም፣ ያንንም ስትተቹ ትቆዩና የሆና ቃለ መጠይቅ ሰዓት ይደርሳል፡፡  አቅራቢው ስክሪኑን ይሞላውና ገና መልኩ ያልታየውን እንግዳ ያስተዋውቃል፡፡
“ተመልካቾቻችን የዛሬው እንግዳችን በፖለቲካው ዘርፍ ሰፊ እውቀት ያላቸው ሲሆኑ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው:: ሆኖም ለረጅም ጊዜ ከፖለቲካው ተገልለው ከኖሩ በኋላ አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከአጋሮቻቸው ጋር አዲስ ፓርቲ አቋቁመው የፖለቲካ ምህዳሩን ተቀላቅለዋል፡፡
“እንግዳችን ጥሪያችንን አክብረው ስለተገኙ በእኔና በጣቢያችን ስም አመሰግናለሁ፡፡”
“እኔም አመ…”
ምን! ምን! ትንፋሽ ሳያሰሙ ጭጭ ብለው የተቀመጡ የቤተሰቡ አባላት ላይ ባዶ ሜዳ እናፈጣለን፡፡ “እስቲ ዝም በሉ፣ ልስማበት፡፡”
“እስቲ ቀደም ሲል ስለነበረዎት የፖለቲካ ተሳትፎ ጥቂት ነገር ቢነግሩን…”
እያያችሁት ያለውን ለማመን ውስጣችሁ ያለው ‘ሶፍትዌር’ በማን ይሁን በማን ‘ሃክ’ ተደርጎ መሆን አለበት!
ሰውየው ደረቱን ለመንፋት ‘ይሞክራል፡፡’ (የሌለ ነገር እንዴት ብሎ!)
“እውነት ለመናገር ወጣትነቴን በሙሉ በፖለቲካው ትግል ውስጥ ያሳለፍኩ ነኝ ብል ማጋነን  አይሆንም፡፡”
ይሄ ነገር “ወቸ ጉድ” በማለት ብቻ የሚታለፍ ስላልሆነ የሆነ ‘ፕሬቬንቲቭ ሜዠር’ ምናምን ነገር ያስፈልገዋል፡፡
“ማነሽ ያቺን ነጯን ነገር እስቲ አምጪልኝ::” የመብገን የመብገን ‘በነጯ’ መብገን ይሻላላ! አጅሬው ጭራሽ ቼ ጉቬራ ምናምን ነገር ሆኖ አረፈው! እና ‘ነጯ’ ትመጣላችሁና አብጋኞቹ ነገሮች አንድም ከመለኪያ፣ አንድም ከቲቪ! ሰውው እያወራ ያለው ነገር አለ አይደል…የሆነ የራሽያ ልብ ወለድ ምናምን ይመስላል፡፡ ‘ኸረ እባክህ ታሪካችንን የምንተዋወቅ ሰዎች ገና እኮ አላለቅንም! ዋ እንትን ሀገር ላለው የሀበሾች የሬድዮ ጣቢያ ደውለን ጉድህን እንዳናፍረጠርጠው!’
“እንደው መጀመሪያ ላይ ወደ ፖለቲካ ለመግባት እንዴት እንደወሰኑ ያስታውሱታል?” ከየዋህ ቃለ መጠይቅ አድራጊ ይሰውራችሁ፡፡
አጅሬ ሳቅ ይላል፡፡ “ምነ መሰለህ እኔ ራሴ ሳስታውሰው ሁልጊዜ ይገርመኛል::” እናላችሁ… ቆም ያደርጋል፡፡ ነገርዬዋ ‘ልብ ማንጠልጠል’ መሆኗ ነው፡፡ የዋሁ ጋዜጠኛ አድሜና ደሞዝ ጭማሪ ይስጠውና አጠንክሮ ይጠይቃል፡፡
“እንደው ተመልካቾቻችንም ማወቅ ስለሚፈልጉ ቢያጫውቱን፡፡”
አሁን ጉድ ሊሰማ ነው፡፡ እጃችሁን ሰደድ አድርጋችሁ የነጯ ነገር ጠርሙስ አለመራቋን ታረጋግጣላችሁ፡፡
“አንድ ጊዜ ምናልባት አስራ ሰባት ወይም አስራ ስምንት ዓመት ቢሆነኝ ነው:: በአራት ኪሎ በኩል ሳልፍ አንድ ወታደር፣ የሆነ ሊስትሮ ልጅ እንዲህ አንቆ ይዞት…” ቆም ያደርጋል፡፡ ግንባሩን ሁሉ ይከሰከሳል:: “ይቅርታ ምስሉ እስካሁን ትዝ ስለሚለኝ ነው፡፡”
የዋሁ ጋዜጠኛም ታሪኩን ጨርሶ ባልሰማው ነገር አብሮ ያዝናል፡፡ (‘አፕስቴርስ’ ያላችሁት…ቦነሱን እንዳትረሱበትማ!)
“ከዛም በዛ በወታደር ጫማ ወገቡን ሲለው ልጁ ፍግም ይላል፡፡ ብቻ ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡” ውይ መብገን! ውይ መብገን! “ብቻ እኔ ብው አልልህም!” ‘ነጯን’ እየገጩ ‘ኸረ አሁንም በድጋሚ ብው ባደረገህ!’ ልትሉ ታስቡና ትተዉታላችሁ:: ስንት ያልተወራረደ ሀጢአት እያለ ሌላ መጨመር አትፈልጉማ!
“ብቻ ሳላስበው ዘልዬ መሀል ገባሁና ምን አድርጎህ ነው የምትመታው ስል ጮህኩበት፡፡”
“እና ወታደሩ ምንም አላለዎትም?”
“ምን ይለኛል! እንደ ጉድ ደነገጠ ነው የምልህ!”
“ከዛስ…”
“ከዛማ ከየት መጡ ሳልል ምድረ አብዮት ጥበቃ አይከበኝ መሰለህ! እኔ ወንድምህ ወይ ፍንክች፡፡ በዛ ሰዓት አይደለም ዲሞትፈር የተሸከመ አብዮት ጥበቃ፣ ቤተ መንግስት የተገተሩትን ታንኮች ቢያመጡ ንቅንቅ አልልም ነበር፡፡”
“ከዛ ወደ እስር ቤት ወይ ወደ ሌላ ቦታ አልወሰዱዎትም?”
“መጀመሪያ ነገር ማን እሺ ብሎ ቢሄድላቸው!” በለው!
“ከወታደሩ ጋር የሆነ ነገር ተነጋገሩና ዝም ብለው ሄዱ፣ ሄዱ!”
“እርሶ ከዛ ምን አደረጉ?”
“ልከ ቤቴ እንደገባሁ ለራሴ ቃል ገባሁ:: ከእንግዲህ ለሰፊው ህዝብ ነጣነት እስከ መጨረሻው መስዋእትነት እታገላለሁ አልኩልህና ፖለቲካ ውስጥ ገባሁ፡፡”
ከቲቪው ሳይሆን ከገዛ ቤታችሁ የጣ ድምጽ ወደዚህኛው ዓለም የመጣ ይመስላችኋል፡፡
“አንተ ሰውዬ፣ ጠርሙሱን ሙሉ ገልብጠህ ልብህን ልታፈነዳ ነው እንዴ!”
ፖለቲካችን እኮ አለነገሩ እንዲህ የልጆች ሰኞ ማክሰኞ ጨዋታ ሆኖ አልቀረም!
‘ፎርጀሪ’ የአማርኛ ቃል ይሁንልን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2123 times