Saturday, 07 July 2012 10:25

የብርሃን ነፍስ

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(0 votes)

ፍልስፍናዊ ወግ

ብርሃን ሲተክዝ አጋጥሞህ ያውቃል? ካላጋጠመህ ዛሬ ይህን ጽሑፍ አንብበህ ስትወጣ ከልብህ አስተውለህ እንድታይ አግዝሃለሁ፡፡ ብርሃን የሚተክዘው ነፍስ ስላለው ነው፤ የሚደምቅ የሚመስለው ነፍሱን ከበርባሮስ (የጨለማ አለም) ደረት ላይ ሲያነግሰው እንደመሳቅ ሲያደርገው ነው፡፡ ሳቁ የመዝለፍለፍ ቅርጽ አለው፡፡ የነፍስ አንኳሮች የመቆሚያ ብሎናቸው የእርግጠኝነት ትርጉም ብቻ ነው፡፡ ብርሃን ስለት ስለሌለው መዋጋት አይችልም፡፡ አለመቻል እርግጠኝነትን የመገፈታተር መብት ተሰጥቶታል፡፡ ብርሃንም ነፍስ ስላለው ከበርባሮስ ላይ ከሚያሳርፈው የደረት ላይ እርግጫ ባለፈ የሚያረምምበትና እስከመቼ? ስለሚለው ደማቄ ሳቁ የሚያሰላስልበት ጊዜ አለው፡፡

ጊዜው የዘመን እንግልትን እያስቀደመ ፍፁማዊነትን ይጣራል፡፡ ፍማዊነትን ለመቀስቀስ የሚበቃ ድምጽ ካላወጣ በድምጽ ቢዝል እንጂ በንቃቱ አንድም የሀሳብ ርምጃ መጓዝ አይችልም፡፡ ስለዚህ ይተክዛል……….በምናልባት የተሸራረፈው ትካዜው የባዶነትን ርግጫ ማቆም ይችል በሚል ያለመጠረቃቀምና ያለመዝመት አዝማሚያን ተሸክሞ፡፡

ቢልለት ብርሃን ወጥ የሆነ የሰበካ ኮንፍረንስ ማዘጋጀት ይወዳል፡፡ ሰበካው የኮንፍረንሱን ሃያልነት የሚናገረው የሚያስተውል ቅን ነፍስ ፈልጐ ነው፡፡ ነፍስ የትም አለ፡፡ አንተ የሰው ልጅነትህን በመታበይ ቀርጥፈህ ይዘህ፤ ነፍስ ያለው በኔ ውስጥና በሆዴና በመጽናናት ስሜቱ ውስጥ ያሉት እንስሳት ጋር ብቻ ነው ትላለህ፤ ይህን ስትል አለማለትህን ትዘነጋለህ፤ አለማለትህ ውስጥ ያሉትን የቆሙ ትርጉሞች እየዘለዘልኩ በረሳኸው የህሊናህ ክፍል ውስጥ እንድበትን የተቀጠርኩ የረሳኸኝ ነፍስን ሆኜ ዛሬን እናገራለሁ፡፡ ብርሃን ነፍስ ኖሮት ሲተክዝ ድንጋይ ነፍስ ኖሮት ይፈራርሳል፣ ይጠነክራል፤ ብርሃን ነፍስ ኖሮት ሲቆዝም ያደረግኸው ጫማ ነፍስ ኖሮት እርግርህን ያቆመዋል፣ ያስበርደዋል፤ ብርሃን ነፍስ ኖሮት ሲዝል ሲጋራህ ነፍስ ኖሮት ይሰቃያል፣ ይሞታል፡፡

ብርሃን መተከዙን ስነግርህ ያልተናገርካቸውን የተንገላቱ ትርጉሞች ደግመህ እንድትመሰጥባቸው ላስገነዝብህ ፈልጌ ነው፡፡ ቅንጣትህን አለመርሳት ከተፈጥሮ እያንዳንዱ ሆኖ ለመቅዘፍና ለመኖር የሚረዳ የትካዜ ብልጠት ነው፡፡ ከቤትህ ወጥተህ የምታየው ቀለም በሙሉ ያንተ አይደለም፡፡ አስቲ ከቤትህ ውጣ….የፈለከውም ያልፈለከውም ቦታ ተሽከርከር….? ያኔ ላንተም ያልተሰማህን ነፍስህን ድምጽ እየሰማ የሚከተልህ ቀለም ታስተውላለህ፤ ያኔ የብርሃን ሳቅ ምን እንደሆነ ትረዳለህ፣ እርደው በፍርሃት በሽሽግ ውስጥ ያሉትን የበርባሮስ ቅንጣቶች ታስተውላለህ፤ ስታስተውል ግን አለማስተዋልህን አትርሳ፡፡ ተጨልፎ የማያልቀው ቅጽበትህን በቀስታ መርምር፡፡ ሁሌ ክፍተት እንዳለ አትዘንጋ፡፡ ነፍስ ያለው አካል በሙሉ ክፍተቱን ተሸክሞ እንደተንከራተተ ነው፡፡ ብርሃንም ክፍተት አለው፤ ለማስተዋል ይቀድማል…ካንተ ቀድሞ ብዝሀውን ክፍተቱን ሲመለከት ይተክዛል፡፡

ካልተናገርካቸው፣ ካላሰብካቸው፣ ካልሰማሀቸው የህላዌ ውዝዋዜዎች ውስጥ ጠሊቁን ስታደምጠው ከብርሃን የተላከን አንድ…ከቀለም ምድር የተላከ አንድ…ከእውነት ምድር የተላከን አንድ ይዘህ መተከዝህ የግድ ይሆንብሃል፡፡ ለንፁህ ነፍስ ትካዜ የመራመድ መልህቅ ነው፡፡ እንደተከዝክ በንፁህ ነፍስህ ውስጥ የብርሃን ሰበካውን ኮንፍረንስ ታደምጣለህ፤ ሳቅህ ሲዝለፈለፍ አትሳቅ፡፡ ለምን አትበለኝ? መጀመሪያ “ለምን?” አለማለትን እወቅ፡፡

ለነገሩ የብርሃን መተከዝ ለራሱ ይሁነው፡፡ ማንባቱ ለምንም ነገር ግድ የማይሰጠው ነፍስህ ላይ ምንም ተጽእኖ ካልፈጠረ ቃላት ሳታበዛ የላይ ቃላቶቼን በስሱ ሰድበህ እንደነገሩ በሃሳብ ተራምደህ እለፋቸው፡፡

……የጨለማን ርምጃ ተመልክተኸው ታውቃለህ? በጣም ይራመዳል፡፡ ሩጫው ወደ አይን ነው፡፡ ወደ አይን እየገፋ የሚወስደው ነፍሱ ነው፡፡ ጨለማ ነፍስ አለው፤ የማይሰማ፣ የማያይ፣ የማይጣራ፣የማያለቅስ ነፍስ፡፡ የነፍሱ አቅም ንፋስን የመግደል ያህል አቅም አለው…….ሁሉንም ነገር ወደ አለማሰብ የሚቀይር አቅም፡፡ ጨለማ የአየርን ቀለም መለወጥ ይቻለዋል…….ጥቁር አየር ያደርገዋል፡፡ ሃያልነትን በመናፈቅ ሰበብ የሚያገኘውን ስነፍጥረት በዝምታው ቅኔ ወደራሱ የመደባለቅ ፍጥነትን ራሱ አብዝቶ ለራሱ ጨምሯል፡፡ ጨለማ አዛዥ የለውም፡፡ ልክ እንደሀይማኖት ተጓዥ ነው፡፡ ትክክለኛው የሃይማኖት ተጓዥ፡፡ ነገር ግን የሀይማኖት ተጓዥ ትክክለኛ የጨለማን ርምጃ መግለጽ አይችልም፡፡ ጨለማም ምንም ቢጨልም፣ ምንም ቢፈጥን የሃይማኖት ተጓዡን ነፍስ መስተካከልም ማነስም አይችልም፡፡

ነፍስህን የማጨለም አላማ የያዝኩ ከመሰለህ ተሳስተሃል፡፡ ጨለማን በአይን ብልሃት መተርጐም የመጨረሻው የሀሳብ ክብደት ነው፡፡ ጨለማን ምን ደጋግመህ ብታስበው የሱን ሁለትና ሶስት እጥፍ በአዕምሮህ መቅረጽ አትችልም፡፡ አይደለም፤ ልገልጽልህ የፈለግሁት ስለመኖሩ ጥቁር ጣዕም ሳይሆን ስለርምጃው ፍጥነት ነው፡፡ ፍጥነቱ ያንተን ነፍስ ይወክላል፣ ነፍስህን መምከር ይችላል፡፡ ከላይ በጽሑፌ እንደተገለፀው፤ ጨለማ አይሰማም ብዬሀለሁ፡፡ ነፍስህን አለመስማት እንዲችል አስለምደው፡፡

ያኔ ፍጥነቱን ያገኘዋል፡፡ ያኔ ፍጥነቱን ያገኘዋል፡፡ ነፍስህ እንዳያይ አድርገው፤ ያኔ የራሱ የሆነ ቀመር ይዞ ከአይን ቀድሞ ለመተርጐም ይፈጥናል፡፡ ነፍስህ እንዳይጣራ ከልክለው፤ ያኔ በመጠራት ውስጥ ያለውን ርቀት በመገኘት ፍጥነት ውስጥ ሆኖ የመኖሩ ሁኔታ በሙሉ በድንገቴነት ተጀቡኖ የማንም ስነፍጥረት የሃሳብ አቅም ውስጥ ራሱን ሳያስገምትና ሳያስንቅ ይኖራል፡፡

ከጨለማ ርምጃውን ስረቀው፡፡ ነፍሱ የማይደገም ብቸኛው የአየር ላይ ንጉስ ነው፡፡ ጨለማው ንፋሱን ሲገለው አንተም የማያባሩትን የትችት ቅጽበቶች ከነፍስ በተላከ ያለመስማትና ያለማየት ስውር የወታደር ሀይል ከንፋሱ ውስጥ መግደል ትችላለህ፡፡ ጨለማው ርምጃውን ወደ አይን አደረገ ስልህ በሰውና በእንስሳት ላይ ብቻ ስለታተመው ልሙጥሙጥ ብልት እያወራውልህ አይደለም፡፡ ነገርኩህ፤ ነፍስ የትም አለ፤ ነፍስ ባለበት ሁሉ አይን አለ፤ አይን ባለበት ሁሉ የጨለማ ርምጃ አለ፡፡ ፍጥነቱ ውስጥ ፍቅር አለ….የበላይነትንና የአንድነትን ህብር የማግኘት ፍቅር፡፡ ፍላጐት ስደት ሆኖ ቢገኝ ጨለማው ፍጥነቱን ገዝቶ ባደረቀው ነበር፡፡ አየህ ሚስጥሩን አብረን ስንፈታው፤ ባንፈታው እንኳን የሃሳብ ወቅታችንን ጠብቀን በቃላት ስንፎልል፡፡ የገለጠከውን ምዕራፍ እየከተለ ህላዌ ይነበባል፤ ራሱን ያነባል፡፡

ሁሌ ስደት ላይ ያለህ እንዳይመስልህ ቃላቶች አበደርኩህ፡፡ ቃላቶቼ ካበዱብህ የመጠጋት ፍልስፍና ይገባሀል፡፡ የጨለማ እርሻ መሀል ሆነን ከብርሃን የሸሸገውን አዝዕርቱን ስንለቃቅምለት ጊዜ የማይፈታው ጥቁር ሚስጥሩ እየዘለለ በረሳነው ህሊናችን ውስጥ ይነጥራል፡፡ ህሊናህ እርጥብ ይሁን፤ አንዳንድ የሚግሉ እውነቶችህን ያቀዝቅዝልህ፡፡

መሀለኝነት ውስጥ ሆኖ ቀጥኖ መኖር የእርምጃህን ብዛት እየለቀምክ እንዳትቆጥር ይጋብዝሃል፡፡ የእርምጃው እኩልነት እንደጨለማ ፍጥነት በተራማጁ ነፍስ ብቻ እየተቀኘ ወደማይተረጐመው የኑሮ ጉድጓድ ይግባ፡፡

…….ሰማይ አንዲያኮርፍህ እድል ስጠው፡፡ ካላኮረፈህ የማይታዩ ረቂቅ ነፍሳት የሚኖሩበትን የጉም ህንፃዎቹን መመልከት አይቻልህም፡፡ ብዙ መናገር ፈልጐ ድምጹ ሳይሰማለት ቀርቶ በዝናብ ብቻ ግጥሞቹን የሚደረድር ምስኪን ስነፍጥረት ሰማይ ብቻ ነው፡፡ ሰማይን የሚወክል አንዳችም ነገር የለም፡፡ አለመመሳሰሉን ራሱ ሰማዩ አያውቀውም፡፡ ሰማዩ አለማወቅን ያልተገነዘበው ነፍስ ስላለው ነው፡፡ የቀን ጥሪዎችን አድምጠህ ታውቃለህ? የቀን ጥሪ ካለ ሰማይ አለ፡፡ ሰማይ ካለ ነፍስ አለ፡፡ አስታውስ ወዳጄ! ሁሉም ነፍስ አለው፤ ነፍስ ያለው ሁሉ ያኮርፋል፡፡

ሰማይ የሚያስኮርፈው አለመታየቱ ነው፡፡ ወቀሳው ወደ ላይ አይሄድም፣ ታች ካሉት ጋር ብቻ ይጋጫል፡፡ ግጭቱን በዝናብ ይገልፃል፡፡ ሰማይ እንዲያኮርፍህ እድል ከሰጠኸው መለማመድ ውስጥ ትገባለሀ፡፡ ልምድ ዜማ አለው፣ ቀለም አለው፣ ዝምታ አለው፡፡ ስፍራ የሚፈልግ በሙሉ የፍላጎቱ ጥሪ ውስጥ ብቻ የማይገኝ ሌላ መጣሪያ ስስ ድምፅ ያስተጋባል፡፡ በቋሚነት ሰማይ የሚፈልገው መታየትን ነው፣ ማኩረፍ የሚፈልገው የመታየቱ ጥሪ ዘግይቶ ይደርስ ብሎ ከመስጋት ጥበቃ ነው፡፡

አንተ አለመታየትህ ስጋት ሆኖብህ የሌሊት እንቅልፍህ ቅጥሩ ሲጣስና በማይገቡህ መናፍስት ስትነጠቅ፣ እንደ ባህር ከነፍስ ስትወራጭ አለማየትን ብመርጥ የሰማይ ኩርፊያን አበድሬህ በልምዴ ልጠጋህ ፈለግሁ፡፡ አሜን ብሎ የሚቀበል ትካዜ ስላለህ የትካዜህ ባጧጭ የሆኑትን በቃላት ዘመቻ ልገታልህ ---- ሰማዩ ጉም ለንቦጩን እንደዘረጋ ምንም ማሻሻያ ሳላደርግልህ አቀረብኩልህ፡፡ ጥያቄህ ውስጥ ተሰውሮ መዝናናት ፈልጎ ወጥቶ ድንገቴ መዘላበድ ሳያመጣብህ ልጠነቀቅልህ አሰብኩና አስቀድሜ ስውር እርግዝናህን አፋጠንኩት፡፡ ያለወቅቱ የሚመጣ የጥያቄ ምጥ ምክንያትነቱ እየተንቀራፈፈ ከሚመጣው መልስ ጋር ህብር የለውም፡፡ ህብሩ ያለው የጥያቄውን ሆድእቃ ከረገጠው ጋር ነው… ረጋጩ እኔ ነኝ፡፡

ራሱን ተርጉሞ ከማያውቅ የሰማይ ስብዕና ጋር እየወረወርኩ የማላትምህ ስለገባኝ ነው፡፡ ከማየት ውስጥ መታየት እንዳለ ገባኝ፡፡ ከመጠራት ውስጥ መጣራትን ተስሎ አየሁት፡፡ ሩቅ ንዝንዝ መቅረብ የሚፈልገው ከተሟጋቹ ቀድሞ በማኩረፍ ነው፡፡ ኩርፊያ መጠጋት ማለት ነው፡፡ ቅርፁ እንደ አየር ነው፡፡ የማይታይ ጠሪ የሚታይ መቅረብ ነው፤ ስለዚህ ቀና በል፡፡

የመጀመሪያ አስተዋፅኦህን አበርክት፡፡ ማየት ማፍቀርን ብቻ ይወክላል ብለህ የምናብ መፈክርህን አንሳ፡፡ ከእናትህ በላይ ያለው ክቡድ ኩርፊያ በአይን ላይ ባለ የማየት ጥሪ ብቻ ካለማሰብ የተገመደ ቡፍ የሚል ሳቅ ይፈጥራል፡፡ አለምን ያንተ እኩያ ማድረግ አስቆ በመሳቅ የሚገኝ የምናብ ብልሀት ነው፡፡

የማይታይ ነገር “ነገር” አለው በል፡፡ ካላልክ ሰማዩን ተጠያቂ አታድርገው፡፡ በተመሳሳይ መልኩም አንተን መስማት የከበደው ማህበረሰብ ከከበበህ ቅደመው … አኩርፈው፡፡ ማኩረፍ ውስጥ መዳን አለ ወዳጄ፡፡

ማልቀስ ውስጥ እፎይታ አለ፣ መጮህ ውስጥ የሚያቃጥልህን ጥም በቀለም የመሙላት የከንፈር ጥሪ አለ፡፡ አኩርፈህ ግን ጥሪህ ካልተሰማህ ዝነብ፡፡ ምንም ያህል ብትበርድ … ምንም ያህል ብታንዘፈዝፍ ከድምፅህ ውጭ የመኖር ብልሀትን ሰማዩ ስላልለገሰህ በመሆኑ ለሚራደው አካል ሀዘኔታ አይሰማህ፡፡ ጥሪው የውጭ አካል ላይ ብቻ ስለሚመላለስ ለማንም ነፍስ መፈራረስ ተጠያቂ አትሆንም፡፡ ድምፅህ አስተጋቢ አይኑረው፡፡

ሰማዩ እየተናገረ ንፋሱም ከተነጫነጨ ታላቅ ጥፋት ይከሰታል፡፡ ሀጥያት የምትለው ብዥታህ ከድምፅህ ውጭ ሆነህ ሌላ ቅርፅ የለሽ አጎብዳጅ ስትጠቀም የሚመጣ የስሜት ቅጥፈት ነው፡፡ ቅጥፈትም አንተን ያልሆነ ነገር ብቻ ነው፡፡

… የመምከር አባዜ የብቸኝነት ቅርፊት ላይ ላይፋቅ የተፃፈ ወግ ነው፡፡ መፈራት የመሸሻ መለከት ሲነፋ ጆሮህን አቅንተህ የምትከተለው የአየር ንጥረ ነገር ነው፡፡ መለከቱ ጥሪቱን አሟጦ በድምፅ የሚተጋው ማለቂያ ቦታ ስለፈለገ ነው፡፡

ይህን ጽሁፍ የምታነብ ማንኛውም ፍጡር ብትሆን ከመለከቱ ጠቀስ በላይ ማሰብ አትችልም፡፡ ከድምፅ ውጭ ያለውን ማድመጥ ብትፈልግ ፅሁፎቼ አይንህ ላይ እየተፈራረቁብህ ዜማ ይስጡህ፡፡ ዜማቸው ምክርን ብቻ ይለፍፋል … ርቀት መጓዝና ፈዞ መጥፋት የማይፈልገውን ምክር ብቻ (የጨለማ መንታ መሆን ቢያሰኘኝ)

… የመምከር አባዜ የብቸኝነት ቅርፊት ላይ ላይፋቅ የተፃፈ ወግ ነው፡፡ መፈራራት የመሸሻ መለከት ሲነፋ ጆሮህን አቅንተህ የምትከተለው የአየር ንጥረ ነገር ነው፡፡ መለከቱ ጥሪቱን አሟጦ በድምፅ የሚተጋው ማለቂያ ቦታ ስለፈለገ ነው፡፡ ይህን ፅሁፍ የምታነብ ማንኛውም ፍጡር ብትሆን ከመለከቱ ጠቀስ በላይ ማሰብ አትችልም፡፡ ከድምፅ ውጭ ያለውን ማድመጥ ብትፈልግ ፅሁፎቼ አይንህ ላይ እየተፈራረቁብህ ዜማ ይስጡህ፡፡ ዜማቸው ምክርን ብቻ ይለፍፋል … ርቀት መጓዝና ፈዞ መጥፋት የማይፈልገውን ምክር ብቻ (የጨለማ መንታ መሆን ቢያሰኝ)

ግን የኔነቴ ግልጦት የቃላት ጨዋታን ማሳመሪያ የሀሳብ ህግ እንዳይሆን እኔም እፈራዋለሁ፡፡ ዳኛ በሌለበት የራስ ቡድን ፈጥሮ እንደልብ በሀሳብ ሜዳ ላይ መራወጥ የሚያመጣውን ድካም ለመጀመሪያ ጊዜ ባንተ ላይ እየሞከርኩብህ በመሆኑ የነገህ ትካዜህ ላይ እየመጣ ለሚደነቀረው የምንምነት እንቅፋት ፈጣሪ እንዳታደርገኝ እፈራለሁ፡፡ የምራመድበት መንገድ እንዳለኝ አትዘንጋ፡፡ አለችኝ የምላት መንገዴ ውስጥ ማንንም አለመፈለጌ የቃላት ድንጋጤ ፈጥሮብኝ፣ እያወቅሁ ሳላውቅ በፃፍኩት ፅሁፍ ውስጥ ገብተህ መንገድህን እንዳትስት እፈራለሁ፡፡

ከንፋሱም ትንፋሽ እየተበደርኩ፣ በፅሀይዋን በሽታ እየተሰቃየሁ፣ የጨረቃን መከራ እየተቀበልኩና በዝናብ መንታ አለም ተመላልሼ እውነትን አገኘኋት ለማለት ድፍረት ቢጤ ማግኘቴን አንተ እንድትነግረኝ ልቀርብህ ፈለግሁ፡፡ ተነባቢው አካል መጠቀም የሚጀምርበት ዘመን መፍጠር አምሮኛል፡፡ ሚስጥሬን እየገለጥኩት ሚስጥር ሆኜ ልናገር ያንቀዠቅዠኛል፡፡

ይታዩ በሚመስሉ፣ ከሰው ስብዕና ጋር የሚስተካከሉ ብዝሀ የምድር ስርና ላይ አካላት እስከ ቆዳዬ ድረስ እየደረሱ ከነፍሰ - ብርሀኔ ላይ የመስተዋል ቤት ተከራይተው መኖር ሲጀምሩ ያዲስነት መንፈስ የደስታ እከኬን ካንተ ጥሩ የህይወት አምድ ላይ አራግፈዋለሁ፡፡ ፈቅደህ ስታነብ መቀራረብ ይሆንሀል፡፡ ስትቀራረብ እውነት ምናልባት በመጠኑ ሊሟዘዝብህ ይችላል፡፡ ቁስ ያልሆነ የመንፈስ ቅርቦሽ እንደ ድር ሲተበትብህ አታውቅም፡፡ ሰማያዊ ጥላሸት እስክትመስል ድረስ መወረወሩን ካልተገነዘብከው ከእውነት ጋር እየተሟዘዝክ ትቀራረባለህ፡፡ ድሩ እድሜውን ጨርሶ መዘውሩ ሲያረጅ ያኔ ወደፊት ለመሄድ በምታፈጥንበት የአዲስነት መንገድ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለም፡፡

ሽርፍራፊ ምክር ብዙ ነው፡፡ የሚረዝም ምክር ይረሳል፡፡ ከህልምህ ጋር ቀለበት ስታስር ለህይወት መደራጃ ብለህ የምትሰበስበው የምክር አስቤዛ የማያልቀው አይነት እንዳይሆን ተጠንቅቀህ ለአንገትህ ምክር ስጠው፡፡ ይሄ አንገትህ የማይሄድበት የወረቀት መንደር የለም፡፡ የወረቀት መንደርተኞችን የፈጠራቸው ብዕር ቢሆንም ፈጣሪያቸው ላይ መልሰው የሚያምፁ፣ ነገር ግን ማንም የማያዳምጣቸው አይነቶች እንደሆኑም አትዘንጋ፡፡ አንተ ትጉህ አንባቢ … አንተ ትጉህ የወረቀት መንደር ደንበኛ … አንገትህን የሚያዘውን ሀይል አመስግን፡፡ ሀይሉ ከብርሀን፣ ከጨለማና ከሰማይ ላይወጣ ይችላል፡፡ ሶስቱ ስነ ፍጥረቶች ከህይወት ዳርና ዳር የተለጠፉ ቅንፎች ናቸው …. ህይወትህ ለአንድ ቃል ተብሎ የተብራራ እንደሆነ ሊነግሩህ የሚመላለሱ ቅንፎች፡፡ ነገር ግን የላይ ንግግሮቼ ምንም ግድ ለማይሰጠው ጭንቅላትህ ተመጣጣኝ የመሆን አቅም ከሌላቸው፣ ቃላት ሳታበዛ በስሱ ሰድበህ እንደነገሩ በሀሳብ ተራምደህ እለፋቸው፡፡

 

 

Read 1920 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 10:33