Saturday, 25 April 2020 13:17

የ‘ክፉ ቀን’ ክፉ ነገር

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 “-ጉድ እኮ ነው! ሰዋችን ለአንዲት ዶሮ ስምንት መቶና አንድ ሺህ ብር የሚጠየቀው ከሌላው የዓለም ህዝብ የተለየ እርግማን አለበት እንዴ! ለስደት የመን ድንበር በእግሯ ደርሳ፣ በእግሯ የተመለሰች የምትመስል ‘በግ’፤ ስድስትና ሰባት ሺህ ብር የሚጠየቅባት ውስጧ የተደበቀ ‘ጎልድ’ ‘ዳይመንድ’ ‘ሜርኩሪ’ ምናምን ነገር አለ እንዴ!?-”
      
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ልጁ የፊት መሸፈኛ እየሸጠ ነበር፡፡ የሆነ ሸለል ያለ ሰውዬ አቅራቢያ ከነበረ የኤሌክትሮኒክስ ሱቅ ይወጣል፡፡ ልጁን ዋጋውን ይጠይቀዋል፡፡
“ሠላሳ ብር፡፡”
ከዛላችሁ…እንድ ነጣ ያለውን ይቀበለውና ከትንሽዬ የፕላስቲክ ከረጢት አውጥቶ አገላብጦ ያየዋል፡፡ እናላችሁ…አገላብጦ ሲያይም በጣቶቹ ጫን፣ ጫን እያደረገ ነበር፡፡ ከዛ አንደኛውን አፍና አፍንጫው ላይ አድርጎ ይሞክረዋል፡፡ ከዛ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው… የሞከረውን አውልቆ ለልጁ ይመልስለትና ሌላ ቡኒ ቀለም ያለው መሸፈኛ ተቀብሎት፣ ሠላሳ ብሩን ይከፍልና ቆማ ወደነበረች ለክፉ የማትሰጥ መኪና ይገባል፡፡ ጉድ እኮ ነው!
ምን ማለት ነው! እንዴት ፊት መሸፈኛ አይነት ነገርን በራሱ አፍ ላይ ካደረገ በኋላ ይመልሳል! የአንዳንዱ ሰው ግዴለሽነት የሚገርም እኮ ነው፡፡ ሌላኛዋ ጎልማሳ ቢጤ ሴት ደግሞ ሶሰት አራቱን እያወጣች በእጆቿ እየጨማመቀች ከሞከረች በኋላ አንዱንም ሳትገዛ ትሄዳለች፡፡ ይቺ ሴት እንግዲህ ስንቱን ነገር ስትነካካ አርፍዳ ይሆናል፡፡  እኔ የምለው እንደው በቃ ‘ክሎዝ’ ማሳመር ብቻ ነው! በአሁኑ ዘመን፣ ያውም ከንክኪ ጋር በተያያዘ ስንት ነገር እየተነገረ ባለበት ጊዜ፣  እንዲህ የሚያስቡ ሰዎች መኖራቸው አስቸጋሪ ነው:: አንዱ በራሱ አፍ ላይ ሞክሮ የተወውን የፊት መሸፈኛ ሌላኛው ሰው ሲጠቀምበት አይታያችሁም! በእያንዳንዳችን ላይ እኮ ስንትና ስንት ነገር አለ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በዚህ በሸመታ ጉዳይ ላይ…አለ አይደል….ከዘመኑ ጋር በተያያዘ መለወጥ ያሉብን መአት ነገሮች ያሉ አይመስላችሁም! ለምሳሌ ትናንት ምሳ ላይ ከቃሪያ፣ ከነጭ ሽንኩርት ከምናምን ጋር ወደ ምግብ መፈጨት ስርአት የተላከችው ቲማቲም፣ ስንቱ እጅ እንዳረፈባት ማን ያውቃል:: እዚህ አገር እኮ ሻኛና ምናምን በነካ፣ ነካ እየተፈተሸ የሚሸመተው በግ ብቻ ሳይሆን እነ ቲማቲምም ናቸው፡፡ የምር እንዲህ አይነት ነገሮችን መለወጥ መቻል አለብን፡፡ ወይም በስነስርዓት በተለያየ መጠን እየታሸጉ የሚሸጡበት ሁኔታ  መፈጠር አለበት፡፡
እኔ የምለው…ብዙ ጊዜ የልብ ጓደኛ የሚባለው የሚለየው፣ የእያንዳንዳችን እውነተኛ ባህሪይ ‘ተቆፍሮ’ የሚወጣው በክፉ ጊዜ ነው ይባላል፡፡ በደህናው ጊዜ፣ ህይወት ዝም ብላ በምትፈስበት ጊዜ ብዙ የሚፈትኑ፣ ወይም “አግዘኝ፣” “ተባበሪኝ፣” የሚያስብሉ ብዙ ነገሮች ላይኖሩ ይችላሉ:: ነገርዬው የሚመጣው በችግር ጊዜ ነው፡፡
እሱና እሱ ጓደኞች ናቸው፡፡ ‘ከመቀራረባቸው’ የተነሳ ‘ጣጥ’ ሲሉ እንኳን በጋራ ነው፡፡ ታዲያ የሆነ ጊዜ አንደኛው ችግር፣ ማለትም የ“ቢራ ጠምቶኛል፣ ግን ኪሴ ባዶ ነው” አይነት ችግር ሳይሆን ከበድ ያለ ችግር ይገጥመዋል እንበል፡፡ እናላችሁ… በደህናው ጊዜ ለ‘ድሪንኩ’ና… አለ አይደል… ‘ተያይዘው ለሚመጡ ተጓዳኝ ፍላጎቶች’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ‘ስፖንሰሩ’ እሱ ነው:: እናላችሁ የሰው እገዛ የሚያስፈልገው ችግር ይገጥመዋል፡፡ መጀመሪያ ሊሄድ የሚችለውም የልብ ጓደኛው ዘንድ ነው፡፡
“ስማ የሆነ ችግር ገጥሞኛል፡፡”
“ምን ሆንክ፣ ከሰው ተጣላህ እንዴ?”
አሁን ከሰው መጣላትን ምን አመጣው! አጠያየቁ “አዎ እባክህ መሥሪያ ቤት ከሆኑ ሰዎች ጋር ተጋጭቼ…” ምናምን ነገር ቢለው ኮቱን እያወለቀ… “የትኞቹ እንደሆኑ አሁኑኑ አሳየኝና የማደርገውን እኔ ነኝ የማውቀው፣” የሚል ነው የሚመስለው፡፡
“እንደሱ ሳይሆን የባለቤቴ ነገር አሳስቦኝ ነው…”
“ምን ሆነች! ተጣላችሁ እንዴ!” ሰውየው ጥል፣ ጥል የሚለው ምን ነክቶታል!
“ተጣልተን ሳይሆን ሆስፒታል ገብታ ኦፕሬሽን መደረግ አለብሽ አሏት…”
“ኦ!…”  ምን!? ኦ ብቻ ነው ምላሹ! ከሰዎች ከመጋጨት ይህኛው ችግር አይብስም? ምን መሰላችሁ… ‘የልብ ጓደኛ’ ሆዬ ቀጥሎ የሚመጣውን ነገር ጠርጥሮ ሊሆን ይችላል::  
“ለምን መሰለህ አንተን የፈለግሁህ፣ ለጊዜው እጄ ላይ ያለውን ገንዘብ ስለጨረስኩ አንድ አስር ሺህ ብር እንድትፈልግልኝ ነው፣ በሦስት አራት ቀን ገደማ ይመለሳል፡፡”
እናላችሁ፣ ይሄን ጊዜ ጓደኝዬው በሀዘን (ወይም ‘ሀዘን በሚመስል ነገር) ፊቱ ኩምትር ይላል፡፡ ልክ የዛሬ አስራ ስምንት ዓመት የሞተ ዘመድ ትዝ ብሎት ሆዱን ባር፣ ባር ያለው ነው የሚመሰለው፡፡
“የሚገርምሀ እኔ ራሴ አንድ አጣዳፊ የቤተሰብ ጉዳይ ገጥሞኝ ገንዘብ ከማን ነው የምጠይቀው እያልኩ፣ እንደውም ልደውልልህ ስል ነው አንተ ደውለህ የጠራኸኝ…” 
ጓደኛውም “እሱን ራሱን ቸግሮትማ አላስጨንቀውም፣ ሌላ ሰው እፈልጋለሁ፣” ይላል፡፡ ታዲያላችሁ… በማግስቱ ግን ‘ታሪካዊዋ’ የስልክ ጥሪ ትደርሰዋለች፡፡
“ስማ፣ ያ ጓደኛህን አንድ ነገር አትሉትም እንዴ! ምን እየሆነ ነው?”
“ምን ሆነ?!”
“በልክ አይጠጣም እንዴ!”
“ምን እያልከኝ ነው?”
“ይሄንን ውስኪ ገጭቶ፣ ገጭቶ ከሰዎች ጋር ጠብ አይፈጥር መሰለህ! ደግሞ ሰዎች ብልህ ዝም ብለው ሰዎች መሰሉህ፡፡ የፈለጉትን ሊያደርጉ የሚችሉ ናቸው፡፡”
“እና መጨረሻ ምን ሆነ ነው የምትለኝ!”
“እንደ ምንም አባብለን በመኪና ቤቱ አደረስነው፡፡ የእሱ መኪና እዛው ቡና ቤቱ ግቢ ውስጥ ነው ያደረችው መሰለኝ፡፡”
እናላችሁ…ያ አጣዳፊ የቤተሰብ ጉዳይ ገጥሞት ገንዘብ አስፈልጎት የነበረው ሰው፤ በውስኪ ሰክሮ ጭራሽ በሀምሳ ምናምን ኪሎው ያለ ክብደቱ ከባለ ሰማንያ ኪሎዎች ጋር ጠብ ፈጥሮላችኋል፡፡ የልብ ጓደኛዬ የሚለው ሰው ግን ባለቤቱ አልጋ ላይ ውላበት ምንም እገዛ ሊያደርግለት አልሞከረም፡፡ እናላችሁ… ክፉ ቀን እውነተኛ ማንነታችንን ፈልፍሎ የሚያወጣ ነው:: ይኸው ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ፣ ሀገር በተጨነቀበት ጊዜ፣ ስንቶቻችን አይደለን እንዴ የ‘ፋስት መኒ’ ሩጫ ላይ ያለነው!
ስሙኝማ…የብዙ ነጋዴዎቻችን በተለይ ከበዓል ጋር ተያይዘው የምንሸምታቸውን ነገሮች የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ነገር ግርም አይላችሁም! ይህን ያህል ጭካኔ ምን ማለት ነው! ጉድ እኮ ነው! ሰዋችን ለአንዲት ዶሮ ስምንት መቶና አንድ ሺህ ብር የሚጠየቀው ከሌላው የዓለም ህዝብ የተለየ እርግማን አለበት እንዴ! ለስደት የመን ድንበር በእግሯ ደርሳ፣ በእግሯ የተመለሰች የምትመስል ‘በግ’፤ ስድስትና ሰባት ሺህ ብር የሚጠየቅባት ውስጧ የተደበቀ ‘ጎልድ’ ‘ዳይመንድ’ ‘ሜርኩሪ’ ምናምን ነገር አለ እንዴ!?
እኔ የምለው… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንድ ሰሞን ሰዉ ሁሉ ይጓጓላት ብቻ ሳይሆን… አለ አይደል… ይሟሟትላት  የነበረችው ‘ሜርኩሪ’ የሚሏት ነገር… ምነው ወሬዋ ጠፋሳ! አንዴ ለመድሀኒትነት ታገለግላለች ሲባል፣ አንዴ ለኑክሌር መስሪያነት ትፈለጋለች ሲባል፣ አንዴ “ከዱቄቱ ይልቅ የሚፈለገው ፈሳሹ ነው…” ሲባል… “እከሌ እኮ ጂ ፕላስ ስሪ የሠራው ሜርኩሪ ቸብችቦ ነው፣” ሲባል ከርሞ እንደው ጥፍት፣ ጥፍት! ‘ከሜርኩሪ መሰወር ጀርባ ያለው ምስጢር ተጋለጠ’ ምናምን የሚል ‘ኢንቬስቲጌቲቭ ሪፖርቲንግ ነገር ይሠራልንማ! አዳሜ ‘የሚድል ኢስት’ ሰዎች አሉበት በተባለው ሆቴል ሁሉ አንድ ቡና ይዞ አምስት ሰዓት ሙሉ ተቀምጦ የሚውለው እኮ ዝም ብሎ አልነበረም፡፡
ስሙኝማ… ‘ሜርኩሪን’ በመሳሰሉት ነገሮች ሰንት ‘የልብ ወዳጅነቶች’ ፈርሰዋል መሰላችሁ! ክፉ ቀን የሰውን ‘ሌቭል አራት’ እና ‘ሌቭል ሰባት’ ባህሪይ ቆፍሮ እያወጣ… አለ አይደል… ለስንትና ስንት ዘመን መልአክ ተደርጎ ይታይ የነበረው ሰው፤ በአንድ ጊዜ  የሉሲፈር ሙሉ ጦር  ፊልድ ማርሻል ነገር ሆኖ ቁጭ ይልላችኋል፡፡
“አንተ፣ እሱ ሰውዬ ምንድነው እንዲህ የለወጠው? እኔ እኮ እንዴት አከብረው እንደነበር አልነግርሀም!”
“እባክህ ድሮም ያው ነበር…”
“ማለት፣ እንዲህ አይነት ሰው መሆኑን ታውቅ ነበር…”
“በእርግጥ ማወቅ ሳይሆን፣ እጠረጥር ነበር…”
አይ ምነው! የምን ‘አትርሱኝ’ ነው! እሱ ራሱ እኮ “እሱ ማለት፣ ምን ልበላችሁ ደግ ከመሆኑ የተነሳ ማዘር ቴሬዛን ማለት ነው፣” ሲል የነበረ ነው፡፡ የ‘ክፉ ቀን’ ክፉ ነገር…በሰላም ጊዜ የተደበቁ ባህሪያትን ቆፍሮ ማውጣቱ!
ደህን ሰንብቱልኝማ!

Read 2318 times