Print this page
Tuesday, 05 May 2020 00:00

ሕገ መንግሥቱን ለምን እንሞግተዋለን?

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

 እንደ መግቢያ
የሕገመንግሥት አመጣጥ ታሪካዊ ዳራ የሚጀምረው ከ1789 የፈረንሳይ አብዮት ነው፡፡ የፈረንሳይ አብዮት፣ በሰው ልጆች ታሪክ ዘንድ፣ እንደ ጉልላት የሚቆጠሩ በርካታ እሴቶችን አበርክቶ ማለፉ ይታወቃል፡፡ በአብዮቱ ላይ ለመስዋአትነት የተሰለፈው ሰፊው ሕዝብ፣ የወንድማማችነት፣የእኩልነት እና የነጻነት አርማን አንግቦ የጭቆና ድባብን በመግፈፍ፤ የአምባገነናዊ ሥርዓትን ማክተሚያ አብስሯል፡፡ ይህ አብዮት በፋና ወጊነቱ ከሚወደስባቸው ገድሎች መካከል መንግሥታት ያሻቸውን የግብር ውጣ አገዛዝ በሕዝቦች ጫንቃ ላይ እንዳይጭኑ የሚያግድ የተጻፈ ሕገ መንግሥትን በማስተዋወቁ ነበር:: ይህ ሕገመንግሥት ገና በጥንስሱ ጥንድ ዓላማን ነበር የሰነቀው፡፡ ሰነዱ በገዢዎች ቅጥያጣ አስተዳደር ላይ ልጓም በማበጀት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብት እንዲከበር ዋስትናን ይሰጣል፡፡
ከፈረንሳይ አብዮት ለጥቆ ባሉት ዘመናት፣ የሕገመንግሥት ቅርጽ ና ይዘት እንደየሥርዓቶች ባሕሪያት ዝግመተ ለውጡ በተለያየ አጽናፍ የሚቀመጥ ነው፡፡ የሊብራል ዴሞክራሲን መርህዎች በውስጡ ያቀፈው ሰነድ፣ በአብዛኛው በምእራባዊያን ሀገራት በስፋት ሲሠራበት ይስተዋላል፡፡ በሌላ ጫፍ ደግሞ፤ የአንድ ፖለቲካ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን ለማንበር፤ እንደ ዋና መሣሪያ የሚያገለግለው የቀድሞዋ የሶቪየት ኅብረት ሕገ መንግሥትን መርህ የሚከተለው ሰነድ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር የሚያያዘው፣ የ1987ቱ የሕወሓት/ኢሕአዴጉ ሕገ መንግሥት፣ የሶቪየት ኅብረት ሕገመንግሥት ግልባጭ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል::
በሕወሓት የሚዘወረው ኢሕአዴግ ያነጸው ሰነድ ከተነሳበት ዓላማ፣በውስጡ ካቀፋቸው አንቀጾችና ከትግበራ አንጻር ብዙ የሚታማባቸው ድክመቶች አሉት፡፡
የሉአላዊ ሥልጣን ጉዳይ
የ1987 ሕገ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሰነድ አይደለም ተብሎ ከየአቅጣጫው የሚወነጨፍበት ኂስ፣ ተራ ውንጀላ እንዳልሆነ አንዱ ማሳያ የሉአላዊ ሥልጣን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሕገመንግሥት፣ ባእድ ጽንሰ ሐሳቦች ሳይፈተሹ  የታጨቁበት እንደሆነ ለማወቅ፣  ከመንደርደሪያው መጀመር ይቻላል፡፡
ገና ከጅምሩ፤ ብሔር፣በሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚለው አደናጋሪ ማንነትን እንደ ቀልድ ደንጉሮ ጭራሽ የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤት ያደርገዋል፡፡ ለመሆኑ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ተብለው የሚፈረጁት እነማን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ ሰነዱ መልስ የለውም፡፡ እስካሁን በዚህ የጠራ ግንዛቤ ባልተያዘበት ፀጉረ ልውጥ ማንነት የተነሳ እርስ በርሳችን ስንናከስ ለመኖር ተገድደናል::
ብሔር የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ከቀደምት ሰነዶች መካከል የማርክስ ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት በእንዲህ መልኩ ነው የሚያብራራው፣
“በሔር በታሪክ ሂደት ውስጥ የተከሰተ የሰዎች ማኅበረሰብ ነው፡፡ አንድ ብሔር በመጀመሪያ ደረጃ የሚለየው ባሉት የወል ቁሳዊ የኑሮ ሁኔታዎች ነው፡፡ በአንድ መልከ ምድራዊ ክልል ውስጥ መኖር፣ በኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች መተሳሰር፣በአንድ ቋንቋ መጠቀም፣በጋራ ታሪካዊ ሒደት ውስጥ የወል ሥነልቦናዊ ገጽታዎችና ባህላዊ አመለካከቶች መከሰት የብሔር መሠረቶች ናቸው፡፡”
ለመሆኑ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ክልል ብሎ ያጠራቸውን ሕዝቦች ከግምት ውስጥ ብናስገባ፤ ከቃሉ ፍቺ ጋር ማዶ ለማዶ መሆናቸውን እንገነዘባለን:: የአርሲ ኦሮሞ፣ ከሸዋ ኦሮሞ ጋር በእንድ የክልል ማእቀፍ ውስጥ የተካተተው፤ የወል ስነልቦና፣ የመልካምድራዊ ኩታገጠምነትና የጋራ ታሪካዊ ሒደት ከግምት ውስጥ ገብቶ አይደለም፡፡ ከአምክንዮ በተራቆተ፣ የምንዝላታዊ መሳሳብ /ethnic identity/መለኪያ ቋንቋን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ቋንቋን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ማንነትን ከግምት የምናስገባ ከሆነ ደግሞ፤ ጎሳ ወይም ነገድ የሚሉ ለዘረ-መል ፖለቲካ የተመቹ ሀገር በቀል ፍረጃዎችን መጠቀም የተሻለ በሆነ ነበር፡፡
በብሔር ደረጃ የዳበረ ሕዝብ ያለው በሰለጠኑት ምእራባዊያን ሀገሮች ነው:: ሕወሓት በበረሃ ቃልኪዳን ለገባለት የአልባኒያ ሶሻሊዝም ታማኝነቱን ያሳየው የእንግሊዝኛውን nation, nationalities and peoples የሚል ጽንሰ-ሐሳብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በሚል እንደወረደ ግንዛቤ፣ የሕገ መንግሥቱ የማእዘን ድንጋይ አድርጎ ማስቀመጡን ስንታዘብ ነው፡፡ በግዕዝ ብሔር ማለት ሀገር ሲሆን ሰብ ደግሞ ሰው የሚለውን ይወክላል፡፡ ብሔረሰብ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሰው ሀገር የሚል ትርጓሜን ይይዛል፡፡ ስለዚህ የግዕዙን ትንታኔ ከወሰድን፣ ጭራሽ ደም እና አጠንት ቆጠራን አልፈን የአዳም ዘርን በሙሉ የሚያቅፍ ዓለማቀፋዊነትን የሚሰብክ አካታች ማንነትን ታሳቢ ያደርጋል ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ሕገ መንግሥቱን የክህደት ሰነድ አድርገን የምንቆጥረው፤ ካላይ ለተነሱት ወሃ የሚቋጥሩ ወቀሳዎችን አብሎ ከሩቁ ምሥራቅ ሶቪየት ሰነድ ቃል በቃል የወሰደውን አንቀጽ ስንመለከት ነው:: ልክ የሶቪየት ኅብረት ሕገ መንግሥት የወዛደሩን የበላይነትን ለማስጠበቅ በሚል እሳቤ፤ ሁሉንም ሉአላዊ ሥልጣን ለወዛደሩ እንደሰጠ ሁሉ፤ የሕወሓት/ኢሕአዴግም ሕገ መንግሥት ሥልጣንን ጠቅሎ ለብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ለሚለው ባእድ ማንነት ይሰጣል፡፡ አንቀጽ 8 ላይ ይህንን ሁኔታ በገሀድ እናገኛለን፡፡ “የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፤ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ሉአላዊነታቸው የሚገለጸው በዚሁ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በሚያደርጉት ተሳትፎ አማካኝነት ነው፡፡” ይላል፡፡
ሰነዱ ለዘር ማንነት የሚሰጠውን ትኩረት ያህል፣ ለዜግነት ወይም ሁለትና ከዛ በላይ የዘር ማንነት ላላቸው/meta-ethnic identities/ እውቅና አይሰጥም፡፡ ሰነዱ ኢትዮጵያዊ አሰባሳቢ ማንነትን ወዳ ዳር ገፍቶታል፡፡  በሕገ መንግሥቱ ፊት ግርማን ለመላበስ፤ በአንድ የዘር ከረጢት ውስጥ ራስን መክተት የግድ ይላል፡፡ ይህ ዓይነት ሥነልቦናዊ ቅኝትን የታጠቀ ከፋፋይ ፖለቲካዊ ስሌት ደግሞ፤ እንደ ሕወሓት ላሉ ሕዳጣን የፖለቲካ ኃይሎች ከፍተኛ ትርፍ ሲያስገኝ ኖሯል፡፡
የሥልጣን ክፍፍል ወይስ የሥራ ክፍፍል?
የሥልጣን ክፍፍል የሚለው መርህ፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ እንደ ዋልታና ማገር የሚቆጠር የአሠራር መንገድ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ልጓም የሚበጅለት በሦስቱ  አካላት ማለትም፡- በሕግ አውጪው፣ በአስፈጻሚውና በሕግ ተርጓሚው መካከል ተግባራዊ በሚሆነው የአግድም የቁጥጥርና ሚዛን (Checks and Balance)  ሥርዓት ነው፡፡
መርሁ የትኛውም የመንግሥት አካል፣ ጡንቻውን አፈርጥሞ፤ በሌሎች አካላት ላይ የአፈና ሥርዓትን እንዳይዘረጋ ያግደዋል፡፡ ለምሳሌ፣ አስፈጻሚው አካል፣ የመንግሥት ሕግን የማስፈጸም አቅሙ ከጥያቄ ውስጥ የሚውድቅ ከሆነ፣ ፓርላማው ተሰብስቦ የእምነት ማጣት ድምጽን (Vote of no confidence) ገቢራዊ በማድረግ፣ የአስፈጻሚው ቁንጮ የሆነውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የሥልጣን ቀነገደቡን ሳይጨርስ ማሰናበት ይቻላል፡፡ እንዲሁም፤ የአስፈጻሚው አውራ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ፤ በአንጻሩ ፓርላማው በሥራ ሒደቱ ላይ እንቅፋት እንደሆነ ካመነ፣ ሸንጎው የሥልጣን ዘመኑን ከመጨረሱ በፊት እንዲበተን፣ ድምጽ የማሰባሰብ ሥልጣን አለው፡፡ ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም ረገድ ደግሞ፤ ድርሻውን የሚወጣው ሌላ ነጻ የሕግ አካል ይኖራል፡፡
ይህ የቁጥጥርና ሚዛን ሥርዓት በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ውስጥ እንደ ካስማ የሚቆጠር መርህ ነው:: ለአብነት ያህል የአሜሪካው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ኮንግረስ)፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት (ሴኔት) እና አስፈጻሚው የበላይ አለቃ ፕሬዚዳንቱ መካከል ቁልጭ ያለ የሥልጣን ክፍፍል አለ:: በዚህም የተነሳ፣ ለየትኛውም የመንግሥት ክፍል ሕገ መንግሥቱ ሥልጣንን ጠቅልሎ አይሰጥም፡፡ ሥልጣን ለአንድ የመንግሥት ከፍል ጠቅልሎ በመስጠት የሚታወቀው ሰነድ፣ እንደ ሶቪየት ኅብረት ዓይነት ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ነው፡፡
የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት፣ በዚህ ረገድ የፀረ ዴሞክራሲያዊው የሶቪየት ኅብረት ካርቦን ኮፒ እንደሆነ ዋቢ የሚሆነን፣ በነገደ ጎበዜ ሕገ መንግሥት ምርጫና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ በሚለው ድርሳን ገጽ 103 ላይ በጉልህ ሰፍሮ እናገኛለን፡፡
“በደርጉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 62 ላይ ይህ ሰፍሯል፡- በኢሕድሪ ከፍተኛው የመንግሥት የሥልጣን አካል ብሔራዊ ሸንጎ ነው ይላል፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ መጀመሪያ ከፍ ብለን እንደጠቀስነው፣ የቡልጋሪያ ሕገ መንግሥትን አንቀጽ 50/2 ላይ ፌዴራል መንግሥቱ የሕግ አውጪነትን የሕግ አስፈጻሚነትንና የዳኝነትን ሥልጣን ጠቅልሎ እንደሚይዝ ይደነግጋል:: የሶቪየትን፣ የደርግንና የሰሜን ኮርያን አባባል ቃል በቃል ወስዶ በአንቀጽ 50/3 በኢፌዴሪ የመንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡” ብሎ ይደነግጋል፡፡
ከዚህ የምንረዳው፣ የሀገሪቱ የበላይ አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ ነው:: የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ራሳቸውን እንደ ሕዝብ ተወካይ ሳይሆን የሚቆጥሩት፣ እንደ መንግሥት ተቀጣሪ ሠራተኛ (ሲቪል ሰርቫንት) ነበር፡፡ ሕወሓት ሲዘውረው የኖረው ኢሕአዴግ፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የእዝ ሰንሰለት ተጠፍሮ የታየዘ በመሆኑ፤ የምክር ቤቱ አባላት ለማእከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ተገዢ መሆን ነበረባቸው፡፡
የሕግ አውጪው፣ የሕግ ተርጓሚውና የሕግ አስፈጻሚው ሥልጣን ተጠቅሎ በማእከላዊ ዴሞክራሲያዊ አሠራር መርህ በፓርቲው እጅ ላይ ተቀምጧል፡፡ ፓርቲውን የሚዘውሩት፣ አንድ ወይም ሁለት ግለሰቦች ደግሞ በቀላሉ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዛቸውን ለማንገሥ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ በሁሉም የሥልጣን ዘርፍ ላይ አምባገነን መሆን የቻሉት በዚህ መንገድ እንደሆነ ይታወቃል:: ሕገ መንግሥቱ ከመንግሥት ሥልጣን ይልቅ የፓርቲ አቅም እንዲፈረጥም ትልቅ እገዛን አደርጓል፡፡
የበይ ተመልካቹ የፌዴሬሽን ምክር ቤት
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተዋቀረበት መርህ፣ ፀረ ፌዴራላዊ መንገድን ተከትሎ ነው፡፡ በፌደራል ሥርዓት ውስጥ እንደ ፌዴረሽን ያሉ የግዛት ተወካዮች የሚካተቱበት ምክር ቤት፣ ዋንኛ ዓላማ፣ ከተወካዮች ምክር ቤት ጋር መሳ ለመሳ ሆኖ ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንዲኖረው ነው፡፡ ለአብነት፤ የአሜሪካውን የፌዴሬሽን ም/ቤትን /ሴኔትን/ብንወስድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት /congress/ጋር እኩል ሕግ የማውጣት ሥልጣን አለው፡፡ ሁለቱ ምክር ቤቶች - ሴኔትና ኮንግረስ ከ 2/3 ድምጽ በላይ አጽድቀው ያሳለፉትን ረቂቅ፣ የአስፈጻሚው ቁንጮ የሆነው ፕሬዝዳንቱ የመሻር ሥልጣኑን/ቬቶ ፓወርን/ ተጠቅሞ ውሳኔውን ማጠፍ አይችልም፡፡
እዚህ ጋ፤ የእኛን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን መለስ ብለን ስንመለከት፣ ከሕግ አውጪ ሚና የተገለለ የበይ ተመልካች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ያላቸው እውቅና የተሰጣቸው 76 የዘውግ ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ፣ ሕገ መንግሥቱ የሰጠው ሥልጣን፣ የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን ጉዳዮችንና አሻሚ የሕገመንግሥት ትርጓሜ ላይ ብይን መስጠት እንዲችል ነው፡፡ ክልሎች ከድንበሮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በራሳቸው እልባት መስጠት ከተሳናቸው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ብይን እንደሚሰጥ አንቀጽ 48 ላይ ተደንግጓል፡፡
ይህ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ያልሆነ የካድሬዎች ስብስብ፣ ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ ሚዛናዊ ፍርድ ይሰጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው የሚሆነው፡፡ በሌሎች ሀገሮች ይህ ሥልጣን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ለሆነ የዳኝነት አካል ነው የሚሰጠው፡፡
የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሕገመንግሥትን ወለፈንዴነት የምንታዘበው፤ ሀገር ለመበተን ቀላል የሆነ አንቀጽን መታቀፉ ሲሆን፣ በአንጻሩ ደግሞ፤ ይኽንኑ አንቀጽ ለማሻሻል  በሚፈልግበት ጊዜ፣ ውስብስብ ሂደቶችን አስቀምጧል፡፡ አንድ ክልል ከፌዴራል መንግሥቱ ተገንጥሎ በራሱ የቆመ ሀገር ለመሆን ከፈለገ፣ የክልል ምክር ቤት 2/3 ድምጽ ማግኘት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡
ከዚህ በመለጠቅ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለሦስት ዓመታት ሪፈረንደም ያዘጋጃል:: በሌላ ጎኑ፤ አንቀጽ 39ን  ለማሻሻል የሁሉም ክልል ምክር ቤቶች ይሁንታ መገኘት ይኖርበታል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አሠራር በኮንፌዴሬሽን  እንጂ በፌደሬሽን አወቃቀር ላይ ፈጽሞ የሚታወቅ አይደለም፡፡
ለምሳሌ አንቀጽ 39ን ከሕገ መንግሥቱ ላይ መፋቅ ቢፈለግ፣ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች ይሁንታቸውን ሰጥተው፣ አንደ መቶ ሺህ የማይሞላ ሕዝብ ያለው ሐረሬ ክልል ውሳኔውን በመጻረር ውድቅ ማድረግ ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአናሳ/ሕዳጣን/ ፍላጎትን በብዙኃኑ ላይ መጫን የሚያስችል ሰነድ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፤ ሰሞኑን የምርጫ 2012 መራዘምን ተከትሎ፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እንደ የተሻለ አማራጭ የሚወስዱ ብዙዎች ናቸው፡፡ በርግጥም፤ አንቀጽ 54ን ለማሻሻል እንደ አንቀጽ 39፣ የሁሉንም ክልሎች ይሁንታን (ቬቶ ፓውር) አይፈልግም፡፡2/3 የሚሆኑት የክልል ምክር ቤቶች ይሁንታ፣ እንዲሁም የፌዴሬሽንና የተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ፤ በቂ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ለዚኽም ደግሞ፤ ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ይቸገራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይኹን እንጂ፤ ይህ አይነት ማሻሻያ፣ እሳት የማጥፋት ሚና ብቻ ነው የሚኖረው፡፡ ዘላቂው መፍትሄ አዲስ ሕገ መንግሥትን መቅረጽ ነው፡፡
ማሰሪያ ነጥብ
ከሕወሓት ጋር ኩታገጠም መርህን የሚያቀነቅኑት የዘውግ ድርጅቶች፣ የሕገመንግሥቱ መርህን ከመሄስ ይልቅ፤ ትግበራው ላይ ጉንጭ አልፎ ክርክርን ያበዛሉ፡፡ ለዚህም፤ እንደ ዋቢ የሚያነሱት፣ ሰነዱ በውስጥ ያቀፋቸውን የሰብኣዊ መብት አንቀጾችን ነው፡፡የቬና አለም አቀፍ ድንጋጌ ውጤት የሆኑት፣ የሰብዓዊ መብትን የሚከላከሉት አንቀጾች ግን፤ በደርግ ሕገ መንግሥት ውስጥ እንደነበሩ፣ እነዚህ ወገኖች ለማንሳት አይደፍሩም፡፡
በአጠቃላይ፤ ሕገ መንግሥቱ ለአፈና አገዛዝ የተመቸ ሰነድ ነው ቢባል፤ ከእውነታው ጋር መጋጨት አይሆንም፡፡ በውስጡ ያዘላቸውም አንቀጾች፣ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ከተጻፉበት ቀለም የበለጠ ዋጋ ሲኖራቸው መታዘብ አልቻልንም፡፡ ስለዚህ፤ ወደፊት ከቅብ ባለፈ የሚቀረጸው ሕገ መንግሥት፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ፍላጎት የተንጸባረቀበት፤ ዘላቂ የሀገር ጥቅምን ከግምት የጣፈ መሆን ይኖርበታል::
ከአዘጋጁ፡- በጽሑፉ ውስጥ የተንፀባረቁት ሃሳቦች የፀሐፊውን አመለካከት ብቻ እንደሚወክሉ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

Read 3088 times