Saturday, 09 May 2020 12:36

“ሌላ ባላውቅ የራሴን ዋጋ አቃለሁ” (ፀ.ገ.መ)

Written by 
Rate this item
(11 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን በጉርብትና የሚኖሩና የሚዋደዱ ሁለት ውድ ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ ሁለቱም ሙልጭ ያሉ መላጣዎች ናቸው፡፡ ገበሬዎች በመሆናቸው በእርሻ ወቅት ይረዳዳሉ፡፡ ይተጋገዛሉ፡፡ በመቀናጆም ያርሳሉ፡፡ የሰፈሩ ሰው በነሱ የመተሳሰብ ሁኔታ ይቀናባቸዋል፡፡
ሁለቱም ፀጉራቸው መላጣ በመሆኑ የቅጽል ስም ወጥቶላቸዋል፡፡ “ሁለቱ ዕንቁላሎች” ይባላሉ፡፡
አንድ ቀን በአንድ አውራ ጐዳና ሽርሽር እያሉ ሳሉ፤ ከሩቁ አንድ የሚያብረቀርቅና የሚያብለጨልጭ ነገር አዩ፡፡
1ኛው - “ባትጋራኝ! በትኩስ እንጀራ!” አለ
2ኛው - “እኔንም ባትጋራኝ - በትኩስ እንጀራ!” አለ
1ኛው -  “እኔ ቀድሜ ብያለሁ!”
2ኛው -  “እኔ ቀድሜያለሁ!”
ቀስ በቀስ ወደሚያበረቀርቀው ዕቃ ዘንድ ገና ሳይደርሱ መጓተት ጀመሩ፡፡ አንዱ ወደ ግራ ሲጐትተው፣ ሌላው ወደቀኝ ይጐትተዋል፡፡ ደሞ እንደገና በተቃራኒ አቅጣጫ ይጓተታሉ፡፡ ወደ ትግል ገቡ፡፡ አሁን አንዱ ተሸክሞ ያንከባልለዋል፡፡ ሌላኛው እንደምንም ይገለብጠውና ከላይ ይሆናል፡፡ ሆኖም አልተላለቁም፡፡ አቧራ በአቧራ ሆኑ!
በመካከል አንድ ቄስ ይመጡና ሁኔታቸውን ያስተውላሉ፡፡
“አንድ ጊዜ እረፉ! ምን ሆናችሁ ነው የምትጣሉት?”
1ኛው  - “እኔ ያየሁትን ዕቃ ሊወስድብኝ ስለሆነና ተው ብለው እምቢ ስላለኝ፤ እዚህ ደፍቼው፣ እንዴት እንደምወስድ ላሳየው ነው!”
2ኛው - “እስቲ በጉልበት እንደሆነ አሁን እናያለን! ከእሱ የሚያንስ ሰው እንዳለ አሁን ልናይ ነው!”
ቄሱ ወደሚጣሉበት ዕቃ ተመለከቱ፡፡ ሄደው ዕቃውን አንስተው፣ ይዘው ወደ ሁለቱ ተደባዳቢዎች መጡ፡፡
ዕቃው የሚያብረቀርቅና ዐይን የሚስብ የብረት ማበጠሪያ ነው!
ቄሱም ማበጠሪያውን ከፍ አድርገው በእጃቸው ይዘው፤
“ለመሆኑ በዚህ ማበጠሪያ ፀጉሩን ቀድሞ የሚያበጥር ከሁለት አንዳችሁ ማን ነው?!” ብለው ጠየቁ፡፡
ሁለቱ መላጦች እርስ በርስ ተያዩ፡፡ አንደኛው የሌላውን መላጣ እያየ ፈገግ አለ፡፡ ሌላኛውም እንደዚያው  ፈገግ ብሎ የፈገግታ አፀፋውን መለሰ፡፡
ይሄኔ ቄሱ እንዲህ አሉ፡-
“አያችሁ ልጆቼ፤ ያደረጋችሁት ነገር ሶስት ትምህርታዊ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያደረገናል፡-
አንደኛ/ ከመልካም ጓደኝነት የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር አለን?
ሁለተኛ/ የሚያብለጨልጭ ነገር ሁሉ ወርቅ ነውን?”
ሶስተኛ/ ስስትና ስግብግብነት ወደመከፋት እንደሚያመራ አስተውላችኋልን?
ከሶስቱ የትኛውን ያስተምረናል? ነው ወይስ ሶስቱንም ነገሮች የሚየስተምረን በሳል ታሪክ ነው ብለው ገላገሏቸው፡፡
***
በዓለም ላይ ጥቃቅን የሚመስሉ ግን ታላላቅ ነገር የሚያስተምሩን አያሌ ክስተቶች አሉ፡፡ “ትልልቁን ነገር ፍለጋ ስንዋትት፤ ከትንንሹ ክስተት የምናየውና የምናገኘው የላቀ ነገር ያመልጠናል፡፡ ትኩረታችን ለማደግ ነውና ወደዚያ ስናንጋጥጥ፣ ልብ ማለት ያለብንን ከትንሽ የሚገኝ ድንቅ ነገር እንስተዋለን! ምን ጊዜም ቢሆን ትንሿ ድርጭት ለትልቁ ተራራ አለች የተባለውን አንርሳ፡-
“If I am not as big as you,
More are you as small as I am”
“ታላቁ ተራራ፣ እንቁ ታላቅ ጋራ
ግዙፍ ነኝ እያልህ፣ እጅግ አትኩራራ
እውነት እልሃለሁ፡-
አንተ ልነስ ብትል አትችልምና
በትንሽነቴ በልጥሃለሁ ግና!”
ከትናንሽ ነገሮች ውስጥ የምናገኘውን ቁምነገር ከላይ የቀረበው ግጥም በቅጡ ያፀኸየዋል፡፡
ማናቸውንም ትንሽ ነው ያልነውን ነገር በንቀት ዐይን አለማየት ከቶም ብልህነት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ ሁልጊዜ ትልቅነትን ከእኛ ውጪ ከመፈለግ እራሳችን ውስጥም መፈለግ ረቂቅ ጥበብ ነው፡፡ ሮበርት ብራውኒንግ የተባለው ገጣሚ እንዲህ ይለናል፤
“ደግሞም ማወቅ ማለት…
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲጠጣ ማድረግ!”
በራሳችን ውስጥ ያሉትን እሴቶች መፈተን፣ ማጤንና ለምን ;;; እንደምናውላቸው ማገናዘብ በእጅግ ጠቃሚና ይሆነኝ ብለን ለፍጆታ ልናውለው የሚገባ ፍሬ - ጉዳይ ነው፡፡ ሁልጊዜ “ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣልን” እና “እኔ የምለብሰው አጥቼ እሷ እስክስታ ትወርድበታለችኝ” እየተረትን ቁልቁል የምናድግ፣ ሁሌ ተመጽዋችና ሁሌ የድህነት ምሳሌ ሆነን መኖር የለብንም፡፡
ለዚህ ደግሞ ቁልፉ መርህ፤ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን “በኦቴሎ” ትርጉሙ ውስጥ፣ እያጐ በተሰኘው ገፀ - ባሕሪው አማካኝነት ያስቀመጠው ሐረግ ነው፡፡
እያጐ፤
“ሌላ ባላውቅ የራሴን ዋጋ አቃለሁ!” ይለናል፡፡ የራስ ዋጋ ባህል ውስጥ አለ፡፡ የራስ ዋጋ ኢኮኖሚ ውስጥ አለ፡፡ የራስ ዋጋ ፖለቲካ ውስጥ አለ፡፡ የራስ ዋጋ ሥነ - አዕምሮ ውስጥ አለ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የራስ ዋጋ ሥነ - ጤና ውስጥ አለ፡፡ ስለሆነም ነገን የራሳችንና የህብረተሰባችን ለማድረግ፣ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ጤንነታችንን መጠበቅን እንደ ባህል ማጥበቅ ይገባናል፡፡
ለወትሮው ስለ ጤና እንደ ፈሊጥ እንናገር ነበር፡፡ ዛሬ ስለ ጤና ስናስብ ትውስ የሚለን አንድ ተረት ነው፡-
“ከሞትና ከህይወት የቱ ይሻልሃል ቢሉት፤ ሲያስብ ዘገየ!”
ዛሬ የህይወት ጉዳይ ወለም ዘለም የሌለበት፣ የቀረጥ ቀን ጥሪ ነው! እገሌ ከእገሌ በማንልበት መልኩ ከቤት ወደ ጐረቤት፣ ከጐረቤት ወደ ሀገር ለመዛመት፣ ከዚያም ዓለምን አሻምዶ ለመዋጥ አሰፍስፎ የመጣውን በሽታ፤ እንደ ወትሮው ከንፈር በመምጠጥ የምንሳለቅበት እንዳልሆነ፣ ጥንቅቅ አድርገን፣ በአጽንኦት ማመን የሚገባን ጊዜ ላይ ነን፡፡
ከቶውንም በበሽታው የተያዘና የሟች ቁጥር ሲበዛና ሲያንስ፤ አንዴ ቸል አንዴ ጠበቅ የምናደርግበት አካሄድ የትም አያደርሰንም! ሥጋቱ የምር ሥጋት፤ ጥንቃቄውም ጥብቅ ጥንቃቄ መሆን አለበት! “ሲበርድ በእጅ፤ ሲፋጅ በማንኪያ” የሚባል አማራጭ የለውም፤ ደግመን እንደምንናገረው፡-
“ከሞትና ከህይወት የቱ ይሻልሃል? ቢሉት፤ ሲያስብ ዘገየ” የሚለው መተረት ያለበት ጊዜ አይደለምና ምርር ክርር ብለን፣ የቁርጥ ቀን ልጆች እንሁን፡፡ በዚህም ለትውልድ፣ ለሀገርና ለአለም እንትረፍ፡፡ በአንድ ምርጥ መንገድ - በጥንቃቄ!! ሌላ ባላውቅ የራሴን ዋጋ አቃለሁ - እንበልና እንጀምር፡፡ ከዚያ ሁሉም ይቀጥላል፡፡ ሁላችንም እንዋደዳለን፡፡ በጥንቃቄም እንተሳሰባለን! የነገ ሰው ይበለን!!   


Read 13799 times