Print this page
Saturday, 09 May 2020 12:38

በእርግዝና ወቅት የደም መፍሰስ…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(6 votes)

 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በአገራችን ከታዘዙት እራስን ከወረርሽኙ የመጠበቅ ሂደቶች መካከል በተቻለ መጠን ከቤታችሁ ሆናችሁ ስራችሁን ስሩ፤ አስገዳጅ ነገር ከሌለ በቀር ከቤታችሁ አትውጡ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ታዲያ የእኔ ባለቤት የስራ ጸባይዋ ከቤት ተቀምጦ የማያሰራ በመሆኑ በቀን በቀን ባይሆንም እንኩዋን ከስራ ጉዋደኞችዋ ጋር ተራ በመግባት በሳምንት ሶስት ቀናት ወደስራ እንድትገባ የስራው ባህርይ ያስገድዳታል፡፡ ባለቤቴ የስድስት ወር እርጉዝ ናት፡፡ ታድያ ባለፈው ሳምንት ውስጥ አንድ ነገር ተከሰተ:: በድንገት ስልኬ ጮኸ፡፡ ሀሎ ….አልኩ:: በአስቸኩዋይ ወደ… ሆስፒታል ብትመጣ…ተባልኩ:: ምክንያቱም ከባለቤቴ ጋር በተገናኘ መሆኑን ደዋዩ አስረዳኝ፡፡ እኔም በፍጥነት ወደ ተጠራሁበት ሆስፒታል ሄድኩ፡፡ ባለቤቴን አገኘሁዋት፡፡ የሆነውን ነገር ስጠይቃት….በስራ ላይ እያለች የደም መፍሰስ እንደታያት እና የመውለጃ ጊዜዋ ገና ሆኖ ሳለ ይህ ለምን ሆነ ብለው አለቆችዋ  ወደሆስፒታል እንደላኩዋት ነገረችኝ፡፡ ባለቤቴ ከቤትዋ ስትወጣ እንቅፋት መትቶዋት ከመውደቅ ባልተናነሰ ብዙ እንደተንገዳገደችና አንድ ሰው እንዳዳንዋት ሙሉ በሙሉ ግን መሬት ላይ እንዳልወደቀች ነገረችኝ:: እኔም እግዚሀርን አመስግኜ…አብሬአት ቆይቼ ባለቤቴን ይዤ ወደቤታችን …ወደ ልጆቻችን ሄድን፡፡ በተቻለ መጠን ግን እረፍት እንድታደርግ ተነግሮናል:: ለመሆኑ ይህ በምን ምክንያት ያጋጥማል?
ቢኒያም ደረጀ …ከለቡ  
ሴቶች በእርግዝና ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች የደም መፍሰስ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ጊዜው እረዘም ቢልም ከአሁን ቀደም ያነጋገርናቸው ባለሙያ ያብራሩትን እና ከተለያዩ ወቅታዊ መረጃዎች ያገኘነውን ለንባብ ብለናል፡፡ ባለሙያው ዶክተር ሽፈራው ነጋሽ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ በማህጸንና ጽንስ ትምህርት ክፍል መምህርና የህክምና ባለሙያ ናቸው፡፡ ሌላው በእርግዝና ጊዜ ስለመድማት ያመሳከርነው መረጃ ዌብ ሜድ የተሰኘው ድረገጽ ነው፡፡
ዌብ ሜድ እንደሚገልጸው ወደ 20% የሚሆኑ ሴቶች በእርግዝና ወቅት በመጀመሪያ ሳምንታት ደም እንደሚያዩና ይህም ሊያጋጥም እንደሚችል ነው፡፡ እርግዝና አለ ከተባለ በሁዋላ ከ6-12 ቀናት በሚሆን ጊዜ ትንሽ እንደ ነጥብ የመሰለ ደም ሊታይ እንደሚችል እና ይህም እንደአደጋ ሊቆጠር የማይችል ነው፡፡
በእርግዝና ጊዜ ደም ከሚፈስባቸው ምክንያቶች አንዱ ከእንግዴ ልጅ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡
ከእንግዴ ልጅ መቅደም ጋራ በተያያዘ የሚመጣው የደም መፍሰስ ምናልባት ቀለል ካለ የወገብ ህመም በስተቀር ብዙ ጊዜ የቁርጠት ስሜት ወይንም የምጥ ምልክት እና ሌላ ሕመም የለውም፡፡ ከእንግዴ ልጅ ጋር በተያያዘ የሚታየው ደም መፍሰስ ንጹህና ቀይ ደም ነው፡፡ ሴቶች እንደዚህ ያለ ነገር በሚያዩበት ጊዜ በአስቸኳይ ወደሚከታተላቸው የህክምና ባለሙያ መሄድና መታየት አለባቸው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ  ከዚሁ ከእንግዴ ልጅ ጋር በተገናኘ የሚመጣው ደም መፍሰስ የሚከሰተው እንግዴ ልጅ ያለጊዜው ቦታውን ሲለቅ ነው፡፡ ይህ ማለትም እንግዴ ልጅ የሚወጣው ከልጅ በኋላ ሲሆን ከማህጸንም መላቀቅ ያለበት ልጅ ከተወለደ በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን በእርግዝናው ወቅት በትክክል ከቦታው ላይ የተቀመጠ የእንግዴ ልጅ ያለጊዜው ማለትም ልጅ ከመወለዱ በፊት ከማህጸኑ ሲለያይ ያለጊዜው ቦታውን ለቀቀ ይባላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ አንዳንዴ የደም መፍሰስ ሊኖር ይችላል:: አንዳንዴ ደግሞ ደም መፍሰስ ላይኖር ይችላል:: የእንግዴ ልጅ ያለጊዜው ከቦታው በመልቀቁ ምክንያት የሚከሰተው የደም መፍሰስ በጣም አስፈሪ የሆነ እና የእናትየውንም ሆነ የልጁን ሕይወት ሊያጠፋ የሚችል ነው፡፡
የእንግዴ ልጅ ያለጊዜው ቦታውን የሚለቅበት ምክንያት …ሴት ልጅ የመውደቅ አጋጣሚ ቢኖራትና ሆድዋ ላይ ብትመታ፣
የደም ግፊት የመሳሰሉት ሕመሞች ቢኖሩዋት፤
በተጨማሪም የሽርት ውሀ ድንገት ቢፈሳት ከማህጽን ውስጥ ያለው ጫና  ስለሚቀንስ እንግዴ ልጅ ካለጊዜው ከቦታው ሊላቀቅ ስለሚችል…ወዘተ፤
የመሳሰሉት የእንግዴ ልጅ ያለጊዜው ከቦታው መላቀቅ እንዲገጥመው ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ እርጉዝ የሆነችው ሴት በሆድዋ አካባቢ አትንኩኝ እስከማለት ከበድ ያለ ሕመም ሊሰማት ይችላል፡፡ እንደዚህ ያሉ ችግሮች ተፈጥረው የሚከሰተው የደም መፍሰስ ጉዳቱ እጅግ አስፈሪ ነው:: ከሴት ማህጽን የሚፈሰው ደም አንዳንድ ጊዜ ከጽንሱ ከራሱ የሚነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ማለት የጽንሱ የደም ስሮች በተለያዩ ምክንያቶች ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ የሽርት ውሀ ድንገት ሊፈስ ይችላል፡፡ ያንን የሽርት ውሀ መፍሰስ ተከትሎ ጽንስ ከራሱ በሆኑ ደምስሮች የሚመጣ የደም መፍሰስ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት የሚከሰተው የደም መፍሰስ  ብዙ ጊዜ በእናትየው ላይ ምንም የህመም ምልክት አያሳይም:: ነገር ግን በአስቸኳይ  ሕክምና ካልተደረገ የልጁን ሕይወት ሊያጠፋ የሚችል ችግር ነው፡፡ ከጽንሱ ከራሱ የሚከሰተው የደም መፍሰስ በእርግጥ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም አይደለም፡፡ ነገር ግን ካጋጠመ ቶሎ ሕክምና ካልተደረገና ካልተገላገለች የደም መፍሰሱ የልጁን ሕይወት ወዲያው አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል::
ምንጭ ዶ/ር ሽፈራው ነጋሽ
ሴቶች በተለያዩ የእድሜ ደረጃ ላይ ሆነው ከማህጸናቸው ደም የሚፈስበት አጋጣሚ አለ፡፡ የደም መፍሰስ ምክንያቱ ግን እንደሁኔታው ይለያያል::
ከማህጸን ገላ ጋር በተገናኙ መመረዝ (Infection)፤
በብልት አካባቢ በሚፈጠሩ ቁስለቶች ወይንም በሚደርሱ አንዳንድ ጉዳቶች፤
እንደ እንቅርት በመሳሰሉት የህመም አጋጣሚዎች፤
የሆርሞን መዛባቶች ወይንም እጢዎች ምክንያትና በሌሎችም ሁኔታዎች ነው፡፡
በእርግዝናም ጊዜ እስከ አምስት ወር ድረስና ከዚያም በላይ ባሉት ወቅቶች ሊከሰት የሚችለው የደም መፍሰስ እንደ ውርጃ የሚቆጠርበትና አንዳንድ ጊዜ ግን እርግዝናው እንዲቀጥል የሚቻልበት ሕክምና ሊሰጥ እንደሚችልም ጥናቶች ያስረዳሉ::  በእርግዝና ጊዜ ከሰባት ወር እርግዝና በሁዋላ ከማህጸን ደም የሚፈሰው በማህጸን መፈንዳት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሴቶቹ ቀደም ሲል በኦፕራሲዮን ልጅ ወልደው ከሆነ ወይንም ደግሞ በሌላ ምክንያት በማህጸን ላይ ኦፕራሲዮን ተደርገው ከሆነ ከመውለድ ወይም ከምጥ በፊት የማህጸን መፈንዳት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይህ ብዜ ጊዜ የሚከሰተው በምጥ ሰአት ሲሆን ነገር ግን ከምጥ ሰአት በፊትም ሊከሰት ይችላል፡፡ ከሰባት ወር የእርግዝና ጊዜ በኋላ የሚከሰተው የማህጸን መፈንዳት ሌላ ምንያትም አለው፡፡  
ጽንሱ እያደገ በሚሄድበት ጊዜ ቀደም ሲል የተደረገው ኦፕራሲዮኑ የመላቀቅ ነገር ስለሚገጥመው፣
የጽንሱ አቀማመጥ ጥሩ በማይሆንበት ጊዜ  በምጥ ሰአት ምጡ ሊቆይ ስለሚችል የልጅ መውጫ መንገዱ ሲዘጋበት ማህጸኑ ደግሞ በበኩሉ ልጁን ለማውጣት ትግል ስለሚያደርግ የማህጸኑ ክፍል እየተነፋ  እየተነፋ  ይሄድና     በተለይ ብዙ የወለዱ  እናቶች  ላይ መጨረሻ ውጤቱ  የማህጽን መፈንዳት     ይሆናል፡፡
ጽንስ በጣም በመፋፋቱ ምክንያት የማህጸን በሩ ሊያሳልፈው ካልቻለም የማህጸን መፈንዳት ሊያጋጥም ይችላል፡፡
Pregnancy birth & baby የተባለው ድረ ገጽ እንደሚያስረዳው በወሊድ ጊዜ የደም መፍሰስን ከሚያስከትሉት ምክንያቶች ውስጥ
ልጅ በሚወለድበት ጊዜ የማህጽን በሮች ላይ የመቀደድ ሁኔታዎች ሲከሰቱ፣
የእንግዴ ልጅ በከፊል ያለመውጣት ወይንም ተቆርጦ በማህጸን ውስጥ መቅረት የደም መፍሰስ ችግር ሊያመጣ ይችላል፡፡
ባጠቃላይም ከማህጸን ደም የመፍሰስ ችግር ሲባል ከሴት ልጅ ማህጸን ባልተጠበቀ ሁኔታ …በውርጃ፣ ካንሰር፣ ከማህጸን በላይ እርግዝናን ጨምሮ የእንግዴ ልጅ መቅደም፣ የእንግዴ ልጅ ከቦታው ያለጊዜው መልቀቅ የመሳሰሉት አደገኛ በሽታዎች መሆናቸውን እናቶች በትክክል መረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በዚህ አይነቱ ችግር እናቶች በወሊድ ወቅትም ሆነ ከወሊድ በሁዋላ ማለትም አንዲት ሴት ሕይወት ለመስጠት ስትል ሕይወት ማጣት የለባትም የሚለውን እምነት ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ በህክምናው ዘርፍ እናቶች በሚወልዱበት ጊዜ የሚደረግ ልዩ አይነት ጥንቃቄ አለ፡፡ ማንኛዋም ሴት ልክ ልጅዋን እንደወለደች የሚሰጥ ማህጸን እዲሰበሰብ ማድረግ የሚችሉ መድሀኒቶች አሉ፡፡ ሴቶች ከወለዱ ከመጀመሪያው ሁለት ሰአት እስከ አራት ሰአት ለሚሆን ጊዜ የማህጸን መሰብሰብን እንዲሁም የደም መፍሰስን መኖር አለመኖርን የህክምና ባሙያዎች በቅርብ ሊከታተሉት የሚገባ ነገር ነው፡፡



Read 10958 times