Print this page
Saturday, 09 May 2020 13:09

“መብራት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ይጠፋል…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

   “--መጀመሪያ ላይ ወንደላጤ ሆዬ፤ የስቴፈን ኪንግን ፊልም ያየ ይመስል ‘ቴረር፣ በቴረር’ ይሆንላችኋል! ከበፊተኛው ቤት ያስወጡት ቀና፣ ቀና ማለት አብዝቶ ነዋ! እሱስ ቢሆን የፈለገ አማራጭ ቢጠፋ ከእሜቴ ጋር የምን “ሲያቃዠኝ አደረ…” ምናምን መባባል ነው!--”
           
                 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በአንድ የውጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የቀረበ ነው፡፡ የሰማንያ አምስቱ ዓመት ሰው ስለ ኮሮናቫይረስ እየተጠየቁ ነው፡፡
“እባካችሁ እኔ ቤት ኮሮናቫይረስ የገባው ገና ድሮ ነው?”
እንዲህ ያሉት ማንን መሰላችሁ…ሚስታቸውን፡፡ እንዴት ቢያበሳጯቸው ነው!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እንደ ዘንድሮ በአከራይና በተከራይ መሀል ወዳጅነት የተፈጠረበት ዘመን ትዝ ይላችኋል?…ልክ ነዋ፣ በፊት እኮ በየአራትና በየአምስት ወሩ… አለ አይደል…
“ኑሮ በጣም ስለተወደደ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ኪራዩ ላይ አንድ ሺህ ብር ጨምረናል፡፡”
“ጋሼ፣ አሁን የምከፍለው ኪራይ እንዴት እንደከበደኝ ያውቃሉ፡፡ አንድ ሺህ ብር ከየት አምጥቼ ነው የምጨምረው?”
“ይህንንም አንተ ስለሆንክ ነው፡፡ እንግዲህ ካልሆነ ሌላ ቦታ መፈለግ ነው፡፡” በሆዳቸው እኮ “እንደው በሄደለኝና ጨመር አድርጌ ባከራዩሁት” ይሉ ይሆናል፡፡ አሀ…ይሄኔ እኮ ከጀርባ ሪሞቱን  የሚነካካው ከእንትኑ የተጣላ ደላላ አለ፡፡
“አምስትና ስድስት ሺህ ብር እጅዎትን ተስመው የሚያከራዩትን ቤት፣ እንዴት በሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር አሳልፈው ይሰጣሉ!” ይህኛውን ተከራይ ያመጣው እኮ እሱ ራሱ ነው!
እናላችሁ…ለጊዜውም ቢሆን “መብራት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ይጠፋል…” አይነት የአከራይ፣ ተከራይ ግንኙነት ትንሽ ጋብ ሲል አሪፍ ነው፡፡
 እናላችሁ…እንዲህ የቤት ባለቤት ‘ውል ባለበት’ ቁጥር ኪራይ እንዳልጨመረ፣ አሁን ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ሰዎች… “የአንድ ወር ኪራይ ትተናችኋል፡፡” “የሁለት ወር ኪራይ ነጻ ነህ” ምናምን ሲባባሉ መስማት አሪፍ ነገር ነው፡፡ አለ አይደል… “እንዲህ አይነቱን መተሳሰብ ምን አለ---ለሁሉም ጊዜ ቢያደርገው!” የሚያሰኝ ነው፡፡
ታዲያላችሁ… አከራይ መሆን ሁልጊዜ ክፋት፣ ተከራይ መሆን ሁልጊዜ ብሶተኛ መሆን ማለት አይደለም፡፡ ልከ ነዋ…ስንቱ ጎረምሳና ጎልማሳ አይደለም እንዴ አልጋና ፍራሽ ይዞ “አይ መንከራተት!” እያለ ገብቶ የባለቤቶቹን ገና ‘የደረሰች’ እና ‘ከደረሰች የከረመች እንትናዬ “ይዟት፣ ይዟት በረረ!” እየተባለለት ይዞ የወጣው!
“የት ተገናኛችሁ?”
“እኔ የአነሱን ቤት ተከራይቼ ነበር ከዛ…” ይሽኮረመማል፡፡ (ኸረ እባክህ…ለመሽኮርምም “ከአስራ ምናምን ዓመት በላይ የተከለከለ” የሚል ያልተጻፈ ህግ አለ!)
“እሱ ነው አንቺ መጀመሪያ የቀረበው?”
ይቺ አንዴት አይነት አስቸጋሪ ጥያቄ መሰለቻችሁ…ማናቸውም እጅ መስጠት አይፈልጉማ! እና ምን ሊባል ይችላል መሰላችሁ… “ሁለታችንም ነን፡፡”
ኸረ በህግ! በ‘ማቴማቲክሱስ፣’ በባዮሎጂውስ እንዴት ነው ‘አንድ ላይ’ የሚቀርቡት!
“ከአድማስ ባሻገር ካለሽ ልታውሽኝ ትችያለሽ!” ማለት መቅደም ማለት አይደለም!
እሷም… “ከአድማስ ባሻገር እንኳን የለኝም:: ከፈለግህ የሚያቃጥል ፍቅርን ላውስህ!” ስትለው መከተል ማለት አይደለም! (ስሙኝማ…ይቺን ሲሰማ እሱ በሆዱ ምን ይል መሰላችሁ… “እንዲህ አይነት ርእስ ያለው መጽሐፍ መኖሩን ባውቅ መጀመሪያውንም ከአድማስ ባሻገርን አልጠይቅም ነበር፡፡”ልክ ነዋ…እንዲህ ቀጥ ያለው አነጋገር እያለ የምን ዙሪያ ጥምጥም ነው!)
ደላላ ይመጣና፤- “እማማ፣ ምን የመሰለ ቤት ተከራይ አግኝቻለሁ፣” ይላል፡፡
“ምን አይነት ሰው ነው?”
“ምን አለፋዎት ተቀብቶ የተላከ በሉት፡፡ እንዴት ግሩም ሰው መሰለዎት…”
“ብቻ ቤተሰብ ያለው እንዳይሆን፣ እኔ እዚህ ግቢ ውስጥ የልጅ ጫጫታ አልፈልግም፡፡”
“ኸረ እሱ ወንደላጤ ነው፡፡ አይጠጣ፣ አያጨስ፣ አይቅም…”
“እንደሱ ከሆነ ጥሩ…”
እናላችሁ፣ ወንደላጤ ይገባል፡፡ አከራይ ደግሞ የደረሰች ልጅ አለቻቸው፡፡ “ቤተሰብ ያለው አልፈልግም…” የሚባለው እኮ ሁልጊዜም ከግቢ ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ሳይሆን… ሰዋችን እንደሚለው ‘ነገሩ ወዲህ ነው፡፡’ ልክ ነዋ… ለልጆቻቸው ውሀ አጣጪ ለመፈለግ ሆነ ብለው ለወንደላጤ ብቻ ያከራያሉ የሚባሉ አሉ!
ታዲያማ…‘አንገቱን የደፋ’ ወንደላጤ ይገባል፡፡ ለመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ቀና ማለት ብሎ ነገር የለም፡፡ እንደውም ለስንት ‘ቁም ነገር’ ያሰቡት እሳቸው “ጠርጥር ገንፎ ውስጥ…” ምናምን ሁሉ ሊሉ ይችላሉ፡፡
“ይህ ሰውዬ ዘላለሙን መሬት፣ መሬት ብቻ እያየ ሊከርም ነው እንዴ!”
ቀና ካላለ እኮ በኋላ ለቲቪ የበዓል ዝግጅት… “ገና መጀመሪያ ቀን ያየኋት ጊዜ ነው፣ በቃ የልጆቼ እናት የምትሆነው ይቺ ነች” ብዬ የወሰንኩት፣ ለማለት አይመችም:: እናማ….እሳቸው የመግቢያ በሩን ማሳየት አለባቸው…
“እንደውም ሲገባም ሲወጣም እንደምን ዋላችሁ፣ እንደምን አመሻችሁ አይባልም!”
መጀመሪያ ላይ ወንደላጤ ሆዬ፤ የስቴፈን ኪንግን ፊልም ያየ ይመስል ‘ቴረር፣ በቴረር’ ይሆንላችኋል! ከበፊተኛው ቤት ያስወጡት ቀና፣ ቀና ማለት አብዝቶ ነዋ! እሱስ ቢሆን የፈለገ አማራጭ ቢጠፋ ከእሜቴ ጋር የምን “ሲያቃዠኝ አደረ…” ምናምን መባባል ነው! (እነ እንትና …ቀና፣ ቀና ማለቱ ታክቲክና ስትራቴጂ ይበጅለትማ!) ደግሞላችሁ… ያ የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ የሚሉት ነገር አለ… “ገና በሁለት ወሬ ኪራይ ሊጨምሩብኝ ነው!”
“አንዳንዴም ብቅ እያልክ ሻይ ቡና በል እንጂ፣ የምን ባዳ መሆን ነው!”
ጎሽ! እንዲህ ነው አንጂ አረንጓዴ መብራት ማሳየት! (አንገቱን ደፋ ማለት እኮ ‘በግንባሩ’ አያይም ማለት አይደለም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ከዛላችሁማ… የአከራዩ ‘ካልኩለስ’ ምናምን የገባው ወንደላጤ፤ “የዓለም ወንደላጤዎች…” በሚለው የራሱን መፈክር ይፈጥራል፡፡ “የዓለም ወንደላጤዎች፤ ፈረስ ያደርሳል አንጂ አይዋጋም::”  (ወንደላጤ ሆዬ እኮ ራሱ ‘ተዋጊ’ ሊሆን ነው!)
“ኸረ እማማ ደስ ይለኛል…” ቀጥሎስ! ቀጥሎማ ‘ቡና ሊጠጣ’ ይገባል፡፡ በ“ማን ያውቃል…” ቀስ እያለ ቤቱን ይቃኛል፡፡ ‘እኛም ኖርን እንላለን፡፡ ይሄ ምን ቴሌቪዥን ነው፣ ግድግዳ ነው እንጂ!’ ‘በዚህ ሶፋ ላይ እየተቀመጡ እንኳን ዳሌ ምንስ ቢሰፋ ምን ይገርማል!’ እናላችሁ…ባይተዋርነቱ ይቀራል::
“እማማ፤ የእርስዎ ቤት ቡና ጣእም አኮ ሼራተንም አይስተካከለው!”
እሳቸውም፣ ‘የደረሰችው’ እንትናዬም ጥርስ በጥርስ ይሆናሉ፡፡ ማንም…“አንተ የሼራተንን ቡና ጣእም ያወቅኸው ገብተህ ጠጥተህ ነው ወይስ ሰው በፔርሙስ አምጥቶ አቅምሶህ ነው!” ብሎ መስቀለኛ ጥያቄ የለማ!
 “እሺ ሥራ እንዴት ነው?”
“ምንም አይል…”
“እጠይቅሀለሁ እያልኩ፣ ለመሆኑ ልብስህን የት ነው የምታሳጥበው?” ‘ገና ምኑም ሳይያዝ እነኚህ ሰዎች ጭራሽ የአለባባስ ኮድ ሊያወጡልኝ ነው እንዴ!’
“ላ…ላውንደሪ ነው፡፡ ብዙ ዓመት ደንበኛ የሆንኩት አንድ ቤት አለ፡፡”
ሀሳብ አለን…“ብዙ ዓመት…” የምትለው ጥሩ ሀረግ አይደለችም፡፡ አሀ… እንደዛ ገና እንደ ኤርታሌ እንፋሎት ትኩስ የሚመስለው… “ለካስ አጅሬ እድሜውን በእንትኑ ቀብሮ ነው!” ሊባል ይችላላ!
እናማ…እሳቸው ቆጣ ይላሉ “እዚህ ማሽኑ እያለ ለምን ብለህ ነው ገንዘብህን የምትከሰክሰው! “ማነሽ…ከዛሬ ጀምሮ የእሱ ልብስ እኛ ቤት ነው የሚታጠበው፡፡”
ስማኝማ አጅሬው…ያቺን ጎርፍ የሸነቆራት የምትመስለውን ካልሲ መላ ፍጠርላታማ! ‘ሳይጀመር በካልሲ ሰበብ ያለቀው ፍጥምጥሞሽ’ ሚል ዘጋቢ ፊልም ነገር በዩቲዩብ እንዳይለቀቅብህ ብለን ነው፡፡
“እማማ ኸረ ችግር የለም…እናንተን ከማስቸግር እዛው ላውንደሪ ሊታጠብ ይችላል…”
“በቃ እዚሁ ይታጠባል ብያለሁ፣ እዚሁ ይታጠባል፡፡” ከፍጥምጥሙ አማትነቱ ሲቀድም ደስ አይልም!
“መብራት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ይጠፋል…” አይነት የአከራይ፣ ተከራይ ግንኙነት እስከ ወዲያኛው ይጥፋልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2018 times