Saturday, 16 May 2020 11:18

“እደጅ ያለው ሰንበሌጥ ሲታጨድ፣ ማድቤት ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ሰፌድ ይንቀጠቀጣል”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን እጅግ ክፉ ሚስት የነበረችው አንድ ቀና ባል ነበረ፡፡
ይህንን ባል ያቺ ክፉ ሚስቱ በጣም በጠዋት ትቀሰቅሰዋለች፡፡ አልጋዋ ላይ እንደተኛች፡-
 “በል ገንፎ አገንፋ” ትለዋለች፡፡
ባል እንደ ምንም ይነሳና ገንፎ ያገነፋል፡፡ ቅቤና በርበሬ ለውሶ
“በይ ብይ የእኔ እመቤት” ይላታል፡፡
ሚስትየውም በቁጣ፤
“ትቀልዳለህ ልበል? አጉርሰኝ እንጂ!” ትለዋለች፡፡
በትህትና ያጐርሳታል፡፡
“ምነው በቤቱ ቅቤ የለም አሉህ እንዴ? ሂድ ከቅቤ ቅል ውስጥ ቅቤ አምጣና በደምብ ለውሰህ አጉርሰኝ!” ትለዋለች፡፡
ባል እንደታዘዘው ከቅቤው ዕቃ ውስጥ ቅቤ አምጥቶ “በደምብ ብይ” ይላታል፡፡
“አንተ ሰውዬ ዛሬ ጤናም የለህ እንዴ? አሁን ቢያንቀኝ ምን ልሆንልህ ነው? በል ተነስና ውሃ ቀድተህ አምጣ!” ትለዋለች፡፡
ባል ተነስቶ ውሃ ይዞ ይመጣል፡፡ መብላት ሲጀምሩ፤
“እቺን የምታህል ቅቤ ለውሰህ ምን ልትሆነን ነው? የምን ቁጥ - ቁጥ ነው? ተነስና ጨምርበት!”
ተነስቶ እንደገና ቅቤና በርበሬ ለውሶ ያመጣና ያጐርሳታል፡፡ ከጠገቡ በኋላ፤
“በል እሳት አያይዝና ቡና አፍላልኝ”
“የእርሻው ሰዓት ይረፍድብኛላ?”
“እኔ ነኝ እርሻው ነው የሚበልጥብህ?”
“እሺ ካልሽ፡፡ ቡናው ይቅደም፡፡”
አያይዞ ቡናውን ይቆላና ሊወቅጥ ሲሰናዳ፣
“አሽትተኝ እንጂ! እንዲሁ ልጠጣልህ ነው እንዴ?”
እያንከሻከሸ ያስሸትታታል፡፡
እንዲህ እንዲያ እያሉ እየኖሩ ሳለ፤ ሚስት ትታመማለች፡፡ በሽታው እየጠናባት ይመጣል፡፡ ባል ያልሞከረው አኪምና የአበሻ መድሃኒት የለም፡፡ አልሆነም፡፡ በሽታው እጅግ በረታባትና በመጨረሻ ህይወቷ አለፈ፡፡
ባል ያለ ሚስት ብዙ ዓመት ኖረ፡፡ ቆይቶ ግን የሰፈሩ ሰው መክሮ ዘክሮ፤
“እስከ መቼ ባዶ ቤት ያለ ሚስት ትቀመጣለህ?” ብለው ብዙ ወትውተውትና መክረውት እሺ ብሎ ሌላ ሚስት አገባ፡፡
ይችኛዋ ሚስት ደግሞ የሟችቱ ተቃራኒ ሆና ቁጭ አለች፡፡
ምን ሲደረግ ካልጋህ ትነሳለህ? ምን ሲደረግ በእጅህ ትጐርሳለህ? እኔ እያለሁልህ? እያለች በአፍ በአፉ ታጐርሰዋለች፡፡ “ከፈለክ ረፈድ አድርገህ ና፤ እኔ ሞፈር ቀምበርህን እርሻው ቦታ አደርስልሃለሁ” ትለዋለች፡፡ ትሄዳለች ተሸክማ፡፡
ማታም ሞፈር ቀምበሩን አግዛው አብረው ያመጣሉ፡፡ እግሩን ታጥበዋለች፡፡ በቅባት ሰውነቱን ታሸዋለች፡፡ በጣም ደስተኛ ሆነ!
ያም ሆኖ የሰው ነገር ይገርማል፡፡ ያ ገበሬ ሲፀልይ እንዲህ አለ አሉ፡-
“አምላኬ ሆይ! የተሻለች ሚስት የምትመጣ ከሆነ ምነው እቺም በሞተች!”  
*    *    *
አዳም ስሚዝ የተባለው የኢኮኖሚክስ ሊቅ፤ “Human wants are unlimited” ይላል፡፡ (“የሰው ልጅ ፍላጐት ማቆሚያ የለውም” እንደማለት ነው) ትንሽ ልጅ፤ ትንሽ አሻንጉሊት ሲገዛለት ትልቅ አሻንጉሊት ይፈልጋል፡፡ ብስክሌት ሲገዛለት ሞተር ይጠይቃል፡፡ ሞተር ሲሰጠው ደግሞ መኪና ይጠይቃል፡፡ ከመኪናም ወዲያ ሌላ ሙግት ይኖረዋል! ይህ የሰው ልጅ ተፈጥሮ የፍላጐት ሂደት ነው፡፡ ይህንን በሀገር ህዝብ መንዝረን ብናየው ህዝብ መንግሥትን የሚጠይቀው ጥያቄ ማቆሚያ የለውም፤ ለማደግና የተሻለ ህይወት ለመምራት ምንጊዜም ከመፍጨርጨር አይቦዝንም፡፡ መንግሥት ደግሞ ልክ በማበጀትና ከዚህ በላይ አቅም የለኝም በማለት ምላሽ ከመስጠት ወደ ኋላ አይልም፡፡ በመካከል ትንቅንቅና ግጭት ሲፈጠር፣ የአምጣ፣ አላመጣም ፍጭት ሲከሰት፣ አልፎ ተርፎም አመፃዊ ሁኔታ ሊጐለብት ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ዲሞክራሲ ይኑር፣ ሰላም ይፈጠር፤ የተሻለ ዓለም እንይ የሚባለው፡፡ ይሄ የምንጊዜም ሂደት ነው፤ ያለ የነበረና ወደፊትም የሚኖር የህልውና ፍሬ ጉዳይ ነው፡፡
በሀገራችን የመብት ጥያቄ፣ የነፃነት ጥያቄና የኢኮኖሚ መሻሻል ጥያቄ ነጋ - ጠባ ሲወተወት ለዓመታት የከረመ ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ዘንድ ወጣቱ፣ ምሁሩ፣ ነጋዴው፣ ሀብታሙና ችግርተኛው በየበኩላቸው ሲፍረመረሙ ብዙ ዘመን ተጉዘዋል፡፡ ዛሬም ገና ይጓዛሉ፡፡ ብዙ ትግል፣ ደም ማፍሰስና ጦርነት በዚሁ ጉዳይ ላይ ተካሂዷል፡፡ ሊካሄድም ይችላል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ብዙ ፍሬ አላፈራንበትም፡፡
ማስተዋል ያለብን አንድ ጉዳይ ግን የምንጠይቀው ጥያቄ አግባብነት ያለው የበሰለና፣ የሀገሪቱን አቅም ያገናዘበ መሆን እንዳለበት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከራስ ጥቅም ይልቅ የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅ የቆሙ ልባም ልጆችን ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ ወጣት፣ ጐልማሳ፣ አዛውንትና አሮጊት ሳይባል ”የሀገር ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ነው” ብለው በቆራጥነት ሌት ተቀን መድከም ዋና ጉዳይ ነው፡፡
በሀገር ጉዳይ ሲመጣ የማይነካካ ነገር የለም፡፡ ሁሉ ነገር ሰንሰለታዊ ብልልት (Chain Reaction) አለው፡፡ ተያያዡን ነገር ሁሉ እያንዳንዱን ቀለበት እየፈቱ ሰንሰለትን ሙሉውን ማጠንከር ተገቢ ነው፡፡
የአገራችን ሰው ሲተርት፣ “እደጅ ያለው ሰንበሌጥ ሲታጨድ፣ ማድቤት ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ሰፌድ ይንቀጠቀጣል!” የሚለው ለዚህ ነው! ነገሮችን በተናጠል ሳይሆን ሙሉ ሥዕላቸውን እንይ!!  

Read 14332 times