Saturday, 16 May 2020 11:19

COVID-19 --እና የቤተሰብ እቅድ ዘዴ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ተግባራዊ ለማድረግ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመቆጣጠር የሚያስችል መከላከያን ወይንም ዘዴን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አለምን በማስጨነቅ ላይ ያለው ኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ መድሀኒቶችን ለመጠቀም አንዳንድ ጥያቄዎች መሰንዘራቸው አይቀርም ከሚል የአለም የጤና ድርጅት ድረገጽ ያወጣውን ጥያቄና መልስ እኛም ለአንባቢዎች ወደአማርኛ መልሰነዋል፡፡
1/ የ COVID-19 ወረርሽኝ ታማሚ በምሆንበት ወቅት ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከያን መጠቀም ይቻላልን?
ማንኛውም በባለሙያ የሚታዘዝ ዘመናዊ የመከላከያ ዘዴን የኮሮና ቫይረስ ታማሚ በሚሆኑበት ወቅት ማቋረጥ አይገባም፡፡ ልክ እንደወትሮው መጣም ይቻላል፡፡ በእርግጥ ልጅ ከወለዱ ገና ስድስት ወር ገደማ ከሆነ እና አንዳንድ ሕመሞች ማለትም የስኩዋር ሕመም፤ ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት፤ የጡት ካንሰር፤ የመሳሰሉት ታማሚ ከሆኑ ወይንም የሚያጨሱ ከሆነ ከሕምና ባለሙያዎች ምክር መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከባለሙያዎቹም ከጤና ጋር በማይጋጭ መልኩ የትኛውን መከላከያ መውሰድ ጠቃሚ ይሆናል የሚለውን ምክር ማግኘት ይቻላል፡፡
2/ የኮሮና ቫይረስ ታማሚ በምሆንበት ጊዜ እርግዝና እናዳይኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ምን ማድረግ አለብኝ?
እርግዝና እንዳይኖር በሚፈለግበት ወቅት ይወስዱት የነበረውን መከላከያ ምንጊዜም ሳይቋርጡ ወይንም እንደአዲስ በመጀመር መከላከያውን መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡ ለማንኛውም ለሚወስዱት እርምጃ ከጤና ተቋማት ወይንም ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት ማግኘት እና በቂ መረጃ እንዲኖርዎ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ ለዚህም የግድ ወደተቋማቱ መሄድ ሳይጠበቅብዎ በቀጥታ መስመር አማካኝነት በመጠቀም ተገቢ የሆነውን ባለሙያ ማነጋገር ይጠቅማል፡፡ ይህንን ዘዴ መጠቀም የማይችሉ ከሆነ ግን በራስዎ ካለሐኪም መድሀኒት ማዘዣ የሚጠቀሙበትን እንደ ኮንዶም የመሳሰሉትን መከላከያዎች በቅርብዎ ከሚገኙ የመድሀኒት ቤቶች በመግዛት መጠቀም ይቻላል፡፡
3/እኔ የምፈልገውን አይነት መከላከያ የማላገኝ ከሆነ ምን ትመክሩኛላችሁ?
የሚስማማውን ወይንም ቀደም ሲል ይወሰድ የነበረውን መከላከያ ማግኝት ካልተቻለ የሚመለከተውን የሙያ ተቋም ወይንም የጤና ባለሙያ በማነጋገር የሐኪም ማዘዣ በመያዝ ወይንም በሕምና ባለሙያ አማካኝነት መከላከያው የሚገኝበትን መንገድ መፈለግ ይገባል፡፡ ምናልባትም ኮንዶምን መጠቀም፤ የማርገዝ እውቀት ላይ መሰረት ያደረጉ ዘዴዎችን ከባለሙያ ማግኘት (ምናልባትም ጡት በማጥባት ላይ ከሆኑ) አለዚያም ሌላ በባለሙያዎች የሚታዘዝ እና በአገር ውስጥ ማግኘት የሚችሉትን የመከላከያ ዘዴ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በአገር ውስጥ ባሉ እድሎች መጠቀም ሲባል በኪኒን መልክ የሚወሰድ፤ወይንም አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ፤ የመሳሰሉትን ሊጨምር ይችላል፡፡
4/COVID-19 ወረርሽኝ ባለበት ሁኔታ የተሻለ የሚባል መከላከያ አለ?
ማኝኛውም ዘመናዊ የመከላከያ ዘዴዎች እርግዝናን መከላከል ስለሚችሉ ይኼኛው ከዚህኛው የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ሴቶችና ቤተሰቦቻቸው የትኛውንም አይነት ተስማሚ የሆነ መከላከያ ለመውሰድ ቢወሰኑ ተቀባይነት የአለውና ጤናማ ሁኔታ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡  እንደ ሚታወቀው ብዙ አይነት የመከላከያ ዘዴዎች ያሉ ሲሆን መም ረጥ አስፈላጊ የሚሆነው ለምትወስደው ሴት ተስማሚ መሆኑ ብቻ ነው፡፡
ኮንዶም በትክክለኛው መንገድ እና ወሲብ በመፈጸሙ ወቅት ሁሉ ከተጠቀሙበት ያልተፈለገ እርግዝናን በመከላከል እና ኤች አይቪን ጨምሮ በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ የሚተላለፍ በሽታን ለመከላከል ብቸኛው ዘዴ መሆኑ የታወቀ ነው:: ኮንዶም ሌላ አይነት የእርግዝና መከላከያ እየተወሰደም ቢሆን በሽታን ለመከላከል በተጨማሪነት በመጠቀም ሊተላለፍ የሚችለውን የህመም አደጋውን መከላከል ይቻላል፡፡
አፋጣኝ የመከላያ ዘዴ (Emergency contraceptive pills) ወሲብ ከተፈጸመ እስከ 5 ቀን ድረስ ከተወሰደ 95% ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ያስችላል፡፡ ይህ መከላከያ በሐኪም ትእዛዝ ወይንም በግል መጠቀም የሚቻል ነው፡፡
5/ ቀደም ብዬ ያደረግሁትን ሉፕ (IUD) የኮሮና ቫይረስ ሕመም ላይ ሆኜ ማስወጣት እችላለሁን?
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ህመም ላይ ሆኖ ቀደም ሲል በሰውነት ውስጥ የተደረገውን  እንደ ሉፕ (IUD) ያለውን የእርግዝና መከላከያ ከጥቅም ላይ እንዲውል ከተወሰነው ቀን እና አገልግሎቱ መጠቀም ከተጀመረ ወዲህ ተገቢውን የህክምና ክትትል ከማድረግ ውጭ አገልግሎቱን ለማቋረጥ ለማስወጣት መሞከርን ያሉበት ሐገር የጤና ተቋም በእንደዚህ ያለ አፋጣኝ የወረርሽኝ ወቅት ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ አይሆንም፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በእርግጥ በተለያዩ እንቅስቃሴዎችና ተግባራት የተነሳ ይህንን የመከላከያ ዘዴ ለመጠቀም የማያስችል ክስተት ቢኖር እና ማውጣት ቢያስፈልግ እንኩዋን በባለሙያዎች በመታገዝ ሌላ የእርግዝና መከላከያን መውሰድ ይገባል፡፡  
ሉፕ (IUD) ወይንም implants የመሳሰሉት የረዥም ጊዜ የእርግዝና መከላከያዎች በአፋጣኝ ከሰውነት ባይወጡም የሚያስከትሉት የህክምና ችግር አይኖርም፡፡ በምንም ምክንያት እነዚህን መከላከያዎች ካለባለሙያዎች እገዛ በገዛ ፈቃድ ማስወገድ አይቻልም፡፡ ተጠቃሚዋ እራስዋ ለማስወጣት መሞከር የለባትም፡፡
6/ በCOVID-19  ወረርሽኝ ጊዜ የእርግዝና መከላከያ፤የቤተሰብ እቅድ ዘዴ፤የቤተሰብ እቅድ ዘዴ አገልግሎት እና እውቀትን ማስጨበጥ ለምን ያስፈልጋል?
ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያና የቤተሰብ እቅድ ዘዴ መረጃና አገልግሎት ህይወትን የማዳን ተልእኮ ያላቸው እና በማንኛውም ጊዜ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ወሲባዊ ድርጊቶች በኮሮና ቫይረስ ጊዜም ይሁን በማንኛውም ጊዜ ይቋረጣሉ የሚባሉ አይደሉም፡፡ ስለዚህም ሰዎች መብታቸውን ባከበረ መንገድ አገልግሎቱን ማግኘታቸውና ሙሉ መረጃ እና እውቀት እንዲኖራቸው ማድረጉ እሳቸው በቤተሰባቸው ጉዳይ ወስነው መከላከያውን እንዲጠቀሙ ስለሚያስችላቸው ነው፡፡
ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያው ያልታቀዱ እርግዝናዎች እንዳይከሰቱ በማድረግ፤ልጃገረዶችና ሴቶች ጤናቸው እንዳይቃወስ እና ወደከፋ ደረጃ እንዳይሄዱ ለማድረግ ያግዛል፡፡ ያልተፈለገ እርግዝና የሚገጥማቸው ሴቶች ብዙውን ጊዜ ደህንነቱ ወደአልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ስለሚሄዱ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ስለዚህም ጽንስ ማቋረጥ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድም ይሁን ባልተጠበቀ መንገድ እንዳይኖር እና የልጃገረዶቹ ወይንም የሴቶቹ ጤና እንዲጠበቅ እና ሕይወታቸው እነዲተርፍ ይረዳል፡፡  
ስለዚህም ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል ያልተፈለገ እርግዝናን በማስወገድ የተዛባ ጤና እንዳይኖር፤ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ እንዳይኖር፤ በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፍ ኤችአይቪን ጨምሮ infection (መመረዝ) እንዳይከሰት ለማድረግ በCOVID-19. ወረርሽኝ ወቅት የሁሉም ሀገራት ጤና ተቋማት በትኩረት የሚሰሩበት ይሆናል፡፡  
ህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት እንዲችል በአለም ጤና ድርጅት የወጡ የተለያዩ መመሪያዎቸ አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑትን እናስነብባችሁ፡፡
የጤና ባለሙያዎች ተገቢውን እውቀትና አገልግሎት ለተገልጋዮች መስጠት እንዲችሉ ማብቃት
የሞባይል ስልኮችና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም በማሳደግ ሰዎች በእርግዝና መከላከያ አወሳሰድ ላይ የሚፈልጉትን ውሳኔ መወሰን እንዲችሉ ማድረግ፤
የቤሰብ እቅድ ዘዴ አገልግትን ህብረተሰቡ በቀላል መንገድ እንዲያገኘው ሁኔታዎችን ማመቻቸት…ወዘተ የሚሉ ይገኙበታል፡፡Read 22062 times