Saturday, 16 May 2020 12:03

በሸርተቴ ሞራል ሰበራ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

"--የእኛ ህዝብ እኮ ይህን ሁሉ ዘመን የኖረው በባህላዊ ህክምና ነው! አሁንም ቢሆን እኮ…አለ አይደል…ምናልባትም ከአራት አምስተኛ በላይ ህዝባችን የሚጠቀመው ባህላዊ መድሀኒት ነው፡፡ ታዲያላችሁ… ለእኛ ሲሆን ነገርዬው ግልብጥብጥ የሚለው ለምንድነው! የእኛ የብዙ መቶ ዓመታት ባህላዊ እውቀቶች ለምንድነው ‘ህቅ፣ ህቅ’ የሚለን! የምር ያሳዝናል፡፡ --"
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ … በአንዳንዶቻችን አስተሳሰብ የ‘ፈረንጅ’ የሆነ ነገር ሁሉ ጥራት ያለው ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ… “አልሰሜን ግባ በለው…” የሚባለው ተረት የሚሠራው፡፡ የተረት ነገር ከተነሳ አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አሁን የእኔ አይነቱ…አለ አይደል… “ጥይትና ክፉ ቀንን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ነው” ብሎ ቢተርት ‘ካልኩሌሽኑ’ ልክ ላይመጣ ይችላል፡፡ “በዚህ ቁመትህ ከዚህ በላይ ምኑን ዝቅ ትላለህ!”  ብሎ ሞራል ላይ ከፍተኛ ጥቃት የሚያደርስ መአት ነዋ! እኛ ዘንድ እንደሆነ ሞራልን በተመለከተ…ነገርዬው ለሞራል ግንባታው ማንም ሰው አልመጣ ለሰበራው ጊዜ ከየቤቱ ወጣ አይነት ነገር ነው፡፡
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምንም ነገር ላይ “የእነሱ አሪፍ፣ የእኛ ቀሺም” አይነት ሀሳብ ያልለቀቀን መአት ነን፡፡ የሆነ ነገር የእንግሊዝኛ ወይም የሆነ የውጪ ቋንቋ ስም ከተለጠፈለት፣ ምን አለፋችሁ… ገና ምኑም ሳይታይ  “ጉደኛ ጥራት” ያለው ነው፡፡ “እነሱ ከሠሩት አሪፍ ነው ማለት ነው” አይነት ነገር ይባላል፡፡  “ስማ ይሄ ዝም ብሎ ከምናለሽ ተራ የመጣ መሰለህ … ኦርጂናል የጀርመን እቃ ነው፡፡”  “ጀርመን! አትለኝም!”
እናላችሁ…የሆነ የሀገርኛ ስም ያለው ከሆነ ‘የማይረባ’ ነው፡፡ “ለምን ብዬ ነው ማንም ለተጫወተበት ገንዘቤን የምከሰክሰው!” አይነት ነገር ይባላል፡፡ የምር እኮ…አለ አይደል…ምንም እንዳንሠራ፣ ምንም ለመፍጠር እንዳንሞክር የሚያደርጉን እንዲህ አይነት አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ ታዲያላችሁ … በየጊዜው ወጣቶች “እንዲህ አይነት ነገር ሠሩ”፣ “በአካባቢው ባገኟቸው እቃዎች አንዲህ የሚባል መሣሪያ ገጣጠሙ” ሲባል እንሰማለን፡፡ እንደዚህ አይነት ችሎታ ያላቸው ልጆች አነሰም፣ በዛም የፈጠራ ዝንባሌ አላቸው ማለት ነው፡፡ ግን ምን ያደርጋል፣ በአብዛኛው “አይዞህ፣ በምትፈልገው ነገር እናግዝሀለን” ብሎ ነገር የለ፡፡ “በዚሁ ከቀጠልክ ነገ አንተም ትልቅ ስፍራ ትደርሳለህ፣ ሀገርም ታስጠራለህ” ብሎ ሞራል ግንባታ የሦስት ደቂቃ ዜና ሆኖ ያልፋል፡፡
እናላችሁ…የውጪዎቹ ሰዎች እኮ ሥራቸውን ሲሠሩ ኖረዋል፡፡ የሚያብረቀርቅ የስፔይን ጫማ ግጥም አድርጎ “የሀገር ውስጥ ጫማ ለምን አትገዙም!” ብሎ የሚተች ‘ቢዝነስማን’ በሽ የሆነበት ዘመን ነው፡፡
ለሞራል ግንባታው ማንም ሰው አልመጣ
ለሰበራው ጊዜ ከየቤቱ ወጣ
ስሙኝማ…አሁን ለወረርሽኙ ከመቶ በላይ ክትባቶች ሙከራ ላይ ናቸው እየተባለ ነው፡፡ እነ ቻይና ባህላዊ መድሀኒቶችን ጥቅም ላይ ስለማዋላቸው ስናወራ ነበር፡፡ (እንደውም ልምድ አካፍለዋል የሚል ዜናም ሰምተናል፡፡) እሰየው ነው፡፡ “እነሱ እኮ በባህላዊ መድሀኒት የሚስተካከላቸው የለም” አይነት ነገር እንላለን፡፡ አንድ ሰሞን ለጨጓራ ለምናምን ፍቱን ናቸው እየተባለ የቻይና ባህላዊ መድሀኒቶች በአምስት መቶና በሰባት መቶ ብር ስንገዛ ከርመናል፡፡
እኛስ! የእኛ ህዝብ እኮ ይህን ሁሉ ዘመን የኖረው በባህላዊ ህክምና ነው! አሁንም ቢሆን እኮ…አለ አይደል…ምናልባትም ከአራት አምስተኛ በላይ ህዝባችን የሚጠቀመው ባህላዊ መድሀኒት ነው፡፡ ታዲያላችሁ… ለእኛ ሲሆን ነገርዬው ግልብጥብጥ የሚለው ለምንድነው! የእኛ የብዙ መቶ ዓመታት ባህላዊ እውቀቶች ለምንድነው ‘ህቅ፣ ህቅ’ የሚለን! የምር ያሳዝናል፡፡  
በዛ ሰሞን ዘመናዊ እውቀትን ከባህላዊ እውቀት ጋር አጣምሮ እየተደረገ ያለ ሙከራ ለኮሮናቫይረስ  መድሀኒት ተስፋ ሰጪ ምልክት አሳይቷል ተብሎ መግለጫ ተሰጥቶ ነበር፡፡ “ድንቄም መድሀኒት!” አይነት ነገር ያልነው እኛው ራሳችን ነበርን፡፡ እንዲህ አይነት ዜና ሊያስደስተን፣ ሊያኮራን፣ “ይበል፣” ሊያሰኘን አይገባም ነበር እንዴ! ግን ምን ያደርጋል…ለረጅም ጊዜ ሰርስረው ሲቀበሩብን የኖሩት “የእነሱ አሪፍ፣ የእኛ ቀሺም” አስተሳሰብ እውነቱን በዓይናችን ሙሉ እንዳናይ አደረገን፡፡ “እኛ ነን ለኮሮናቫይረስ መድሀኒት የምናገኘው!” አይነት መሳለቅ ነበር፡፡
እናማ…የአንዳንዶቻችን “ድንቄም፣ ተመራምራችሁ ልባችሁ ወልቋል” አይነት አባባል ላይገርም ይችላል፡፡ ምኑንም፣ ምናምኑንም የምናየው በ‘ቦተሊካ’ ዓይን ነውና! (በቃ ይሄ አይነት ነገር ላይለቀን ነው!) ሌሎቻችን ግን ‘የውጭው አሪፍ፣ የሀገር ውስጥ ቀሺም’  አመለካከት ደግ እንዳናስብ አድርጎናል፡፡ ምን መሰላችሁ…ስለ ምርምሩ መግለጫ በሚሰጥበት ጊዜ አብሮ አንድ ‘ፈረንጅ’ ቢኖር ኖሮ ጭብጨባው እስካሁን አያቆምም ነበር፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ዘንድሮ እኮ በዚህ በወረርሽኝ የተነሳ “የፊተኞች የኋለኞች ይሆናሉ…” አይነት ነገር እየሆነ ነው፡፡ ስንት ሲወራለት የኖረው የሰው ልጅ የስልጣኔ ጥግ እየታየ ነው፡፡ ‘ሳይንስ ፊክሺን’ ውስጥ የሚገኙ የሚባሉ አይነት ህይወት ማጥፊያ ጦር መሳሪያዎች እንደ ጉድ እየተፈበረኩ አንዲት ትንሽዬ ቫይረስ የሰው ልጅን ዳር እስከ ዳር ስታምስ ‘የክፉ ቀን ደራሽ’ የሆነ እውቀት አልተገኘም፡፡ “ለካስ ሀያልነት ሲባል የኖረው እዚሁ ድረስ ነው!” የሚያስብል ነው፡፡
“ምነው ጠፋህ፣ ድራፍት እርግፍ አድርገህ ተውክ እንዴ?!”
“የሆነ ሥራ ጀምሬ ብዙ ጊዜ ከቤት አልወጣም፡፡”
“ምን እየሠራህ?”
“የሆነ ልብወለድ መጽሀፍ መጻፍ ጀምሬ እቤት…”
“ቆይ፣ ቆይማ! ምን ጀምሬ ነው ያልከው?”
“መጽሀፍ መጻፍ ጀምሬ…”
“አንተ ሰውዬ፣ አንደኛውን ለይቶልህ መዘባረቅ ጀመርክ! ተሳስተህ መጽሐፍ መሸጥ ጀምሬ ማለትህ አንዳይሆን!”
ለነገሩማ…እውነተኛ ወዳጅ ማለት የነበረበት… “አትለኝም! እንዴት እንዳስደሰትከኝ አታውቅም፡፡ ብቻ መሀል ላይ ሳትጨርሰው ታቋርጥና ቅልጥ ያለ ጠብ ውስጥ ነው የምንገባው፡፡” እንዲህ አይነቱ ማበረታቻ ነው የናፈቀን፡፡
 ለሞራል ግንባታው ማንም ሰው አልመጣ
ለሰበራው ጊዜ ከየቤቱ ወጣ
ግርም የሚል ነገር አለ፡፡ አሁንም እኛ ስላልሞከርነው ወይም “እኛ ልንሠራው አንችልም” ብለን ግጥሚያው ሳይጀመር የሽንፈታችንን ፎጣ መድረኩ ላይ ስለወረወርን ሌላውም ሊሠራው የማይችለው ይመስለናል፡፡ እናላችሁ…ዘንድሮ ‘ሸርተቴ’ እየገቡ ሞራል ሰበራ በሽ፣ በሽ ሆኗል፡፡
 “ዩኒቨርሲቲ ምን ለማጥናት ወሰንሽ?”
“ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪነግ፡፡”
“ምን!”
“ሰምተሽኛል፣ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ፡፡”
“አታስቂኝ እባክሽ፣ አምፖል መለወጥ የማትችይ ሴትዮ እዛ ድረስ ምን ያንጠራራሻል!”
“ተንጠራራሁ እንዴ!”
“እኔ ነገሬያለሁ፣ የማትችይው ነገር ውስጥ ገብተሽ በኋላ ገና በሁለት ወርሽ ጨርቅሽን ጥለሽ መንገድ እንዳትወጪና ጦስሽ ለእኛ እንዳይተርፍ!”
አያችሁልኝ አይደል! የመጀመሪያ ጥያቄ አምፖል ቅየራን ምን አመጣው! ልክ እኮ አምፖል ቅየራ ራሱን ችሎ እንደ አንድ ኮርስ የሚሰጥ አስመሰለችው፡፡
እናላችሁ…  በዚህ ዘመን የሸርተቴ ሞራል ሰበራ በሽ፣ በሽ ነው፡፡
ምናለ. አለ አይደል… “ብራቮ ጓደኛዬ! እንኳን ይሄ የፈለገው ቢመጣ እንደማያቅትሽ እተማመንብሻለሁ” ብትላት ምኗ ይጎድላል!  
ስለ ‘ሸርተቴ’ ስናወራ እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው…እንግሊዞቹ ምን አያሉ ነው! ፕሬሚየር ሊግ ሲጀመር ታክል፣ ሸርተቴ ብሎ ጨዋታ የለም ምናምን የሚባለው ምን ሲሉ ቢያስቡት ነው! አሀ…ቫንዳይክ በ‘ታክል’ ስተርሊንግን ካላንደባለለው ምኑን ከመቀመጫችን ተነሳን! አለበለዛ ስር ስሩ ጎል ድረስ አጅቦ የሚከተለው ‘ቦዲጋርዱ’ አይደል!  ደግነቱ ሰርጂዮ ራሞስ ወደ ጨዋታ ዘመኑ መጨረሻ ደረሰ እንጂ በዚህ ህግ ብቻውንም ቢሆን ሰልፍ ይወጣ ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ለሞራል ግንባታው ማንም ሰው አልመጣ
ለሰበራው ጊዜ ከየቤቱ ወጣ
በሸርተቴ ሞራል ሰበራን ይዞ ብን የሚል ነፋስ ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኛማ!


Read 2100 times