Tuesday, 19 May 2020 00:00

አይባልም

Written by  ኤልያስ ሽታሁን
Rate this item
(0 votes)

  የአፍሪቃ ሽግግር........ሺ' ግርግር
                    
    መንግስት የሚለውን ቃል በምድር ላይ የሚቆም ፅነሰ-ሀሳብ አይደለም፡፡ በሰማይ በዛኛው አለምም የፈጣሪ መንግስት እንዳለ ሀይማኖት የመሰከረው መፅሀፍ ያጠነከረው ሀቅ ነው፡፡ "...መንግስትህም ትምጣ ...."  እያልን እንፀልይ የለ፡፡ ያኛው መንግስት ግን የማይወጣ የማይወርድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡
ስናደምቀው...# ...
መንግስት የሚለውን ቃል  ስንሰማ አብዛኞቹ የአፍሪካ ወጣቶች ላይ የሚመጣው ምስል አንድ አይነት ነው፡፡ምስሉ ካየነየው ከሰማነው አይደል የሚቀዳው፡፡
ብዙዎቹ አፍረቃውያን የአፍሪቃ ጨለማነት ከራሳቸው ከተወላጆቹ አፍሪቃውያን ይመነጫል ባይ ናቸው፡፡
አንዳንዶች የአፍሪቃ ወድቆ መቅረት የተጠና የተሰላ የታሰበበት በዘመን ሂደት የተደገሰበት ነው ብለው ይናገራሉ፡፡ ብቻ ወዲህም አልን ወዲያ የአህጉሪቱ የመከራ ስንክሳር ዛሬም ያልተቋጨ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ አብዛኞቹ የሰላም ኖቤል እንጂ የትምህርት የእውቀት ኖቤል አለመውሰዳችንም የሚነግረን ሀቅ በተቃራኒው ሰላም አልባ መሆናችንን ነው፡፡  (ነገር ግን በስነፅሁፉም እነ ነጂብ መሀፉዝን ሳንረሳ ማለት ነው፡፡) የዘሬን ያንዘርዝረኝ አይነት ነገር ሆኖብኝ ስለ አህጉረ አፍሪቃ መነፋረቄን አልተውኩም፡፡  ለዚህም ነው በተከታታይ ባነበባችሁት ፅሁፌ ውስጥ የአፍሪቃን ነገር ማወሳሳቴም፡፡ማነሳሳቴም፡፡
ወደ መሬት ስናወርደው.....
የአፍሪቃ የስነ መንግስት ጉዳይ በእንቶፈንቶ የተሞላ ነው፡፡ ከአፍሪቃ ቤተመንግስቶች የአስተዋይ ባልቴቶች ማጀት የተሻለ ነው፡፡ የሰው ዘር ምንጭ አፍሪቃ ለሰው የማትመች ሆናለች፡፡ ፖለቲካዋ ከሀይማኖቷ ሀይማኖቷ ከተፈጥሮ ሀብቷ የተፈጥሮ ሀብቷ ከሙስናዋ ተደበላልቆባት መስማትም ማየትም መናገርም የማትችል መሬት ከሆነች ሰነበተች፡፡ ወገን የማታውቁትን አይደለም የምነግራችሁ፡፡ የረሳችሁትን አልያም ለምዳችሁ የናቃችሁትን እንጂ፡፡ የሆነ ጊዜ ባነበብኩት ጥናት የአፍሪቃ መከራ አምጪ መሪዎች መሀል 70 በመቶ የሚሆኑት የሽግግር ነን ብለው ስልጣኑን የተቆናጠጡ ናቸው፡፡ ( ስልጣን መቆናጠጥ የሚለው አገላለፅ ይደንቃል፡፡ መቆናጠጥ ማለት አንድን ነገር  መያዝ በሚችሉበት አካል ሁሉ ወጥሮ መሰብሰብ በእጅ መዳፍ ውስጥ ማስገባት እንደማለት ነው፡፡ ምንም ቀዳዳ አይገኝበትም፡፡ መቆናጠጥ ነዋ፡፡ ከዛ ህዝብን ወደ መቆን....ይገባል እንደማለት ነው፡፡)
ከቀደመው ያየነውም ይሄንኑ ነው፡፡
ሀገረ ኡጋንዳን ከቀኝግዛት መሪዎች የተረከባት ሌላኛው ተወላጅ ቀኝ ቀዢዋ ኢዲ አሚን ዳዳ የሽግግር መንግስት የመከራ ምንጭነት ምስክር ነው፡፡ ( ኢዲ አሚን 1916 ወይም 1918 እንደተወለደ ይነገርለታል፡፡ የቀን ስራ እየሰራ በእናቱ ቤት ያደገው ኢዲ አሚን ከ4 ክፍል የዘለለ የአስኳላ ታሪክ የለውም፡፡ በእንግሊዝ ጦር ውስጥ ወጥ ቤት በመሆን ተቀጥሮም አገልግሏል፡፡ በዚህ የአግልግሎት ዘመኑ ነው እንግዲህ ከ10 አለቅነት እስከ ጀነራልነት የደረሰው፡፡ ሙሉ ስሜም  'ክቡር ጀነራል ፊልድ ማርሻል የጆግራፊ ፕሮፌሰር ሀጅ የኡጋንዳ የምንግዜም ፕሬዘዳንት ኢዲ አሚን ዳዳ' ነው አለ፡፡የሄ ስም እና ማዕረግ ያጎደለ ሰው ከህይወት ድጎድላል፡፡ ኢዲ አሚን ከ1963-1971 ዓ.ም ኡጋንዳን ገዛ፡፡) ሰውየው ለአንድ ሳምንት ላሸጋግራችሁ መጣሁ አለ፡፡ ኡጋንዳውያን አሜን አሉ፡፡ በዚህ ሳምንት የሀገሪቱን ስር መሰረት የሚሆኑ ተቋማትን እንፈጥራለን አለ፡፡ ኡጋንዳውያን አሜን አሉ፡፡ዲሞክራሲያዊ ነፃ ምርጫ እናደርጋለን አለ፡፡ ኡጋንዳውያን አሜን አሉ፡፡ ከዚህ ቡኃላ ጥጋብ ነው አለ፡፡ ሰላም ነው አለ፡፡ እድገት ነው አለ፡፡ ኡጋንዳውያን አሜን አሉ፡፡ ጊዜ እና ሰይጣን ለኢድያሚን ምን ሹክ እንዳሉት አይታወቅም፡፡ በሳምንቱ በቀጥታ ስርጭት   " ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የኡጋንዳ መሪ እኔ ነኝ፡፡ የማይከሰስ መሪ የማይታረስን መሬት ይዣለሁ፡፡ የኡጋንዳ የዘላለም ንጉስ በሚል ተቀጥላ ጥሩኝ፡፡ " አለ፡፡ አለ፡፡  ኡጋንዳውያን አሜን ጠፋባቸው፡፡ ክፋ መሪ አሜንህንም ያጠፋብሀል፡፡ ለያዥ ለገናዥ የከበደ ዘመን አሳለፉ፡፡ በየአቅጣጫው የሚነሳውን ግርግር እያስታከከ የመቃብር መሬት እስኪጠብ ወጣቶችን በወጡበት አስቀራቸው፡፡ ፀጥ ለጥ ቀጥ አደርጎ አንቀጥቅጦ ገዛ፡፡ ሽግግር ያለው ስርአት ሺ' ግርግር ወለደ፡፡
ልክ እንዲሁም  ከንጉሳዊው ስርዓት ወደ ሌላ ንጉሳዊ ስርዓት(ደርግን ማለቴ ነው)  የተሸጋገርንበት የ66ቱ አብዮትም ርዕሱ ሽግግር ነው፡፡ ውስጠ ታሪኩ ግን ግርግር ነው፡፡  ሌላ መሬት ስናወርደው..... በሀገረ ጦቢያም :- የሽግግር መንግስት ..የምርጫ መራዘም... የህገ-መንግስት መጣስ....የመገንጠል ድፍረት....ሌላም ሌላም ሲባል ሰማሁ፡፡ ሰማን፡፡ ይህ ሀሉ ነገር ሲፈተፈት "ህዝብ" የሚባል ክቡር ክቡድ ነገር የት ተጥሎ ይሆን ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ምሁር እና ፖለቲከኞቻችን  ለህዝብ ያላቸውን ንቀት በስድብ መግለፁን አቁመዋል፡፡ ተመስገን፡፡ አሁን ንቀቱን ጭራሹን ህዝቡን በመርሳት መግለፅ ጀምረዋል፡፡ የተረሳ ህዝብ ለመታወስ ሲል ድንጋይ መወርወር ግድ የሆነባት አህጉረ አፍሪቃ ነገሯ ግራ ነው፡፡ ከሁሉም ገራሚው ነገር ከታሪክ ያልተማሩ ነገር ግን ታሪክ በየካምፓሱ የሚያስተምሩ ሰዎች እንደማየት ምን ያስደነግጣል፡፡ ወገን ቁማሩ የተበላ ቢመስልም፡፡  የትኛውም ፖርቲ ደጋፊ ባልሆንም የኢትዮጵያ ምንነት እና ማንነት ግን ደጋፊ ነኝ፡፡ ምንነቷን ከማንነቷ የሚነጠሉትን ሁሉ ነጥዬ ማየት እችልበታለሁ፡፡ መብትም ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅለቱን ታዘቡልኝ፡፡ ህገመንግሰቱ ላይ ስነ መንግስቱ ላይ ቤተመንግስቱ ላይ በየቀኑ ስንተነትን መዋላችን አጀብ ነው፡፡ በዚህ 50 አመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ፖለቲካ መተቸት ቀሏል፡፡ ፖለቲካውም ቀሏልና፡፡ ህገ መንግስቱን እኔም እኩዮቼም እንተቸዋለን፡፡ አስቅኙ ነገር ህገ-መንግስቱ 1987 ዓ.ም ሲፀድቅ እኔ እናቴ ሆድ ውስጥ ነበርኩ፡፡
 በኔ የሚተች በወጣቶች የሚነቀፍ ቀሊል አውድ ሆኖ መቅረቱ የየዕለት ትዝብታችን፡፡ ስለዚህ ለከበረችው ሀገር የከበረ ሀሳብ እንፍጠር፡፡ ቢያንስ በኛ የማይገመገም ፖለቲካ፡፡ እንደነ አክሊሉ ሀበተወልድ የነጠረ የጠጠረ ሀሳብ  እናምጣ ወይ ለሚችሉት ትተን  እንውጣ፡፡  
ወገን... ወደ ከባዱ ግን ወደ ትክክሉ ፖለቲካ መሄድ ድልም እድልም ይጠይቃል፡፡
የሀሳብ ሽግ ሽግ የሌለው ፖለቲካ ግርግር እንጂ ሽግግር አይባልም፡፡


Read 4494 times