Saturday, 23 May 2020 15:04

ከአንበሳና ከነብር ማን ያሸንፋል ሲሉት፤ ከሁሉም ከሁሉም አሣ ሙልጭልጭ ነው

Written by 
Rate this item
(6 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን ረዥም ጊዜ ሰፈሩ ሳይታይ ቆይቶ የመጣ አንድ ሰው፣ አንድ ወዳጁን መንገድ ላይ ያገኘዋል፡፡
ወዳጁም- እንዴ አንተ ሰውዬ፤ ለረጅም ጊዜ አልተያየንም እኮ፤ ታመህ ሆስፒታል ገብተህ ነበር እንዴ? ሰውዬው- አረ አልታመምኩም፤ ሆስፒታልም አልገባሁምለ፤ ምነው አሟረትርክብኝ!
ወዳጁም -- ሟሟረቴ አይደለምለ፤ ታስታውሳለህ ብዙ አመታችን እኮ ነው ከተያየን፡፡ እዛ አቶ አስማማው ልጅ ሠርግ ላይ የተያየን እኮ ነን፡፡ ስንት አመት ሆነው? ሦስት አራት? አረ እንጃ፤ አራትም አይጠቅመው፡፡ ምን ሆነህ ጠፋህ?
 ሰውየውም - አለሁ የት እሄዳለሁ ብለህ ነው?
ወዳጁም - ወይ ከአገር ወጥተህ መሆን አለበት
ሰውየው - ኧረ የትም አልወጣሁ
ወዳጁም - ታዲያ የት ሄደህ ነው፣ ሰው ሁሉ ጠፋህ ጠፋህ  የሚልህ
ሰውየው - ምን እባክህ ለአንድ አራት አመት አስረውኝ ነበር
ወዳጁም - አራት አመት? አራት አመት እኮ ብዙ ነው፤ ለመሆኑ ምን አድርገሃል ብለው ነው
ሰውየው - ኮርቻ ሰርቀሃል ብለው ነው
ወዳጁም - ለአንድ ኮርቻ አራት ዓመት፤ እንዴ የማይመስል ነገር ነው
ሰውየው- ምን እባክህ ከስሩ አንድ የማትረባ በቅሎ ነበረች
*   *   *
ሁልጊዜ ቀጥተኛውን እና ዋነኛውን ነገር ትተን፣ ርዝራዡንና የማያስጠይቅ የሚመስለንን እናስቀድማለን፡፡ ውሎ አድሮና የማታ ማታ ግን እውነቱ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ አጥብቆ ጠያቂ እንደሚኖር አለመገንዘብ የዋህነት ነው፡፡ ሠርቄያለሁ ላለማለት ሳያዩኝ ተዋስኳቸው ይላል፤ እንደተባለው ነው፡፡ ይልቁንም “አዘለም አንጠለጠለም ያው ተሸከመ ነው፡፡” የሚለውን ተረት አበክሮ ማሰብ ይሻላል፡፡ ወደ ዋናው ጉዳይ ወይም እንደ ዘመኑ አባባል፣ ወደ ገደለው መግባት ይሻላል፡፡ እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር የሚለው ሁለተኛ አገላለጽም፣ እንደዚያው ወደ ሃቁ የሚያስጠጋን ሁነኛ ብሂል ነው፡፡
በተለይ በፖለቲካዊ አካሄዳችን ውስጥ መሸፋፈንን እንደ ልማድ እንደያዝነው የረዥም ጊዜ እውነት ነው፡፡ አበው አንድን ሰው ፖለቲካ ተናገረ ሲሉ፣ ዋሸ የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ በቃሉ ውስጥ መስክረው ነው፡፡ እንደ ወትሮዋዊ አነጋገርም ቦተለከ ይሉታል፡፡ ይሄ የመነጨው ገዥዎች አብዛኛው ጊዜ መዋሸታቸው አሌ የማይባል ነገር በመሆኑ ነው፡፡ በገዥነት የመቆያ ትልቁ መላ፣ ያልሆነውን ሆኗል፤ የሆነውን አልሆነም ማለት ነበረ፡፡ ነውም፡፡
ወደፊትም የሚቀጥል እውነት ነው፡፡ የዲሞክራሲ አንዱ ገጽታው ግልጽነት ነው. የምንለውም ይሄን ሃሳዊ ዲስኩር ወይም ዴማጐጂ ለማስወገድ አልያም ለመከላከል ነው፡፡ በአንድ ትንሽ ውሸት የተጋለጠ መንግሥት፤ በትልቅ ውሸት መጠርጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
ሌባው ለማ
ቢተው ይተው
አለበለዚያ እኛ ጀንበር በሰረቀ ቁጥር አውጫጭኝ ተቀምጠን እስከ መቼ እንችለዋለን አሉ ይባላል፡፡ አንድ አዛውንት አንድ ስብሰባ ላይ፣ ለማ ቢተው እና ጀንበር የተባሉ ሌቦች ሰፈሩን እየሰረቁ ስላስቸገሩ በቅኔ ወይ በዘዴ መናገራቸው ነው፡፡ በግልጽ መናገር ስለሚያስፈራም ነው፡፡
እስከ ዛሬ ብዙ ሽፍንሽኖችን አልፈናል፡፡ ስለ ረሃብ ተዋሽተናል፡፡ ስለ ጦርነት ተዋሽተናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኮሌራን እንኳ አጣዳፊ ተቅማጥ ነው ተባብለናል፡፡ አሁን ግን የፈጠጠ ነገር መጣ፡፡
“ኮሮና!” በይፋ እንድንናገረው አስገድዶናል፡፡ በግልጽ እንድንወያይበትም ወጥሮ ይዞናል፡፡ ለሁሉም ችግሮቻችን ግልጽነትን እና ውይይትን መሣሪያ ማድረግ ባህል ሊሆን ይገባል፡፡
የተጠየቅነውን ጥያቄ በግልጽና በማያወላዳ መንገድ መመለስ፣ ለችግሮቻችን ቢያንስ በሃምሳ ፐርሰንት መልስ እንደ መስጠት ነው፡፡ በግልጽና በቀጥታ ምላሽ መስጠት እንልመድ፡፡
 አለበለዚያ “ከአንበሳና ከነብር ማን ያሸንፋል ሲሉት፣ ከሁሉም ከሁሉም አሣ ሙልጭልጭ ነው” አለ እንደተባለው እንሆናለን፡፡  
ይህንን መዋጋት አለብን፡፡ መከላከል አለብን፡፡ ባህል ማድረግ አለብን፡፡ ነገ ብሩህ ይሆንልን ዘንድ ብሩህነትን ከዛሬ እንጀምረው፡፡


Read 13567 times