Saturday, 23 May 2020 15:14

‘ሹሮ በአናት’ እና ‘የመሬት ጥበት…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

  “እግረ መንገድ እኛም ሀገር ሁሉም በሳጥን፣ በሳጥኑ እየተደለደለ ይለይልንማ! ልክ ነዋ…ዘላለማችንን ግራ እየገባን ልንኖር ነው እንዴ! ምንድነው አስር ጊዜ ‘ቆዳ መለዋወጥ!’ እናማ ሀሳብ አለን… “እነ እከሌ አንዴ እንደ ቅዱስ፣ ሌላ ጊዜ እንደ ተቃራኒው የሚያደርጋቸው ጭር ሲል ስለማይወዱና ተርመስመስም ማድረግ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ እነ አከሌ ደግሞ በአንድ ራስ ሁለት ምናምን የሚሆኑት ‘ነካ ሊያደርጋቸው’ ዳር ዳር እያላቸው ስለሆነ ነው፣ ይባልልና … ቁርጣችንን እንወቅ፡፡--”
             ኤፍሬም እንዳለ


             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ምንድነው እንዲህ ለምቦጭህን የጣልከው?”
“እባክሽ ደብሮኛል…”
“ታዲያ ፊልም አታይም!”
“ፊልም ራሱ ሰልችቶኛል…”
“እውነት! እንግዲያውማ የእኔ አንበሳ፣ ምን አድርግ መሰለህ… የቢዮንሴን ሙዚቃ ክፈትና እንደ እሷ ዝለል፡፡ ያኔ የተከመረብህ ድብርት ሁሉ እርግፍ ይልልሀል፡፡”
“አንቺ ደግሞ አርእስት አትለውጪ እንጂ! ደብሮኛል ብዬ በጽሁፍ ማመልክቻ ማስገባት አለብኝ! ቀጥተኛውን አማርኛ ቅኔ አታድርጊው…”
“ሰውዬው ዛሬ ምን ነክቶታል! …ስማ (ይጨበጨባል) እህ...እህ…እህ! እንዲህ ነው ነገሩ! እየው እንዲች ብለህ ጫፌን እነካለሁ ብትል የሚንተከተከውን ሹሮ አናትህ ላይ ነው የምቸልሰው!”
እናማ፣ ምን መሰላችሁ…ለሆድ የታሰበው ሹሮ አናት መቸለስ፣ አለመቸለሱ ሰበር ዜና ወይም ‘የጋራ መግባባት’ ላይ ተደርሶ የመሆኑ ‘ሰበር ስኩዌርድ’ ዜና እኛ ዘንድ የሚደርሰው መቼ መሰላችሁ…ከዘጠኝ ወር በኋላ! ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን የዓለም የጤና ድርጅት ሰዎችም፤ ሰዉ ሁሉ ቤቱ ተቆልፎ ወደዚች ዓለም የሚመጡ አዳዲስ እንግዶች ቁጥራቸው በጣም ይጨምራል … ምናምን ነገር ሲሉ ነበር፡፡ እኔ የምለው…በቃ ገና ለገና ሁሉም ነገር…አለ አይል…‘ሬዲ ፎር አክሽን’ መሰለና ‘ፋሚሊ ፕላኒንግ’ ምናምን የሚባለው ሁሉ ፉርሽ ሆነ ማለት ነው! 
አንድ ሰሞን መብራት በፈረቃ ወይ ፈረቃ ሊመስል በቀረበ አይነት፣ ጨለማ በጨለማ አድርጎን በነበረ ሰሞን እኮ ሰዉ ሁሉ ቁጭ ከማለት ጋደም ማለት አበዛና… በተሰረገ በአስር ዓመትም… “የዛሬ ዓመት፣ የማሚቱ እናት” አይነት ነገር በዝቶ ነበር ይባላል:: በነገራችን ላይ…ባለሙያዎቹ ቢያንስ በቀን ለሠላሳ ደቂቃ ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሥሩ ብለዋል:: እናማ…ይሔ ነገር ‘ምክር እንደ ፈቺው ነው፣’ አይነት ሆነ እንዴ!  
ስሙኝማ… ብዙ ጊዜ እንዳሁኑ ሁሉም ነገር የጨላለመ በመሰለ ጊዜ ከጨለማው ውስጥም ትንሽ የብርሀን ጭላንጭል አይጠፋም ነው የሚባለው፡፡ ብዙ ሰዎች ቤታቸው በመሆናቸው መጽሀፍ የማንበብ በጎ ምልክት እየታየ ነው ተብሏል፡፡ 
አለ አይደል…ይህንንም ያንንም ማነባበቡ ቢያንስ፣ ቢያስ ነገሮችን በጥቁርና ነጭ ብቻ ከምናይበት ልማድ በትንሹም ሊገላግለን ይችላል፡፡ አሀ…ዘንድሮ የብዙዎቻችን ችግር እሱ ነዋ! ሁሉን ነገር ወይ አሳንሶ ጥሬ ማሳከል፣ ወይ አግንኖ ቋጥኝ ማሳከል! የምር ግን… ብዙ ነገር ላይ አይደለም መግባባት፣ በስነስርአት ተነጋግረን መደማመጥ ያቃተን ይሄ… “ወይ ጥቁር ነው፣ ወይ ነጭ ነው፣ አራት ነጥብ!” በሚል ዓይነት አመለካከት ነው፡፡
የመጽሀፍ ማንበብ ነገር ሲነሳ የማይሞቃቸው፣ የማይበርዳቸው ወዳጆች አልፎ፣ አልፎ ይገጥሙናል፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘አይሞቀንም፣ አይበርደንም’ የምትለው የአንድ ሰሞን ‘የቦተሊካ ማሟሟቂያ’ ነገር. በቃ ወራሽ አጣች ማለት ነው! ልክ ነዋ… እየሰማናቸው ባሉ ብዙ ፍሬ ከርስኪ ነገሮች ውስጥ አልፎ አልፎ ሸጎጥ ብትደረግልን…“ቢያንስ አባባሏ የሆነ ስነጽሁፋዊ ነገር አላት” ብለን ብሽቀታችንን እናስታምምባት ነበር፡፡ እዚህ ሀገር ቲራቲር በዛብን  እኮ!  
እኔ የምለው… እግረ መንገድ ለጨዋታው ያህል…  ለወባ ተሠራ የተባለውን መድሀኒት ስወስድ ነው የሰነበትኩት ያሉት ሰውዬ፤ አንዳንዴ ግርም አይሏችሁም! አለ አይደል…አንዳንዴ ሁሉንም ነገር ‘ፌክ ኒውስ’ ሲሉ…አለ አይደል… “ከአንጀቱ ሳይሆን ጭር ሲል ስለማይወድ ተርመስመስ ማድረግ ፈልጎ ነው” ምናምን ትላላችሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ‘ዘ ሞስት ፓወርፉል ማን ኢን ዘ ወርልድ’ የሚባልላቸው ሰውዬ ጸረ ተዋህስያን የሆነው የመጠዳጃ ቤት  ሳሙና “ለምን በመርፌ መልክ እየተሰጠ አይሞከርም ሲሉ፤ “አይ የሆነ አብሾ ነገር ቢኖርበት እንጂ ማንም ጤነኛ ሰው እንዲህ አይነት ‘ነካ የሚያደርገው ሰው’ ሀሳብ አያመጣም” ትላላችሁ፡፡ ብቻ…ምን አለፋችሁ… እስከ ህዳሩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ  ድረስ ብዙ ትርኢቶች ማየታችን አይቀርም፡፡
እግረ መንገድ እኛም ሀገር ሁሉም በሳጥን፣ በሳጥኑ እየተደለደለ ይለይልንማ! ልክ ነዋ…ዘላለማችንን ግራ እየገባን ልንኖር ነው እንዴ! ምንድነው አስር ጊዜ ‘ቆዳ መለዋወጥ!’ እናማ ሀሳብ አለን… “እነ እከሌ አንዴ እንደ ቅዱስ፣ ሌላ ጊዜ እንደ ተቃራኒው የሚያደርጋቸው ጭር ሲል ስለማይወዱና ተርመስመስም ማድረግ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ እነ አከሌ ደግሞ በአንድ ራስ ሁለት ምናምን የሚሆኑት ‘ነካ ሊያደርጋቸው’ ዳር ዳር እያላቸው ስለሆነ ነው፣ ይባልልና … ቁርጣችንን እንወቅ፡፡ እንደውም የተሻለ ሀሳብ… መለያቸው የኮሚኒስትም ይሁን፣ የሊበራልም ይሁን፣ የምንም ይሁን… ብቻ ‘ማኒፌስቷቸው’ ላይ ይካተተልን፡፡ እንዲህ መገላገል እያለ! 
ደግሞላችሁ “ከእንግዲህ መጽሀፍ የማነበው የት ለመድረስ ነው!” የሚሉ አሉ፡፡ ወይም ደግሞ ምን የሚሉ ሊገጥሟችሁ ይችላሉ መሰላችሁ፡፡
“አንብብ፣ አንብብ የምትሉኝ አነበብን የሚሉትን ይኸው እያየናቸው አይደል! ሀገር ከመበጥበጥ ሌላ ምን ቁም ነገር ሠሩና!” የሚሉ አሉ፡፡ ይሄን እንኳን ሙሉ ለሙሉ ለማስተባበል ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ልክ ነዋ…ምንም እንኳን ሁሉንም ጠቅልሎ መፈረጁ ልክ ባይሆንም፣ እንዲህ የሚያስብሉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ “እምዬ ድራፍት ምን አለን… ጭቅጭቅ የለ፣ ንትርክ የለ…ጭራሽ ምናምኒዝም፣ ትርኪምርኪዝም እያልን፣ እነሱን እንሁንልህ!” የሚሉ ወዳጆችን፤ ‘ድራፍቱን ሶስት ጊዜ አዙረው ጥለውባቸው ነው’ ምናምን ማለቱ ልክ አይሆንም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…፣ አንዳንዴ ሠላሳ ምናምነኛ ፎቅ ላይ አውጥታችሁ ያስቀመጣችሁት ሰው፤ በንግግሮቹና በሚሰጣቸው አስተያየቶች ምድር ቤት ስታገኙት እንኳን እንዲህ ሌላም ያስብላል!
“ስማ፣ ትናንት ማታ እንትና የተናገረውን ሰማህ አይደል! አንጀትህን አላራሰውም?”
“አንጀቴን እንኳን አላራሰውም፡፡ ግን ጥሩ ነገር ነው የተናገረው፡፡”
“ነግሬሃለሁ ሰውየው ፖለቲካዋን ምጥጥ ነው ያደረጋት፡፡”
ከወር ምናምን በኋላ…
“አንተ! እኔ በተራዬ ልጠይቅህ…ያ ሰውዬህን ማታ ሰምተኸዋል? ምን ነክቶት ነው እንደዛ የሚዘባርቀው!”
“እባክህ እኔም ግራ ገብቶኛል…እየተገለባበጡ ጦጣ አደረጉን እኮ!”
እናላችሁ… ከተሰቀሉበት ‘ወርዶ ዘጭ’ አይነት ነገር በየእለቱ የምናየው ቲራቲር ሆኗል! አንድዬ፣ ‘በቃችሁ’ እስኪለን እየጠበቅን ነው፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የአንባቢዎች ቁጥር መጨመሩ ደስ የሚል ነው:: ልክ ነዋ…ገና ሳይሞከር ከሩቁ “ኸረ እዛው በጠበላችሁ…” ምናምን ከማለት ሞክሮ ‘ጉዱን ማየት’ ይሻላል፡፡ ለነገሩ መጽሀፍ ማንበብ ሲባል ዶስቶይቭስኪ፣ ዲክንስ ምናምን ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ‘የሚያቃጥል ፍቅር’ ምናምን የሚል መጽሀፍ አይጠፋም፡፡ (እነ እንትና ‘ፋታል አትራክሽን’ ‘ቦዲ ሂት’ ምናምን የሚባሉ ፊልሞች፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ ከታየ በኋላ ‘ሽቅብ’ ሲደረግ ስለነበረው ሩጫ፤ “እኛና ቦዲ ሂት” ምናምን የሚል መጥሀፍ ቢጤ የሚጥፍልን ይጥፋ! እግረ መንገድ… እነዚህ ፊልሞች ከ‘ሚያቃጥል ፍቅር’ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ እንዳልሆነ ልብ ይባላልንማ! ‘ጀስት ፎረ ዘ ሬከርድ…’ እንዲል ‘ፈረንጅ!’)
በዛ ሰሞን ኪራይ ቅነሳ ያደረጉ አከራይ ወገኖቻችንን እያመሰገንን ነበር:: ደግሞላችሁ… ልክ አመሻሹ አሥራ አንድ ሰዓት ተኩል በረንዳ ላይ ‘ነፋስ የሚቀበሉ’ መስለው ተቀምጠው ተከራዮች የሚገቡበትን ሰዓት የሚቆጣጠሩትም ትንሽ እፎይ ይላሉ፡፡
ስሙኝማ...የምር ግን በብዙ ስፍራ የምትሰሟቸው ነገሮች…አለ አይደለም…የምቀኝነት ይመስላል፡፡
“ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ የግቢ በር ይዘጋል” ከማለት ተገላገሉ ማለት አይደል፡፡  
ተከራይም ቢሆን… አለ አይደል… “አይደለም በዚህ እድሜዬ የአሥራ ሦስት ዓመት ልጅ እያለሁ እንኳን ፋዘር ማታ እስከ ሁለት ሰዓት እንዳታመሽ ብሎኝ አያውቅም” ብሎ ከመበሳጨት ለጊዜውም ቢሆን እፎይ ይላል፡፡ ለነገሩ…በአስራ ሦስት ዓመቱ ፋዘር.. “እስከ ሁለት ሰዓት እንዳታመሽ”  የሚሉት አራት ሰዓት ተኩል ላይ ከቤታቸው በታች ካለችው ‘የሎው ቤት’ ማን ደግፎ ያምጣቸው! እናማ… በዚህ በቤት ውስጥ ቆይታ ቀደም ብለው ያልነበሩንን ብዙ አሪፍ ባህሪያት መልማድ ይቻላል…ሹሮ በአናትን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ ግዴለም… ለሹሮ በአናት የሚሆን ‘ምቹ’ ጊዜ አይጠፋም:: በ‘ድብርት ሰበብ’…በዝተን መሬት እንዳይጠበን በሚል ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2391 times