Saturday, 30 May 2020 13:06

የኮሮና ጥቃት በዓለማችን ታላላቅ ፕሮፌሽናል የስፖርት ሊጎች ላይ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    • ከ22.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለስፖርተኞች ደሞዝ ወጭ ይሆን ነበር
         • በአሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪ ቅርጫት ኳስ፤ ቤዝቦልና ሆኪን ገበያቸው ተናግቷል
         • ‹‹የዝውውር ገበያው በ20 በመቶ ይቀዘቅዛል›› ትራንስፈርማርከት
        • ‹‹ በወረርሽኙ የሊጎች፤ የክለቦችና የተጨዋቾች የዋጋ ተመን ወርዷል›› ኬፒኤምጂ
       • በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ከቀጠሉ 6.6 ቢሊዮን ዩሮ፤ ከተሰረዙ 10.5 ቢሊዮን ዩሮ ይከስራሉ
      • የተጨዋቾች የዋጋ ተመን ሊጎች ከቀጠሉ በ17.7%፤ ከተሰረዙ በ26.5% ይወርዳል


             የዓለማችን ታላላቅ ፕሮፌሽናል የስፖርት ሊጎች በ2019/20 የውድድር ዘመን በኮሮና ሳቢያ ውስብስብ ቀውሶች አጋጥሟቸዋል፡፡  በየሊጎቹ የሚካሄዱ ውድድሮች ተቋርጠው መቆየታቸው ከፍተኛ ኪሳራ ከማስከተሉም በላይ ውድድሮች ካቆሙበት ቢቀጠሉና ቢሰረዙም ስፖርተኞች፤ ክለቦች የለመዱትን ገቢ ማጣታቸው አይቀርም:: የዓለም ኢኮኖሚ በመናጋቱ የስፖንሰርሺፕ እና የኢንቨስትመንት ውሎች ተቀንሰዋል፤ በድርድርም ተሰርዘዋል፡፡ ከቴሌቭዥን ስርጭትና ብሮድካስት መብት የሚፈሱ የገቢ ምንጮች በመርሃግበሮች መስተጓጎል ውሎች እንዲከለሱና በካሳ ክፍያዎች እየቀነሱ ናቸው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በዓለማችን ታላላቅ ፕሮፌሽናል የስፖርት ሊጎች ፤ቡድኖች እና ስፖርተኞች ላይ ያስከተለው ተፅእኖ 2019/20 የውድድር ዘመን በኢንዱስትሪው ታሪክ የማይረሳ አድርጎታል፡፡
ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ፕሮፌሽናል የስፖርት ሊጎች ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ የሚመለከት ሲሆን በተለይም ከፍተኛ መዋዕለንዋይ በሚንቀሳቀስባቸው የአውሮፓ እግር ኳስ አምስት ታላላቅ ሊጎችና ቅርጫት ኳስ፤ አሜሪካን ፉትቦል፤ ቤዝቦልና ሆኪን በሚያስተዳድረው የአሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ ያተኩራል፡፡
ፕሮፌሽናል የስፖርት ሊጎችና የደሞዝ ክፍያቻው ከኮሮና በፊት
ስፖርት ኢንተለጀንስ የተባለ ዓለም አቀፍ የስፖርት ዘጋቢ ድረገፅ Global Sport Salaries survey 2019 በሚል ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከኮሮና በፊት በዓለም ዙርያ ከ22.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለስፖርተኞች ደሞዝ ወጭ ይሆን ነበር:: ከኮሮና በኋላ ግን ይህ ዓመታዊ የደሞዝ ወጭ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ የማይቀር ይሆናል:: በሁሉም ፕሮፌሽናል ሊጎች ያሉ ስፖርተኞች የደሞዝ ቅነሳ እንደሚያጋጥማቸው ባለፉት ሁለት ወራት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ የእግር ኳስ ሊጎች የደሞዝ ቅነሳው በምርጥ ተጨዋቾች ላይ እስከ 25 በመቶ እየደረሰ ሲሆን በአሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ በከፍተኛ ገቢው እና ደሞዝ ክፍያ በሚታወቀው የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ሊግ NBA ተጫዋቾች ካለፈው ሰሞን ጨምሮ ከደሞዛቸው ላይ 25% ቅነሳ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
Global Sport Salaries survey 2019 በሚል ከ1 ዓመት በፊት ይፋ በተደረገው ሪፖርት በዓለማችን ፕሮፌሽናል ስፖርት  በ12 አገራትና በ8 ስፖርቶች፤ የሚወዳደሩ 350 ቡድኖች ፤18 ሊጎች ፤ ተዳስሰዋል:: sport intelligence ይህን ሪፖርት ለመስራት ተጨዋቾች በደሞዝ ክፍያቸው፣ በስፖንሰርሺፕንና የተለያዩ ንግድ ስራዎች፣ በማስታወቂያ፣ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች የሚኖራቸውን ገቢ አስልቷል:: ከዚሁ ሪፖርት ያገኘናቸው የተለያዩ መረጃዎች ከኮሮና በፊት የዓለም ስፖርት ኢንዱስትሪ በደሞዝ ክፍያ የደረሰበትን ጣሪያ የሚያመለክቱ ናቸው::  ከአውሮፓ እግር ኳስ በከፍተኛ ደሞዝ ከፋይነት ሪያል ማድሪድ፤ ባርሴሎና እንዲሁም ጁቬንትስ ከ1 እስከ 3 ደረጃ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ከኮሮና በፊት የዓለማችን ትልቁ ተከፋይ ስፖርተኛም የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ ሲሆን በ2017 /18 የውድድር ዘመን ላይ በክለቡ ያለውን ቆይታ እስከ 2021 ሲያራዝም ደሞዝን ጨምሮ በዓመት የሚከፈለው እስከ 55.34 ሚሊዮን ዩሮ ደርሷል፡፡ የሜሲ ከፍተኛ ገቢ  ከሁሉም ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ አንደኛ ሆኖ ሲቀመጥ ከደሞዝ፤ የቦነስ ክፍያዎች እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ጋር የምስል መብቱንም ስለሚጠቀም ነው፡፡ ከባርሴሎናተጨዋቹን ለመግዛት የሚፈልግ ማቅረብ ያለበት ክፍያ እስከ 686 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚጠይቅም ተገልፆ ነበር፡፡ ከኮሮና በኋላ ግን ይሄው የሜሲ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ በዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ እንኳን ወደ 127 ሚሊዮን ዩሮ ወርዷል፡፡
በመላው ዓለም በሁሉም የስፖርት አይነት ከሚከናወኑ ፕሮፌሽናል የስፖርት ሊጎች ለስፖርተኛ በአማካይ ከፍተኛውን ዓመታዊ ደሞዝ በመክፈል ከ1 እስከ 5ኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ከዚህ በታች የቀረቡት ናቸው፡፡
1. 30 ቡድኖችና 440 ፕሮፌሽናል ቅርጫት ኳስ ተጨዋቾች ተመዝግበውበት በሚካሄደው በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ በድምሩ $3,661,652,248 ዓመታዊ የደሞዝ ክፍያ በመፈፀም ከዓለማችን የስፖርት ሊጎች ቀዳሚው ነው፡፡ ከ440 ቅርጫት ኳስ ተጨዋቾች 123 ያህሉ በአማካይ 10 ሚሊዮ ን ዶላር ዓመታዊ ክፍያ የሚያገኙ ሲሆን የሊጉ ስፖርተኛ አማካይ ደሞዝ $8,321,937 ይሆናል፡፡
2. 8 ክለቦች በሚወዳደሩበትና 128 ተጨዋቾችን በሚያሳትፈው የህንድ ክሪኬት ፕሪሚዬር ሊግ $90,893,850 ዓመታዊ የደሞዝ ክፍያ ይፈፀማል፡፡ የሊጉ ስፖርተኛ አማካይ ደሞዝ 5.3 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡
3. 30 ቡድኖችና 856 ፕሮፌሽናል ቤዝቦል ተጨዋቾች ተመዝግበውበት በሚካሄደው በአሜሪካ ሜጀር ሊግ ቤዝቦል በድምሩ $3,451,005,858 ዓመታዊ የደሞዝ ክፍያ ይፈፀማል፡፡ የሊጉ ስፖርተኛ አማካይ ደሞዝ $4,031,549 ይሆናል፡፡
4. 20 ክለቦችና 4966 ፕሮፌሽናል ኳስ ተጨዋቾች ተመዝግበውበት በሚካሄደው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በድምሩ $1,967,423,750ዓመታዊ የደሞዝ ክፍያ ይፈፀማል፡፡ የሊጉ ስፖርተኛ አማካይ ደሞዝ $3,966,580 ይሆናል፡፡
5. 32 ቡድኖችና 1696 ፕሮፌሽናል የአሜሪካንፉትቦል ተጨዋቾች ተመዝግበውበት በሚካሄደው በአሜሪካፉት ቦል ሊግ በድምሩ $5,524,555,998 ዓመታዊ የደሞዝ ክፍያ ይፈፀማል፡፡ የሊጉ ስፖርተኛ አማካይ ደሞዝ $3,257,403 ይሆናል፡፡
ከላይ ከእንድ እስከ አምስት ደረጃ ተሰጥቷቸው ከተዘረዘሩት የስፖርት ሊጎች ባሻገር የአሜሪካ ፕሮፌሽናል ሆኪ ሊግ 2.69 ሚሊዮን ዶላር፤ የስፓኒሽ ፕሪሚየራ ሊጋ 2.55 ሚሊዮን ዶላር፤ የጣሊያን ሴሪኤ 2.3 ሚሊዮን ዶላር፤ የጀርመንን ቦንደስሊጋ 1.98 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የፈረንሳይ ሊግ ዋን 1.23 ሚሊዮን ዶላር ለ1 ስፖርተኛ  ዓመታዊ ደሞዝ በዓማካይ በመክፈል እስከ 10 ያለውን ደረጃ ይወስዳሉ፡፡

Read 1151 times