Print this page
Saturday, 30 May 2020 13:50

‘ሀርድቶክ’ ወይም ‘ሀርድሳይለንስ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ! ዛሬ ወደ ቃለ መጠይቅ አድራጊነት ሽግግር ተደርጓል፡፡ (‘ጊዜያዊ’ የምትለው አንዲት ቃል እንደየ ተርጓሚዋ አንድ መቶ አንድ ቦታ ተበልታ የ‘ሀርድቶክ’ ሙከራዬን…“ድሮስ የማይችልበትን ማን ሞክር አለው!” አስብላ ፉርሽ እንዳታደርግብኝ ‘ተዘላለች፡፡’) እናላችሁ…“ቃለ መጠይቅ አድራጊ እንደዛ በበዛበት ጊዜ አንተ የማንን ጎፈሬ ስታበጥር ነበር!” የሚል ጥያቄ ከተነሳ ለማስረጃነት እንዲሆን ነው፡፡  ተመልካቾቻችን… (እንዴት ነው ነገሩ፣ ወይ ከፍ ያለ ወንበር ስጡኝ፣ ወይ ካሜራውን ዝቅ አድርጉልኝ፡፡ ቃለ መጠይቅ ላድርግ አልኩ እንጂ ባስኬትቦል ልጫወት ስቱድዮ አልገባሁ!)  ተመልካቾቻችን እንደምን አመሻችሁ… (የእኔን ፊት እያያችሁ እራቱ ሽቦ ጥብስ አልታኘክ ካለ ተጠያቂ እንዳልሆንኩ ልብ ይባል፡፡) ቢቸግር በጊዜው እባላለሁ፡፡ የዛሬ እንግዶቼን ለማስተዋወቅ  በስተግራዬ የሚገኙት አቶ ጥምዙ ቋጠሮ በቅርቡ የተቋቋመው የ‘አቋራጭ ቢሆን ለዲሞክራሲ ፓርቲ’ አመራር አባል ናቸው፡፡ (አቶ ጥምዙትንሽዬ እንኳን ደረት የፈጠረላቸው ቢሆን ኖሮ ፊኛ ያደርጓት ነበር፡፡ ገና ከአሁኑ እንዲህ ‘አንደርዌይት’ የሆኑ ለከርሞ ፖለቲካው …ይቅር ብቻ!)
በስተቀኝ የሚገኙት ደግሞ ከተቋቋመ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረው የ‘ዘላላም በተስፋ ሊግ’ የአባላት ምልመላና አደረጃጀት ሀላፊ አቶ ለከርሞም እዚሁ ናቸው፡፡ እንግዶቻችን ጥያቄያችንን ተቀብላችሁ …(ቀሪውን ስለምታውቁትና ስለሰለቻችሁ እናንተው ጨርሱልኝማ!) አቶ ጋዜጠኛ፡— አቶ ጥምዙ ጥያቄዬን በእርሶ ልጀምርና ድርጅታችሁ ከተቋቋመ ምን ያህል ዓመት ይሆነዋል? አቶ ጥምዙ፡— እ…ምን መሰለህ… (እኔ የምለው ይህ ሰውዬ ሳውቀው ድምጹ እንደ ወስፌ ጠቅ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን የሚጠቀጥቅ አልነበር እንዴ! ምን ቢውጥበት ነው ድምጹ እንዲህ ቁርጥ ሞርጋን ፍሪማን ሆኖ ቁጭ ያለው! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ይሄ የቲቪ ካሜራ ስንቱን የእኔ ቢጤ ‘ነፋስ የሚያሳልፍ ድምጽ የኦፔራ ዘፋኝ ድምጽ አስመሰለውሳ!) እንደ እውነቱ ከተደራጀን ወደ ስምንት ወይም ዘጠኝ ወር ገደማ ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን ምን መሰለህ… (የሆነ ነገር ብልጭ አለብኝሳ…ለእኔ ኢንተርቪው ብሎ እንደ ምንም ተሟሙቶ አዲስ ሙሉ ልብስ በመግዛቱ ሊያመሰግነኝ አይገባም እንዴ! “መጀመሪያ በአንተ የተነሳ በሰባት ዓመት ተኩል ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ልብስ በመግዛቴ ባለውለታዬ ነህ” ሊለኝ አይገባም እንዴ! የምን የሰውን ‘ክሬዲት’ ማሳጣት ነው!) የተቋቋምነው በቅርብ ቢሆንም ሀሳቡን ስናንከባልለው ከአስር ዓመት በላይ ይሆናል፡፡ “እኮ! እኛም የተቸገርነው ነገር አስር፣ ሃያ፣ አርባ ዓመት እየተንከባለለ ነው” ልለው ፈልጌ ከመቶ ምናምኑ መቶ ምናምን የጋራ የውግዘት መግለጫ ሊያወጡበኝ ‘የማይችሉበት ምክንያት የለም፣’ በሚል ተውኩት፡፡ እኔ የምለው… እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው…ለምንድነው ብዙ ጊዜ የጋራ መግለጫዎች የሚወጡት የውግዘት፣ የውግዘት ብቻ የሆነው! የ‘ሎካል ፖለቲክስ አፕቲትዩድ ቴስት’ የሚባል ነገር ከመጣ … ‘ጦጣ’ ላለመሆን ያህል ነው፡፡)  
አቶ ጋዜጠኛ፡— በአሁኑ ጊዜ እንደ አዲስ መደራጀት ለምን አስፈለገ? ለማለት የፈለግሁት… (በቃለ መጠይቁ ስድሳ አምስት በመቶ የአየር ሰዓትማ የእኔ የጠያቂው ነው! በገዛ ኢንተርቪዌ ልብ ልቡን ማጣት የለብኝማ! ስለዚህ ጥያቄው ውስጥ ተጠያቂው ሊሰጥ የሚችለውን መልስ በማስገባትም ይሁን ረዘም እያደረጉ የስድሳ አምስት በመቶ እቅድን ማሳካት ያስፈልጋል፡፡) ከመቶ ሠላሳ በላይ ቡድኖች ባሉበት (ማንቼና አርሴ መሰልነው እንዴ ቡድኖች እያለ ተቀባይነታችንን ሊያሳጥን የሚሞክረው? የማንን ስውር ተልእኮ ይዞ ነው!” ብለው የሚቀየሙኝ ይኖሩ ይሆን  እንዴ!) አቶ ጥምዙ፡— (ይስቃሉ፡፡ ሳቋ ራሷ እኮ ለቲቪ ካሜራው እንድትሆን በምናምን ሜጀርና በምናምን ማይነር ‘አፕዴት’ የተደረገች ነች፡፡  እናማ… የእሳቸው ሳቅ ማስመሰል ሜጀር ትባላለች፡፡) ስማኝ… አቶ ቢቸግር፣ መቶ ሠላሳ በለው፣ ሺህ ሠላሳ በለው ቁም ነገር የሌለበት ቁጥር ምን ያደርጋል! (በለው! የቃለ መጠይቅ አድራጊነት የመጀመሪያ ዙር እንጀራዬን ገና ጎረስኩ ስል ሊያስጥለኝ ነው እንዴ!) እንዲሁ ድርጀት ነኝ ብሎ ዓመት መቁጠር ምንም ማለት አይደለም፡፡ እድርም እኮ ሰባና ሰማንያ ዓመት ይቆያል፡፡ (ሰውዬ! የመቶ ምናምኖቹ አልበቃ ብሎት ከእድሮችም ሊያጣላኝ ነው እንዴ! ደግሞም…በዛች ሰዓት የሌላኛው እንግዳዬን የአቶ ለከርሞም እዚሁን ኩርፊያ ያየ በቃላት አይጫወትም! ቂ…ቂ…ቂ… ግዴለም የእሳቸው ተራ ሲደርስ በስፖንጅም ይሁን በብርጭቆ ወረቀት ለማለስለስ ይሞከራል፡፡) አቶ ጋዜጠኛ፡— ቢሆንም አቶ ጥምዙ… ህዝቡን ግራ ከማጋባት አንደኛውን ቡድን ተቀላቅሎ  በምክክር ነገሮችን ማሻሻል አይሻልም ነበር?
አቶ ጥምዙ፡— እሱም እኮ የሚሻሻል ሲኖር ነው፡፡ ምንም ነገር በሌለበት ላሻሽል ብትልስ ባዶውን አየር ምኑን ታሻሽለዋህ! (‘ብሬኪንግ ኒውስ’…ዘንድሮ የእኛ ‘ቦተሊካ’ ጦዘችላችሁ! የእነ እንትና ተላላኪ፣ የእነ እንትና ናፋቂ፣ ‘ምናምኒስት…መባባል ቀርቶ፣ አለ አይደል… “ከባዶ አየሪስቶች ጋር አብሮ መሥራት አይቻልም፣” ወደሚል የሆነ መቶ በመቶ ሀገር በቀል የሆነ ‘ቦተሊካዊ እመርታ’ አይታያችሁም!
አቶ ጋዜጠኛ፡— አቶ ለከርሞ፣ ወደ እርሶ ልምጣና የእናንተን ድርጅት የማያውቅ ዜጋ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ (ይኸው! እኔስ ምን አልኩ…ደግሞ የእኛን ሰው ለማለስለስ! እንደ ፈገግታቸው ከሆነ የ‘አሜሪካ ጎት ታለንት’ ምርጥ ኮሜዲ ያዩ ነው የሚመስለው!) ድርጅታችሁ ከተቋቋመ ባልሳሳት ሐያ አምስት ዓመት የሞላው ይመስለኛል፡፡
አቶ ለከርሞ፡— ትንሽ ለማስተካከል ያህል፣ ሀያ አምስት ሊሞላው ገና አንድ አስራ አምስት ቀን ይቀረዋል፡፡ (እርሶ የተነገ ወዲያው የዞር ድምር እስኪለቅዎት እኮ አስራ አምስት ቀኗ ከች ትላለች! ቂ…ቂ…ቂ…)
አቶ ጋዜጠኛ፡— ጥሩ፣ ግን ብዙ ሰዎች እንድንጠይቅላቸው የሚፈልጉት በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ምን እንደሠራችሁ ነው፡፡
አቶ ለከርሞ፡— በእውነቱ አንተም እንደምታውቀው ባለፉት ዓመታት በጣም በርካታ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ (እንደምታውቀው! የምን ማነካካት ነው! ገና ለገና የሺቫዝ ሬጋል ጣእም ምን ቃና እንዳለው እንዳውቅ አንድ ቀን በሦስት ደብል ጠድቀውብኛልና የምን የቡድንና የቡድን አባቶች ምናምን ነው!) የሠራናቸውን ነገሮች አይደለም እንደዚህ በአንድና በሁለት ሰዓት ዘርዝሮ ለማውራት፣ አንድና ሁለት ሳምንትም አይበቃም፡፡ (ከሦስት ዓመት በፊት በተጋበዝኩት ሺቫዝ ሬጋልማ አፌን አልዘጋም!)
አቶ ጋዜጠኛ፡— ከሠራችኋቸው ሥራዎች ለምሳሌ ያህል አንድ ሁለቱን ቢነግሩን፡፡ (ግንባራቸው የሰው ገላ ሳይሆን እርከን የተቆፈረበት ጋራ መሰለ፡፡) ልጄ ካርታው ላይ ዘጠኝ አበባ፣ ሶስት ዳይመንድ፣ ኪንግ፣ ኩዊን ምናምን አያስፈልግም…ሁሉንም በር በምታስከፍተው በጆከሯ መጫወት ነው፡፡ ጥምዙ በደስታ ተጠምዝዟል፡፡ አቶ ለከርሞ ደግሞ የተቆጣ ኮርማ መስለዋል፡፡)
አቶ ለከርሞ፡— ነገርኩህ እኮ…በአጭሩ የሚያልቅ አይደለም፡፡ እኛ ደግሞ እንዲህ ሠራን እንደዛ ሠራን ብሎ መመጻደቅ የድርጅታችን ባህል አይደለም፡፡ (አሁን ይሄ… “እንደው ጋዜጠኛ ከምታደርገኝ ምናለ ጋዝ አዳይ ብታደርገኝ ኖሮ!” አያሰኝም! በሀያ አምስት ዓመት ሀምሳ አምስት ጊዜ ወንበር ተገለባብጠው የድርጅታችን ባህል ይሉኛል!) በነገራችን ላይ ሁሉንም በመጽሀፍ መልክ አሰባስበን ለማሳተም እቅድ አለን፡፡ (ይቺ እንኳን በተቋቋሙ በሁለተኛው ዓመት ያወጧት ነጠላ ዜማ ‘ሪፕሌይ’ ነች!)
አቶ ጋዜጠኛ፡— አቶ ጥምዙ ወደ እርሶ ልመለስና…በድርጅታችሁ ላይ የሚነሱ አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ ምናልባት እርሶ መልስ ቢሰጡበት ብዬ ነው… (መቅለስለስ አበዛሁ እንዴ!) ድርጅታችሁ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን እንደ መንደር እቁብ አይነት አደረጃጀት ነው ያለው ይባላል፡፡ እዚህ ላይ የሚሉኝ ነገር ይኖራል? (“ይሄንን በወይራ ዱላ ወገቡ መቀንጠስ ነበር!” የሚለውን ምኞት ግንባራቸው ላይ አነበብኩ፡፡ አሀ… ኢንቬስቲጌቲቭ ጋዜጠኝነት ስለሚሞካክረኝ እውነቱን ፈልፍዬ ማውጣት አለብኛ! በቃ…ግንባራቸው ላይ አነበብኩ፣ አነበብኩ!)
አቶ ጥምዙ፡— በእውነቱ እንድትጠይቀኝ የፈለግሁትን ጥያቄ ነው ያነሳህብኝ፡፡ ገና  የድርጅታችንን መመስረት ይፋ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ እያለን ነው ዘመቻ የተጀመረብን፡፡ (አሁን ጨዋታ ሊመጣ ነው፡፡) የእኛ ድርጅት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከስረ መሰረቱ ለመለወጥ የተመሰረተ ነው፡፡ (አዲሱ አለቃዬ “ይሄ ሰውዬ ማንንም እያስወሻከተ ገና የመቶ ሺዋን ላፕቶፕ ሳልይዝ ከወንበሬ ሊያስፈነቅለኝ ነው እንዴ!” በሚል ወይ ሊጠምደኝ፣ ወይ ሊያስጠምደኝ፣ ወይ “ስውር ተልእኮ ያላቸው” ከሚላቸው ጋር በ‘መግለጫ ዳምጠው’ ሊመላለስብኝ ይችላል፡፡)  
አቶ ጋዜጠኛ፡— ጥሩ ነው፡፡ ግን አቶ ጥምዙ፣ ጥያቄዬን አልመለሱልኝም፡፡ በህዝቡ ውስጥ እየተወራ ስላለው መልስ እንዲሰጡኝ ነበር የፈለግሁት፡፡ (አቶ ለከርሞ በልጅነታቸው ደስታ ከረሜላ ሲገዛላቸው እንኳን እንደዛ ተፍለቅልቀው አያውቁም!)
አቶ ጥምዙ፡— ህዝብ! ህዝብ ነው ያልከኝ! ስለ የትኛው ህዝብ ነው የምናወራው? (ደግሞ ጀመረኝ የሚለውን የዘፈነው ማን ነበር! ደግሞ ጀመራቸው፡፡) ምን መሰለህ…
አቶ ጋዜጠኛ፡— ይቅርታ እንግዶቼ… የተወሰነልን ሰዓት ማለቁን ዳይሬክተሩ ምልክት እየሠጠኝ ነው፡፡ (ዳይሬክተሩ እኮ ምልክት መስጠቱ ሳይሆን የቂማው ሰዓት ስላለፈበት ነው  ያዛጋው! ቂ…ቂ…ቂ…) ጥሪያችንን አክብራችሁ እዚህ በመገኘት…. ሌላውን ስለምታውቁትና ስለሰለቻችሁ ጨርሱልኝማ!
“አንተ ሀርድቶክ ሳይሆን የሚያምርብህ ሀርድሳይለንስ ነው” የሚለውን ሰው ብዛት የሚያሰላ አፕሊኬሽን ሳያስፈልገኝ አይቀርም... በሰው ሀይል ተቆጥሮ ላያልቅ ይችላላ! ደግሞም ‘ሀርድሳይለንስ’ ሊያምርባቸው የሚችል ብዙ፣ በጣም ብዙ ስላሉ “እንዳንደበር ፓርቲ እንፍጠር፣” ልንባባል እንችላለን! ‘ካሚንግ ሱን!’
ደህና ሰንብቱልኝማ!   
 
 

Read 2126 times