Saturday, 06 June 2020 14:24

“አንድን ግንድ አሥር ዓመት ውሃ ውስጥ ብታስቀምጠው አዞ አይሆንም!”

Written by 
Rate this item
(8 votes)


           ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ አንድ ትልቅ የቋንቋ አካዳሚ ሊጐበኙ ወደ ዩኒቨርሲቲ ይሄዳሉ፡፡ ያ ዩኒቨርስቲ ሊቅ የተባሉ የቅኔ ምሁራን የሚማሩበት ነው፡፡ የንጉሡን ጉብኝት ምክንያት በማድረግ ለሶስት የተመረጡ ተማሪዎች የቅኔ ትርጉም ጥያቄ ይቀርብና ትክክለኛውን ፍቺ በጥሩ ሁኔታ ያቀረበ ይሸለማል ይባላል፡፡
ቅኔው እንደሚከተለው ቀረበ፡-
HERE LIES A DENTIST IN GRAVITY
FILLING HIS LAST CAVITY.
የመጀመሪያው ተወዳዳሪ፤
ቅኔው ያለው “LIES” የሚለው ቃል ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ ትርጉሙ፤ “ተኝቷል፤ ተጋድሟል ማለት ሲሆን፤ ሁለተኛው ትርጉሙ ደግሞ ዋሽቷል፤ ሐሰት ተናግሯል” ማለት ነው አለ፡፡
ሁለተኛው ተወዳዳሪ ደግሞ “ቅኔው ያለው “GRAVITY” የሚለው ቃል ላይ ነው፡፡ መንታ ትርጉም አለው፡፡ ባንድ መልኩ የመሬት ስበትን ሳይንስ የሚያሳይ ሲሆን፤ በሌላ መልኩ “የሰው ልጅ ሟች መሆኑንና ግብዐተ - መሬት የማይቀርለት መሆኑን የሚያሳይ ነው” አለ፡፡
ሦስተኛው ተወዳዳሪ ደግሞ “የለም፤ የቅኔው ቃል ያለው፡-
“CAVITY” የሚለው ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የጥርስ ሐኪሙ ሞቷልና፤ “ጉድጓድ ውስጥ መግባቱ ነው ወይም መቃብሩ ውስጥ ተኝቷል” የሚል ትርጉም ሲኖረው ሁለተኛው ፍቺው ደግሞ የጥርስ ሐኪሙ የተቦረቦረውን ጥርስ (CAVITY) እየሞላ ነው” ማለት ነው አለ፡፡
ዳኞቹ የሶስቱንም መልሶች ከመረመሩና ካጤኑ በኋላ፤
“ሶስተኛው ተወዳዳሪ፤ ያስቀመጣቸው ሁለት ፍቺዎች ማለት፤
CAVITY - የመቃብር ጉድጓድ እና
CAVITY - የጥርስ የተቦረቦረ ጉድጓድ ነው ያለውን በማድነቅ የሽልማቱ አሸናፊ እንዲሆን ወሰኑ፡፡
*   *   *
ጤናማ ውድድር ወይም ቀና ፉክክር የአንድን ህብረተሰብ ንቁ ተሳትፎ ከማበረታታቱም በላይ፤ በተለይ ወጣቱ የሰላና የተባ እንዲሁም አመዛዛኝ አዕምሮ ይኖረው ዘንድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
ይህንኑ አበርክቶ በማጤን ይመስላል የጥንቱ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ ንጉሡ ይጐበኙና የላቀ ችሎታ በየዘርፉ ላሳዩ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ይሰጡ ነበር፡፡
ተማሪዎች የቅጥር ግቢውን አካዳሚያዊ ነፃነት በመጠቀም ያለ አንዳች ፍራቻ ማናቸውም ዓይነት ይዘት ያለው ግጥም በመፃፍ፣ በይዘትም በቅርጽም በሳል አቀራረብ ያለው ያሸንፍ ነበር:: ጃንሆይም ለአሸናፊው ተገቢውን ሽልማት ይሰጡ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ የግቢው ባህል ዛሬም ቢነሳሳ መልካም ነው! አንድም የአስተሳሰብ መለኪያ ነው፡፡ አንድም የሃሳብ ነፃነት መጠየቂያ ነው፡፡ ሁለትም ደግሞ የነፃነቱን መግለጫ በጽሑፍ ነፃነት ማሳያ ነው፡፡
“ቁማር ጨዋታ ተጫውቼ
ተበልቼ ገባሁ ተረትቼ
ምንኛ ዕድሌ በሰመረ!
ዘውዱን ገልብጬ በነበረ!”
ዓይነት ድፍረት የተሞላ ቅኔ ማቅረቢያም ስለነበር የፖለቲካ አንድምታውም ቀላል አልነበረም:: ምንም እንኳን ዛሬ በዓለም - አቀፉ ወረርሽኝ በኮሮና ምክንያት ትምህርት ቤቶች ቢዘጉም ነገ ከነገ - ወዲያ ሁኔታዎች መቀየራቸው አሌ አይባልምና፤ ወጣቱን ትውልድ በገፍ የምናሳድግባቸውን እኒህን የዕውቀት መገንቢያዎች ለአንዲት አፍታም ቸል ልንላቸው አይገባም፡፡ ህብረተሰባችን መቼም ቢሆን፣ የተማረ ትኩስ ኃይል ይፈልጋል፡፡ ይህ ትኩስ ኃይል ከወጣት ጥፋተኝነት (Juvenile Delinquency)፣ ከአባካኝነት (Spend thrift)፣ ከተንኳሽነት (Provocation) እንዲገላገል የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን፡፡
ዞሮ ዞሮ አዲሱ አሸናፊ ነው! (The New is Invincible) አዲሱ አሸናፊ ኃይል ደግሞ ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱ በትምህርት ሊገነባ ይገባል፡፡ ወጣቱ ጤናው የተጠበቀ ሊሆን ይገባል፡፡ ወጣቱ የታረመ፣ የተኮተኮተና ከዋልጌነት የፀዳ መሆን አለበት፡፡ አካላዊ ብቃቱን ከትምህርት ውጪ ባለ ብልጽግና ማዳበር (Extra – curricular activity) ይኖርበታል፡፡ ምንም ሳናግዘው ብንወቅሰው ዋጋ የለውም፡፡ ከትምህርት ጠልነት፣ ከጨለምተኝነትና ከዳፍንተኝነት ልንገላግለው ይገባል፡፡ ከሱስ አባዜና ከቀቢፀ - ተስፋ ግራ-ገብነት እንድናወጣው ይሆነኝ ብለን መፍረምረም ተገቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት ያለፈበትን ታሪክ ዛሬም አድሶ ወደፊት እንዲራመድ ድልዳሉን ማመቻቸት የሁላችንም ዙሪያ - መለስ ኃላፊነት ነው፡፡ “ወደቀ ሲሉት ተሰበረ ነው” ወጣቱ፤ እያልን በስላቅ የምናልፈው ጉዳይ አይደለም፡፡ የኮሮና መምጣት “በደምባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንዳይሆንብንም፤
ጥናት
ጥንቃቄና
ጥረት፤ አይለየን!
ተንቀሳቃሽና ታታሪ ህብረተሰብ፤ እንዲሁም የለውጥ መሽከርክሪት ኃይል (Dynamism) ያለውና ለለውጥ ዝግጁ የሆነ ማህበረሰብ ለማፍራት እንንቀሳቀስ! እጅና እግርን አጣጥፎ በመቀመጥ የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡፡ “አንድን ግንድ አሥር አመት ውሃ ውስጥ ብታስቀምጠው አዞ አይሆንም” የምንለው ለዚህ ነው! በማናቸውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ መንገድ ብናጤነው ለውጥን የማይዋጅ ህብረተሰብ እያደር እየዘቀጠና ቁልቁል እየወረደ ይሄዳል::
(ፈረንጆቹ degeneracy, decadence እንዲሉት) የኩሬ ውሃ የሆነ ትውልድ መሆን አይገባም፡፡ የውሃ ወለድ በሽታ መቀፍቀፊያ እንደመሆን የሚቆጠር ነውና፡፡ ይልቁንም የወንዝ ውሃ መሆን ይበጃል፡፡ “የወንዝ ውሃ አለትን ያነጋግራል” ይባላል፡፡ ተንቀሳቃሽ ነውና ይጠራል፡፡ ሁሌም መንገደኛ ነውና አዳዲስ ነገር ይገጥመዋል፡፡
“እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል
ደሀ ሞኝ ነው ሞቱን ይመኛል”
የሚለውን ጥንታዊ አባባል መጠቀምን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ግንዱ ውሃ ውስጥ በመክረሙ ይበሰብሳል እንጂ አዞ አይሆንም፡፡ ይሄንን ታሳቢ ያደረገ ትውልድ ተስፋ ይኖረዋል፡፡ የለውጥን ፀሐይ ይሞቃልና!   Read 10045 times