Saturday, 06 June 2020 15:57

ወንፊት ሙሉ፤ ትሪ ባዶ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

       እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የተከበራችሁ ተመልካቾቻችን ቃለ መጠይቁ ቀጥሏል፡፡ እናማ… ቃለ መጠይቅ ማድረግን በተመለከተ ‘የሚናገረው ሃሳብ የሌለውን ሰው ቃለ መጠይቅ ስለማድረግ’ የሚል መጽሐፍ ይጣፍልንማ! የምር ግን…መአት ቃለ መጠይቅ ወንፊት ላይ ተደርጎ ቢጣራ፣ ስር ያለው ትሪ ምንም የተጣራ ነገር ስላማያርፍበት፣ በውሀና በሳሙና ሙልጭ ተደርጎ የታጠበ መስሎ ወደ ቦታው ባይመለስ ነው! ‘ይህ’ ጋዜጠኛ ግን የድንኳን ሰባሪ ቃለ መጠይቅ አድራጊነቱን ይቀጥላል፡፡
የዛሬዎቹ እንግዶቼን ለማስተዋወቅ ያህል ሁለቱም በተለያዩ ዘርፎች፣ በተለይም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ናቸው … (ዲፕሎማሲያዊ ፈገግታ እያሳየሁ እንደሆነ ልብ ይባል:: አክቲቪስቶች ፊት ‘አክት ማድረግ’ ግድ ነዋ! ቂ…ቂ…ቂ…) በእርግጥ እነኚህን እንግዶች ለተመልካቾቻችን ማስተዋወቅ ማለት ልክ ለአንድ ሰው የገዛ ወንድምና እህቱን እንደማስተዋወቅ ማለት ይሆናል:: የእንግዶቼን ፈገግታ ብታዩ ነገ ማለዳውን “ቃለ መጠይቅ የማድረግ ሰብአዊ መብታችን ይጠበቅ!” “ቃለ መጠይቅ አድራጊዎችን በመቅጠር የሚታየውን የዘመድ አሠራር እንቃወማለን!” የሚሉ መፈክሮች የያዙ ሰልፈኞች ቲቪ ጣቢያዎችን ሊያጨናንቁ ይችላሉ፡፡)
በስተቀኝ ያሉት አቶ ነቅንቅ አሳየው ሲሆኑ በስተግራ ያሉት ደግሞ ወ/ት ምንአይተሽ ዳርከዳር ናቸው፡፡
(ያኔም ከግራ ጎን፣ አሁንም በስተግራ! ወ/ት ምንአይተሽ ካወቀችበት አጄንዳ አገኘቻ! “ሁልጊዜም በግራ በኩል ሊያስቀምጡን የሚሞክሩትን ከለየላቸው ሾቪኒስቶች ለይተን አናያቸውም!” እንደ መፈክር ይጠቅም እንደሆን ብለን ነው፡፡  ‘ሾቭኒስት’ የምትለዋ ቃል አገባብ አክቲቪሰት ነን የሚሉት ሁሉ ‘የፈረንጅ አፍ’ ቃል እዚህም መሰንቀር፣ እዛም መሸጎጥ ስለሚቀናቸው ስሜታቸውን ለመጠበቅ ያህል ነው፡፡ “መጀመሪያስ ስሜት የሚባል ነገር አላቸው እንዴ!” ለምትሉ ይህን ጉዳይ በ‘ዙም’ ምናምን ነገር ‘እንድትጨቃጨቁበት’ የታሸገ ውሀውን ወጪ እኔ እችላለሁ፡፡ የታሸገ ውሀ የሌለበት ውይይት ‘ፎርጅድ’ ነው፡፡)
አቶ ጋዜጠኛ፡— እንግዶቼ ጥሪያችንን አክብራችሁ ስለመጣችሁ… (ገና ሳልጨርስ ራሳቸውን በመነቅነቅ ‘ይንቀባረሩብኛል’:: ምን ይደረግ… ‘ነቅንቅ’ እና ‘ምንአይተሽ’ የሚሉ ስሞች ይዘው ያልተንቀባረሩ በምን ይንቀባረሩ! እኔም ‘አቶ ጋዜጠኛ’ በሚለው ራሴን በሾምኩበት መጠሪያዬ የዘመድ ጉባኤ ላይ እንቀባረር የለ! ስሙኝማ…ዘንድሮ ያልተንቀባረረ ቲቪ ስቱድዮ መግባት ውድ በሚሆንበት ጊዜ… “በገዛ እጄ ሳንቀላፋ…የከተማ አውቶብሱም፣ ቀላል ባቡሩም አመለጠኝና አረፈው!” ማለት እንዳይመጣ ለማለት ያህል ነው፡፡)
እንግዶቼ፣ ጥያቄዎቼን በአቶ ነቅንቅ ልጀምርና፣ ለመግቢያ ያህል ስለ ራስዎ አንዳንድ ነገሮች ቢነግሩን፡፡ (እንዴት አይነት ጥያቄ ነው! ምርመራ ነው ቃለ መጠይቅ?) ተመልካቾቻችን በተደጋጋሚ ጠይቁልን ስለሚሉ ነው፡፡ (ጠይቁልን! ሳይቸግረኝ የቴክኖሎጂ  ዘመንን ልቀላቀል ብዬ ፌስቡክ ላይ ሁለቱን ‘ኢንተርቪው’ እንደማደርግ ለጥፌ አይደለም እንዴ ስንትና ስንቱ ነገር ሲለጠፍብኝ የሰነበተው!)
አቶ ነቅንቅ፡— ዋናው ነገር ምን መሰለህ…ብዙ ነገር ካየሁና ካዘንኩ በኋላ ዳር ቆሜ ተመልካች ከመሆን መሀል ገብቼ  ለህዝቡ መብቶች ለመታገል ቆርጬ ነው ፖለቲካ የገባሁት፡፡ (ቆይማ…‘ታይምአውት!’ ማነህ ካሜራማን፣ የጠየቅሁትን ጥያቄ ሪፕሌይ አድርግልኛማ! የምን ሌባና ፖሊስ ድብብቆሽ ነው!)
አቶ ጋዜጠኛ፡— ለማለት የፈለግሁት እንደው ሙያዎ ምን እንደሆነ፣ እስካሁን ድረስ በየትኞቹ ሙያዎችና ስፍራዎች…
አቶ ነቅንቅ፡— (ሰውየው ግንባሩን ቋጠርብኝ፡፡) እየነገርኩህ ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ሰው ሲበደል ማየት አልወድም ነበር:: ገና ከወጣትነቴ ጊዜ ጀምሮ ለተጨቆኑ ሰዎች ስቆም ነው የኖርኩት፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ መስዋእትነት ስከፍል ኖሬያለሁ፡፡ (ጉድ መፍላት ብቻ ሳይሆን ‘ትክትክ’ ነው የሚለው!)
አቶ ጋዜጠኛ፡— ወይዘሪት ምንአይተሽ፣ (ወይዘሪት ብሎ አንቱታ ባይመቸኝም ምን ይደረጋል… ሽማግሌ ልኮ በጎን ያስከለከልኩት የለ!) እርስዎ እንዴት ትግል ውስጥ እንደገቡ ቢያጫውቱን፡፡ (አደራ ብቻ ሴትዮዋ፣ “አሽሙር መሆኑ ነው ወይስ ስለ የትኛው አይነት ትግል ነው የምትጠይቀኝ!” እንዳትለኝ! ሌላ ‘ወይዘሪት ዋኔ’ ምናምን የምትባል አክቲቪስት ኢንተርቪው አደርጋለሁ እንጂ በወይዘሪት ምንአይተሽ ቃላትና ነገር ጥምዘዛ እንጀራዬ እያየኋት አትደርቅም! ያውም ‘ትራንስፓረንት’ እንጀራ!) 
ወይዘሪት ምንአይተሽ፡— (ፈገግ ትላለች:: “እሰይ” ትንፋሼ ተመለሰ፡፡) የሚገርም አጋጣሚ ነው… (ጎሽ፣ ቼኮቭ ቢሰማው ይቀናበት የነበረ ‘ሾርት ስቶሪ’ ሊጀመር ነው:: ኮሚክ እኮ ነው…ሁሉም ሲጀምሩ ውል ገብተው ማፍረስ የፈሩ ይመስል “የሚገርም አጋጣሚ ነው” ይላሉ፡፡) የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ገና ጩጬ ነገር እያለሁ ነው… (እሪ በል አገር! ኸረ ካልኩለስ ምናምኑ የክሊማንጀሮ አቀበት ቢሆንብን ‘ሠርቲ’ ‘ፎርቲ’ አይነት ገራገር ቁጥሮችን መደመርና መቀነስ አያቅተንም! ጩጬነት አዲስ መስፈርት ወጣለት እንዴ! አንድ ጊዜ የኬንያ የፓርላማ አባላት የወጣትነት የእድሜ ጣራ ሀምሳ አምስት ካልሆነ ሲሉ ነበር አሉ፡፡) መንገድ ላይ አንዲት ትንሽዬ ልጅን… (“እንደ እርስዎ ጩጬ  የነበረች ማለትዎ ነው?” ልበላት እንዴ!) አንድ ጉልበተኛ ነገር እንዲህ አንገቷን ይዞ ሲያንገላታት ሳይ ብው አልል መሰለህ! (የጠዋት ጸሎቴን ባያበላሽብኝ ኖሮ “አሁንም በደገመሽ!” ላለማለቴ ዋስትና የለም፡፡)
ተንደርድሬ ሄጄ እንዲህ ምንጭቅ አደረግሁና አፈጠጥኩበት፡፡ (ይቺን ‘አክሽን’ አንጀሊና ጆሊ ‘ላራ ክሮፍት’ ምናምን ላይ ሠርታው ነበር ልበል!) ያኔ ነው ህይወት ያለ መብት ትግል ትርጉም የላትም ብዬ የወሰንኩት፡፡ (አይን ራንድ ነው ምናምን የሚሏት ሴትዮ በዘመዶቿ ዘይቤያዊ አነጋገር… ይሄኔ ጉድጓዷ ውስጥ እየተገለባበጠች ነው:: አቶ ነቅንቅ ግንባሩ ላይ የደረደራቸውን መስመሮች ብቆጥራቸው ሳይጨምር፣ ሳይቀንስ ልክ አናቱ ላይ አርባ ሦስት ይሆናሉ:: ቀይ መብራት መሆኑ ነው::)
አቶ ጋዜጠኛ፡— አቶ ነቅንቅ ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ብዙ ሰው የሚቸገርበት ነገር አለ፡፡ አክቲቪስት ማለት ምን ማለት ነው? ማለቴ አንድ ሰው አክቲቪስት መሆን ከፈለገ መስፈርቶች አሉት?
አቶ ነቅንቅ፡— በእርግጥ እንደ እውነቱ ከሆነ አክቲቪስትነት ማንም ሰው ስለፈለገ ብቻ ዘሎ ዘው የሚልበት አይደለም፡፡
(“አንዳንድ በገንዘብ የተገዙ የሚዲያ ሰዎች…” ምናምን መባሌ ላይቀርልኝ ነው ማለት ነው! ደግሞ ሰረቅ አድርጎ ወደ ምንአይተሽን የሚያየው…አለ አይደል…እያስተላለፈ ያለው የፖለቲካ ነው ወይስ የ‘ላቭ አት ፈርስት ሳይት’ መልእክት! ከሁለተኛውስ ይሰውረን፡፡ “ባለፈው እሁድ አክቲቪስት ነቅንቅ አሳየው እና አክቲቪስት ምንአይተሽ ዳር ከዳር የጋብቻ ስነ ስርአታቸውን አከብረዋል፡፡” የተባለ ጊዜ ከህዝቡ አንድ አስራ አምስተኛው በባዶ እግር ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅጠኑ አይቀርም:: አንድ በአንድ መከራችንን እያየን ነው እንደገና በጥምረት! ያውም “እነሆ በረከት…” ምናምን አይነት ‘ፕሪቪሌጆች’ ያሉበት ጥምረት! ቂ…ቂ…ቂ…)
አቶ ጋዜጠኛ፡— ይህን ጉዳይ ቢያብራሩልኝ፡፡ ማንም ስለፈለገ ብቻ አክቲቪስት መሆን አይችልም ሲሉ ምን ማለት ነው? (እናማ… ቃለ መጠይቅ አድራጊ… ‘ሳሙና’ ካልሆነ ‘ታርጌት’ ይሆናል:: ማንም ሰው ስለፈለገ ብቻ ዘሎ ዘው የሚልበት አይደለም ሲል እኮ አንድ፣ ሁለት ብቻ ሳይሆን ድፍን ብርጌድ ሊሞላ የሚችል ሊኖር ይችላላ!)
አቶ ነቅንቅ፡— አክቲቪስት ለመሆን ብዙ ማወቅ፣ ብዙ ማንበብ፣ ብዙ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የዓለምን አጠቃላይ ሁኔታ መከታተል ያስፈልጋል፡፡ በእኔ የግል አስተያየት አክቲቪስትነት የፖሊቲከኝነት ከፍተኛው ደረጃ ነው፡፡ (ምን! ኸረ ለእኔም ቲቪ ላይ ከች አድርጌ ሀገር እንዲያያችሁ ላደርገሁት እዘኑልኝ! ሰውየው የኦክሲጅን ድርሻዬን ሰባ አምስት በመቶ እኮ ነው የመነተፈኝ! ወደ አንጀሊና ጆሊዬ ብመለስ ይሻለኛል፡፡)
አቶ ጋዜጠኛ፡— ወይዘሪት ምንአይተሽ፣ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የጾታ እኩልነት አንዴት ያዩታል?
ወይዘሪት ምንአይተሽ፡— አመሰግናለሁ፣ (ለምኑ?) የጠየቅኸኝን ከመመለሴ በፊት ወንድሜ አሁን በተናገረው ላይ ለመጨመር ያህል…አክቲቪስትነት ዝም ብሎ ሰተት ብለህ የምትገባበት የሰንበቴ ድግስ አይደለም፡፡ (አይ ምነው! እዛው ሰፈርሽ ቆዪ! የምን ሰው ሰፈር ሄዶ ትንኮሳ ነው!) ሰዉም ግራ የገባው ያም እየነተሳ፣ ይሄም እየተነሳ አክቲቪስት ነኝ በሚል ቴሌቪዥኑን ስለሚሞላው ነው፡፡ (አሁን የተጨቆነ ካለ እኔ ነኝ፡፡ አለቆቼ  ከፍተኛ የሀሳብ ልውውጥ እንዲኖር እያደረግን ነው እያሉ ጭራሽ “ቴሌቪዥኑን ስለሚሞላው” ብላ በሞራላችን ሰኞ፣ ማክሰኞ ትጫወታለች!)
አቶ ጋዜጠኛ፡— እንግዶቻችን፣ ይቅርታ ሰዓታችን እየተገባደደ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ሌላ ጊዜ በስፋት እንመለስበታለን:: (በለብ፣ በለብ ነገር በስፋት በምናምን ብሎ ነገር! ይኸው…ቃለ መጠይቁ ወንፊት ላይ ተቀመጠ! “ማነህ…ትሪው ምንም ስላልነካው ቦታው መልሰው፡፡፣ ወንፊቱ ግን እንዳይቀደድ መገልበጫ ፈልግማ!”)
እናማ… ዘንድሮ ብዙ ቃለ መጠይቆች ሲጣሩ ወንፊት ሙሉ፣ ትሪ ባዶ እየሆኑ ተቸግረናል ለማለት ያህል ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1793 times