Saturday, 13 June 2020 12:07

ስለየወር አበባ መቋረጥ መታወቅ ያለባቸው ምንድናቸው?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  Medically reviewed by Debra Rose Wilson, PhD, MSN, RN, IBCLC, AHN-BC, CHT on September 15, 2017
ሁሉም ሴቶች ስለየወር አበባ መቋረጥ (Menopause) ማወቅ ይገባቸዋል የተባሉ አንዳንድ ነጥቦችን ባለፈው እትም ለንባብ ማለታችን ይታወሳል፡፡ ለማስታወስ ያህል ሴቶች የወር አበባ መቋረጥ የሚያጋ ጥማቸው በተፈጥሮአዊ መንገድ ሲሆን ከአንዳንዶቹ ወይንም ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው እድሜአቸው ከ45-50 አመት ሲደርስ ነው፡፡ አንዲት ሴት በተከታታይ ለአንድ አመት ያህል የወር አበባ ሳታይ ከቀረች የወር አበባዋ ተቋረጥ (Menopause) ገባች ይባላል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያትም በሰውነት ውስጥ ይመረት የነበረው ኢስትሮጂን እና ፕሮጀስትሮን የሚባለው ንጥረ ነገር በወር አበባ መቋረጥ ወቅት መመረቱ ስለሚቀንስ ነው፡፡
የወር አበባ መቋረጥ፤
ድንገተኛ ሙቀትና የላብ ስሜት አለው፤
የአጥንትን ጤንነት ይጎዳል፤
የሚሉትን እና እነዚህን ችግሮች ለመከላል ምን ማድረግ እንደሚገባ በባለሙያዎች የተጠቀ ሰውን ምክር ለንባብ ብለናል፡፡ ይህን ቁምነገር ለንባብ ያሉት Debra Rose Wilson, PhD ናቸው:: ለሌሎች ጥያቄዎች የተሰጠውን መልስ በዚህ እትም ለንባብ ብለናል፡፡
የወር አበባ መቋረጥ ከልብ ጋር የተያያዘ ሕመም ያስከትላልን?
ከልብ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር አንዳንድ ችግር በወር አበባ መቋረጥ ወቅት ሊከሰት ይችላል:: ለምሳሌም ድካም፤ መደበር፤ የልብ ምት ትክክለኛውን ሂደት አለመጠበቅ ወይንም በድንገት እና በፍጥነት የመምታት ስሜት የመሳሰሉት ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
ከልብ ጋር በተያያዘ ለሚከሰተው ችግር እንደመፍትሔ ከተቀመጠው ውስጥ ክብደትን መቆጣጠር፤ ጤናማ እና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እና ሲጋራ አለማጤስ የመሳሰሉት የልብን ደህንነት ለመጠበቅ እንደመፍትሔ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡  
የወር አበባ መቋረጥ የሰውነት ክብደት መጨመርን ያስከትላልን?  
በሰውነት ውስጥ ያለው የሆርሞን ለውጥ ክብደት ለመጨመር ምክንያት ሊሆን ይችላል:: የወር አበባ መቋረጥ ብቻም ሳይሆን የእድሜ መጨመርም ክብደት እንዲጨምር ምክንያት መሆኑ አይቀርም፡፡
ለክብደት አለመጨመር እንደመፍትሔ ከተቀመጡት ነጥቦች ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እና ጤናን ለመጠበቅ የሚረዱ ሌሎች ልምዶችን መተግበር ክብደትን ለመቆጣጠር ይረዳል:: ክብደት መጨመር ለልብ ሕመም፤ ለስኩዋር ሕመም እና ለመሳሰሉት ችግሮች ሊያጋልጥ ይችላል፡፡  
ክብደትን ለመቆጣጠር፤
ጤናማ አኑዋዋርን መልመድ፤
ካልሲየም ያለባቸውን ምግች በመመገብ እና ስኩዋርነት ያላቸውን ምግቦች በማስወገድ የተሟላ እና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፤
በሳምንት 150/ደቂቃ ያህል መካከለኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ወይንም በሳምንት 75 ደቂቃ ያህል ከበድ ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማለትም እንደሩጫ የመሳሰሉትን ማድረግ ይጠቅ ማል፡፡
በቀን ተቀን ውሎ ዝም ብሎ ከመቀመጥና ከመተኛት ይልቅ አኑዋኑዋርን በእንቅስቃሴ ማጀብ ይጠቅማል፡፡
በወር አበባ መቋረጥ ወቅት እንደ ቤተሰብ ወይንም ጉዋደኛ ተመሳሳይ ስሜት ሊኖር ይችላልን?
የወር አበባ መቋረጥ ስሜቶች በቤተሰብ ውስጥም ቢሆን እንኩዋን ከአንዱዋ ሴት የሌላዋ ሊለያይ ይችላል፡፡ የመቋረጫው እድሜ እና የማህጸን ሆርሞን የማምረት ተግባርን የመቀነስ ሂደትም እንደዚሁ ሊለያይ ይችላል፡፡ ይህ ማለት የማንኛዋም ሴት የወር አበባ መቋረጥ ባህርይ ከማንም ጋር የማይመሳሰል የግል ተደርጎ የሚወሰድ ነው ማለት ነው፡፡ ለእናት፤ እህት ወይንም ለጉዋደኛ የሚሰማው ስሜት በውርስ የሚተላለፍ ወይንም ሴት በመሆን ብቻ በአንድ አይነት የሚጋሩት የህመም ስሜት አይደለም፡፡
ስለወር አበባ መቋረጥ menopause ማንኛውም አይነት ጥያቄ ቢኖር ሐኪምን ማማከር ይጠቅማል፡፡ ከባለሙያዎች የሚገኘው ምክር ተፈጥሮአዊው ሂደት ምን እንደሚመስል እና በምን መንገድ መስተናገድ እንዳለበት ለማወቅ ይረዳል፡፡
በቀዶ ሕክምና ማህጸን ያስወጣች ሴት የወር አበባ መቋረጡን እንዴት ልታውቅ ትችላለች?
በእርግጥ በወር አበባ መብዛት ምክንያት በማህጸን አካባቢ የሚሰጠውን የቀዶ ሕክምናን ጨምሮ በሌላም ምክያት ማህጸን በቀዶ ሕክምና ከወጣ ድንገተኛ በሚከሰተው ሙቀትና ላብ ካልሆነ በስተቀር የወር አበባ መቋረጥ menopause መገባቱን ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ የህክምና ባለሙያዎች በሚያደርጉዋቸው ምርመራዎች የኢስትሮጂንን መጠን ለማወቅና ማህጸን ተፈጥሮአዊ ሂደቱን እንደጠበቀ መስራት መቻል አለመቻሉን ለማወቅ ይረዳል፡፡ ይህ ሕክምና የወር አበባ የመቋረጥ ጊዜውን ከመለየት ባሻገር የአጥንት መሳሳት ሕመም መኖር አለመኖሩን ለማወቅ ጭምር ይረዳል፡፡
ሆርሞንን መተካት በወር አበባ መቋረጥ ምክንያት የሚመጡ ችግሮችን ለመቋቋም ይረዳልን?
የተለያዩ ተቋማት ድንገት የሚከሰተውን ትኩሳትና ላብ ለመከላከል እንዲሁም የአጥንት መሳሳት እንዳይደርስ ለማድረግ ይረዳል በሚል ሆርሞን እንዲወሰድ ይመክራሉ፡፡ ነገር ግን የሚሰጠው ጥቅምና የሚያደርሰው ጉዳት እንደሚደርሰው ሙቀትና ላብ ክብደት፤ የአጥንት መሳሳት እና ጤንነት ይለያያል፡፡ ይህ የሆርሞን መድሀኒት ለሁሉም ሰዎች ትክክል ነው ሊባል አይችልም፡፡ ስለሆነም ይህንን መድሀኒት ከመውሰድ በፊት የህክምና ባለሙያን ማነጋገር ይመከራል፡፡
በወር አበባ መቋረጥ menopause ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስወገድ የሚችሉ ከሆርሞን ውጭ የሆኑ የህክምና እርዳታዎች ይገኛሉ?
ከላይ እንዳነበባችሁት የሆርሞን መድሀኒቶች ትክክለኛ ምርጫ አይደሉም፡፡ ስለሆነም የአኑዋኑዋር ዘዴን በመለወጥ ሆርሞንን ከመጠቀም ውጭ በሆነ መንገድ ጤንነትን ለማስተካከል መሞከር ይቻላል፡፡
ውፍረትን መቀነስ፤
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፤
የሚውሉበትን ወይንም የሚተኙበትን ክፍል ሙቀት መቀነስ፤
ሙቀቱንና ላቡን የሚያባብሱ ምግቦችን ከመመገብ መቆጠብ፤
ቀለል ያሉ እና ከጥጥ የተሰሩ ልብሶችን መልበስ፤
የመሳሰሉትን እርምጃዎች በመውሰድ ጤንነትን ማስተካከል ይቻላል፡፡
ባጠቃላይም የወር አበባ መቋረጥን menopause ተከትሎ የአጥንት መሳሳት፤ የልብ ሕመም የመሳሰሉ ህመሞች መከሰታቸውን ልብ በማለት ችግሩን ለመከላከል ጤናማ ምግቦችን መመገብን፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግን እና አላስፈላጊ ውፍረትን ማስወገድ ጠቃሚ መሆኑን Debra Rose Wilson, ይገልጻሉ፡፡



Read 12723 times