Print this page
Saturday, 20 June 2020 11:48

የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ (WWЕ)

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 • በኮሮና ምክንያት እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር አጥቷል፡፡
    • በዓመት ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ፤እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ንፁህ ትርፍ ያስገኛል፡፡
    • 180 አገራትን ያካልላል ፤ ከ800 ሚሊዮን በላይ ቤቶችን በማዳረስ፤ በ28 ቋንቋዎች ይሰራጫል፡፡
    • ከ220 በላይ ፕሮፌሽናል ነፃ ታጋዮችን ቀጥሯል፡፡ በዓመት ከ500 በላይ የነፃ ትግል ግጥሚያዎችን ያዘጋጃል፡፡
    • ከሰሜን አሜሪካ ው ጭ በ ሳዑዲ አ ረቢያ ፕ ሮፌሽናል ውድድሮች በ እንግሊዝ፣ በሜክሲኮ፣ ጃፓንና ህ ንድም ተ ወዳጅ ነው፡፡ በ ሌሎች የ ዓለም ክ               ፍሎች ከተስፋፋ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ሊያስገኝ ይችላል፡


                 የኮሮና ወረርሽኝ በፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርት ላይ ተፅእኖ እያሳደረ ነው፡፡ በተለይ በአሜሪካው የመዝናኛ ኩባንያ (WWЕ) የሚዘጋጁ ግጥሚያዎች በመስተጓጐላቸው እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ መድረሱ እየተገለፀ ይገኛል፡፡   የስፖርቱ አፍቃሪዎች የነፃ ትግል ግጥሚያዎችን በውድድር ስፍራዎች ተገኝተው እንዳይመለከቱ ተከልክለዋል፡፡ የዓመቱን መርሃ ግብሮች ተለያዩ ከተሞችና በተከታታይ ማድረግ ያልተቻለ ሲሆን ትልልቅ ፍልሚያዎችም ተሰርዘዋል፡፡ የፕሮፌሽናል ነጻ ታጋዮች የስራ ዋስትናንም እያሳጣ ነው፡፡
የዓለማችንን ግዙፍ ፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ኩባንያ የሚያንቀሳቅሰው WWЕ በወረርሽኙ የገጠሙት ፈተናዎች ብዙ ናቸው፡፡ ባለፉት 3 ወራት ፍልሚያዎችን ያለ ተመልካች ሲያካሂድ በርካታ የገቢ ምንጮች ደርቀውበታል፡፡  የነፃ ትግል ግጥሚያዎቹን በልዩ የፊልም ቀረፃዎች አማካኝነት በቲቪ እና በኢንተርኔት  በማሰራጨት ብቻ የስፖርቱን ህልውና ለመጠበቅ ጥረቱ ቀጥሏል፡፡  ፍልሚያዎችን ተመልካቾች በማይገኙበት ሁኔታ ማዘጋጀት  ከየአቅጣጫው ትችት ገጥሞታል፡፡  የስፖርቱን ማራኪ ድባብ ማሳጣቱ የመጀመርያው ስጋት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነፃ ታጋዮች ሌሎች ባለሙያዎችን ለኮሮና ወረርሽኝ ማጋለጡና የስራ ዋስትና ማሳጣቱ ነው፡፡
ከኮሮና በኋላ የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ Wоrld Wrеѕtlіng Еntеrtаіnmеnt (WWЕ) እስከ 140 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ የውድድር ዓመቱን ለመጨረስ መወሰኑን አስታውቆ፤ በኮቪድ 19 ምርመራና ክትትል ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድም ገልጿል፡፡ የስፖርትን ህልውና ለመጠበቅም እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘት እንደሚችልም ተናግሯል፡፡ ተመልካቾች ባይኖሩም እንኳን በእንጥልጥል የቀሩ የፍልሚያ መርሐ ግብሮችን መቀጠል እንዳለባቸው ታምኖበታል፡፡ ይሁንና ነፃ ታጋዮች፤ አሰልጣኞች፤ ማናጀሮችና ሌሎች ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ በውሳኔው አልተስማሙም:: ከ2 ወራት በፊት የኮሮና ወረርሽኝን እንደምክንያት በመጥቀስ ከ36 በላይ ፕሮፌሽናል ነፃ ትግል ስፖርተኞችና ሌሎች ባለሙያዎች ኮንትራታቸው መቋረጡ ሲያወዛግብ ሰንብቷል፡፡ የWWЕ አመራሮች ግን ነፃ ታጋዮችና ሌሎች ባለሙያዎችን አዲስ የኮንትራት ውል ለማስፈረም ወደ ውድድር ለመመለስ ፍላጎት መኖሩን በመግለፅ ቅሬታዎችን አስተባብለዋል፡፡
የWWЕ አስተዳደር ባለፉት 3 ወራት በተለያዩ የመወዳደርያ ስፍራዎች በየቀኑ ይካሄዱ የነበሩ ግጥሚያዎችና ተያያያዥ ትእይንቶቻቸው በሳምንት አንዴም ለመፍጠር አልተቻለም፡፡ ከውድድር መርሃግብሮቹ ከ75 በመቶ በላይ ተሰርዘዋል፡፡ በተለይ WRESTSLMANIA 36 በሚል ስያሜ የሚካሄደውን ግዙፍ ሻምፒዮና ሙሉ በሙሉ አቋርጦታል፡፡ ዋና ዋና ፍልሚያዎቹን ደግሞ በአንድ ከተማ ለማካሄድ ወስኗል:: በላስቬጋስ፤ በዲትሮይት እና ሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች መዘዋወር የማይቻል ሆኗል፡፡ ስለዚህም  የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ (WWЕ)  ውድድሮችን በፍሎሪዳ በሚገኘው የስልጠና ማዕከል ማካሄድ ብቸኛው አማራጭ ሆኖበታል፡፡ የነፃ ትግል ግጥሚያዎችን ያለተመልካች ማካሄድ የስፖርቱን ድባብ በማቀዝቀዝ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡  ከትኬት ሽያጭ የሚገኘውን ከፍተኛ ገቢ ያስቀራል፡፡ በኢንተርኔት ድረገፆች ላይ በቀጥታ የሚተላለፉትን ግጥሚያዎች በማራኪ ቀራፂዎች ማቅረብን አዳጋች ያደርገዋል፡፡ ተመልካቾች ባለመኖራቸው ማናቸውንም ስርጭት በድምቀት ለማጀብ የሚከብድ ነው፡፡ ተመልካቾች ባለመግባታቸው ግን የውድድሩን አስተዳደር ከፍተኛ ገቢ እንዳሳጣው ምሳሌ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ዘንድሮ በWrestlemania 36 የመጀመርያው ውድድር  በባዶ ስታድዬም ተደርጓል፡፡ ይህም ከትኬት ሽያጭ የሚገባውን 16 ሚሊዮን ዶላር አሳጥቷል፡፡ የነፃ ትግል ፍልሚያው ባለፉት ዓመታት የሚካሄደው በ70ሺ ተመልካች በፊት ነበር፡፡
ስለፕሮፌሽናል ነፃ ትግል እንደመግቢያ
የነፃ ትግል ስፖርት በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳና ሜክሲኮ፤ በአውሮፓ፤ በእንግሊዝ እንዲሁም በኤሽያ በህንድና በጃፓን ተወዳጅነት ያለው ነው፡፡ በከፍተኛና ፕሮፌሽናል ደረጃ ውድድሮች መካሄድ የጀመሩት ግን በአሜሪካ ነው:: በ1952 እኤአ ላይ ጆስ ማክማን እና ቱትስ ማንዶት በተባሉ ፈር ቀዳጅ የነፃ ትግል ስፖርተኞች አማካኝነት፤ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናና ሊዘጋጅ በቃ:: አሁን የሚገኝበት ደረጃ ለመድረስ 68 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ደግሞ የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ Wоrld Wrеѕtlіng Еntеrtаіnmеnt (WWЕ) በሚል ኩባንያ ስር ከዓለማችን ታዋቂ የስፖርት ኢንዱስትሪዎች ተርታ ተሰልፏል፡፡ ፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ውድድሮች  ብዙዎቹ በአሜሪካ የሚካሄዱት ሲሆን ዎርልድ ሬስሊንግ ኢንተርቴይመንትን በቅርበት ከሚፎካከሩት  ኦል ኤሊት ሬስሊንግ ፤ ኢቮልቭ፤ ናሽናል ሬስሊንግ አሶሴሽን እንዲሁም ፕሮ ሬስሊንግ ጎሪላ የተባሉ ትልልቅ ሻምፒዮናዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በፕሮፌሽናል ነፃ ትግል ስፖርት ታላላቅ ነፃ ታጋዮች የሚገናኙባቸው ፍልሚያዎች በየመወዳደሪያ ስፍራቸው ከ20-70ሺ ተመልካቾች የሚያስተናግዱ ሆነዋል፡፡ እንደ ዓለም ዋንጫ የመላው ዓለም ትኩረት ይስባሉ፡፡ በግዙፍ የብሮድካስት ኩባንያዎች ውድድሮች በመላው ዓለም የስርጭት ሽፋን የሚያገኙ ሲሆን፤ በኢንተርኔት ሰብስክሪብሽን፤ የቅድመ ክፍያ አገልግሎት፤ የቀጥታ ስርጭት የሚሰጠው አገልግሎትም የስፖርቱን ተወዳጅነት ጨምሮታል፡፡
በፕሮፌሽናል ነፃ ትግል እያንዳንዱ ግጥሚያ አዳዲስ ትእይንቶች የሚታዩበትና ድራማዊ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ነው፡፡  ፕሮፌሽናል ነፃ ታጋዮችም በዓለም ዙርያ ከፍተኛ ታዋቂነት ያላቸውና ክብር የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ከነፃ ታጋዮች ብዙዎቹ በተለያዩ በዩኒቨርስቲ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለፉና በፕሮፌሽናል የስፖርት መስኮች የተወዳደሩና የሰሩ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስልጠና ከፍተኛ ደረጃ ባለው ተቋም ወስደዋል::  የትወና ሙያን ያጠኑ በተለያዩ የትምህርት መስኮች  የኮሌጅ ዲፕሎማ እና ዲግሪ የያዙም ይገኙበታል:: እያንዳንዱ ፕሮፌሽናል ነፃ ታጋይ በሚያስገርም የአካል ብቃት፤ የጅምናስቲክ ቅልጥፍና፤ የትግል ቴክኒክ መታወቅ ይኖርበታል፡፡  ፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርት በመላው ዓለም እንዲገን ካዳረጉ ነፃ ታጋዮች መካከል ሃልክ ሆገን ፤ ቪንስ ማክማን፤  ጎልድበርግ፤ ሪክ ፍሌር፤ ብሮክ ሌንሳር፤ ጆን ሴና፤ ስቲቭ ኦስተን፤ ሮማን ሪጂንስ፤ ትሪፕል ኤች፤ ሴዝ ሮሊንስ፤ ራንዲ ኦርተን፤ ሮክ ወይም ድዋይን ጆንሰን…ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ፕሮፌሽናል ነፃ ታጋዮች በአሜሪካና በዓለም  የስፖርት ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጥረዋል:: በነፃ ትግል ስፖርትም ከፍተኛ ገቢ ያገኙ፤ በርካታ የሻምፒዮና ቀበቶዎችን የታጠቁ እንዲሁም ከስፖርቱ ሌላ በፊልምና ሌሎች መስኮች  ተጨማሪ ስኬቶችን ያገኙ ናቸው፡፡
ትውውቅ ከዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ አዘጋጅ
Wоrld Wrеѕtlіng Еntеrtаіnmеnt (WWЕ)
የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ Wоrld Wrеѕtlіng Еntеrtаіnmеnt (WWЕ) አሜሪካዊ የመዝናኛ ኩባንያ  ነው፡፡ ኩባንያው በዓለማችን ስፖርቱን በከፍተኛ ደረጃ በማስተዳደር ተስተካካይ ያጣ ሲሆን በፊልም፤ በሪል እስቴት እና በተለያዩ የኢንቨስተመንት መስኮችም ይንቀሳቀሳል፡፡ በፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርት የWWЕ ዋና ሃላፊነት ፍልሚያዎችን መቀመር፤ የግጥሚያ መርሃ ግብሮቹን መንደፍ፤ ማዘጋጀት፤ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄዱ ማድረግ ነው፡፡ ስፖርቱን ከመዝናኛው ኢንዱስትሪ ጋር በማቀራረብ በሙዚቃ፤ በቲቪ ፕሮግራሞችና በፊልም ወሳኝ ድባቦችን መፍጠር እና በቀጥታ ስርጭት በማስተላለፍ እንደሚሰራም ይታወቃል፡፡
የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ Wоrld Wrеѕtlіng Еntеrtаіnmеnt (WWЕ) በአሁኑ ወቅት ከ220 በላይ ፕሮፌሽናል ነፃ ታጋዮችን በኮንትራት ቀጥሮ ያሰራል:: በዓመት ውስጥ ከ500 በላይ በመላው ዓለም የቀጥታ ስርጭት የሚያገኙ የነፃ ትግል ግጥሚያዎችን ያካሂዳል:: በብሮድካስት እና በኢንተርኔት የሚዲያ አውታሮች የስርጭት ሽፋኑ በ180 አገራት ፤ በ28 ቋንቋዎች 800 ሚሊዮን ቤቶችን የሚያዳርስም ነው፡፡ ከ18 ዓመታት በፊት ዎርልድ ሬስሊንግ ፌደሬሽን የሚለውን ስያሜ ወደ ዎርልድ ሬስሊግ ኢንተርቴይመንት የቀየረው ኩባንያው፤ በየውድድር ዓመቱ 18 የተለያዩ ሻምፒዮናዎችን በማካሄድ ቀበቶዎቹን የሚያስታጥቅ ነው፡፡   ባለፉት 10 ዓመታት በመላው ዓለም ለመስፋፋት ባደረገው ጥረትም እየተሳካለት መጥቷል፡፡ 2020 እኤአ ከገባ በኋላ የWWЕ ዩቲውብ ገፁን ሰብስክራይብ ያደረጉት ብዛታቸው ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሲሆን የተለቀቁ ቪድዮዎች ከ9.6 ቢሊዮን በላይ ተመልካች አግኘተዋል፡፡  በዲጂታልና የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች የነፃ ትግል ግጥሚያዎቹ ለ344 ሚሊዮን ሰዓታት ተላልፈዋል፡፡  WWЕ ካሉት የገቢ ምንጮች መካከል ከተመሰረተ 6 ዓመታት ካስቆጠረውና በስሩ የሚያስተዳድረው የቲቪ ኔትዎርክ ይገኝበታል፡፡ ይህ ኔትዎርክ በክፍያ የነፃ ትግል ግጥሚያዎችን በድረገፁ ከማሰራጨቱም በላይ፤ ስለነፃ ትግል ታጋዮች የእለት እለት ህይወት ዘጋቢ ፊልሞች፤ የማይረሱና ታላላቅ ግጥሚያዎችን በድጋሚ በማሳየት እና የተለያዩ ልዩ ትርኢቶችን በየጊዜው በማቅረብ ይሰራል፡፡  በየሳምንቱ ሁለት መደበኛ የስርጭት ፕሮግራሞች ሌሎች ንፁስ መርሃ ግብሮችን በዓለም ዙርያ ያስተላልፋል፡፡ ሁለቱ መደበኛ የቲቪ ስርጭቶች በየሳምንቱ ሰኞ ምሽት ለ3 ሰዓት የሚተላለፈው ዘ መንዴይ ናይት ሾው እና በየሳምንቱ አርብ ምሽት በስማክዳውን አማካኝነት ለ2 ሰዓት በመላው ዓለም ስርጭት የሚያገኘው ናቸው፡፡ ሮው ፤ ሮያል ራምብል እና ሌሎች የተለያዩ ንዑስ መርሃ ግብሮችም በየጊዜው የስርጭት ሽፋን ያገኛሉ፡፡
በዎርልድ ሬስሊንግ ኢንተርቴይመንት የሚንቀሰቀሰው ፕሮፌሽናል ነፃ ትግል በእያንዳንዱ የግጥሚያ ቀን በርካታ ትርኢቶችን የሚያስተናግድ ነው፡፡ በመድረኩ ላይ ቲያትር፤ የቲቪ ድራማ፤ ኦፔራ፤ ስፖርት፤ ልዩ የመድረክ ላይ ፍልሚያዎች፤ የማጀቢያ ሙዚቃዎች፤ የደጋፊዎች ዝማሬና መፈክር  ተቀላቅለውበታል፡፡ እነዚህም የሚፈጥሯቸው ትእይንቶች ከዓለም ስፖርቶች ሁሉ የላቀውን የመዝናኛ ባህርይን ተላብሷል፡፡  ባለው በገቢ፤ በተመልካች እና ተከታታይ ብዛት፤ በፈጣን እድገቱ፤ ለስፖርተኞቹ በሚያስገኘው ከፍተኛ ገቢ ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች እና ከአሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪ ተርታ የሚያሰልፈው ደረጃ ሰጥቶታል፡፡
በ2019 እኤአ አጋማሽ ተቋሙ የስርጭት አድማሱን ለማስፋት በማህበራዊ ሚዲያዎች እና የተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ያለውን ተደራሽነት ማሳደጉ የሚጠቀስ ነው፡፡ የኩባንያው መስራች ባለቤትና ሊቀመንበር ቪንስ ማክማን እንደተናገረው በይዘቱ እና በአቀራረቡ በሁሉም እድሜ እና ፆታ ላይ በማተኮር በመስራቱ የመዝናኛውን ዓለም ለመቆጣጠር አስችሎታል፡፡  
የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ ዎርልድ ሬስሊንግ ኢንተርቴይመንት ከዓመት በፊት ከ960.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጠቃላይ ገቢ በማድረግ አዲስ የገቢ ሪከርድ ያስመዘገበ ሲሆን ንፁህ ትርፉ 77 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡  በ2020 እኤአ ላይ ግን ይህ ገቢው በተለያዩ ምክንያቶች መቀነሱ የማይቀር ይሆናል፡፡ ለገቢው መቀነስ ከቀረቡ ምክንያቶች የመጀመርያው ከትኬት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ እና በውድድር ስፍራ አካባቢ የሚካሄዱት የተለያዩ የስፖርት እና ተያያዥ ቁሳቁሶች ንግድ በመዳከሙ ነው፡፡ ከገቢው 77 በመቶውን ከሚዲያ መብቶች የሚሰበሰበው ሲሆን የተቀረውን 23 በመቶ ደግሞ በኢንተርኔት ከሚካሄድ የቀጥታ ስርጭት፤ ከትኬት ሽያጭ እና ከተለያዩ ተያያዥ ንግዶች ያገኛል፡፡
ከአሜሪካ ባሻገር
በሳዑዲ አረቢያና ሌሎች የዓለም ክፍሎች...
ፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርት በአሜሪካ ከፍተኛውን ደረጃ እና ገቢ ቢያስመዘግብም በሜክሲኮና በጃፓንም በስፋት የሚዘወተር ነው፡፡ የWWЕ ዋና መስርያ ቤት በኬኔክቲኬት ቢሆንም ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ በሌሎች 10 ታላላቅ ከተሞች በኒውዮርክ፤ ሎስአንጀለስ፤ ለንደን፤ ሜክሲኮ፤ ሙምባይ፤ ሻንጋይ፤ ሲንጋፑር፤ ዱባይ፤ ሙኒክና ቶኪዮ ከተሞች ላይም አሉት፡፡ ዎርልድ ሬስሊንግ ኢንተርቴይመንት በ2018 እአኤ ላይ በስፖርቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡ የነፃ ትግል ግጥሚያዎችን ከአሜሪካ ባሻገር በተለይ በሳዑዲ አረቢያ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለማካሄድ በሚንቀሳቀስበት እቅድ ነው:: የWWЕ አስተዳደር ከሳውዲ አረቢያ መንግስት ጋር ከ2018 እስከ 2028 እኤአ በአጋርነት ለመስራት ነው የተስማማው፡፡ በዚህ መሰረትም የመጀመርያው ውድድር በ2019 እኤአ በሳኡዲ አረቢያዋ ከተማ ሪያድ ተካሂዷል:: ታዋቂዎቹ ነፃ ታጋዮች ጎልድበርግ እና አንደር ቴከር የተፋለሙበት ነው፡፡ አንዳንድ የስፖርት ተንታኞች እንደሚገልፁት ፕሮፌሽናል ነፃ ትግል የሳኡዲ አረቢያን ግዛት መርገጡ ከዚያም በሌሎች የዓለም ከተሞች ሊካሄድ መቻሉ የስፖርቱን ዓለም አቀፍ የዋጋ ተመን ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊያደርገው ይችላል፡፡  ይህን ለማሳካትም ከWWЕ የሚሰሩት ታላላቅ የቲቪ ጣቢያዎች ፎክስ እና ስማክ ዳውን ሲሆኑ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር በሚደርስ ውል ተስማምተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛን በሳኡዲ አረቢያ በማካሄድ ጀምረዋል፡፡  በቀጣይ ዓመታት በኤሽያ እና በአውሮፓ አገራት በሚገኙ ትልልቅ ስታድዬሞች ውድድሮችን የማካሄድ  እቅድ መኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
ቪንስንት ኬንዲ ማክማን
የፕሮፌሽናል ነፃ ትግል አድራጊ ፈጣሪ
የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ Wоrld Wrеѕtlіng Еntеrtаіnmеnt (WWЕ) መስራች ባለቤትና ስራ አስፈፃሚ በሙሉ ስሙ ቪንስንት ኬንዲ ማክማን ተብሎ ይታወቃል፡፡ በአባቱ የተመሰረተውን የዎርልድ ሬስሊንግ ፌደሬሽን   ገና በ12 ዓመቱ የተቀላቀለው ቪንስ ማክማን፤ በነፃ ትግል ስፖርት ያለው ልምድ ከ49 ዓመታት በላይ ነው፡፡ በ1984 እኤአ ላይ አባቱ በሞት ከተለዩ በኋላ ከትዳር አጋሩ ጋር በመሆን በነፃ ትግል ስፖርት ውድድሮች  በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ የሚሰራውን ኩባንያ በሙሉ ሃላፊነት ለመቆጣጠር ችሏል፡፡  ቪንስ ማክማን በቀድሞው የዎርልድ ሬስሊንግ ፌደሬሽን ሁለት የሻምፒዮንነት ቀበቶዎች ያገኘ ነው::  በዎርልድ ሬስሊንግ ኢንተርቴይመንት ሃላፊነቱ ደግሞ የነፃ ትግል ስፖርትን በከፍተኛ ደረጃ ወደ ፕሮፌሽናሊዝም እንዲገባ፤ ከመዝናኛው ዓለም ጋር ጥምረት በመፍጠር የዓለምን ቀልብ መግዛት እንዲችል ፈር ቀዳጅ ሚናዎችን ተጫውቷል፡፡
የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ Wоrld Wrеѕtlіng Еntеrtаіnmеnt (WWЕ) ዋና ስራ አስፈፃሚ በመሆኑ በዓመት እስከ 2.4 ሚሊዮን ዶላር የሚከፈለው ቪንስ ማክማን በኩባንያው እስከ 42 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ አለው፡፡ አጠቃላይ የሃብት መጠኑም ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሲሆን ይህም በነፃ ትግል ብቻ ሳይሆን በዓለማችን የስፖርት ኢንዱስትሪ ከፍተኛውን ገቢ በማግኘት አንደኛ ደረጃ ያሰጠዋል፡፡ ከአሜሪካ የሪፖብሊካን ፓርቲ ጋር ቅርበት ያለውና ደጋፊ የሆነው ቪንስ ከነፃ ትግል ስፖርተኛነቱ፤ ፕሮሞተር እና አስተዳዳሪነቱ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ሙያዎችም አሉት፡፡ የመድረክ መሪ አስተዋዋቂ፤ የስፖርት ኮሜንታተር፤ የቴሌቭን እና የሲኒማ ዲያሬክተርና ተዋናይ እንዲሁም የፊልም ፅሁፍ ደራሲም ነው፡፡ በአስተዳደር ብቃት ብቻ ሳይሆን እድሜው እየገፋ ቢሆንም ሙሉ አቋሙን እና ጥንካሬውን ጠብቆ መቆየቱን ፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርተኞች ያደንቁለታል፡፡
የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ ፕሮፌሽናል ነፃ ታጋዮች
በፎርብስ መፅሄት ማብራርያ የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ Wоrld Wrеѕtlіng Еntеrtаіnmеnt (WWЕ) ተቀጣሪ በመሆን የሚወዳደሩ ፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርተኞች ተጠቃሚነታቸው በየዓመቱ እያደገ ነው፡፡ ዘንድሮ ፕሮፌሽናል ነፃ ታጋዮቹ ብዛታቸው ከ220 በላይ ናቸው፡፡ ታዋቂዎቹ በደሞዝ ብቻ በአማካይ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሌሎች እስከ 500 ሺ ዶላር እንዲሁም የሚከፈላቸው ናቸው፡፡የዓለማችን ትልልቅ ፕሮፌሽናል ነፃ ታጋዮች በየራሳቸው የትግል ስልት የሚታወቁ፤ የየራሳቸውን ቡድን በማቋቋም ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ፤ በየግጥሚያው በሙዚቃ እና በድራማዊ ትእይንቶቻቸው ተወዳጅ የሆኑ፤ ትርኢቶቻቸውን በትግል መድረኩ ላይ በድምቀት በማቅረብ የተሳካላቸው ናቸው:: የፕሮፌሽናል ነፃ ታጋዮች በየውድድር ዓመቱ ደሞዛቸው እየጨመረ፤ ከስፖንሰሮች ጋር ያላቸው ውል እየተሻሻለ፤ ከግጥሚያዎች በተገናኘ በሚፈጠር ገበያ እና ንግድ ያላቸው ድርሻ እያደገ፤ ከቲቪ ስርጭት ጋር በተያያዘ እውቅናቸው እየጨመረ እንዲሁም ከአሜሪካ አህጉር ባሻገር ውድድሮች በሌሎች ዓለም ክፍሎች የሚካሄዱባቸው እቅዶች መፈጠራቸው የገቢ ምንጮቻቸውን አሳድጎላቸዋል፡፡ዘንድሮ ከፕሮፌሽናል ነፃ ታጋዮች ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ የሚያገኙ ብዛታቸው 13 ሲሆን ከሴቶች አንድ ብቻ ነው ያለችው፡፡
የዓለም የነፃ ትግል መዝናኛ (WWЕ) ለነፃ ታጋዮች እንደየደረጃቸው በመደራደር እና ኮንትራት በመፈራረም መሰረታዊ ክፍያዎችን በመጀመርያ የቅጥር ውል ይፈፅምላቸዋል፡፡ ከፍተኛ ገቢ በሚያስገኙ ልዩ እና ትልልቅ ግጥሚያዎች ከመደበኛ ክፍያቸው ባሻገር ከሚገኘው ገቢ የቦነስ ክፍያዎችን ያስብላቸዋል፡፡ ከትኬት ሽያጭ እና ከውድድር ስፍራ የተለያዩ ንግዶች ገቢ 5 በመቶ ድርሻ የሚወስዱ ከመሆኑም በላይ በ3ኛ ወገን በሚካሄዱ ተያያዥ ንግዶች 25 በመቶ ተካፋይ ይሆናሉ፡፡
ዘ አንደርቴከር
ከ31 በላይ የሻምፒዮንነት ክብሮች የተጎናፀፈ
በሙሉ ስሙ ማርክ ዊልያም ካለዌይ ቢባልም፤ ዘ አንደርቴከር ወይም ዘ ኤጅ በተሰኙት የነፃ ትግል ስሞቹ በመላው ዓለም ይታወቃል፡፡ በፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርት ከ31 በላይ የሻምፒዮነት ክብሮችን ተጎናፅፏል:: ከአስደናቂ ውጤቶቹም መካከል 11 ግዜ የዓለም ሻምፒዮንና 5 ጊዜ የአሜሪካ ሻምፒዮን፤ እንዲሁም በቡድን ፍልሚያ ለ11 ጊዜያት ማሸነፉ ይጠቀስለታል፡፡ ከ9 ዓመታት ከነፃ ትግል ስፖርት በጡረታ ተሰናብቶ የነበረው ዘ አንደር ቴከር ዘንድሮ ከጡረታ በመመለስ ወደ ውድድር ገብቷል:: ከነፃ ትግል ሙያው ባሻገር በፊልም ተዋናይነትም ከፍተኛ ልምድ አለው፡፡
ዴብራ ማክሚካኤል
ከሴት ነፃ ታጋዮች ከፍተኛዋ ተከፋይ
ከሴት ነፃ ትል ስፖርተኞች የምንግዜም ከፍተኛውን ገቢ በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃ የወሰደችው ዴብራ ማክሚካኤል ናት፡፡ ከስፖርቱ በፊት ተዋናይ ነበረች:: በታዋቂ ነፃ ታጋይ ማነጀርነት ዎርልድ ሬስሊንግ ኢንተርቴይመንትን ተቀላቅላለች፡፡ ዴብራ ባለፉት 20 ዓመታት ከፍተኛ ክብር ካገኙ ነፃ ታጋዮች አንዷ ናት፡፡ በ60ኛ ዓመቷ ላይ ከስፖርቱ የምንግዜም ከፍተኛ ገቢዋ 45.4 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡
ዘ ሮክ
የተሳካለት ነፃ ታጋይና ተዋናይ
በፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርት ታሪክ በምንግዜም ከፍተኛ ውጤት ከ1 እስከ 10 ባለው ደረጃ ውስጥ የሚገባው የ47 ዓመቱ ድዋይኔ ጆንሰን ወይም ዘ ሮክ ከፕሮፌሽናል ነፃ ታጋይነቱ ባሻገር ተዋናይና የፊልም ፕሮዲውሰር መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከ320 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሃብት እንዳለው ይገመታል፡፡
ዘ ሮክ 7 ጊዜ WWE ሻምፒዮን፤ 2 ጊዜ    WCW ሻምፒዮን፤ 2 ጊዜ WWE Intercontinental ሻምፒዮን፤ 5 ጊዜ  WWE Tag Team ሻምፒዮን፤ 1 ግዜ Royal Rumble አሸናፊ፤ እንዲሁ 5 ግዜ የWrestleMania ድሎችን አግኝቷል፡፡ በፊልሙ መስክ ከ41 በላይ ፊልሞችን በመሪ ተዋናይነት፤ በረዳት ተዋናይነት፤ በፕሮዲውሰርነት እና በተለያዩ የሃላፊነት ድርሻዎች የሰራው ዘ ሮክ፤ በአሜሪካ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመላው ዓለም ደግሞ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱን በድረገፁ የሚያመለክተው ቦክስኦፊስ ሞጆ ነው፡፡
ጆን ሴና
የምንግዜም ምርጡ ነፃ ታጋይ
ጆን ሴና በዓለም የነፃ ትግል ስፖርት አፍቃሪዎች በተለይ በህፃናት እና በሴቶች ከፍተኛ ተወዳጅነት አለው:: የዓለም አቀፉ ኩባንያ የፊት ምስል ተደርጎም ይገለፃል:: ከምንግዜም ስኬታማ ነፃ ታጋዮች አንዱ ሊሆን ሲበቃ 2180 ፍልሚያዎች አድርጎ 1731 ድሎችን በማስመዝገቡ ነው፡፡ በሪንግ ውስጥ ካስመዘገበው ስኬት ባሻገር በተለያዩ ምርቶች ሽያጭ ከፍተኛ ገቢም ያስገኛል፡፡  16 ጊዜያት በነፃ ትግል የዓለም ሻምፒዮን መሆኑ ከፍተኛ የውጤት ክብረወሰን ሲሆን በአጠቃላይ 25 የሻምፒዮናነት ክብሮችን ተጎናፅፏል፡፡
ትሪፕል ኤች
የታላላቅ ፍልሚያዎች ዲያሬክተር
በሙሉ ስሙ ፖል ሚኬል ሌቨስኩዌ  ተብሎ ይታወቃል፡፡ ፕሮፌሽናል ነፃ ታጋይ፤ የማኔጅመንት ባለሙያ እና ተዋናይም ጭምር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዎርልድ ሬስሊንግ ኢንተርቴይመንት በቀጥታ ስርጭቶች ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ የያገለግላል፡፡ በታላላቅ ፍልሚያዎች ዲያሬክተር ሆኖ በመስራት ትሪፕል ኤች 1.1 ሚሊዮን ዶላር በዓመት ይከፈለዋል፡፡ በፕሮፌሽናል የነፃ ትግል ስፖርት ውስጥ ከ26 ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን 24 የሻምፒዮናነት ክብሮችን ተጎናፅፏል፡፡9 ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ሻምፒዮና መሆኑ ከፍተኛ ውጤት ነው፡፡
ሃልክ ሆገን
የፕሮፌሽናል ነፃ ትግል መሰረት
በዓለማችን የፕሮፌሽናል ነፃ ትግል ስፖርት ከፍተኛ ዝና እና ክብር ካገኙት መካከል ይጠቀሳል፡፡ አሁን 66ኛ ዓመቱን የያዘው ሃልክ ሆገን በሙሉ ስሙ ቴሬ ጌኔ ቦሌላ ተብሎ ይጠራል፡፡
በፕሮፌሽናል ነፃ ትግል ስፖርት ከ43 ዓመታት በላይ በመወዳደር አንጋፋው ሲሆን 1003 ፍልሚያዎችን ያሸነፈ ነው፡፡ ሃልክ ከነፃ ታጋይነቱ ባሻገር፤ ተዋናይ፤ የቲቪ ስብዕና፤ ስራ ፈጣሪ እና ሙዚቀኛ ነው፡፡
በ2020 እኤአ ከፍተኛ ተከፋይ ነፃ ታጋዮች
ብሮክ ሌስነር 12 ሚሊዮን ዶላር
ጆን ሴና 8.5
ሮማን ሬጂስ 5 ሚሊዮን
ራንዲ ኦርቶን 4.5
ሴት ሮሊንስ 4
ከእነሱ ባሻገር የሊቀመንበሩ እህት የሆነችውና በነፃ ታጋይነት የምትወዳደረው ሌሲሊ ሊንች በ3.1 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ክፍያ 6ኛ ደረጃ ስትይዝ እዚህ ደረጃ ላይ በመደረስ የመጀመርያዋ ነፃ ታጋይ ሆናለች፡፡
5 ነፃ ታጋዮች ብዙ የተፋለሙና ድል ያደረጉ
ጆን ሴና  2180 ፍልሚያዎች 1731 ድሎች
ዘ አንደር ቴከር 2186 ፍልሚያዎች 1697 ድሎች
ኬን 2813 ፍልሚያዎች 1497 ድሎች
ብሬት ሃርት 2141 ፍልሚያዎች 1459  ድሎች
ሽዋን ማይክልስ 2250 ፍልሚያዎች 1224  ድሎች
የፕሮፌሽናል ነፃ ትግል 5 ሃብታሞች
ቪንስ ማክማን 2.2 ቢሊዮን ዶላር
ድዋይኔ ጆንሰን 320 ሚሊዮን ዶላር
ጆን ሴና 55 ሚሊዮን ዶላር
ስቲቭ አስቲን 50 ሚሊዮን ዶላር
ስቴፋኒ ማክማን 45 ሚሊዮን ዶላር

Read 6042 times