Saturday, 20 June 2020 11:56

“ሞቷል፤ ቢሆንም ዐይንጋለልም” - (ታዋቂ ዜማ)

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   --ሐሳቡ የታየኝ ሰው ሠራሽ ጥርሴን በገዛሁ ቀን ነበር፡፡ የማለዳውን ሁኔታ በጥራት አስታውሳለሁ፡፡ ለሁለት ሩብ ጉዳይ ሲሆን ነበር ከአልጋዬ በመውረድ ልጆቼ ሳይቀድሙኝ መታጠቢያ ቤት የገባሁት፡፡
የወርኅ ጥር የማለዳ አየር ቀዝቃዛ ሲሆን ሰማዩም በተበጣጠሱ ቢጫ ደመና የቆሸሸ መስሏል፡፡ በጠባቡ የመታጠቢያ ቤት መስኮት ቁልቁል ዐሥር በአምስት ሜትር ስፋት ያለውን የሳር መስክና አጭር አጥር አያለሁ፡፡ የሁሉም ቤት የጀርባ አፀድ ተመሳሳይ የኤልዝሚር ጐዳና ቤቶች አፀድ አንድ ልዩነት ብቻ ይታይባቸዋል፡፡ እርሱም ሕፃናት የሌሉበት ግቢ፣ ሳሩ ያልተመለጠና አረንጓዴ ምንጣፍ መመስሉ ነው፡፡
ውኃው ገንዳውን እስኪሞላው ድረስ ፂሜን በደነዘው ምላጭ ለመላጨት እየታገልኩ ነው፡፡ የእኔው ፊት ከመስታወቱ ጀርባ አፍጥጦ ያየኛል፡፡ ከፊቱ ጋር የሚመሳሰለው ሰው ሠራሽ ጥርሴ ደግሞ ከታች የውኃ ብርጭቆ ውስጥ ተቀምጧል:: ሃሰተኛውን ጥርስ የሰጠኝ የጥርስ ሃኪማ ዋርነር ሲሆን አዲስ ጥርስ እስኪሠራልኝ ድረስ የሰጠኝ ጊዜያዊ ጥርሴ ነው፡፡
ፊቴ አስቀያሚ አይደለም፡፡ እውነቱን ነው የፊቴ ቀለም ከቀይ የሸክላ ጡብ ጋር የሚቀራረብ ሲሆን ከቅቤ መሰል ቢጫ ፀጉሬና ፈዛዛ ሰማያዊ አይኖቼ ጋር ህብር የሚፈጥር ሆኗል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ፀጉሬ አልተመለጠም፤ አልሸበተምም፤ ሰው ሠራሽ ጥርሴ ሲደርስልኝ ምናልባት ከአርባ አምስት ዓመት ዕድሜዬ በታች ወጣት እመስል ይሆናል፡፡
አዲስ የፂም መላጫ ለመግዛት እያሰብኩ ገላ መታጠቢያ ገንዳው ውስጥ ገብቼ፣ ሰውነቴን ሳሙና መምታት ጀመርኩኝ፡፡ የአጭሩ ክንዴ ቆዳ እስከ ክርኔ ድረስ ጥቁር ነጠብጣብ አለበት፡፡ እርሱን ሳሙና ከቀባሁ በኋላ ወትሮም በእጄ የማልደርስበትን ትንሽዬን በገላ መታሻው ሳሙና መምታት ቀጠልኩኝ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጄ የማልደርስባቸው የሰውነት ክፍሎቼ በዝተዋል፡፡
እውነቱን ለመናገር ሰውነቴ ከወፍራሞች ጐራ ሊቀላቅለኝ ተቃርቧል፡፡ ድቡልቡል የምባል ባልሆንም በቅርቡ ስመዘን ክብደቴ ከ90 ኪሎ አልበለጠም፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ እንደለካሁት የወገቤ ቁጥር 48 ወይም 49 እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ትክክለኛው የወገብ ቁጥሬ የትኛው እንደሆነ ግን አላስታውስም፡፡ ውፍረቴ ለእይታ የሚቀፍ ዓይነት አይደለም:: ሆኖም ግን ሰውነቴ ሰፋ ያለ ጉርድ በርሜል መሰል ነው፡፡ እንደ አስቀያሚ ወፍራሞች ቦርጬ ከጉልበቴ አልፎ አልተዘረገፈም:: በአጠቃላይ ለሚመለከተኝ ወፍራም፣ ሰውነቱን በቅልጥፍና የሚያንቀሳቅስ ደልዳላ ነኝ፡፡ “ዱብዬ” ወይም “ፈርጣማ” የሚል ተቀጽላ ያላቸውና የፓርቲው ዓይን የሆኑ ቀልጣፋ ሰዎች ታውቃላችሁ  እመስላለሁ! ሰዎች “ዱብዬው ቦውሊንግ” በማለት አቆላምጠው ይጠሩኛል፡፡ እውነተኛ ስሜ ደግሞ ጆርጅ ቦውሊንግ ነው፡፡
በርግጥ በዚህ ወቅት የፓርቲው ዓይን የምባል ዓይነት አይደለሁም፡፡ በቂ እንቅልፍና ጤናማ አመጋገብ ኖሮኝ እንኳን ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ጀምሮ ግልፍተኛ እሆናለሁ፡፡ ምክንያቱን አውቄዋለሁ፤ ሃሰተኛ ጥርሴ ነው፡፡ አሁን እንኳን በብርጭቆው ውኃ መጠኑ ጐልቶ ስመለከተው ያገጠጠ የራስ ቅል ይመስላል፡፡ ጥርሱን ስታጠልቁት መራራ ፖም የገመጣችሁ ዓይነት ጎምዛዛ ስሜት ይሰማችኋል፡፡
እናንተ የፈለጋችሁትን በሉት እንጂ ሃሰተኛ ጥርስ የሕይወትን ምዕራፍ የሚያሳይ ጉልህ ምልክት ነው፡፡ የመጨረሻው እውነተኛ ጥርሳችሁ ከተነቀለ በኋላ ራሳችሁን እንደ ሆሊውድ ሽቅርቅር ወጣት በመገመት ራሳችሁን ማሞኘት ስትጀምሩ፣ በእርግጥም ለፍፃሜ ተቃርባችኋል ማለት ነው፡፡ እነሆ የአርባ አምስት ዓመት ወፍራም ጐልማሳ ነኝ፡፡ ማንኛውም ወፍራም ሰው እንደሚገጥመው ሁሉ እኔም አጐንብሼ ማየት የቻልኩት፣ የእግሮቼን ግማሽ የፊት አካልና ጣቶቼን ብቻ ነው፡፡ መታጠቢያው ጓዳ ውስጥ ቆሜ ሰውነቴን ለማየት ብሞክርም የሚታየኝ ግማሹ ብቻ ሆኗል:: ቦርጬን ሳሙና እየቀባሁ ስለ ሰውነቴ ሳስብ፣ አንድ ሴት ገንዘብ ካልተከፈላት በቀር የእኔን ሰውነት በፍላጐቷ ሁለት ጊዜ ማየት እንደማትወድ ተሰማኝ፡፡ እኔም ብሆን አንዲት ሴት ሰውነቴን ደግማ እንድትመለከተው አልፈልግም፡፡
ዛሬ በማለዳው መንፈሴን ያነቃቁት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ዛሬ ሥራ አለመሥራቴ ነው፡፡ አሮጌዋ መኪናዬ ለጊዜው ጥገና ላይ ብትሆንም የሥራ ቀጠናዬን በእርሷ ነበር የማካልለው (በነገራችን ላይ የኢንሹራንስ ሠራተኛ መሆኔን ብነግራችሁ ጥሩ ነው፡፡ የበረራ የሕይወት፣ የእሳት ቃጠሎ፣ የዘረፋ፣ የመንትያ ልጆች ውርስ፣ የመርከብ ጉዞ…የሁሉንም ነገር መድህን ዋስትና እሠራለሁ)፡፡ የለንደኑ ቢሮዬ ጐራ ብዬ ወረቀት አስቀምጣለሁ፡፡ መኪናዬ ብትኖር እንኳን ዛሬ አዲሱ ጥርሴን ስለምቀበል ሥራ አልሠራም፡፡
ሌላው ነገር ደግሞ ከእኔ በቀር ማንም የማያውቀው ዐሥራ ሰባት ፓውንድ አለኝ:: ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ ሜሎር የተባለ የሥራ ባልደረባዬ አንድ የኮከብ ቆጠራ መጽሐፍ እጁ ገብቷል፡፡ መጽሐፉን ለፈረስ ግልቢያ ውድድር መጠቀም እንደሚያስችልና ለማሸነፍ የሚያበቃው ሁኔታ ደግሞ ፕላኔቶች ጋላቢው በሚለብሰው ልብስ ቀለም ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ ነው፡፡ በዚያው ሰሞን የኮርሳር ዝርያ የሆነችውን ባዝራ የሚጋልባት ተወዳዳሪ አረንጓዴ የሚለብስ መሆኑንና ቀለሙም በዚያው ወቅት ለሚደረደሩት ፕላኔቶች ተመራጭ መሆኑን ነገረኝ፡፡ ሜሎር ባዝራዋን ወክሎ ብዙ ፓውንድ የተወራረደ ሲሆን እኔም እንዳስይዝ እግሬ ስር ወድቆ ተማፀነኝ:: ቁማር አልወድም ሆኖም ግን ከሜሎር ለመገላገል ብዬ ዐሥር ሽልንግ አስያዝኩኝ፡፡ በእርግጥ ባዝራዋ አሸነፈች፡፡ የውርርዱን አሠራር ባላውቀውም ግን በዐሥር ሽልንጌ ያገኘሁት ዐሥራ ሰባት ፓውንድ ሆነ፡፡ ይህ ሌላው የሕይወቴ ጉልህ ምዕራፍ መሆኑ ነው፡፡ ገንዘቡን በተመለከተ ለማንም ሳልናገር ባንክ አስቀመጥኩት፡፡
ከዚያ በፊት እንደዚያ ያለ ድብቅነት አልነበረብኝም፡፡ እንደ ጥሩ ባልና አባት በገንዘቡ ለሚስቴ ሂልዳ ቀሚስ፤ ለልጆቼ ደግሞ ቦቲ ጫማ መግዛት ነበረብኝ፡፡ ሆኖም ግን ላለፉት ዐሥራ አምስት ዓመታት መልካም አባትና ጥሩ ባል ሆኜ በመኖሬ፣ አሁን አሁን መሰልቸት ጀምሬያለሁ፡፡
ገላዬን ሳሙና ከቀባሁ በኋላ መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ተደላድዬ በመቀመጥ ዐሥራ ሰባት ፓውንዱን ምን እንደማደርግበት ማሰላሰል ጀመርኩኝ፡፡ በመጀመሪያ የታዩኝ ሁለት ነገሮች ሲሆኑ እነርሱም በገንዘቡ የሳምንቱን መጨረሻ ከአንዲት ሴት ጋር ዘና ማለት፤ አሊያም ደግሞ በሲጋራና ደብል ውስኪ መዝናናት፡፡
ሙቅ ውኃውን ከፍቼ ስለ ሴትና ሲጋራ ማሰላሰል ስጀምር፣ ከውስጥ የጐሽ መንጋ የሚመስል የሩጫ ድምጽ ወደ መታጠቢያ ቤቱ በር ሲቃረብ ሰማሁ፡፡ የልጆቼ ኮቴ ነው፡፡ እንደ እኔ ዓይነት ጠባብ ቤት ውስጥ ሁለት ልጆችን ማኖር ማለት በአንዲት የቢራ ብርጭቆ ውስጥ ሙሉ ጆግ ቢራ ለመያዝ እንደ መሞከር ነው፡፡ የመታጠቢያ ቤቱን በር እየደበደቡ ተጣሩ፡፡
“አባ - መግባት እፈልጋለሁ”
“አትችልም፡፡ ጥፋ ከዚህ”
“ሌላ ቦታ ልሸና ነው አባዬ”
“የትም ሽና አሁን ግን ገላዬን ልታጠብበት ሂድ”
“አባ…የሆነ ቦታ ልሄድ ነው”
ክርክሬ ዋጋ ቢስ መሆኑን አውቃለሁ:: የሽንት መቀመጫው መታጠቢያ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ለነገሩ እንደ እኛ ባለች ጠባብ ቤት ሁለተኛ መፀዳጃ ሊኖር አይችልም:: ከገንዳው ወጥቼ ሰውነቴን አደራረቅኩና በሩን ከፈትኩለት፡፡ የሰባት ዓመቱ ትንሹ ልጄ ቢሊ ተወርውሮ ገባ፡፡ ልብሴን ለባብሼ ከረባት ስፈልግ ነበር ሳሙናውን ከአንገቴ ላይ በአግባቡ አለማስለቀቄን ያወቅኩት:: ሰውነታችሁ ላይ ሳሙና ካለ አስቀያሚ ስሜት ይፈጥርባችኋል፤ ቀኑን ሙሉ ይረብሻችኋል፡፡ እኔም እየተነጫነጭኩኝ ወደ ምድር ቤት ወረድኩኝ፡፡
መመገቢያ ክፍላችን በኤቢዝሚር ጐዳና እንዳሉት ቤቶች ሁሉ ጠባብ ነው፡፡ ዐሥራ አራት በዐሥራ ሁለት ጫማ የማይሞላ ስፋት አላት፡፡ የጃፓን የእንጨት ጠረጴዛችን ግማሹን ወለል ይዞታል፡፡ የሂልዳ እናት ለሰርጋችን ያበረከቱልን ሁለት ባዶ የወይን በርሜሎች ከነብረት እግሮቻቸው ቀሪውን ቦታ ስለያዙት እልፍኛችን ብዙም አያፈናፍንም፡፡ አሮጊቷ ሚስቴ ሂልዳ ከሻይ ጀበናው ጀርባ ፊቷን ቋጥራ ቆማለች፡፡ የዛሬው ስጋቷ ምናልባትም ከ “ኒው ክሮኒክል” ጋዜጣ ላይ የቅቤ ዋጋ መናሩን አንብባ ይሆናል፡፡ በጭንቀት ተሞልታ በመቆሟ የምድጃውን ጋዝ እንኳን አላበራችውም፡፡ ቁና ቁና እየተነፈስኩ አጐንብሼ ለኮስኩላት (ማጐንበስ አልወድም)፡፡ “ምን አለፋህ?” የሚል አንድምታ ባለው ሁኔታ የጐንዮሽ አየችኝና ወደ ቁዘማዋ ተመለሰች፡፡
ሂልዳ ገና 39 ዓመቷ ነው፡፡ ያኔ ሳገባት ነጭ ጥንቸል ትመስል ነበር፡፡ መበሳጨቷ ለዚህ አብቅቷታል፡፡ አንዳንዴ በጣም ስትናደድ ቀጭን እጇን በጡቷ ዙሪያ ጠምጥማ ስትታይ እሳት ዳር የቆመች የጂፕሲ ጠንቋይ ትመስላለች - ታስፈራለች፡፡ ሂልዳ በጥቃቅን ነገሮች የመከሰት ዕድል ከወዲሁ በስጋት የምትሞላ ዓይነት ሴት ናት፡፡ የሚያስጨንቋት ነገሮች ደግሞ ተራና መናኛ ናቸው፡፡
መፃኢ ጦርነት፤ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ወረርሽኝ፤ ርሃብና የመሳሰሉት አደጋዎች ምንም እያሰጓትም፡፡ የቅቤና የጋዝ ዋጋ መጨመር፤ የልጆቻችንም ቦቲ ጫማ ማለቅ ግን ከምንም በላይ ያስጨንቃታል፡፡ በዚህ ማለዳ እንደገመትኩት ወዲያ ወዲህ እየተመላለሰችና ቀጫጭን ክንዶቿን ደረቷ ላይ አጣምራ እንዲህ አለችኝ፡-
“ጆርጅ - ነገሩ እኮ አስጊ ነው፡፡ አንተ ፈጽሞ ሊታይህ አልቻለም፤ እሺ ገንዘቡን ከየት ልናመጣ ነው? ምን እንሆናለን? ምን ይውጠናል? ለመሆኑ የት እንወድቅ ይሆን…?”
(1984 እና ሌሎች፤ጆርጅ ኦርዌል፤ ትርጉም፡-ሙሉቀን ታሪኩ፤ መጋቢት 2012)


Read 2090 times