Wednesday, 24 June 2020 00:00

“ከዕውቀት የመጣ ኀዘን”

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

    የሰው ልጅ እያወቀ በሄደ ቁጥር ሊደሰት እንጂ ሊያዝን አይገባውም ተብሎ ይታመናል፡፡ ነገር ግን ማወቅ ባላዋቂዎች ዘንድ አስቸጋሪና ችግር ፈጣሪ ሆኖ መታየቱን ብዙ የታሪክ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የቀድሞው ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የእውቀትን አስፈላጊነት ሲያስገነዝቡ ብትማሩ፤ ብታውቁ የሚንቋችሁ ያከብሯችኋል፤ የሚጠሏችሁ ይወድዷችኋል፤ ማለታቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ማወቅ የጥፋት ምልክት እንደሚሆን ደግሞ
ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ፤
እያወቁ ማለቅ መጣ በሰዓቱ፡፡
ተብሎ ተገጥሟል፡፡ ‹‹ከዕውቀት የመጣ ኀዘን›› የሚለውን ኮሜዲ የደረሰው ቴህራን ውስጥ ዲፕሎማት ሆኖ ይሠራ የነበረው ሩሲያዊ አሌክሳንደር ሰርጌይቪች ግሪባየዶቭ ነው፡፡ አሌክሳንድር ሰርጌይቪች ግሪባየዶቭ  ከ‹‹ዕውቀት የመጣ ኀዘን›› በሩሲያኛ አጠራሩ (ጎሬ አት ኡማ) በሚል  እ.ኤ.አ በ1824 የደረሰው ይህ ኮሜዲ የሚያትተው ስለ ታኀሳሳውያን ተጋድሎ ነው፡፡ ታኅሳሳውያን ከሩሲያ ገዥ መደቦች ይልቅ የተማሩ፤ የለውጥ አስተሳሰብ የሚያራምዱ፤ የዓለምን ሁኔታ አሻግሮ ለማየት ብሩህ አእምሮ የታደሉ ወጣቶች ነበሩ፡፡
  አሌክሳንደር ሰርጌይቪች ግሪባየዶቭ
 እ.ኤ.አ በ1812 መጨረሻ የሩሲያ ጦር ናፖሊዮንን አሸንፎ እየገፋ ወደ ፈረንሳይ ሄዶ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ ወደ ሀገሩ ሩሲያ ተመልሷል፡፡ ወደ ሀገሩ ከተመለሰው ተዋጊ ውስጥ አብዛኛው የመኮንኖች ክፍል እ.ኤ.አ በ1819 ራሱንም ማኅበረሰቡንም ለመለወጥ ተዘጋጀ፡፡ እናም እ.ኤ.አ ከ1818-1821 በሞስኮ ውስጥ መንግሥትን የሚቃወም አብዮታዊ ድርጅት ተመሠረተ፡፡
የእነ ዡኮቭስኪ የሮማንቲስዝም የሥነ ጽሑፍ ፈለግ በታወቀበት ጊዜ ላይ አብዮታውያን የነበሩት ታኅሳሳውያን ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1821 በተመሳሳይ መልኩ በፔተርቡርግ የንጉሡን አገዛዝ ደምስሶና የገባሩን ሥርዓት አጥፍቶ የሪፐብሊክ /ሕዝባዊ/ መንግሥት መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን የሚያምን ድርጅት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በኅቡዕ ተመሠረተ፡፡ ይህ ድርጅት ከኅቡዕነትም እየወጣ በግልጽ በሚቻለው ሁሉ ሥራውን መሥራትና ቅስቀሳውን ማጧጧፍ ጀመረ፡፡
እንደዚሁም እ.ኤ.አ በ1818 በፔተርቡርግ ‹‹አረንጓዴ መብራት” የተሠኘ የሥነ ጽሑፍ ክበብ በሕጋዊ መንገድ ተቋቁሞ ሥራውን ይሠራ ጀመር፡፡ በየጊዜው ለውይይት ከሚሰባሰቡት ውስጥ ታዋቂው ፑሽኪንና ፊዎዶሮቪች ክሪሎቭ ይገኙበታል፡፡ ወጣቶቹ በተገናኙ ቁጥር ስለ ወደፊትዋ ሩሲያ እድል ፈንታ ይወያዩና ይከራከሩ ጀመር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከዘውዳዊው ሕገ መንግሥቱና ከገባር ሥርዓቱ ጋር መደምሰስ እንዳለበት አመኑበት፡፡ ወጣቶቹ ‹‹ሰሜናዊ ኮከብ›› የተባለ ሌላ የሥነ ጽሑፍ ክበብም አቋቋሙ፡፡
 የሩሲያ ወጣቶች ድሀውና ዝቅተኛ ኑሮ ሲመራ የነበረው አብዛኛው የሩሲያ ማኅበረሰብ፣ በጭቆና ቀንበር ሥር ገብቶ ሲማቅቅ በእጅጉ በማዘናቸው ከዝምታ ይልቅ ተጋድሎን፤ ከሕይወት ይልቅ ሞትን መርጠው ተነሣሥተዋል፡፡ የክሪሎቭ መነሻ ሐሳብም ይኸው ነው፡፡ እያዝናና እና እያሣቀ በሩሲያ ገዥ መደቦች ላይ በሚሳለቀው ኮሜዲ (ከዕውቀት የመጣ ኀዘን)፤ ዋናው ገጸ ባሕርይ (ተዋናይ) ቻትስኪ ሲሆን  የሩሲያን ማኀበራዊ ሕይወት ታግሎ ለመለወጥ የተነሣ ወጣት ነው።
የሚኖረው ሞስኮ ውስጥ ሲሆን ወደ ሚስተር ፋኑሶቭ ቤት በየጊዜው ሲመላለስ የፋኑሶቭን ልጅ ሶፊያን አይቶ ያፈቅራታል:: ነገር ግን ሶፊያ ሚልቻኒን የተባለ ወጣት ፍቅረኛ ነበራት፡፡ እርስዋ ከትልቅ ቤተሰብ የተወለደች ስትሆን ቻትስኪ ግን የድሃ ልጅ ነው፡፡
በመሆኑም በቻትስኪ፣ በአባትዋ በፉኑሶቭና በእርሷ መካከል ውስጣዊ የህሊና ጦርነት ይካሄዳል፡፡ እናም ሶፊያ ሜልቻኒን የተባለ ፍቅረኛ ያላት መሆኑን ቻትስኪ ከተረዳ ለእኔ ጥሩ አይደለም ብላ ስለሰጋች፣ በአባትዋ ቤት አንድ ቀን ማታ እንግዶች በተገኙበት ሰዓት፣ ቻትስኪ በእርስዋ ፍቅር አብዶና ጨርቁን ጥሎ በመሄድ ላይ መሆኑን ታስረዳለች፡፡ የቻትስኪ ቀንደኛ ጠላት ሆናም ትቆማለች፡፡ በዚህ ድርጊቷ የተነሣም ቻትስኪ ምንም ሳይናገር አዝኖ ከሞስኮ ከተማ ወጥቶ የትም ይሄዳል፡፡ ከሞስኮ ወጥቶ የትም የሄደበት ዋና ምክንያት ሶፍያን፣ የሩሲያ መሳፍንትና ከበርቴዎችን፤ ሕገወጥ ድርጊታቸውንና ሥርዓቱን በመጥላትና በመቃወም ነው፡፡
ግሪባየዶቭ በትያትር መልክ አዘጋጅቶ ለሕዝብ እይታ ያቀረበው ‹‹ከዕውቀት የመጣ ኀዘን››፤ ድርሰቱ እንዳይታተም የሩሲያ ሳንሱር አግዶት ቆይቷል፡፡ ደራሲው ግሪባየዶቭ ቴህራን ውስጥ በዲፕሎማሲ ሥራ ላይ እንዳለ ከሞተ በኋላ ግን ለኀትመት በቅቷል፡፡ ‹‹ከዕውቀት የመጣ ኀዘን›› በሪያሊዝም ላይ የተመሠረተ፣ አጻጻፉ ተራና ግልጽ በሆነ የንግግር ቋንቋ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሕዝባዊ ተረቶችንና የአነጋገር ፈሊጦችን የያዘ በመሆኑ በሕዝብ ዘንድ እንዲወደድ አድርጎታል፡፡
 ይህ መጽሐፍ በሩሲያ የድራማ ታሪክ የመጀመሪያው የሪያሊዝም ሥራ ውጤት ተደርጎ ይታያል፡፡ በመሆኑም ‹‹ከእውቀት የመጣ ኀዘን›› የሩሲያን የማኀበረሰብ ችግር አጉልቶ በማሳየትና ለትግልም በማነሳሳት ረገድ የመጀመሪያው ኮሜዲ ነው ማለት ይቻላል፡፡
አሌክሳንደር ግሪባዶቭ የተወለደው እ.ኤ.አ ጃኑዋሪ 4 ቀን 1795 ሞስኮ ውስጥ ሲሆን ያረፈው በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን፣ ጃኑዋሪ 30 ቀን  1829 ነው፡፡ የሞስኮ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የነበረው ግሪባየዶቭ፤ ኑሮውም ያማረና የሰመረ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1812 ናፖሊዮን ሩሲያን በወረረበት ወቅት በወታደርነት አገልግሏል፡፡
የውትድርና ሕይወቱን በመተውም እ.ኤ.አ በ1816 ፔተርቡርግ በመኖር ላይ ሳለ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ገብቶ በቴህራን የሩሲያ ኤምባሲ ዋና ጸሐፊ ሆኖ ተሾሟል:: የአሌክሳንደር ፑሽኪን የቅርብ ጓደኛ፣ የታኅሳሳውያን ቀንደኛ ደጋፊና የግርማዊ ቀዳማዊ ዛር ኒኮላዎስ ተቃዋሚ የነበረው ግሪባዶቭ እ.ኤ.አ በ1825 እሥራት ተፈርዶበት ታስሯል፡፡
በርካታ የቴአትር ሥራዎችን የጻፈው ግሪባየዶቭ፤ ከእሥራት ተፈትቶና በቴህራን የሩሲያ ኤምባሲ ዋና ጸሐፊ ሆኖ በመሥራት ላይ እያለ በኤምባሲው ላይ በተፈጸመ የውንብድናና የአፈና ጥቃት ህይወቱ ሊያልፍ  ችሏል፡፡


Read 1228 times