Saturday, 27 June 2020 13:02

በኮሮና ሳቢያ የ2020 የዓለም አትሌቲክስ ክፉኛ ተቃውሷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

• ለምርጥ አትሌቶች ድጎማ መሰጠት ተጀምሯል
     • ዓለም አቀፍ ውድድሮች የተለመደ ድባባቸውን ይቀይራሉ
     • 13ኛው የቶኪዮ ማራቶን ብቻ ሲካሄድ ፤ 124ኛው የቦስተን፤ 50ኛው የኒውዮርክ፤ 44ኛው የበርሊን ማራቶኖች ተሰርዘዋል


            ከኮሮና ጋር በተያያዘ በ2020 የውድድር ዘመን በዓለም አትሌቲክስ በተለይ ለረጅም ርቀት አትሌቲክስ ፤ ለምስራቅ አፍሪካ  አትሌቶች ምቹ ሁኔታዎች አልነበሩም፡፡ በርካታ አትሌቶች በሁሉም የውድድር መደብ ችግር ላይ ናቸው:: በማራቶኖች እና በጎዳና ላይ ሩጫዎች የባሰ ቢሆንም:: አትሌቶች እንዲሁም በዙርያቸው ያሉ ባለሙያዎች ውድድር ከሌለ ምንም አይነት ገቢ የላቸውም፡፡ ስለሆነም ከዓለም አትሌቲክስ የቀረበውን የድጋፍ ጥሪ አስመልክቶ የኢትዮጵያ አትሌቶች በማናጀሮቻቸው በኩል አመልክተዋል፡፡ በዳይመንድ ሊግ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች ተሳትፎ ላይ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም:: በተለይ የ5ሺ ሜትር ውድድሮች ከዳይመንድ ሊግ መሰረዙም ችግሮችን አባብሷል፡፡ በሌላ በኩል የዓለም አትሌቲክስ  በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ ውድድሮች ልዩ መመርያና ደንብ ይፋ አድርጓል፡፡ ይሄው መመርያ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቻ ሳይሆን ለማናቸውም የአገር ውስጥ ውድድሮች መተግበር ያለበት ይመስላል፡፡ በኮሮና ሳቢያ የኢትዮጵያ አትሌቶች በየተኛውም የዓለም ክፍል ለመወዳደር እንደዚህ ቀደሙ ምቹ ሁኔታዎች የሉም:: በማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮችም የተፈጠሩ ሁኔታዎች የውድድር ዓመቱን በጉዳት የተሞላ አድርጎታል:: የማራቶን ሊግ ዘንድሮ የሌለ ሲሆን፤ ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ የሚያስገኙ የማራቶን ውድድሮችም ተሰርዘዋል፡፡ በአጠቃላይ አትሌቲክስ ስፖርቱ በአገር ውስጥ ምንም አይነት የገቢ ምንጮች የሌሉት በመሆኑ፤ የሚያገኘውም ትኩረት በማነሱ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የፈጠሩት የበላይነት ውድድሮችን ማጥፋቱ እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የውድድር ዘመኑ ተተኪ አትሌቶች የሚገኙበት ሳይሆን ተተኪ የሚጠፉበት አድርጎታል፡፡
ለምርጥ አትሌቶች ድጎማ መሰጠት ተጀምሯል
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በኮሮና ሳቢያ ችግር ውስጥ ለገቡ የዓለማችን ምርጥ አትሌቶች የገንዘብ ድጋፍ መስጠት ጀምሯል፡፡ Athlete Welfare Fund በሚል የተሰየመውን ድጎማ በ58 የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ስር የተመዘገቡ 193 አትሌቶች የሚቀበሉ ሲሆን እያንዳንዱ አትሌት 3ሺ ዶላር በነፍስ ወከፍ እንደሚደርሰው ታውቋል፡፡ የገንዘብ ድጋፉን ለማግኘት ከዓለም ዙርያ ከ261 በላይ አትሌቶች አመልክተው ነበር፡፡  
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር World Athletics  እንዳስታወቀው የዓለም አትሌቲክስ ይህን ለዩ ድጎማ ለመስጠት ከዓለም አትሌቲክስ ፋውንዴሽን International Athletics Foundation (IAF) በትብብር መሰራቱን ሲሆን በሁለት ወራት ውስጥ ስፖርቱን ለመታደግ 600ሺ ዶላር መሰብሰቡንም ጨምሮ ገልጿል:: ሞሮኳዊው የመካከለኛ ርቀት ምርጥ አትሌት ሂካም አልገሩዥ መነሻ ሃሳቡን አፍልቆ ከሴባስቲያን ኮው ጋር ከመከረ በኋላ በተቋቋመው ኮሚቴ ታዋቂ ኦሎምፒያኖች፤ የዓለም አትሌቲክስ ስራ አስፈፃሚ አባላት፤ ከዓለም አቀፉ የዶፒንግ ኤጀንሲ ፤ ከአትሌቶች ምክርቤት ተወካዮች በዘመቻው ተሳትፈዋል፡፡
በገንዘብ ድጎማው ተጠቃሚ የሚሆኑ አትሌቶችን ለመምረጥ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መስፈርቶች ቀርበው ማመልክቻዎች ተገምግመዋል፡፡ በ2020 እኤአ ከ2019 በጫም ያነሰ ገቢ ያስመዘገቡ፤ ለቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚያሳልፍ ሚኒማ አሟልተውበችግር ዝግጅት የተስተጓጎለባቸው፤ በዓለም አትሌቲክስ በ2010 የደረጃ ሰንጠረዥ እስከ 6ኛ ደረጃ የያዙ፤ በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ በተሰጣቸው የጎዳና ላይ ሩጫዎች እስከ 6ኛ ደረጃ ያገኙ፤ በ2019 እኤአ የዳይመንድ ሊግ ውድድር እስከ 6ሺ ዶላር ተሸልመው ዘንድሮ ይህን ማሳካት ያዳገታቸውን አትሌቶች ማወዳደርያ መስፈርቶች ሆነዋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮው፤ የድጋፍ ሰጭ ቡድኑ አባል በመሆን ለመስራት ከጅምሩ ፈቃዳቸውን በማሳየት እና የበኩላቸውን በመደጎም አትሌቶች መረባረባቸውን አድንቀዋል፡፡ የገንዘብ ድጋፉ ክፉኛ ለተጎዱ አትሌቶች እንዲደርስ፤ ሁሉንም የሚያስፋፋ መስፈርት እና ዝርዝር ማብራርያ በመቅረፅ የሰሩትን አመስግነዋል፡፡ ሂካም አልገሩዠ ከመጀመርያው  ፅንሰ ሀሳቡን በማፍለቁ እና  ለግል ልግስናው ልባዊ ምስጋና አቀርባለሁም ብለዋል ሴባስቲያን ኮው
ዓለም አቀፍ ውድድሮች የተለመደ ድባባቸውን ይቀይራሉ
የዓለም አትሌቲክስ በጤና እና ሳይንስ ዲፓርትመንቱ አማካኝነት ለዓለም አቀፍ ውድድር  የሚሆን መመርያውንም ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ውድድሮችን ለማካሄድ መተግበር አለባቸው በሚል አሳስቧል፡፡ የጤንነት እና የደህንነት መመሪያዎቹ አጠቃላይ ይዘት ቦሮና ሳቢያ የዓለም አትሌቲክስ የተለመዱ ድባቦች በጣም ይቀየራሉ፡፡  የዓለም አትሌቲክስ  ማህበር ልዩ መመርያውን ያወጀው በሚቀጥሉት ወራት በመላው ዓለም የአትሌቲክስ ውድድሮች ይጀመራሉ የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ መመርያው ሁሉን ባለድረሻ አካላት ይመለከታል፡፡ ፕሮፌሽናል አትሌቶች፤ ድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች፤ የቴኪኒክ ባለሙያዎች፤ የስታድዬም ግብረሃይል፤ በጎ ፈቀዳኞች የህክምና እና የሚዲያ አባላትን ተሳትፎ በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት የወጣው ልዩ መመርያ በዋናነት 4 የአደጋ ግዜ ምርመራዎችን እንዲተገበሩ ይጠይቃል፡፡ ከመመርያው በአጭሩ የተቀነጫጨበው ከዚህ በታች የቀረበ ነው፡፡ በየውድድራቸው ሙሉ ፈቃድ አግኝተው ለሚሳተፉ ሁሉ ነው፡፡
ከውድድር በፊት
የውድድር አዘጋጆች የውድድር ተሳታፊዎችን በአውሮፕላን ማረፊያዎች ወይም በባቡር ጣቢያዎች ተደራጅተው መጠበቅ አለባቸው የጤና እና ደህንነት ፕሮቶኮሎች አብራዋቸው ይሰራሉ። የእንኳን ደህና መጡ መድረክ አዘጋጅተው እያንዳንዱን የውድድር ተሳታፊ በነፍስ ወከፍ  ጭምብል (በቀን ሦስት ጊዜ)፣ የእጅ ማጽጃ ጠርሙሶች ፣ ፀረ-ተባይ መድኃኒቶች ርጭት እና  የሚያብራራ በራሪ ወረቀት ማቅረብ አለባቸው ፡፡
የውድድር ተሳታፊዎች ከአውሮፕላን ማረፊያ ወይም ከባቡር ሐዲድ ወደ ውድድር ሆቴሎች በሚጓዙበት ጊዜ ጭምብል መልበስና አግባብ ባለው ርቀት ላይ መቀመጥ አለባቸው ፡፡ ሰዎችንየውድድር ተሳታፊዎችን ከህዝብ አለመቀላቀል ተገቢ ሲሆን ለዚህም ባለአንድ አቅጣጫ ፍሰቶች መተግበር አለባቸው ፡፡
በኤሌክትሮኒክ ሲስተም ላይ የተመዘገበ የህክምና አጋዥ ምዝገባን ማደራጀትና መጠቀም በጥብቅ ይመከራል፡፡  
በስታድዬም ውስጥ
ተመልካቾች እና እውቅና የተሰጣቸው ሰራተኞች ሁለት ሙሉ ለሙሉ የተለያዩ መግቢያዎች ያስፈልጋቸዋል:: በምንም አይነት ርስበራስ መሸጋገር የለባቸውም። እውቅና የተሰጠው የውድድር ተሳታፊ የፊት ጭምብል ለማድረግና  የእጅ ንጽህና አጠባበቅ ለመሳተፍ ወደ ውድድር ውድድር ስፍራ መድረስ አለባቸው፡፡ በስታድዬም ውስጥ የፊት ጭምብሎች ሁሉም የውድድር ተሳታፊዎች መልበስ አለባቸው ፡፡
የማሞቂያ ቀጠናዎች በውድድር ስታዲየም በአጭር የእግር ጉዞ ርቀት ውስጥ ትልቅ ክፍት የአየር ቦታዎች መሆን አለባቸው፣ መግቢያ ምውጫ በጥብቅ ቁጥጥር መሆን አለበት። የተወሰኑ የጊዜ ሰሌዳዎችን ተከትሎ አትሌቶች ወደ እንዲገቡ መጋበዝ አለባቸው ፡፡ ሁሉም እውቅና የተሰጣቸው ሰራተኞች  ከመግባታቸው በፊት ጭንብል ማድረግ እና እጃቸውን መታጠብ አለባቸው ፡፡
ጭምብሎች በጥሪ ክፍሎች ውስጥ መታጠቅ አለባቸው ፣ እነሱ ከቤት ውጭ መቀመጥ አለባቸው ፡፡ እንዲሁም በእያንዳንዱ አጠቃቀም መካከል ወንበሮችን መበታተን ግዴታ ነው ፡፡
በውድድር ላይ
በውድድር ሜዳ ላይ ያሉ ሰዎች ቁጥር በትንሹ መቀመጥ አለበት፣ እና ከአትሌቶች ጋር የሚቀራረቡ ባለሙያዎች ጭምብላቸውን በተጨማሪ የመከላከያ መነጽር ወይም የፕላስቲክ የፊት መከላከያ ሊለብሱ ይገባል፡፡
አትሌቶች የማጠናቀቂያ መስመርን ከተሻገሩ በኋላ ከህብረተሰቡ እና ከባለሙያዎች ርቀታቸውን ለመያዝ መሞከር አለባቸው
ከውድድር በኋላ
ሚዲያዎች አትሌቶችን ከውድድር በኋላ ለማነጋገር የሚጠቀሙባቸው ኮሪደሮች ውጭ መሆን አለባቸው:: እንዲሁም የሚዲያዎች ቁጥር ውስን መሆን አለበት፡፡ በአትሌቶችና እና የመገናኛ ብዙኃን መካከል የመስታወት ገጽ መቀመጥ አለበት እና ከእያንዳንዱ ቃለ መጠይቅ በኋላ መጽዳት አለበት ፣ እንዲሁም በርካታ የሥራ ቦታዎች ካሉ ልዩ የቃለ-መጠይቅ ሳጥኖች ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው:: ጋዜጠኞች ለአትሌቶች ቃለ መጠይቅ በሚያደርጉበት ጊዜ የሦስት ሜትር የሞተ ቀጠና መተግበር አለበት፣ እና ጭምብሎች በሁለቱም አካላት ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው::  የቀጥታ ሽልማት ሥነ ሥርዓቶች አይመከሩም፣ ግን አማራጭ ዲጂታል መፍትሄዎች ይበረታታሉ።
ኮሮና ያቃወሰው የ2020  የማራቶን ሊግ
13ኛው የቶኪዮ ማራቶን ብቻ ሲካሄድ
124ኛው የቦስተን፤ 50ኛው የኒውዮርክ፤ 44ኛው የበርሊን
ማራቶኖች ተሰርዘዋል
በ2020 እኤአ ላይ በኮሮና ሳቢያ  በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ መቃወስ ከደረሰባቸው ውድድሮች ዋንኛዎቹ በርካታ ተሳታፊዎች ያላቸው የማራቶን እና ሌሎች የጎዳና ላይ ሩጫዎች ናቸው፡፡ በተለይ የዓለማችንን 6 ትልልቅ ማራቶኖችን የሚያካትተው ዓመታዊው  ዎርልድ ማራቶን ሜጀርስ Abbott World Majors ወይንም (የማራቶን ሊግ) ዘንድሮ መቋረጡ ግድ ሆኗል፡፡
ከማራቶን ሊጉ የማራቶን ውድድሮች  ለመካሄድ የቻለው የቶኪዮ ማራቶን ብቻ ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ለ124ኛ ጊዜ ሊካሄድ የነበረው የቦስተን ማራቶን ተሰረዘ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ 44ኛው የበርሊንና 50ኛው የኒውዮርክ ማራቶኖች እንደተሰረዙ ተገልጿል፡፡ ከማራቶን ሊጉ የቀሩት የለንደንና የቺካጎ ማራቶኖች ናቸው፡፡ የእነሱም መካሄድም ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ነው፡፡
ዘንድሮ ለ50ኛ ጊዜ እንደሚካሄድ የተጠበቀው የኒውዮርክ ማራቶንን ለመሰረዝ አዘጋጆቹ የተገደዱት ከከተማዋ ከንቲባ ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ ነው:: በአሜሪካ ወረርሽኙን ለመግታት አለመቻሉ ማራቶኑ የተሰረዘበት ምክንያት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል 62ሺ ተሳታፊ እንደሚኖረው የተጠበቀውን የበርሊን ማራቶን አዘጋጆቹ ለመሰረዝ ግድ ይሆነባቸው ከ5000 በላይ የሚሰበስብ ዝግጅት በጀርመን ለማካሄድ ስለማይቻል እንደሆነ ታውቋል፡፡ የውድድር ተሳታፊዎች ጤንነትና ደህንነትን ለመጠበቅ አስተማማኝ ሁኔታዎች አለመፈጠራቸው፤በርካታ ተሳታፊዎች ያሏቸው ማናቸውም ዝግጅቶች ክልክል መሆናቸው፤ የዓለም አቀፍ ጉዞዎች ጉዳይ እልባት አለማግኘቱ እንዲሁም የአየር ሁኔታዎች ምቹ አለመሆን በመላው ዓለም የሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮችን እንዳይካሄዱ ያደርጋቸዋል፡፡ ከማራቶን ሊጉ ወሳኝ ውድድሮች መካከል በያዙት እቅድ ላይ የሚገኙት የለንደንና የቺካጎ ማራቶኖች ናቸው::  የኮሮና ችግር በዚሁ መርሃ ግብራቸው ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እና እንዴትም ሊያስኬዱ እንደሚችሉ ግልፅ ማብራርያ አልሰጡም፡፡
በማራቶን ሊጉ  የቶኪዮ ማራቶን ሊካሄድ የበቃውም በኮሮና ወረርሽኝ ዋዜማ የነበረ ውድድር በመሆኑ ነው፡፡ የውድድር አዘጋጆች ማራቶኑን በዋና የአትሌቶች መርሃ ግብር ብቻ ሲያካሄዱት ሲሆን ተሳታፊዎቹ 200 ብቻ ነበሩ፡፡ በዓለም ዙርያ በትልልቅ የማራቶን ውድድሮች የ2020 ሻምፒዮኖቹን ለማግኘት የቶኪዮ ውድድር ምስሌ እንዲሆን እየተጠየቀ ነበር፡፡ በአሜሪካ የኮሮና ወረርሽኝ እየተባባሰ ከመሄዱ አንፃር በቀጣይ ከማራቶን ሊጉ ሊሰረዝ የሚችለው ማራቶን በቺካጎ ከተማ የሚካሄደው ነው፡፡ የቺካጎ ማራቶን 40000 ተሳታፊዎች የሚሮጡበት ሲሆን በየጎዳናዎቹ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ የሚያገኝና ለቺካጎ ከተማ ኢኮኖሚ ከ282 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያየሚያስገኝ ነበር፡፡
 የዓለማችንን ምርጥ ማራቶኒስቶች ኤሊውድ ኪፕቾጌ እና ቀነኒሳ በቀለን ያገናኛል የሚባለው የለንደን ማራቶን በተራዘመው ግዜ ለማካሄድ ፍላጎት መኖሩን ዘገባዎች እየገለጹ ናቸው፡፡ ይሁንና ሰሞኑን በኒውካስትል የሚደረገውና ከ60ሺ በላይ ተሳታፊ የነበረው የዓለማችን ግዙፍ ግማሽ ማራቶን ውድድር ግሬት ኖርዝ ራን ከተሰረዘ በኋላ ፤ ለ40ኛ ጊዜ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ለንደን ማራቶንም አጠያያቂ አድርጎታል፡፡ የለንደን ማራቶን መስራች የሆኑት ብሬንዳን ፎስተር እንደተናገሩት የማራቶን ውድድሮችን ለሟካሄድ ምንም አይነት መላ እስካሁን አልተገኘም፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ውድድሮችን ማካሄጃ ፎርሙላ ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ በ2020 ከተካሄዱ የማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች  ኤሊውድ ኪፕቾጌ ከ2 ሰዓት በታች የገባበት ልዩ ውድድር ተጠቃሽ ሲሆን፤ በሴቶች የዓለም ግማሽ ማራቶን ሪከርዶች መመዝገቡና፤ እንዲሁም በወንዶች ሌሎች የማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች መመዝገባቸው ይታወቃል፡፡
የማራቶን ሊጉ ዘንድሮ ለ13ኛ ይካሄድ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁቱም ፆታዎች ተፎካካሪዎች ነበሩ፡፡ በማራቶን ሊጉ በሴቶች ምድብ ብሪጊድ ኮሴጊ እና ጆይሲሊን ጄፕኮሴጌ ከኬንያ እንዲሁም ሎናህ ቼማቲ በ25 ነጥብ እስከ 3 ያለውን ደረጃ ሲይዙ ኢትዮጵያዊቷ አባቤል የሻነህ በ16 ነጥብ 4ኛ ናት፡፡ አባቤል የሻነህ በ2020 መግቢያ የዓለም ግማሽ ማራቶን ክብረወሰን እንዳስመዘገበች ይታወቃል፡፡ በወንዶች ምድብ ደግሞ ብርሃኑ ለገሰ፤ ጂዮፌሪ ኩምዎርር፤ ሎውረንስ ቼሮኖ እና ሌሊሳ ዴሲሳ በእኵል 25 ነጥብ ላይ ናቸው፡፡ ብርሃኑ ለገሰ በቶኪዮ ማራቶን 2፡04፡15 በሆነ ግዜ የ2020 ፈጣን ሰዓትን ያስመዘገበ ነው፡፡
በማራቶን ሊግ የኢትጵያ አሸናፊዎች
የማራቶን ሊጉ ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ሊካሄድ የነበረ ሲሆን በወንዶች ምድብ 12 ጊዜ የኬንያ አትሌቶች ሲያሸንፉ በሴቶችም 8 ጊዜ የኬንያ አትሌቶች አሸንፈዋል፡፡ ሁለት ኢትዮጵያውያን አሸናፊዎች በማራቶን ሊጉ ነበሩ፡፡ እነሱም በ2006/ 07 ጌጤ ዋሚ እንዲሁም በ2012/13 ፀጋዬ ከበደ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ የሽልማት ገንዘብ የዓለማችን 5 ማራቶኖች
ለንደን ማራቶን 11163000 ዶላር
ቦስተን ማራቶን1050000 ዶላር
በርሊን ማራቶን 1000000 ዶላር
ኒውዮርክ ማራቶን 825000 ዶላር
ቺካጎ ማራቶን 80300 ዶላር
ለአሸናፊዎች በሁለቱም ፆታዎች በሚሰጡት ሽልማት  የዓለማችን 10 ማራቶኖች
ቦስተን 155ሺ ዶላር
ዱባይ 152 ሺ ዶላር
ኒውዮርክ 140 ሺ ዶላር
ቺካጎ 100 ሺ ዶላር
ለንደን 77500 ሺ ዶላር
ሲኦል 77000 ሺ ዶላር
ቶኪዮ 72317 ሺ ዶላር
በርሊን 72176 ሺ ዶላር
ሆንግ ኮንግ 61 ሺ ዶላር
ኢስታንቡል 58 ሺ ዶላር

Read 866 times