Saturday, 27 June 2020 13:02

እጅህን እባህሩ ውስጥ ክተት፡፡ ካገኘህ አሣ ትይዛለህ፤ ካልሆነ እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ!;

Written by 
Rate this item
(3 votes)

     ከዕለታት አንድ ቀን በመንግሥት ላይ አሲሯል፣ ወንጀለኛ ነው የተባለ አንድ ሰው የቀበሌው ፍርድ ሸንጐ ዘንድ ይቀርባል፡፡
ዳኛ - ስምህ ማን ነው
ወንጀለኛ - አናጋው አናውጤ
ዳኛ - ዕውነተኛ ስምህ ነው?
ወንጀለኛ - አዎ ጌታዬ
ዳኛ - የአንተ አናጋው ነው በእርግጥ?
ወንጀለኛ - አዎ ጌታዬ
ዳኛ - የአባትህም አናውጤ?
ወንጀለኛ - አዎ ጌታዬ
ዳኛ - እንዴት ነው ነገሩ? የአመጽ ስም መሰለ’ኮ ስምህ? አመጽ ይዘህ ነው እንዴ የምትዞረው?
ወንጀለኛ - ኧረ ጌታዬ፤ እንኳን አመፀኛ ልሆን ከሰውም ተጣልቼ አላውቅም
ዳኛ - መልካም አረፍ በልና የሚቀጥለው ማረፊያ ክፍል ውጤትህን ተጠባበቅ
ወንጀለኛ - ለክቡር ፍርድ ቤቱ የማቀርበው ጥያቄ ነበረኝ?
ዳኛ - መልካም ተፈቅዶልሃል
ወንጀለኛ - ክቡር ፍርድ ቤት፤ ገደልክ የተባልኩት ሰው እኮ፤ የመጨረሻ ጥጋበኛ የመጨረሻ ሞገደኛ ሰው ነው፤ ስለዚህ ዞሮ ዞሮ ማንም ሰው ሊገድለው የሚችል አጉራ - ዘለል ነው፤ እንዲያው ለምን ከሌላ ሰው ቀድመህ ገደልከው ካልሆነ በስተቀር የእኔ ወንጀለኛ መባል አይገባኝም
ዳኛ - አሁን መግደልህን ታምናለህ አታምንም?
ወንጀለኛ - መግደሉንማ ገድዬዋለሁ! ግን ተገቢ ግድያ ነው የፈፀምኩት እኮ ነው የምለው፤ ጌታዬ?!
ዳኛ - ገብቶናል፡፡ በቃ የፍርድ ውሳኔህን ትሰማለህ ታገሥ…
ዳኛው  የሚያጉረመርመውን ህዝብ ፀጥ ካሰኙ በኋላ፤
ዳኛው - ፍርድ ቤቱ፤ የአቶ አናጋው አናውጤን ጉዳይ ግራ ቀኙን ካጠና በኋላ በሞት ፍርድ እንዲቀጣና ፍርዱም በዛሬው ዕለት እንዲካሄድ ወስኗል፡፡
ፍርደኛው ቅጣቱ ወደሚፈፀምበት ቦታ በሁለት አጃቢ ወታደሮች ተይዞ እንዲሄድ  መመሪያ ይሰጣል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ለሚፈጽሙት ወታደሮች፣ ፍርደኛውን  ከከተማው ህዝብ ራቅ አድርገው፣ ተኩሱ ወደማይሰማበት ቦታ እንዲወስዱትና እንዲገድሉት አዘዘ፡፡
ስለዚህም ወታደሮቹ ወደ ሩቅ ጫካ ይዘውት ይሄዳሉ፡፡
መንገዱ አላልቅ አለ፡፡ ፍርደኛው በጣም ደከመው፤ ቢቸግረው፤
“ወንድሞቼ፤ መገደሌ ካልቀረ ይሄን ያህል መንገድ ይዛችሁኝ ለምን ታንገላቱኛላችሁ?”
ከወታደሮቹ አንዱ እንዲህ አለው፤
“የእኔ ወንድም አንተስ አንደኛህን ሞተህ እዚሁ ትገላገላለህ፤ እኛ አለን አይደል ገና እምንመለሰው”
*   *   *
መንገዶች ሁሉ እንደ ሂያጁ ይለያሉ፡፡ ህይወት ግን ለሁሉም ህይወት ናት፡፡ ለአንዱ ወንጀል የሚመስለው ለሌላው ወንጀል ሳይሆን ይባስ ብሎም የመልካም ድርጊት ማመልከቻ መስሎ ሊታየው ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን  የማንም ይሁን የማን ነብስ ክቡርነት አይታበልም፤ እንዳለ ነው:: መጥፎ ድርጊት መልሶ የሚያስጠይቅ የመሆኑን ያህል፣ በተዛምዶ ሲጤን የሰውን እኩይና ሰናይ ጉዳይ እንድንመረምርና ፈለጉን እንድንፈትሽ ግድ ይለናል፡፡ በሀገራችንም፣ በጐረቤት አገራትም ሆነ በዓለም እንደሚታወቀው፣ ድርጊቶች በፖለቲካ ሥልጣን፣ በኢኮኖሚ ኃይልና በባህል አንፃር ሲጤኑ መጠንጠኛቸው የህግ ዳኝነት ነው! ህግን የሚያከብር ህብረተሰብ እንዲፈጠር ለማገዝ የመንግሥት፣ የምሁራን፣ የህግ ተቋማት በተዋረድም እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው እንደ ዜጋ እስካለበት ኃላፊነት ድረስ የሀገር ጉዳይ እንደየ ደረጃና ቦታው ይመለከተዋል፡፡ ስለሆነም የመብትና ግዴታን ነገረ - ሥራ ይሁነኝ ብሎ መገንዘብ ተገቢ ነገር ነው፡፡
የህግን - መጣስ ለማስቆም የዜጐችን ለሕግ ተገዥነት አበክሮ ማሳወቅና ማስከበር ይገባል፡፡ ያ ደግሞ ከቤት አስተዳደግ ጀምሮ፣ በትምህርት ተቋማት ተደግፎ፣ በህብረተሰቡ ንቃተ - ህሊና የታቀፈ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሄ የሚመለከታቸው አካላትም በንፁህ የሀገር ስሜት፣ ከሙስና በፀዳ መንገድ ከዕድገት ጋር ተሳስሮ መዳበር ያለበት ጉዳይ እንዲሆን መጣር አለባቸው፡፡ ለዚህም ሁነኛ ጥናት ያሻዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ እንደ ዋና ማዕቀፍ ሆኖ የሚያገለግለን የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የወንድማማችነት፣ እሴት ማወቅ፤ የባለሙያነትና ለትክክለኛው ሥራ ትክክለኛውን ሰው የማስቀመጥ አሠራር ቢጋር (Frame work) ይሆነን ዘንድ የዲሞክራሲያዊነትን ባህል ማዳበር ነው፡፡ የዲሞክራሲያዊነት ባህል የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መበልፀግ ውጤት ነው፡፡ ከቶውንም ከግብረገብነት ጀምሮ እስከ ፖለቲካዊነት የምንጓዝባቸው ዋናም ሆኑ መጋቢ መንገዶች ሥረ መሠረታቸው ዲሞክራሲያዊ አመለካከት ነው፡፡ ደግነት፣ መረዳዳት፣ የእኔ መከራ የአንተም መከራ ነው ብሎ በቀውጢውም በፌሽታውም ሰዓት መተሳሰብ፤ በመካያው የመልካም ኑሮን ምሰሶና ማገር  መሥሪያ፣ የጋራ ቤታችን መሥሪያችን በአግባቡ መተከል ዋና ነገር ነው፡፡
ዛሬ እንደ ዱሮው የዘመነ - ብሉይያውያን ማርክሳዊ እሳቤ፣ ባህል የፖለቲካውና የኢኮኖሚው ሂደት ነፀብራቅ ነው የምንልበት ዘመን አይደለም፡፡ ባህልም ራሱን የቻለ አቅም የገነባበት ጊዜ ነውና ይልቁንም “የፖለቲካን፣ የኢኮኖሚንና የባህልን አንድም ሶስትም ናቸው” እሳቤ ጆሮ ሰጥቶ ማዳመጥ ደግ ነው፡፡ የአንድም ሶስትም ናቸው እሳቤ በጥቅሉ ሲታይ፣ የህይወትን ትርጓሜ ማፀህያ (Verification) ነው፡፡ ማለትም ፖለቲካው አመራሩ ተስተካክሎ፣ ኢኮኖሚው ንብረት አደላድሎ፣ ከእሱ የአኗኗር ልማድ አበልጽጐ የምናይባትን አገር እንጤን፡፡
ለዚህም፤
ያሰፈሰፈውን መዓት (The Impending Catastrophe)፣ የኮሮናን ዘመን መፍትሔ ያስገኝልን ዘንድ ዘመኑን እንማጠነው፡፡ የማይፈታ ዕንቆቅልሽ እንደሌለ ሁሉ መድሃኒት የማይገኝለት በሽታም የለም! ረብ - ያለው ተስፋ (Optimism) የልባዊ አዎንታዊነት ውጤት ነው! በዚህ ላይ ጽኑ መንፈሳዊነት ሲታከልበት ዓለም ምሉዕነት ያገኛል፡፡
በሁሉም ረገድ አዎንታዊነታችንን እናጽና፤ ምንጊዜም ህይወት ሰፊ ባህር ናት፡፡ ይሄንን ልብ ካልን፤
“እጅህን እባህሩ ውስጥ ክተት፡፡
ካገኘህ አሣ ትይዛለህ፤
ካልሆነ እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ!”
የሚለውን አገራዊ ተረት ልብ የምንለው የዘመናችንን እሳቤ ጥንታዊነት እያሳየን ይሆናል!

Read 27995 times