Saturday, 27 June 2020 15:35

‹‹አባይ ወንዝ አይደለም!›› አለ!

Written by  (ከበድሉ ዋቅጅራ)
Rate this item
(0 votes)


 አባይ፣
አልሰማም
አላይም
ባይ፡፡
የጀግንነት የእምቢታ ምስክር፤
አባይ ሽፍታው፣
አባይ ፋኖው፣
አባይ ቆላው፣
አባይ ደጋው፣
አባይ ሜዳው አባይ ዱሩ፤
ባደገበት ባይተዋሩ፤
አይቀመር የእድሜው ሰገግ፣
አይደበዝዝ የዘሩ ሀረግ፤
አይነጥፍ
አይታጠፍ . . . ቃልኪዳኑ፤
የነፍስ ኩራት - ሰመመኑ፤
ምታት- ደዌ - ሰቀቀኑ፡፡
አባይ ግዝፈት - አይፈተን፤
አባይ ወረት - አይዘገን፤
አባይ የእምቢታ፣ የጀግንነት ማሰሪያ፤
አባይ የብቸኝነት፣ የመነጠል መጠሪያ፤
የሀብታምነት ጣሪያ፤
የንፉግነት መስፈሪያ፤
መንታ ቅኝት፣
መፎከሪያ፤
መቆዘሚያ፡፡
አባይ ችኩል ተጓዥ፤
አባይ ነቃይ አጋዥ፤
ከወለደው - ካደገበት፣
ማርፍድ ቢያምረው፤
ባዶ ሆዱን ለዘፈነለት፣
ከወለደው - ካሳደገው
ደርቆ ልሳን ሳያጥረው፣
ውቅያኖስ ሳይሰለቅጠው፤
ከዘመናት ግርጌ ላይ፣ በወገኖቹ ሸንጎ
ቢታደም፣ በጉማ ልታረቅ ባለ፤
በሄድሮስ ‹‹የአባይ ስጦታ›› ብሂል፣ ርእዩን
የሰነከለ፤
በኤሊያድና ኦዲሴይ፣ በሆሜር የምናብ
ማሳ፣ ህልሙን ዘርቶ ያበቀለ፤
አባይ ወንዝ አይደለም አለ!
አባይ አይጨበጥ - መንፈስ ወረት፣
አባይ ግጥም- አባይ ተረት፤
አባይ ጩኸት
አባይ ቅዠት
አባይ ደራሽ
አባይ ገስጋሽ
አባይ ገንቢ - አባይ አፍራሽ፤
አባይ ተካይ፣
አባይ ነቃይ፡፡
የአፍሪካ - የጥቁር መሬት ወንዞች አባት፣
አይደክም አይታክት ብርቱ፤
ታሪክ - አይደለዝ ፍሰቱ፤
ሀቅ - አይታክት ጩኸቱ፤
ወላድ አምካኝ ስስቱ፤
በረሀ አልሚ ትሩፋቱ፡፡
አመት ቆጥሮ በክረምት ዶፍ፣
እንደመነቸከ ሸማ፣ ሀገር እየዘፈዘፈ፤
ተራራና ሸንተረሩን፣ አሽቶ
እያለቀሰ፣ ጨምቆ እያራገፈ፤
የሀገሬን ድንግል አፈር፣
ሰሀራ ላይ ቢያሰጣለት፤
እንደ ዱር ወፍ፣ ያለሀሳብ - ያለጭንቁ
ቢመግበው፤
ስስቱ የሰነከለው፤
ያ ያልታደለ፤
አባይ ወንዝ አይደለም አለ!
አባይ . . . . .
ያጨለምኩትን ላብራ፣
የነቀልኩትን ላጽድቅ ባለ፤
በሄድሮስ ‹‹የአባይ ስጦታ››
ብሂል፣ ወደፊቱን የደለለ፤
በኤልያድ ኦዲሴይ ተረት፣ ርእዩ የማለለ፤
አባይ ወንዝ አይደለም አለ!
አባይ የምናውቅህ የምታውቀን፤
ያሳደግንህ - የማትጦረን፤
አባይ አብሮአደጋችን . . .
የልጅነት - ተረታችን
የወጣትነት - ግጥማችን
የጉልምስናችን ፉከራ - የበስተርጅናችን
ጸጸት፤
አይጨበጥ አይደርስ ስለት፡፡
አባይ የሰሀራ በረሀ፣ ስለት በረከት፤
የፈርኦን ተአምር፣ ከየት መጣ ምታት፣
የአልሲሲ የእንቅልፍ ልብ፣ ጭራቅ - ቅዠት፡፡
ወንድሜ ‹‹ወንዝ አይደለም›› ያልከው፤
ከቀን ቅዠትህ ተፋትተህ፣
እስቲ አባይን ጠይቀው!
ማን አምጦ እንደወለደው፤
ማን መግቦ ቅስም እንደሆነው፤
አባይ ይንገርኸ ጠይቀው፡፡
አዛውንትነቱን አይደለም፣
አስተዳደጉን ጠይቀው፤
እሱ ነው እውነቱ ያነቀህ፣
እሱን ነው የዘነጋኸው፤
ጠይቀው!
የወፌ ቆመች ጊዜውን፣ ዳዴ ያለበትን ደጃፍ፤
‹‹ማማ! ባባ!›› ያለበትን፣
የተኮላተፈበትን አፍ፤
ከቤትህ ውሎ ሳያድር፣
አረብኛ ሳታስለምደው፤
ቋንቋው ምን እንደነበር፣
አባይ - እራሱን ጠይቀው፡፡
ይነግርሀል . . .
የደንቢ መስክ የዶፍ ምጡ፣
ከጣና ማህጸን ገላግሎት፤
ከጎጃም እስከ ቤንሻንጉል፣
በለስ ግራውን ደግፎት፤
ከሻንቦ እስከ ጊንቢ፣ ባንኮ እስከ ነቀምት፣
ከቱሉ ወሊ እስከ አሶሳ፤
አልቦ እያጠባው ዲዴሳ፤
የሱሉልታ - ገብረ ጉራቻ፤
የንፋስ መውጫ - ቤተሆር፣
የመርጦ ለማርያም - የአርባ ፈሪ ተራራ፣
የቢሻሎ አይደርቅ እምባ፤
የአልዲያ ተራራ ወዝ፣
የቦረንቲ ዙሪያ፣ የቦሎ ቀርሳ፣
ተልተሌና ቀራሴ ጥንስስ፤
ከሁሉቃ እስከ ደቢስ፤ . . . . .
አይጻፍ አባይ ድርሳኑ፤
አይቀመር እድሜው ዘመኑ፡፡
ድርሳኑ ከቋንቋ ይሰፋል፤
እድሜው ከዘመን ይተርፋል፡፡
ወንዝ ሆኖ አይታሰር፣
ውሀ ሆኖ አይሰፈር፤
አባይ ሀገር ነው መስፈሪያው፣
ነጻነት አቻ ትርጉሙ፤
ከሰንደቅ ጋር ህመሙ፡፡
አባይ የሴም፣ የኩሽ የካም ህዝቦች ሙሾ፣
የእድሜ ሙሉ ጸጸቱን፤
ለበደለው - ለነቀለው፣
ቆንጥሮ ቢሰጥ ወረቱን፤
እድሜ ሙሉ የታወረ አይኑ በርቶ፣
ከወለደው - ካሳደገው፣ ልታረቅ ባለ፤
ለበደለው - ለነቀለው፣
ጸጸት - እምባውን ባካፈለ፤
ከወለደው - ካደገበት ማርፈድ ቢያምረው፤
ባዶ ሆዱን ለዘፈነለት፣
ደርቆ ልሳን ሳያጥረው፣
ውቅያኖስ ሳይሰለቅጠው፤
ከዘመናት ግርጌ ላይ፣ በወገኖቹ
ሸንጎ ቢታደም፣ በጉማ ልታረቅ ባለ፤
በሄድሮስ ‹‹የአባይ ስጦታ››
ብሂል፣ ወደፊቱን የደለለ፤
በኤልያድ ኦዲሴይ ተረት፣ ርእዩ የማለለ፤
አባይ ወንዝ አይደለም አለ!
አባይ ሰንደቅ - አይታጠፍ፤
አባይ ጽናት - አይዛነፍ፤
አባይ የሀገር ህይወት - ታሪካችን፣
ይፈሳል፤
አይገሰስ ነጻነታችን፣
ይጸናል፡፡
አባይ ወረት፣
አባይ ኩራት፣
አባይ አፈር፣
አባይ ሀገር፡፡
(ከበድሉ ዋቅጅራ)


Read 1870 times