Print this page
Saturday, 04 July 2020 00:00

“ደጅ ያለው ሰንበሌጥ ሲታጨድ ማድቤት ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ሰፌድ ይንቀጠቀጣል!” - (ሀገርኛ ተረት)

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ወጣት መንገድ ላይ ብርቱካን እየበላ ሲሄድ፤ ሌሎች የሰፈሩ ወጣቶች ወደሱ መጥተው እንዲያካፍላቸው ይጠይቁታል፡፡
አንደኛው - አንዲት ዘለላ ብቻ ስጠኝ?
ባለብርቱካን - እቺ ብርቱካን ብቻ ናት ያለችው - ለእኔም አትበቃኝ!
ሁለተኛው - ሳገኝ እተካልሃለሁ - ስጠኝ
ባለብርቱካን - አንተ እስክታገኝ ምን አስጠበቀኝ፡፡ ድርሻዬ ነው - የራስህን ፈልግ፡፡
ሦስተኛው - ልግዛህ - ግማሹን!
ባለብርቱካን - የሚገርመው አንዳችሁም ከየት አመጣህ? አላላችሁም
ሶስቱም - ከየት ነው ያመጣኸው? ቦታውን አሳየንና እኛም ሄደን እናግኝ…
ባለብርቱካን - ያውላችሁ!
አለና ራቅ ወዳለ ቦታ ወደ ኋላ ጠቆመ፡፡
ሦስቱም ተያይዘው ወደተፈለገው አቅጣጫ ሩጫውን ቀጠሉ፡፡
በሚሮጡበት መንገድ ላይ ያገኙዋቸው ሰዎች፤ ወዴት ነው የምትሮጡት ሲሉ ይጠይቋቸዋል:: “እዚያ መንገድ ማዶ ብርቱካን ይታደላል” ብለው ሩጫቸውን ቀጠሉ፡፡
በመጨረሻ ግን ያ መጀመሪያ ብርቱካን ይዞ የነበረውና “እዚያ ማዶ ሂዱ” ያለው ባለብርቱካን ዘወር ብሎ ወዳሳየው አቅጣጫ ሲያይ፤ በመንገዱ ላይ ወሬውን እየሰሙ ከሚሮጡት ሰዎች የሚቀላቀሉትን ብርቱካን ፈላጊዎች ብዛት ሲመለከት፤
“እንዴ! ይሄ ነገር ዕውነት ይሆን እንዴ?” ብሎ ራሱ መሮጥ ጀመረ!!
*   *   *
በተለይ ዛሬ በዘመነ - ኮሮና! ያለው የሌላቸውን አለማሰቡ ጐጂ ነው! ያለንን አለማካፈል ደግ አይደለም፡፡ ያለው ለሌለው አላማጋራቱ ቢያንስ የርህራሄ ማነስን ያሳያል፡፡ ከዚህ በላይ ግን የሌላቸው ከአጠገብ ገለል እንዲሉ ብቻ መዋሸት በጭራሽ ትክክል አይደለም፡፡ የብርቱካን ጠያቂዎቹም አንዱ ካንዱጋ እንኳ ሳይነጋገር ሳይመካከር በመንጋ መሮጥ ትክክል ያልሆነና የግብዝነት ሩጫ ነው፡፡ በቀላሉ የመታለልም ምልክት ነው፡፡ ከሁሉ በላይ እጅግ አስገራሚውና አስቂኙ ነገር ግን ራሱ በፈጠረው ውሸት የሚታለል ሰው መኖሩ ነው! ከተጠቀሱት ነጥቦች ሁሉ ሊሰመርበት የሚገባው ግን የአብዛኛው የሀገራችን ሰው ችግር የሆነው የመንገኝነት አባዜ ነው (herdism)፡፡ እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁሉ በመንጋ እሚነዳ ሲሆን፣ ላቅ መጠቅ ያለ አስተሳሰብ ያለው ሰው ይጨፈለቃል፡፡ መደማመጥ ሳይኖር፣ መጠያየቅ ሳይኖር፣ መወያየት ሳይኖር፣ መተሳሰብ ሳይኖር፣ አንዱ የተናገረውን ነገር እያስተጋቡ መነዳትና መነዳዳት እንከንን ልብ ሳንል እንድንጓዝ፣ የተሻለ ሀሳብ እንዳናስተናግድ፣ የሃሳብ ልዩነቶቻችንን እንዳንመረምር፣ በተለይም በልማድ ብቻ እንድናዘግም ያደርገናል፡፡ የሼክስፒር ሐምሌት እንዳለው፤ (በፀጋዬ ገ/መድህን ትርጓሜ)፡-
“…ዛሬ ለወግ ያደረግሺው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል!”
ዕውነትም፤ ፊት ከሰጡት፣ “ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል፡፡” ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ራስን መግራት ያስፈልጋል፡፡ ቀናውን ለውጥ አይቶ ተለውጦ መጓዝ፣ ይህንንም የመለወጥ ባህል ማዳበር ከመንተብ፣ ከመቸከል፣ አንድ ቦታ ከመቆምና ከመንቀዝ (Degeneration) እና ከመዛግ ያድነናል፡፡
ስለ ፍትሕ፣ ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ እኩልነት፣ ስለ ወንድማማችነትና ስለ ለውጥ ስናወራ ራሳችንን ገትተን መሆን የለበትም፡፡ እየተንቀሳቀስን፣ እየተቀያየርን እንጂ! በእንደኛ ዓይነት ዝግ ማህበረሰብ (Closed Society) ውስጥ ለውጥን ለማምጣት የተዘጋውን የሚከፍት፣ ምን ቢደረግ ይሻላል (“What is to be done?”) የሚል ጥያቄ ያስፈልጋል፡፡ ትክክለኛ ጥያቄ መጠየቅ ግማሽ መልስ ነው እንዲሉ፤ ሦስቱ ዋና ዋና መልዕክቶቻችን፡- ትክክለኛውን ጥያቄ መፈለግ፣ ትክክለኛውን ጥያቄ ማግኘትና ትክክለኛውን ጥያቄ መጠየቅ ናቸው!
“ትላንትና ማታ እቤትህ ስትገባ ደጅህ ላይ ያነቀፈህ ድንጋይ ዛሬም ከመታህ፤ ድንጋዩ አንተ ነህ!” የሚለው የቻይናዎች አባባል፣ ተደጋጋሚ ስህተት ላይ ላለመውደቅ መልካም መመሪያ ነው! ቢያንስ የተሻለ ስህተት መሥራት የለውጥ መነሻ ይሁነን! እንቅፋትን ማወቅ ጠላትን ማወቅ ነው! ወደፊት መራመድ የሚቻለው 1) እንቅፋትን በመሸሽ 2) እንቅፋትን በመዝለል 3) እንቅፋትን በማያወላዳ መንገድ ከናካቴው ጠራርጐ በመጣልና ከመንገዳችን ጨርሶ በማስወገድ ነው፡፡ ለማራምደው ፖለቲካ እንቅፋቴ ምንድነው? ለማበለጽገው ባህል እንቅፋቴ ምንድነው? እነዚህን ጥያቄዎች አብጠልጥሎ ማየት ምንጊዜም ተገቢ ነው፡፡ ሦስቱንም ጥያቄዎች ለማስተዋል መጀመሪያ አጉሊ - መነጽር (Microscope) ሊኖር ግድ ይላል! እንቅፋቶች ጐልተው ሲወጡ ለማስወገድ ቀላል ይሆናሉና፡፡
ዛሬ በሀገራችን ለፖለቲካዊ ሂደታችን ቁልፉ የሰላም መኖር ነው፡፡ (ግርግርና ሁከት ቤት አይሠራም!) ስለሆነም የፀረ - ሠላም ኃይሎችን መወገድ መሪ ጥያቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ሰላም ሳይኖር እንኳንስ ፖለቲካዊ ዓላማን ማሳካት ወጥቶ መግባትም ዘበት ይሆናልና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ወሳኝ ነው”፡ ለዚህ ደግሞ የአገር ውስጥና የውጭ ጠላቶችን ነቅቶ መጠበቅ፣ መከላከልና ቦታ ማሳጣት ተገቢ ነው! የጠላቶቻችን አንዱ እኛን ሰላም - መንሻ ዘዴ ኢኮኖሚያዊ ግንባታን ማቃወስና ማህበራዊ አለመረጋጋትን መፍጠር መሆኑን በጭራሽ አንዘንጋ! “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚሉ ወገኖችን እንጠንቀቅ! የፀረ - ኮሮና እርብርብ ላይ ሰላምን ማጣት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ነው፡፡ የግድቡ ሥራ አለመሳካት ለአንዳንዶች የምሥራች ነው፡፡ ስለሆነም የውስጥ ሰላም እንዲጠፋ ማናቸውንም ዘዴ ይጠቀማሉ - ለዚህ አይተኙም፡፡
የውጪ ጠላቶች ሲመቱ የውስጥ ጠላቶች መራድ ይጀምራሉ፡፡ ምነው ቢሉ “አፍንጫን ሲመቱት ዐይን ያለቅሳልና ነው!” “ደጅ ያለው ሰምበሌጥ ሲታጨድ ማድቤት ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ሰፌድ ይንቀጠቀጣል” የሚባለው ለዚህ ነው! የውጪንም የውስጥንም ጠላት ማስወገድና ሰላምን ማረጋገጥ የወቅቱ ጠቅላይ ጥያቄ ነው - የሁላችንንም መደጋገፍ ይሻል! ውጤቱን ብቻ ሳይሆን መንስዔውንም እንይ!!


Read 3578 times
Administrator

Latest from Administrator