Print this page
Saturday, 11 July 2020 00:00

"የፊት ወዳጅሽን በምን ቀበርሺው በሻሽ፤ ለምን? - የኋለኛው እንዳይሸሽ!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ መንደር ውስጥ አንዲት ጦጣ የምታስቸግረው አንድ ገበሬ ይኖር ነበር።
ጦጢት ያ ገበሬ የሚዘራውን ዘር እየተከታተለች እየሄደች ገና በአፍላው የተዘራውን እያወጣች ትቦጠቡጥበታለች። ስለዚህ በተቻለው መጠን የሚዘራውን አይነግራትም ወይም አያሳያትም።
ጦጢት ገበሬው የሚመጣበትን ሰዓት ስለምታውቅ ዛፍዋ ላይ ሆና ትጠብቀዋለች።
ልክ ገበሬው ብቅ ሲል ወደ ዛፍዋ ትሮጥና ትወጣለች። ምክንያቱም መሬት ሆና ካገኛት እርሻው ቦታ ሄዳ የሚዘራውን ስታይና ስትመዘብር እንደቆየች አድርጎ ይጠረጥራል። እንደዚያ ከተጠራጠረ ደግሞ ከዚያ አካባቢ ሙሉ ለሙሉ እስከሚጨልም ድረስ አይንቀሳቀስም። ጦጢት በጣም ብልጥ ስለሆነች የእሱን ሁኔታ ተከታትላ በመሰለል ጨርሶ እስከሚሄድ ትታገሳለች። ትጠብቀዋለች።
አንድ ጊዜ ገበሬው ድምፁ ሲጠፋና በአካባቢው ያሉትን ገበሬዎች የሚያነጋግርበትን ሁኔታ ሲያቆም፤ አገር አማን ነው ብላ እርሻ ውስጥ ትገባለች። ገበሬ ሆዬ፤ አንዲት የሀብታም ነጋዴ ሚስት ቤት ቡና ሊጠጣ ይገባና እግረ መንገዱን ማዶ ማዶ እያየ ይጠባበቃት ኖሮ፣ በፍጥነት እመር ብሎ ገርበብ ያለውን የውጭ በር ገፍትሮ ከግቢው ወጥቶ ይደርስና ይይዛታል። ከዚያም እንዳትሞት እንዳትሽር አድርጎ ይደበድባታል። ከዚያ ቀን በኋላ ወደ እርሻው ድርሽ ሳትል ቆየች።
አሁን አሁን ግን ቀስ ብላ እያዘናጋች ገበሬውን እያግባባች መጥታ ሰላም መባባልና አንዳንዴ ጭውውት ውስጥ ገብተው እንዲያወሩ ማድረግ ችላለች።
እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ዛሬ ገበሬ ሥራውን ጨርሶ እየወጣ ሳለ፣ እሜቴ ጦጢት በፍጥነት ዛፏ ላይ ወጥታ ትጠብቀዋለች፡-
“አቶ ገበሬ እንደምን አምሽተሃል?” ትላለች።
ገበሬ፤ “ደህና፤ እግዚአብሄር ይመስገን። ውሎሽ እንዴት ነበረ?”
ጦጢት - “ሰላም ነው። ካንዱ ዛፍ አንዱ ዛፍ ላይ እየዘለልኩ ፍሬ ስለቅም ዋልኩኝ። አንተን እየለመንኩ ማስቸገሩ ሰልችቶኛል።”
ገበሬ - “አይ መልካም ነው። ጥሩ ዘዴ ዘይደሻል።” ብሎ መንገድ ሊጀምር ሲል፤
ጦጢት - ;እኔ እምለው ገበሬ፤ ዛሬ ምን ስትዘራ ዋልክ?;
ገበሬ በሀሳቡ ጦጢት የምትጠላውን እህል አሰበ። በመጨረሻ አንድ ሀሳብ መጣለት፡-
“አይ ዛሬ እንኳን የረባ ነገር አልዘራሁም…” ብሎ አመነታ። እሜቴ ጦጢትም ጥርጣሬዋ ያይልና፤
ጦጢት - “ምነው ዘገየህ ገበሬ? ንገረኝ እንጂ?”
ገበሬም - “ተልባ። ተልባ ነው የዘራሁት” አላት፡፡
 ጦጣ ተልባ እያሙለጨለጨ አልያዝ እንደሚላት ገበሬ ያውቃል።
ጦጢትም - “ይሁን እንግዲህ! ወርደን እናየዋለን!” አለች።
*   *   *
መሬት ወርዶ መሬት የያዘችውን ሀብት ማወቅና መመርመር መልካም ነገር ነው። እንደ ጦጢት የሰው ሀብት ለመበዝበዝ ሳይሆን አቅምን ለማወቅ የሚበጅ ሲሆን፣ በአንፃሩም ሁሉን ነገር መርምሮና ተጨባጭ ሂደትን የመፈተሽ ባህል፤ መዳበሩ እጅግ አስፈላጊ እርምጃ ነው። የአገርን ህልውና ከሚወስኑ ዋንኛ ነገሮች መካከል ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን (Objective and Subjective realities እንዲል መጽሐፉ) መገንዘብና ማገናዘብ በቅጡ ሊታሰብበት ይገባል። ነገርን ከሥረ መሰረቱ ማጤን ለፖለቲካም፣ ለኢኮኖሚም፣ ለማህበራዊ መስተጋብርም እጅግ ትልቅ ጉዳይ ነው! የፖለቲካ ብስለት የኢኮኖሚን ውስጠ ነገር ለማውጠንጠንና የዕድገትና ልማትን አንድምታ ለማስተዋል፣ መሬት የጨበጠ ትንታኔንም ለማበልፀግ ይረዳል። መሬቱን አሽትቶ አቅምን ማወቅ ራስንም፣ ጎረቤት አገርንም፣ ዓለምንም የመመልከቻ መነጽር ይቸረናል። አርቆ ማየት ወሳኝ ነው! ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው፤ ;ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ እንዳንሆን የቅርብም የሩቅም ዕይታችንን እናጠንክር፡፡;  
“You need a drought - breaker
You go find yourself a rain - maker”
“ድርቁን ሰባሪ ከፈለግህ፣ ዝናብ አዝናቢ ፍጠር” እንዲሉ፤ ሁሉ ነገር በእጅህ ይሆን ዘንድ በራስህ ተማመን ነው ነገሩ። በራሳችን መተማመን ለስህተታችን ተጠያቂ መሆንን አለመፍራት፣ ያለንን የምናውቀውንና ለአገር ይበጃል የምንለውን ሁሉ በግልጽነት ማሳየትን፣ ለውጥ ሂደት እንጂ የአንድ ጀንበር ነገር አለመሆኑን መቀበልን፤ የአገርና የሕዝብ ጥቅም ከራስ ጥቅም በላይ መሆኑን በጥሞና ማመንን ይሻል። ይሄ ደግሞ በራስ አቅም ብቻ ሳይሆን፤ በጋራ፣ በደቦ፣ በመተጋገዝ፣ አብሮ ከማቀድ እስከ አፈፃፀም መጓዝና መዝለቅን ይጠይቃል። ዕቅድን ከሙያዊነት ክህሎት (Professionalism) አጋብቶ መራመድ፣ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ ከማስቀመጥ ጋር ሲዋሃድ፤ ውጤታማነት በተጨባጭ ሚዛን ላይ ይቀመጣል።
ዞሮ ዞሮ ግን ለውጥ ሁሉ ሂደት መሆኑን በሚገባ መረዳት ወሳኝ ነው! በአሁኑ ሰዓት ባለፈ ነገር መፀፀት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ስህተትን ለማየት ቆም ብሎ አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነው ማለት ያስፈልጋል። የያዙትን ሙጭጭ ብሎ በመያዝ ‘ካፈርኩ አይመልሰኝ’ ማለት ችግርን እንዳናይ ይጋርደናል። ያባብሰዋልም! እያዩ ማረም፣ አዲስን የመቀበል ዝግጁነት፣ ተለዋጭና ለዋጭ የመሆን ብቁነት የተሻለ ሕይወትን ያስጨብጣል። ለዚህ አዕምሮንም፣ ልብንም ክፍት ማድረግ ወሳኝ ነው።
 የነገሮች ድንገተኝነት እንዳያስደነግጠን ትዕግሥትን፣ ብስለትን፣ ዕውቀትን መከታ እናድርግ! ትላንት የነበረውን በዛሬ እናጥራና ለነገ ብሩሁነት እንሰለፍ! ብዙ አይተናልና ከታሪክ እንማር። ትላንትና ያሳለፍነውን በቀና እንፈትሸው። በቀና እናሸንፈው ዘንድ የነገ ፀሐይ ይታየን። “የፊት ወዳጅሽን በምን ቀበርሽው? - በሻሽ። ለምን? የኋለኛው እንዳይሸሽ!” የሚለውን ተረት የራሳችን መስተዋት አድርገን እንየው! የሁሉም መጠንጠኛ ግን አገርና ሕዝብ ይሁን!
ለማንኛውም ሳንረብሽ እንጠንቀቅ!! 

Read 3894 times
Administrator

Latest from Administrator