Saturday, 11 July 2020 00:00

በኮሮና ሳቢያ ለኢትዮጵያ ስፖርት የማገገሚያ ዕቅድ ተዘጋጅቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  የማገገሚያ እቅዱ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ በኮሮና ሳቢያ እየደከሙ፤ እየፈረሱ ያሉና አስቸኳይ ድጋፍ ለሚሹ የተዘጋጀ ነው፡፡ በእቅዱ ዝግጅት ላይ የስፖርት ኮሚሽን፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ የስፖርት ማህበራት፤ የእግር ኳስና የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች፤ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተሳትፈዋል፡፡  በማገገሚያ እቅዱና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስፖርት አድማስ የስፖርት  ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ከዱቤ ጁሎ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡
የተከበሩ አቶ ዱቤ ጁሎ በኢትዮጵያ የስፖርት አመራር ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሲሆኑ ባለፉት 12 ዓመታት በአትሌቲክስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባልነት፤ በቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢነት፤ በአትሌቶች ተወካይነት አገልግለዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር World Athletics  በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት አጠቃላይ ሂደትና እድገት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በማድነቅ ‹‹ዎርልድ አትሌት ፒን››  ሽልማትን አበርክቶላቸዋል፡፡

          የኮሮና ወረርሽኝ  በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ ያደረሰውን  ቀውስ እንዴት  ይገልፁታል? ቀውሱን ለመቋቋም በመንግስት በኩልስ ምን ተሰርቷል?
ሁላችንም እንደምናውቀው የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ ነው:: በሌሎች መስኮች እንቅስቃሴዎች እየተጀመሩ ቢሆንም  በተለይ የስፖርት ኢንዱስትሪውን ግን ሙሉ ለሙሉ አቁሞታል ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ደረጃ በስፖርቱ መስክ ስልጠና ቆሟል፤ ውድድሮች ተቋርጠዋል፤ በአደረጃጀትም አዳዲስ ፈተናዎች ተጋርጠዋል:: ሁሉም ነገር ዝግ እንደሆነ ነው፡፡ ስፖርተኞች እና ክለቦች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀዋል:: የኢትዮጵያ ስፖርትም እጅግ አስደንጋጭና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ስለዚህም የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ነው የከረመው፡፡ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ጋር በመተባበር ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በስፖርቱ ላይ ያጋጠመውን ቀውስ የማገገሚያ ዕቅድ በሰፊ ጥናት አዘጋጅቶ ለመንግስት ቀርቧል፡፡ የስፖርት ማህበራት፤ የእግር ኳስና የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች፤ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተሳትፈውበታል፡፡  በ2013 የመንግስት በጀት ለስፖርቱ ተብሎ የተደረገ ልዩ ነገር የለም፡፡  ምናልባት መንግስት ለስፖርቱ የሚያደርገውን ድጋፍ በአንዳንድ መልኩ የሚያዘጋጀው ሊሆን ይችላል እንጅ፡፡
የኢትዮጵያ ስፖርት በስልጠና፤ ውድድርና አደረጃጀት ያለምንም እንቅስቃሴ ከተዘጋ 4 ወራት ሞልተዋል፡፡ የስፖርት ኮሚሽኑ በአጠቃላይ የተጋረጡትን አደጋዎችን እንዴት ተመልክቷቸዋል?
የኮሮና ወረርሽኝ በስፖርቱ ላይ የሚያስከትለውን አደጋ እንደ ኢፌድሪ የስፖርት ኮሚሽን ከሁሉ ቀድመን ተረድተናል፡፡ ስፖርቱ በወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስበት ከባለድርሻ አካላት ጋር ብዙ መክረናል፡፡ የማገገሚያ ዕቅዱን ያዘጋጀነው   በኮሮና ወረርሽኝ ውስጥ ከዚያም በኋላ ስፖርቱን የምንመራበትን አቅጣጫ ለመንግስት ለማሳወቅና የምንጠብቀውን ድጋፍ ለመጠየቅ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይ ስፖርተኞች ከስልጠናና ውድድር መቆም በተያያዘ የሚያሳስብ ሁኔታ ላይ ናቸው:: በተለይ በአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ ውድድሮች መቋረጣቸው  አትሌቶችን ለችግር አጋልጧል::  በዋናነት እግር ኳስ ላይ ቢሆንም በተለያዩ ስፖርቶች የሚንቀሳቀሱ ክለቦች በሚፈርሱበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል:: እየፈረሱም ናቸው:: ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዳለው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በራሳቸው የሚተዳደሩ ክለቦች ጥቂት ናቸው:: አብዛኛዎቹ ከመንግስት በሚያገኙት የበጀት ድጋፍ ይተዳደራሉ፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በኢትዮጵያ ስፖርት በርካታ ነገሮች መቆማቸው የሚያሳስብ ነው፡፡ ስፖርተኛው ከውድድር መራቅ የለበትም፡፡ ያለምንም እንቅስቃሴ በየቤቱ ተወስኗል፡፡ ስልጠና የለም፤ ውድድር የለም:: ይህ ደግሞ ስፖርቱ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል:: ስለዚህም ወደፊት ስፖርቱን ቀጣይ እና ተከታታይነት ያለው ለማድረግ የመንግስትና የህብረተሰቡን ድጋፍ በስፋት የምንጠብቀው ይሆናል፡፡  የማገገሚያ ዕቅድ ከባህልና ቱሪዝም ጋር ተባብረን በመስራት ሰነዱን ለመንግስት ያቀረብን ሲሆን ምላሹንም እየተጠባበቅን ነው:: በመንግስት በኩል ለስፖርቱ መስክ የነበረው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማመን ነው:: ስፖርቱን ለማዳን ልዩ ርዳታ ያስፈልገናል፡፡
በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ የስፖርት ውድድሮች መቆማቸው ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከቶናል፡፡ በተለይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ ኦሎምፒክና ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች መቋረጣቸውና መስተጓጎላቸው የስፖርተኛውን ህልውና የሚፈታተን ነው:: ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ በግል የሚወዳደሩት አትሌቶች ብዛታቸው በፌደሬሽኑ ስር ከሚወዳደሩት ይበልጣል:: በቻይና  በዓመት ውስጥ ከ250 በላይ ውድድሮች ይዘጋጃሉ፤ በየውድድሮቹ ላይ ደግሞ በርካታ የኢትዮጵያ አትሌቶች ይሳተፉ ነበር:: ውድድሮች ባለመደረጋቸው ከባድ ችግር ውስጥ መግባታቸው አልቀረም፡፡  በእግር ኳስም ችግሩ የሰፋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ፤ ሱፕር ሊግ በሌሎችም የሚሳተፉ ክለቦች እና ተጨዋቾችም ከላይ እስከታች ውድድሮች በመቆማቸው ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል:: ክለቦች የገቢ ምንጮቻቸው ተቋርጦባቸዋል፡፡ በፋይናንስ እጥረት እና ስፖርቱ ላይ በተፈጠሩ አዳዲስ አቅጣጫዎች አደረጃጀታቸውን ለማስቀጠል ፈተናዎች ተጋርጦባቸዋል፡፡  እንደውም አንዳንድ የእግር ኳስ ክለቦች ችግሮችን መቋቋም አዳግቷቸው እየፈረሱ ናቸው፡፡ የመፍረስ አዝማሚያ ውስጥ የገቡትም ጥቂት አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአትሌቲክስና በእግር ኳስ የተመለከትናቸው ሁኔታዎች ጠቀስኩ እንጅ በሌሎች ስፖርቶችም ያጋጠሙት ችግሮች የሚያሳስቡን ናቸው፡፡
የማገገሚያ እቅዱ አጠቃላይ ይዘት ምን ይመስላል?
የማገገሚያ እቅዱን ያሰናዳነው በአጠቃላይ  በኮሮና ሳቢያ የኢትዮጵያ ስፖርት ለወደፊቱ አደጋ ላይ መውደቁን ተገንዝበን ነው፡፡  ስለዚህ በተቻለን መጠን ባለድርሻ አካላቱን በማወያየት ሰነዱን ስናዘጋጅ እንዴት ወደ ስልጠናው እንመለስ?  ወደ ውድድሮች እንግባ ? በሚሉ ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ጥናት አድርገን ነው:: የመፍትሄ ሃሳቦችንም አያይዘን አቅርበናል፡፡ የሌሎች አገራት ተመክሮን በመቀመር ያከናወነው ሰፊ ስራ ነው፡፡
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ውስጥ ሆነን እንዴት  ስፖርተኛውን ወደ ስልጠና መመለስ እንችላለን የሚለውን ቅድሚያ ሰጥተነዋናል፡፡ በአገራችን ወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ በመምጣቱ ስፖርተኛው ወደ ቤቱ እንደተመለሰና በዚያው እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ሰነዱን ስናዘጋጅ ስፖርቱ እንዴት መቀጠል ይችላል፤ ስልጠናዎች በምን አይነት ሂደት፤ ምድብ እና መመርያ መካሄድ አለባቸው የሚለውን ተመልክተናል:: ከዚያም በኋላ ወረርሽኙ ባለበት ደረጃ ሆኖ ውድድሮችን  እንዴት ማካሄድ እንደሚቻል ጥናት አድርገናል:: በተለይ የሌሎች አገራትን ተመክሮ በመቀመር ሰነዱን ለኢትዮጵያ ስፖርት በሚያመች ሁኔታ አዘጋጅተነዋል፡፡ በሌላ በኩል በማገገሚያ እቅዱ የኮሮና ወረርሽኝ ቀጣይነት ካለው የስፖርቱ ዕጣ ፋንታ ምን እንደሚሆን በመገመትና አዳዲስ ሃሳቦችን ያፈለቅንበት ነው፡፡ በወረርሽኙ የተጎዱ ስፖርተኞች፤ ባለሙያዎች እና የስፖርት ዘርፎችን ለየተናል:: እያንዳንዳቸው የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍም በዝርዝር ያጠናንበትም ነው፡፡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እና ውድድሮችን ወደነበሩበት ለመመለስ ካደረግናቸውን ጥናቶች በነመነሳት ያቀረብናቸው የመፍትሄ ሃሳቦችም ይገኙበታል:: ህብረተሰቡ ደግሞ ቤት ውስጥ ሆኖ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግና ስፖርቱን እንዲያዘወትርም ትኩረት ሰጥተናል፡፡ በተለይ ሚዲያውን ተጠቅመን ስፖርቱን በየቤቱ ለማድረስ የያዝናቸውን ጅምሮች ለማጠናከር ያቀድንበት ነው፡፡
በመጨረሻም በሂደት ላይ ያሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እንዴት ማስቀጠል እንዳለብንም እቅዱ ይዳስሳል፡፡  የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በብቁ ስታድዬሞች እንድናስተናግድ የሰጠውን መመርያ መሰረት አድርገን ትኩረት የሰጠናቸው የልማት ስራዎችም አሉ፡፡ የአዲስ አበባ ስታድዬምን ሙሉ መስፈርቱን እንዲያሟላ ሆኖ በመታደስ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ የሚያስተናግደበት ደረጃ ለመመለስ  እንፈልጋለን፡፡ እንዲሁም  የብሄራዊ ስታድዬም ግንባታውን በኮሮና ወረርሽኝ ውስጥ ሆነን ሳናቆም እንዴት መቀጠል እንዳለብንም በእቅዳችን ውስጥ አስቀምጠነዋል::  በአጠቃላይ በስትራቴጂክ ሰነዱ ስፖርተኞች፤ ክለቦች፤ አደረጃጀት እና የተለያዩ ዘርፎች በወረርሽኙ ሳቢያ የተጎዱበትን ሁኔታ በዝርዝር ያጠናና የሚያስፈልገውን እርዳታ   ለመንግስት ያቀረብንበት ነው፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የአዲስ አበባ መስተዳደር ከተማዋን ለሚወክሉ ሁለት ክለቦች ለቅዱስ ጊዮርጊስና ለኢትዮጵያ ቡና ለእያንዳንዳቸው 15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ክለቦቹ በወረርሽኙ ገቢ ማጣታቸውን በማመልከት መስተዳድሩን ድጋፉን እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ስፖርት በተለይም በእግር ኳስ በርካታ ክለቦች በመንግስት ትከሻ ላይ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ የተጨዋቾች ደሞዝን አጠቃልሎ ለመክፈል እና በያዙት አደረጃጀት ለመቀጠል መቸገራቸው ይስተዋላል:: ለመሆኑ የመፍረስ አደጋ ላይ የወደቁ ክለቦች ምን ያህል እንደሆኑ ይታወቃል? በአጠቃላይ ከስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ስለሚጠበቀውስ ምን አስተያየት ይኖርዎታል?
እንግዲህ የአዲስ  አበባ ምክር ቤት የራሱ አሰራር አለው፡፡ በዚህ መሰረት ካቢኔው ለሁለቱ ክለቦች የሰጠው ድጋፍ ጥሩ ነው፡፡ ከመንግስት የሚጠበቀውም ይህ በመሆኑ የተሰጠው ድጋፍ ሊበረታታ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ በቀጣይ በሌሎች ችግር ላይ በወደቁት ዙርያ  መሰራት ያለበትንም ያመለክታል፡፡ የመፍረስ አደጋ ውስጥ የወደቁ ክለቦች ብዛት ይታወቃል ወይ? ብለህ ላቀረብከው ጥያቄ  አሁን በይፋ የምገልፀው አይደለም:: በስትራቴጂክ ሰነዱ ላይ በጥናት ውጤት ያስቀመጥነው ነው፡፡ ለመንግስት ባቀረብነው ጥያቄ የትኞቹ ክለቦች የመፍረስ አደጋ ውስጥ ገብተዋል፤ እነማን በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉበት ሁኔታ ጨልሟል የሚለውን አሳውቀናል፡፡ ወደፊት እንደአስፈላጊነቱ በግልፅ የምናብራራው ይሆናል፡፡
የስፖርት ኮሚሽኑ የማገገሚያ ዕቅዱን ከባለድርሻ አካላቱ ጋር አዘጋጅቶ ለመንግስት ያቀረበ ቢሆንም፤ በተለያዩ ስፖርቶች አመራር ላይ ያሉ ፌደሬሽኖችም የራሳቸውን ስትራቴጂ በማዘጋጀት እንዲሰሩና ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ ምክር ሰጥተናል፡፡ ይህኑ በተመለከተም ለሁሉም ፌደሬሽኖች  በደብዳቤ ለማሳሰብ ሞክረናል:: ፌደሬሽኖች እንዴት ስልጠና መጀመር እንደሚችሉ? ወደ ውድድሮች እንዴት እንደሚገቡ? በፋይናንስ የተጋረጡባቸውን ችግሮች እንዴት እንደሚፈቱ?  የስፖርቱን ቀጣይነት በምን አቅጣጫ መምራት እንደሚፈልጉ?... ከአባላቶቻቸው ጋር በመመካከር በየስፖርታቸው የሚያቅዱትን ስትራቴጂ ነው የጠየቅነው፡፡  በሌሎች የዓለም አገራት የተነደፉ ስትራቴጂዎችን መመርመር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበን ነው፡፡ በተለይ የአቻ ፌደሬሽኖችን ለምሳሌ በኬንያ፤ በናይጄርያ የተሰራውን  መነሻ ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁመናል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ፤ የዓለም አትሌቲክስ የበላይ አካል ‹‹ዎርልድ አትሌቲክስ››፤ የአፍሪካ እግር ኮንፌደሬሽን ሌሎች ተቋማት ያወጧቸውን መመርያዎችና ስትራቴጂዎች ማጥናትም ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የስፖርት ማህበራትና ፌደሬሽኖች የኮሚሽኑን እቅድ መነሻ በማድረግ የራሳቸውን ስትራቴጂ ነድፈው እንዲያቀርቡልን ጠይቀናል፡፡ እግር ኳስ ፌደሬሽን የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግና ሱፐር ሊግ ውድድሮችን እንዴት ማስጀመር ይችላል? የኬንያ እና የናይጄርያ ፌደሬሽኖች  በቤት ውስጥ ስልጠና እና ውድድር የሚጀምሩበትን ሁኔታ እያመቻቹ ሲሆን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ይህን እንደተመክሮ በመውሰድ ሊሰራ ይችላል፡፡ የስፖርት ኮሚሽኑ ያንን መነሻ በማድረግ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም የስፖርት እንቅስቃሴ ከቆመ በኋላ ወደዋና ስልጠና ለመመለስ አዳጋች ነው ስለሚሆን በኮሚሽኑ በኩል ሰፊ ግዜ በመስጠት ቅድመ ዝግጅቶች እየተሰሩ ነው፡፡
ጃፓን በምታስተናግደው ኦሎምፒክ  መሸጋሸግ በኢትዮጵያ ተሳትፎ ላይ ያሳደረው ተፅእኖ አለ ወይ? ከኦሎምፒኩ ጋር በተገናኘ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ብሄራዊ ማዕከል እስከመገንባት የሚያደርሱ እቅዶችም ነበሩት… የስፖርት ኮሚሽኑ ምን አስተያየት አለው?
የኦሎምፒክ ኮሚቴው ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ነው የከረመው፡፡ የኦሎምፒክ ችቦውን በየክልሎች በማዘዋዋር አገር አቀፍ ንቅናቄ ለመፍጠር ችሏል፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያ በማዘጋጀትም ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጓል:: እንቅስቃሴዎቹ በኮሮና ሳቢያ አሁን የቆሙ ቢሆንም፡፡ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክን በአንድ አመት አሸጋሸገው እንጅ አልሰረዘውም፡፡ ስለዚህም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ  የሚሰሩት ተግባራት ከኦሎምፒኩ መካሄድ ጋር ተያይዞ መልሶ ሊቀጥል ይችላል፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ለቶኪዮ 2020 በሚደረግ ዝግጅት ስልጠናዎች እንዴት ማካሄድ እንደሚችል ከአባል ፌደሬሽኖች ጋር በመካከር እንደሚሰራበት ነው የምናምነው:: በስፖርት ኮሚሽን በኩል የመነሻ ሃሳቡን አቅርበናል ኦሎምፒክ ኮሚቴው የራሱን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ ለማገዝ ነው፡፡ በኦሎምፒክ ቡድን ቀደም ሲል የተያዙ አትሌቶችንና ሌሎችን ጨምሮ  ከሚመለከታቸው አባል ፌደሬሽኖች ጋር በመወያየት ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሚሰጠው መመርያ አቅጣጫ መሰረት ዝግጅት እንዲደረግ በስፖርት ኮሚሽን በኩል መመርያ ሰጥተናል፡፡
የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ወደ ስልጠና ከመመለስ፤ ወደ ውድድሮች ከመግባት እና ሙሉ እንቅስቃሴ ከመጀመራቸው በፊት ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ልዩ መመርያ ይወጣል ወይ? በአጠቃላይ የሰፖርት ኮሚሽኑ ምን ለመስራት አስቧል?
ወደ ስፖርት ስልጠና እና ውድድር እንመለስ ቢባል ምን ይደረጋል? ለሚለው ከጤና ሚኒስቴር እና ከማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሰፊ ውይይት እናደርጋለን፡፡ ወደ ስፖርቱ በስልጠናም በውድድርም የሚመለስ ሁሉ የኮቪድ 19 ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል:: በሌሎች አገራት ያየናቸው ተመክሮዎችን መነሻ ማድረግ የሚያስፈልግ ነው:: ወደ ስፖርቱ ለመመለስ በተለያዩ ምዕራፎች የህክምና ምርመራ ሂደቶችን መከተል አለብን:: ከጤና ሚኒስቴር በምናደርገው ውይይት ወደ ስልጠና እንግባ ሲባል በምን አይነት የአሰራር መመርያና ዘዴዎች መሆን አለበት?  ስፖርተኛው እንዴት ምርመራ ያደርጋል? ወደ ስልጠና ስፍራው ገብቶ እንዴት ይቆያል? የሚሉትን እንመለከታለን::
በመጨረሻም የማነሳው የስፖርት ኮሚሽኑ  በኮሮና ወረርሽኝ የኢትዮጵያ ስፖርት ከገባበት ቀውስ ለመታደግ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ባሻገር ሌሎች የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግን የሚያረካ አይመስልም፡፡ በስፖርት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ ስፖርተኞች፤ ክለቦች፤ የሚዲያ ባለሙያዎች፤ አሰልጣኞች፤ ስፖርቱን የሚደግፉ ኩባንያዎች እና የመንግስት ተቋማት በኮሮና ወረርሽኝ የቆመውን ስፖርት ወደ ስልጠና እና ወደ ውድድር ለመመለስ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ በኩል ትጋታቸው አንሶብኛል፡፡ አቶ ዱቤ እንደስፖርት ባለሙያነትዎ ያዘጋጃችሁት የማገገሚያ እቅድ የባለድርሻ አካላት የተሟላ ግብዓት እንዴት ለማግኘት ይቻላል…
በስፖርት ኮሚሽን በኩል በይፋ ባለመገለፁ እና ዝርዝር ማብራርያ ስላልተሰጠበት እንጅ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ አሁን ለመንግስት ያቀረብነው የማገገሚያ እቅድ በኦፊሴላዊ ደረጃ አልገለፅነውም እንጅ ይዘቱን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ነው የሰራነው::  የተለያዩ አገራትን ተመክሮ  በመውሰድ የኢትዮጵያ ስፖርት በኮቪድ ውስጥ እና ከኮቪድ በኋላ በሚል ዝርዝር ጥናትና እቅድ ሰርተናል፡፡ ምናልባት ለህዝቡ በማውጣት ረገድ የተወሰነ የግንኙነት ገደብ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል:: ከስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ለምሳሌ ከስፖርት ማህበራት ጋር እንደቻልነው ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በእርግጥ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ተሰብስቦ ውይይት ለማድረግ መከልክሉ ወስኖን ሊሆን ይችላል:: ክለቦችን የስፖርት ኮሚሽን ሰብስቦ ሊያወያይ አይችልም:: የማገገሚያ እቅዱን ስናዘጋጅ በቀጥታ መነጋገር የቻልነው ከማህበራቱ እና ከፌደሬሽኖች ጋር ነው፡፡ የእቅዱን ዝርዝር ለመገናኛ ብዙሃናት በማቅረብ ለሰፊው ህዝብ አለማድረስ ፍላጎት አለን፡፡ ከመንግስት በምናገኘው መመርያ መሰረት እቅዱን ለሚዲያው በመግለፅና በማስተላለፍ የባለድርሻ አካላትን አስተያየት እንደግብዓት ለማግኘት አስበን ነው፡፡
በአጠቃላይ የስፖርት ኮሚሽን በክለቦች ስታንዳርድ ዙርያ በከፍተኛ ደረጃ ሰርተናል፤ በማህበራትና በፌደሬሽኖች አደረጃጀት እና አሰራር ዙርያ የደረጃ እርከን አውጥተናል:: መተዳደርያ ደንቦችን ባለድርሻ አካላትን በማወያየት አሻሽለን አቅርበናል፡፡ በኮቮድ 19 ተፅእኖ ውስጥ ሆነን በስፖርት ማዘውተሪያ ዙርያ ከሰራናቸው ተግባራት በአዲስ አበባ የሚገኘው የካፍ ማሰልጠኛ ማዕከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ለ16 ዓመታት ግንበታው ተጓቶ የነበረውን ይህን አህጉራዊ ማዕከል ሙሉ ለሙሉ ሰርተን በማጠናቀቅ ወደ ስልጠና የሚገባበት ምዕራፍ ላይ አድርሰነዋል፡፡
የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኑ በማዕከሉ ካምፕ አድርጎ ወደ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች የሚገባበትን ዝግጅት አድርገናል፡፡ በስታድዬሞች እዳሳት እና አዲስ ግንባታ ያከናወናቸው ተግባራትም አሉ፡፡ በሚዲያ እየገለፅናቸው ባለመሆኑ ነው፡፡


Read 19719 times