Saturday, 11 July 2020 00:00

የአብዬ መንግሥቱ ለማ ቁጣ

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሰማ
Rate this item
(0 votes)

   መኖር መላ አገኘ
መኖር መላ አገኘ - እንደገና ደሞ
ቢሞቱም ግድ የለ መስኩ ላይ ተጋድሞ
መቅረትሽን ቃዥቶ መምጣትሽን አልሞ
ቢሞቱም ግድ የለ
የአብዬ መንግሥቱ ለማ ሥነ ፅሁፋዊ ሥራ አሀዱ ብሎ የጀመረው ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ “የአንድ ጌታ አስተዋይነት” በሚል ርእስ የፃፉት ግጥም ለማስተማሪያነት ተመርጦ በታተመላቸው ጊዜ ነበር፡፡ በብሪታንያ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ያሳትመው በነበረው (The Lions Cub) ወይም የአንበሳ ደቦል የተባለ መፅሄት ላይ “ኢትዮጲስ” በሚል የብዕር ስም ግጥሞችና መጣጥፍ ሲያቀርቡ ደግሞ ይህ የሥነ ፅሁፍ ስጦታ እንደገና ወደ አደባባይ ወጣ፡፡
አብዬ መንግሥቱ የመጀመሪያ የግጥም መድበላቸውን በ1950 ዓ.ም “የግጥም ጉባኤ” በሚል ርእስ አሳተሙ፡፡ በዚህ መድበል ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች በብሪታንያ ተማሪ በነበሩ ጊዜ የፃፏቸውና ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የደረሷቸው ነበሩ፡፡ የመፅሀፉ የመጀመሪያ እትም 18 ግጥሞች የያዘ ሲሆን በታይፕ ተተይቦ የተባዛ ሆኖ 70 ገፆች ያሉት ነበር፡፡
አብዬ መንግሥቱ በ”የግጥም ጉባኤ” መፅሃፋቸው መቅድም ላይ “የሐሳብ፣ የጨዋታ፣ የተረት ግጥሞቼ ለልጅ እግሩም ለአዋቂውም የሚስማሙ ናቸው ባይ ነኝ” ካሉ በኋላ “ለያንዳንዱ ግጥም የምትሰጡት ፍቺና ትርጓሜ ከኔ ከራሴ አስተያየት የተለየ ቢሆንም ከናንተ ጠብ የለኝም” በማለት ትሁት አስተያየታቸውን ገልፀው አንባቢን ወደ ግጥሞቹ ጋብዘዋል፡፡
ይህ መፅሀፍ ከታተመ በኋላ በጊዜው እንደተለመደው የነቀፋም የድጋፍም አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም የተለየው አስተያየት የተሰነዘረው ግን መፅሀፉ ከታተመ በኋላ 23 ዓመታት ዘግይቶ ነው፡፡ ይኸውም አስተያየት ከግጥሞቹ መካከል “መኖር መላ አገኘ” የተባለችው ባለ አራት ስንኝ ግጥም ፖለቲካዊ ትርጉም ያላት ነች የሚል ነበር፡፡ ግጥሟ ከዚህ በታች ቀርባለች፡፡
መኖር መላ አገኘ
መኖር መላ አገኘ - እንደገና ደሞ
ቢሞቱም ግድ የለ መስኩ ላይ ተጋድሞ
መቅረትሽን ቃዥቶ መምጣትሽን አልሞ
ቢሞቱም ግድ የለ
በዚህ ግጥም ውስጥ “ቅኔ የለበሰውን የፖለቲካ ሀሳብ” ተመራምሬ አገኘሁ የሚለው ሩዶልፍ ሞልቬር የተሰኘ ፈረንጅ ነው፡፡ ሞልቬር የኖርዌይ ዜግነት ያለው ሚስዮናዊ ሲሆን በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በደብረዘይት ወንጌላዊ ኮሌጅ በመምህርነትና በኋላም በምስራች ድምፅ ሬዲዮ የፕሮግራም አዘጋጅ ሆኖ አገልግሏል፡፡
ይህ ሰው በ1973 ዓ.ም የአማርኛ ሥነ ፅሁፍ በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ ማህበራዊና ባህላዊ ህይወት ላይ የነበረውን ተሳትፎ የዳሰሰ፤ (Tradition and Change in Ethiopia) የተባለ መፅሀፍ አሳትሟል፡፡ በዚህ መፅሀፍ ነው ከላይ የተጠቀሰችው ባለ አራት ስንኝ ግጥም የምትመደበው ከፖለቲካ ተርታ እንጂ ከፍቅር አይደለም ያለው፡፡ ሞልቬር “መኖር መላ አገኘ” ስለተባለችው ግጥም በመፅሀፉ ሲገልፅ እንዲህ ብሎ ነበር:-
“በዚህ ግጥም ‘መስኩ’ የተባለው ቅኔ ለበስ ቃል ሞስኮ ለማለት ሊሆን ይችላል፤ እናም ደራሲው (መንግሥቱ ለማ) ተስፋቸውን በሞስኮ (ሶቭየት ሕብረት) ላይ አድርገው የሶሻሊስት አብዮትን እያለሙ፣ በጉጉት በሚጠባበቁት በእነ ግርማሜ ንዋይ (የ1953 መፈንቅለ መንግሥት ተዋናዮች) ላይ እያሾፉባቸው ሊሆን ይችላል” (ገፅ 180)
“የኔ ፍቺ ትክክል ከሆነ ‘መኖር መላ አገኘ’ በተባለው የአቶ መንግሥቱ ለማ ግጥም ውስጥ ያለው ‘መስኩ’ በሞስኮ ላይ የቀረበ የቅኔ ቃል ነው፤ እናም ደራሲው በግጥማቸው የሚጠቁሙት በሞስኮ እርዳታ የሚመጣን አብዮት የሚያልም ሰውን ነው” (ገፅ 232)
የኢትዮጵያን ሥነፅሁፍ በተለይም የአማርኛን እና የግእዝን ቅኔ በቅጡ መረዳትና መተንተን ሳይችሉ ስለዚሁ ነገር አዋቂ መስለው መጣጥፍ በሚያቀርቡና መፅሀፍ በሚፅፉ የውጭ ሰዎች ላይ አብዬ መንግሥቱ ብዙ ጊዜ ይበሳጩባቸው እንደነበር ደራሲውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ ይህንን አስመልክቶ የአብዬ መንግሥቱ የሕይወት ዘመን ጓደኛ የነበሩት ሪቻርድ ፓንክረስት የማይዘነጉት ትውስታ አላቸው፡፡
አብዬ መንግሥቱ ስለ ሥነ ፅሁፍ መወያየትና መከራከር ይወዱ ነበር የሚሉት ሪቻርድ ፓንክረስት፤ “ከእንደዚህ አይነት ክርክሮች አንዱ ስሜቱን በጣም ስለያዘው፣ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪንን ወርፎ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ መንግሥቱን ያስቆጣው ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን (Wax and Gold) በሚል ርእስ ስለ “ሰምና ወርቅ” ያዘጋጀው መፅሀፍ ነው፤ ዶን (Wax and Gold) ብሎ የተረጐመው “ሰምና ወርቅ” የቅኔ አይነትን በሙሉ ለመግለፅ ይረዳል የሚል እምነትና አስተሳሰብ የነበረው ሲሆን መንግሥቱ ግን በፍፁም አልተቀበለውም” ይላሉ፡፡
ሪቻርድ ፓንክረስት ትውስታቸውን በመቀጠል፤ “መንግሥቱ “ሰምና ወርቅ” ከግእዝ ቅኔያት ስልቶች አንዱ ብቻ መሆኑን፣ ይህንንም ቢሆን ዶናልድ ሌቪን በቅጡ እንዳልተረዳው የሚገልፅ ፅሁፍ በማዘጋጀት ተቃወመ፡፡ “ሰምና ወርቅ” ከብዙዎቹ የግእዝ የቅኔ ቤት ወይም አይነት አንደኛው ብቻ እንጂ ሁሉንም እንደማይጨምር በብዙ መጨነቅና መጠበብ ለማስረዳት መሞከሩ ትዝ ይለኛል” ብለዋል፡፡
ወደተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ ሞልቬር ግጥሙ ለታህሳስ አብዮተኞች መልእክት ለማስተላለፍ ነው የተፃፈው ብሎ የራሱን ፍቺ ሲሰጥ፤ ግጥሙ ተፃፈላቸው ወይም ተፃፈባቸው የተባሉት አማፅያን በአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያደረጉት መፅሀፉ ከታተመ ከሦስት ዓመት በኋላ፣ በ1953 ዓ.ም መሆኑን እንኳ ያስተዋለው አይመስልም፡፡ አቶ መንግሥቱ  ይህንን የሞልቬር ፍቺ በጭራሽ አልተቀበሉትም:: በሞልቬር ተቆጡበት እንጂ “ድሮስ የፈረንጅ ቅኔ ተርጓሚ” ብለው በተለመደው ቀልደኛነታቸው ስቀው አላለፉትም፡፡ ምክንያቱም ሞልቬር ይህንን አስተያየቱን ያሰፈረበት መፅሀፍ በ1973 ዓ.ም ሲታተም በኢትዮጵያ ስልጣን የያዘው የማርክሲስት ወታደራዊ መንግሥት ሲሆን የሞስኮ (የሶቭየት ሕብረት) የቅርብ የርእዮተ ዓለም አጋር በመሆኑ በሶሻሊዝምም ሆነ በሞስኮ ላይ የሚቀርብ ቀልድም ሆነ ተቃውሞ የሚያስቆጣው በመሆኑ የግጥሙ ባለቤት የሆኑት አብዬ መንግሥቱን  አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይከታቸዋል፡፡
ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው አብዬ መንግሥቱ ራሳቸውን መከላከል እንዳለባቸው ወስነው ታህሳስ 13 ቀን 1974 ዓ.ም በታተመው የኢትዮጵያ ሔራልድ ጋዜጣ (A Letter to an Ethiopicist) የሚል ርእስ ያለውን ረጅም ማስተባበያ እንዲወጣ አደረጉ፡፡
አብዬ መንግሥቱ ረጅሙን ማስተባበያቸውን የጀመሩት በ(Tradition and Change in Ethiopia) መፅሀፍ ውስጥ ከተመረጡትና ስራቸው ከተዳሰሰው የአማርኛ ሥነ ፅሁፍ “አስራ ሁለት ሃዋርያት” መካከል አንዱ ሆነው መነሳታቸውን በማስታወስ እና በመፅሀፉ ውስጥ የእርሳቸው ሥራ የተዛባ ትርጉም ስለተሰጠው ይህንኑ ለማስተባበል መሆኑን በመጠቆም ነው፡፡
አብዬ መንግሥቱ በመቀጠልም “ይቺ ‘መኖር መላ አገኘ’ የተባለች ስራ የግጥም ጉባኤ በተሰኘው መፅሀፌ ውስጥ ገብታ በማባዣ በተሰናዳ ህትመት የተዘጋጀችው በ1950 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚያች ቀጭን ጥራዝ ባላት መፅሀፍ ውስጥ ያሉት ግጥሞች የሃሳብ፣ የተረት፣ የፍቅርና የጨዋታ በሚሉ አራት ንዑሳን ክፍሎች ውስጥ የተከፋፈሉ ነበሩ” በማለት አስታውሰዋል፡፡
ይህቺ መፅሀፍ በታተመችበት ጊዜ፤ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ርእሶች ውስጥ የሚካተቱ ሌሎች ግጥሞች እንደነበሯቸው አቶ መንግሥቱ ለማ ጠቅሰው፤ “በመፅሀፍህ አንተ ሳትጠቅሰው ችላ ባልከው ሳንሱር የተነሳ ግን በጊዜው ላሳትማቸው አልቻልኩም፡፡ እነዚህን ግጥሞች ለማሳተም የቻልኩት ከ17 አመታት በኋላ ነበር (ባሻ አሸብር በአሜሪካ /ከእሥር የተፈቱ ግጥሞች/ 1967 ዓ.ም)፤ ይህ ሁኔታ ራሱ ቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ ሳንሱር በፈጠራ ሥራ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በብዙ ሊያስረዳ የሚችል ነው” በማለት ተንትነዋል፡፡
ደራሲው፤ የፈረንጁን የፖለቲካ ጥብቆ ወዲያ አውልቀው በመጣል፣ የራሳቸውን የፍቅር ሸማ አጐናፅፈው የግጥሙን እውነተኛ መልእክት ሲገልፁት፤ “ክርክር ያስነሳችው ‘መኖር መላ አገኘ’ የተባለችው ስራ በግጥም ጉባኤ ውስጥ በግልፅ የሰፈረችው ተመሳሳይ ግጥሞች ባሉበት “የፍቅር” በሚለው ንዑስ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ግጥሙ የሚያስተላልፈው ግልፅ የሆነ የፍቅር መልእክት አለው፡፡ ይኸውም በትኩስ ፍቅር የተያዘ ወጣት፣ በውስጡ ባደረበት አዲስ የመኖር ጉጉት፤ አዲስ መንፈሳዊ ሙላትና እርካታ የተነሳ ያፈቀሩትን አግኝቶ ቢሞቱም አይቆጭ ብሎ መናገሩን ይጠቁማል” ብለዋል፡፡
አብዬ መንግሥቱ የግጥሙ ትርጓሜ የማያሻማ መሆኑን ለመጠቆም “ግልፁ ነገር ግጥሙ የፍቅር መሆኑ ነው፤ ባይሆን ኖሮ በሌላ ንዑስ ክፍል ውስጥ ይካተት ነበር፡፡ ግጥሙ የፖለቲካ አለመሆኑም እንዲሁ ግልፅ ነው፤ ፖለቲካዊ ቢሆን ኖሮ የአጤውን ዘመን ሳንሱር አልፎ የህትመት ብርሃንን አያይም ነበር፡፡ የግጥም ጉባኤ በ1955 ዓ.ም በድጋሚ ሲታተምም ይኸው ‘መኖር መላ አገኘ’ የተሰኘ ግጥም “የፍቅር” ከሚለው ክፍል ውስጥ አልወጣም ነበር” ሲሉ ግጥሙ ንፁህ የፍቅር ግጥም መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
ሞልቬር “መኖር መላ አገኘ” የተሰኘችውን ግጥም የተፃፈችበትን ዓላማ በተዛባ ትርጉም እንዴት እንዳሳተው ሲጠቁሙም፤ “በግጥሙ ውስጥ ያለውን የፍቅር አላባ ጨርሶ ዘንግተኸዋል፡፡ ተዘክሮህን (memory) ለማንቃት የሚረዳ ከሆነ ብዬ የታወቀውን መርሆ ላስታውስህ ወደድኩ (It is a love poem if there is a she in it!); በማለት እንደ ተማሪ ገስፀውታል፡፡
አብዬ መንግሥቱ ለሞልቬር የሰጡትን መልስ በመቀጠል፤ “እንደገና አፅንኦት ሰጥቼ ለማስታወስ የምወደው በግጥሜ ውስጥ “ቢሞቱም ግድ የለ መስኩ ላይ ተጋድሞ” በማለት የሚናገረው ወንድ ሲሆን፤ መምጣቷን ያለመላት ወይም የቃዠላት ደግሞ ከሥጋና ደም የተሰራች እንስት ነች፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በግጥሜ ላይ የተጠቀሰው “መስኩ” የሚገኘው በኢትዮጵያ ደጋማ ስፍራዎች ወይም ቆላ ውስጥ ይሆናል እንጂ በሩሲያ ሜዳማ ክልሎች አይደለም፡፡ ስለዚህ መስክ ማለት ሞስኮ ነው የሚለው ስሌትህ የተቀዣበረ ሂሳብ ነው ማለት ነው” በማለት በሚፋጅ የንግሥት ቪክቶሪያ ዘመን እንግሊዝኛ ሞልቬርን ሸንቁጠውታል፡፡
አብዬ መንግሥቱ ረጅሙን ማስተባበያቸውን ከመቋጨታቸው በፊት ለሞልቬር ባስተላለፉት መልእክት፤ “በመጨረሻም የፃፍክለት የአማርኛ ቋንቋንም ሆነ የፃፍክበት እንግሊዝኛ ቋንቋን በኋላ ያጠናሃቸው እንጂ አፍ መፍቻ ቋንቋዎች አለመሆናቸውን እረዳልሀለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ቋንቋውንና ባህሉን አለማወቅህ ብቻ ግን ሳትመራመርና ሳትጠይቅ ለሰራኸው አጉል ሥራ ጠበቃ ሆኖ ይቅርታን አያስገኝልህም” ብለዋል፡፡ አብዬ መንግሥቱ ለማ ማስተባበያቸውን ሲደመድሙም:-
መጠየቅ
 ያደርጋል ሊቅ
ተከብሮ
 ያደርጋል ደንቆሮ”
በማለት ሳይጠይቁና ሳይመራመሩ በጥራዝ ነጠቅነት አዋቂ መስሎ መታየት ከማይማን ተርታ እንደሚያስመድብ በመግለፅ ረጅሙንና ኃይለኛውን ማስተባበያቸውን ይገታሉ፡፡
ሞልቬር በዚህ ማስተባበያ ላይ አስተያየት የሰጠው ከአሥር ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ደራሲያንን ግለ ታሪክ የያዘውን (Black Lions) ወይም “ጥቁር አናብስት” የተባለ መፅሀፉን ሲያሳትም ነበር፡፡
“መንግሥቱ በሰጡት ጠንካራና ኃይለኛ ማስተባበያ ባልስማማም በነበረው ሁኔታ ከእርሳቸው ጋር በመጣጥፍ በመመላለስ ችግር እንዲፈጠርባቸው አልፈለግሁም፡፡ ግጥሙ ጥርት ያለ የፍቅር ግጥም ነው ብለው ምላሽ ቢሰጡም እኔና ገጣሚ ልባቸው ግን አንስማማም” በማለት ሞልቬር በሰጠው ትርጉም ፀንቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ግን አብዬ መንግሥቱ ለማ በህይወት አልነበሩም፡፡
(ከአዲስ አድማስ ድረገጽ ላይ ተመርጦ ለትውስታ ያህል በድጋሚ የወጣ፤ 22 ሴፕቴምበር 2012)Read 639 times