Saturday, 11 July 2020 00:00

ሞረሽ (ወግ)

Written by  በእምሻው ገ/ዮሃንስ
Rate this item
(0 votes)

   እዚህች ላይ ስለምንወጋወግበት ስለ ስም እና አሰያየም ጉዳይ ከተነሳ መቼስ “ውድነሽ በጣሙን” “ቦጋለ መብራቱ" ይሁን "በፈቃዱ አንተነህ ተስፋዬ፣" … እነዚህን ስሞች ከነማንነታቸው እንደምታውቋቸው ለማስታወስ የሐዲስ አለማየሁን ፍቅር እስከ መቃብር እስከ መጥቀስ የሚያስጉዘን አይመስለኝም፡፡
ከመግቢያው በተረዳችሁት በዚሁ በስም ዙሪያ የሚስማማውን ዘፈን ለመምረጥ ሳስብ አንዱ ላይ ለመወሰን ድፍረት አጣሁና የጂጂ (እጅጋየሁ ሽባባው፣ ስም የለኝም በቤቴ…)፤ የሂሩት በቀለ “እንቅፋት ሲመታኝ ስሄድ በጎዳና፣ ድረስልኝ ብዬ በስምህ ልጠራ" የሚለውንና በቅኔ ለአቶ ድረስ አንተነህ የተዘፈነ ነው የሚባለውን እንዲሁም ዘወትር ለየት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በዘፈን ከሽኖ በማቅረብ የሚታወቀውንና የመሰንቆው ዳኛ አርቲስት ኤልያስ ተባባል “የሀገሬ ሴቶች “በሚል አዝማች የኢትዮጵያዊያት ዕንስትን ስሞች በአብዛኛው በዜማ በመጥራትና በመደርደር፣ በአንድ ዘፈን ከድምፃዊነት ወደ “ሆም ካንትሩም ቲቸርነት ያደገበትን ዘፈን ለጊዜው የእነዚህን ብፌ ጋባዥም፣ ተጋባዥም ሆነን እና አስማምተን በቀጥታ ወደ ወጋችን እንሻገርና በስምና አሰያየም ድግሳችን እየተጎነጨን እንወጋወጋለን፡፡
ስም ለምሳሌ ከመጠሪያ አልፎ ለመተንበያነት እንደሚያገለግል በዚሁ በዘመናችን ለማረጋገጥ ይገደብ የሚለውን የአቶ አባይን ልጅ ስም ማየቱ በቂ ይመስላል፤ ትንቢት ይቀድሞ ለገቢር እንዲል መጽሀፍ:: (ማነህ ጎበዝ እዚህች ላይ አንተ እድሜ ልክህን የገደብከው የጠጅ ጎርፍ መብራት ለ”ኤሌክትሪክ” ይሆነኛል ስትል ይልቅ ለ"ሰልፈሪክ" ሆኖ አንተኑ ከእነ ቆጣሪህ እንዳያጠፋህ አስብበት)፡፡
ስም አንዳንዴ የትውልድ ዘመንን ወይም ዕድሜን ለሆነ ኦብጀክቲቭ ለሆነ ጉዳይ ለመሸወድ ኦብስታክል ነገር እንደሚሆን ነፃነት፣ ተፈሪ፣ ጠቅሌ መኮነን “አብዮት”፣ “ደርጉ” የሚሉ ጥቂት ስሞችን ለአብነት ማየት ሲቻል (እዚህች ላይ! ማነሽ! ወይዘሮ አብዮት! ባለፈው ቀን የተወለድሁት በ1974 ነው ያልሽኝን ጉዳይ ሳስበው እንዲያው ቁጥሩ ባያጣላንም ግን እንዲያው የአቆጣጠሩን ጉዳይ በሀገርኛ ነው በፈረንጅኛ? የሚለውን እባክሽ ለይተሽ አስረጅኝ?) ከአባታቸው ስም ጋር ሲነበቡ በሚሰጡት ትርጓሜ ወቅት አልፎ፣ አልፎ በመጠሪያነት ፋንታ ስጋትነታቸው የሚያይል ስሞችን ለማየትም በአለፈው ስርዓት ውስጥ አቶ በለጠ ለወለዷቸው ልጆቻቸው ያወጡላቸው “ደርጉ” “አብዮት” “መንግስቱ” “ደህንነት” የሚባሉ ስሞች በመንግስት ለውጥ ምክንያት የአራቱ የልጆቻቸውን ስያሜ በጋዜጣ አሳውጀው ለማስለወጥ አስበው፣ አሰላሰሉ፤ አንድ ብልሀት ዘየዱ፤ አቶ በለጠ፡፡ ይኸውም በልጆቻቸው አራት ስሞች ፋንታ የእሳቸውን አንድ ስም አሳውጀው አስለወጡ አሉ፤ “በለጠ”ን ወደ ቀለጠ፤ እናም ከእዳም ከስጋትም ተገላገሉ፤ አሁን “ደርጉ ቀለጠ”፣ “አብዮት ቀለጠ”፣ "መንግስቱ ቀለጠ”፣ “ደህንነት ቀለጠ; የሚባሉ እንዲሉ፡፡
የነገስታትና የመንግስታትን ስሞች ተገን አድርጎ ለልጅ ስም የመሰየምን ነገር ቴዎድሮስ፤ ዮሀንስ፤ ሚኒሊክ፤ እያሱ፤ ሃይለስላሴ፤ ጠቅሌ፤ ደርጉ፤ መንግስቱ የሚሉ ብዙ ስሞችን ባውቅም ባለፉት ሃያ ስምንት አመታት ውስጥ የወጣ ኢህአዴግ ወይም መለስ የሚባል ስም አጋጥሞኝ አለማወቁ ግን ለራሴ ይገርመኛል፡፡
ደግሞም ስም አንዳንዴ ከመጠሪያነት ይልቅ ለመጠርጠሪያነት እንደሚሆን የአንድ አብሮ አደጌ እውነተኛ ገጠመኝ ለጉዳዩ ማሳያ መሆን የሚችል ነውና ነገሩ እንዲህ ነው፡-
“ልንገርህ” የተባለው ይሄ አብሮ አደጌ፤ ወደ አንድ አገልግሎት መስጫ በአንድ ወቅት ለሆነ ጉዳይ ይሄድና ለስም መዝጋቢው ስሙን ለማስመዝገብ ይቀርባል እናም፡-
“ስምህን ንገረኝ” መዝጋቢው
“ልንገርህ” ወዳጄ
“እሽ ነገረኝ” መዝጋቢው
“ልንገርህ አልኩህ” ወዳጄ
“እኔምኮ ንገረኝና ወደዚያ ልመዝግብህ ነው ያልኩህ!; መዝጋቢው ይሄኔ ብዙ፣ ብዙ ነገር መጠርጠር ይጀምራል፤ የወዳጄን አመሉንም፣ ጤናውንም - "ልንገርህ”
“ንገረኝ?” … በመጨረሻም አጠገብ ሆኖ ይከታተል በነበረና ነገሩን በተረዳ የሶስተኛ ሰው አስረጅነት ነገሩ ተብራርቶ ጓደኛዬ “ልንገርህ; ስሙን ነግሮ ማስመዝገብ ቻለ፡፡
በስም ጉዳይ ላይ አንዳንዴ አንዳንድ ስሞች ከመለያነት ይልቅ ለመለያያነት እንደሚውሉ ለማጤን በአንድ መዝናኛ ውስጥ ተዋውቀው እየተጫወቱ እዚያው፣ በዚያው በመግባባት ስም ሲለዋወጡ በራሴ እተማመናለሁ የሚለው ወጣት ኮስተር ብሎ “ቅርጢው ጋንፉሬ; እባላለሁ ብሎ እንደ ልጅቱ አገላለፅ ስም እና እበቱን ሲለቀልቃት እግሬ  አውጭኝ ብላ ወንበር መቀየሯን ሰምተናል፡፡
አንዳንድ ስሞች ደግሞ አሉ ለማቆላመጥ ሲሞከሩ “የሚቆላመሙ” በአክብሮት ጥሪ ግዜም "አክሮባት” የሚሰሩ፤ ይህንን ለመረዳት እንዲያው እስኪ ለምሳሌ አንዱን “በድሉ” የሚል ስም አቆላምጣችሁ ለመጥራት አንዴ ብቻ ሞክሩት፤ እርግጠኛ ባልሆንም አትደግሙትም፡፡
ደግሞስ አንድ “ዳኘ” የሚባል ሰው አርጅቶ “አባ” በሚል ክብር ሊጠራ ቢፈለግ የሚባለው እንዴት እንደሆነ ከአንደበታችሁ በፊት መጀመሪያ በልባችሁ ሞክሩት፤ ከዚያ በኋላ እንግዲህ አንዳንዴ “ስም” “ስብ” ሊሆን እንደሚችልም ትረዳላችሁ ማለት ነው፡፡
ስም ትርጉሙ ከሚታወቅበት መደበኛ ቋንቋው ሲወጣ ለሰሚው ወይም ለጠሪው የሚፈጥርበትን ስሜት ለመጋራት “አባዲት” የሚለውን የትግርኛ ስም የአማርኛ አነባበብና ትርጉም እንዲሁም “ውዱ” የሚለውን የአማርኛ ሸጋ ስም "ሁዱ" ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ጋር ያለውን የድምፅ አንድነትና የኦሮምኛውን ትርጉም ማየቱ በቂ ሲሆን በአነሳነው ምሳሌ መሰረትም ለአቶ ውዱ በአማርኛ ስሙ ሲሆን በኦሮምኛ ደግሞ ስድቡ ይሆናል ማለት ነው:: (እዚህች ላይ ማነህ ውዱ የኔ ጌታ፤ ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል እንጂ እኔ አንተን እንደ ስምህ ውድድ ነው እማረግህ)፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የአደባባይ ስሞች የሚባሉ ስሞችን ቢያንስ በአባት እያገናኙ ሰዎችን እያዛመዱ ማስተሳሰር እንዴት እንደሆነ በተለይ ክፍለ ሀገራት ላይ ቅድመ እውቅና እና እውቅና ካላቸው የአደባባይ ስሞች መካከል የሙዚቀኛ ስሞቹ ነፃነት፣ ዳዊትና አበበ የአንድ የአቶ መለሰ ልጆች ሲሆኑ ማለፊያ፣ አበበ እና ተመስገን ደግሞ የእናታቸውን እንጃ እንጂ በአባታቸው ግን ወንድማማች እና እህት ናቸው፤ የአቶ ተካ ልጆች ማለትም እንደ ፍቅርአዲስ እና ጌራወርቅ ከደግአረገ ጋር የአያ ነቅአ ጥበብ ልጆች መሆን ማለት ነው፡፡ በስነ ጽሁፍም ቢሆን ያው ነው፤ በዚህ ታናሽና ታላቅ በማይለይበት የማዛመድ ህግ (ጎበዝ ማነህ፤ እዚህች ላይ ሁል ግዜ ታላቅና ታናሽ ሲባል አብሮ በአይን በአይንህ የሚሄደው “ሽንጥ” ከእንግዲህ እሴት ልጅ ወገብ ላይ ካልሆነ በአይንህም እምታየው አይመስለኝምና በግዜ ቬጅቴሪያን ብትሆን ይመረጣል) በአሉ እና ሌሊሳ የአቶ ግርማ ልጆች፡፡
በአንድ አባት ልጅነት ጉዳይ ከሰዎች አልፈን ሀገራትንም ብናይ፣ የአቶ ያ ን ልጆች የሚያህል የለም፤ ከሀገራት መካከል ለምሳሌ ማየት ቢያስፈልግም ከእኛው ለመጀመር ኢትዮጵያ፣ ቀጥሎ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ማሌዥያ፣ ራሽያ አውስትራሊያ፣ ቡልጋሪያ፣ ላይቤሪያ፣ ሳይቤሪያ (የማነህ ጎበዝ ወርልድ ማፕን ጠጥቼዋለሁ ስትለኝ የነበረው፤ ለነገሩ እኔ እንኳን አጣጥመህ የጠጣህውና ከትንፋሽህ ዘወትር የሚቆርጥልህ የአለም ካርታ ሀገሮች ሳይሆን የግብጦ፣ የነጭ ሽንኩርት፣ የኮሶ፣ የማር፣ የጤናዳም፣ የጥይት፣ …..አረቄ ሁሉ እንዳልተረፈህ ነው፡፡
ከሀገራችን ከተሞችም ቢሆን የአቶ “ሌ”ን ልጆች የሚያህል አይኖርም፤ እህትማማቾቹ እነ ባሌ መቀሌ ሰገሌ ሞላሌ ሲሉ ሰምተህ በባሌም በመቀሌም ብዬ ውጭ እወጣለሁ ስትለኝ የነበረው በባሌ እንኳን እኔጃ የመቀሌው ምናልባት አዲግራትና ዛላንበሳ ውጭ ሀገር ናቸው ትል እንደሆን እንጃ፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ስም እንደ ክፉ አድራጊ በከንቱ ሊያሰጋ እሚችል መሆኑን ለማየትም አሸባሪነትን ለማጥፋትና ደምስሶ ለማደር ስንትና ስንት ስልቶች ሲታቀዱበትና ሲዘየዱበት የሚውሉበት “አዳራሽ” ውስጥ ያውም አሸባሪነትን የማጥፋት ስልት ቅየሳው አካል ሆኖ መልሶ ራሱ “አሸብር” የሚል ስም ይዞ መገኘት እንዴት ላይከብድ ይችላል (ጎበዝ ማነህ አንተ አብሮ አደጌ፤ “ፀጉር ቆራጩ አሸብር ለማንኛውም ይሄ አሸባሪነትን ለማጥፋት የሚቆፈረው ጉድጓድ ካልሞላ ቀጥሎ ለማሟያ እንዲሆን “አሸብር የሚባሉ ስሞች ይግቡበት" ሊባል እንደሚችል “ዝሆኖች ይታደኑ ሲባልና ዱሩ ሲሸበር ሰምታ ከፊት፣ ከፊት ስትበር ያገኟት “ወ/ሪት ጥንቸል ደግሞ አንች ምን ሆነሽ ነው ዝሆኖች ለሚታደኑ እንዲህ ልብሽ እስኪፈርስ እምትሮጪ?" ቢሏት እስኪጣራ ማን ይጉላላል ካለችው ጥንቸል የምትማረው ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡
ስም በአወጣጡ ከማዕረግ ጋር እንዴት እንደሚጋጭ ለማየት በእውነቱ ሻምበል ብለው ስም ያወጡለት ወታደር፤ ሻምበልነት ቢሾም እንዴት ተብሎ ይጠራል፡፡
በሰራዊቱ ውስጥ ሲያገለግል የ”ባሻ”ነት ማዕረግ የመጣለት ወታደር “ሆዴ” ሲጠራ እንዴት ተብሎ ነው (ማነህ! ጎበዝ አንተ በበነነ በተነነው ሆድ የሚብስህ “ባሻ” የሚለው ማዕረግ የመጣው ካንተ ፀባይ ነው መሰል፤ ሌላው ደግሞ ስም በአጠራር ግጥምጥሞሽ ምን ያህል እንደሚሄድ ለማስተዋል የታዋቂው ድምፃዊና የሙዚቃ ሰው የአቶ እሳቱ ተሰማ “አትንኩት” እና “ይፋጃል” የሚባሉ ልጅና የልጅ ልጅ አላቸው ሲባል ሽው ያለኝ ያልተጣራ ዜና እውነት ከሆነ፣ በእኔ በኩል የአቶ አትንኩት ልጅ አጓጉል ተብሎ እንዲጠራ ሀሳብ አቅርቤአለሁ፡፡ እዚህች ላይ ማነህ የክቡር አርቲስት ልጅ አትንኩት ምናልባት ማስጠንቀቂያውን ጥሼ አጓጉል ነክቼህ ከሆነ፣ ይሄው ይቅርታ ጠይቄያለሁ)፡፡
እንዲሁም የረጅም አመታት የቅርብ ወዳጄ የሆነው ዳር እስከ ዳር ሞላ ተረፈም ቀጥሎ የሚወልደው ልጁን ግድቡ ብሎ ቢጠራው ደስታዬን አልችለውም፡፡
ከቅፅል ስምነት ባሻገር ልጅን ከብርጭቆና ሲኒ ባነሰ ስሜት፤ “ቡጢ” “ጡጢ” “ዙጢ” እያሉ መጥራቱ በራሱ ምን ለማለት እንደሆነ ባይገባኝም “አቶ ቡጢ” እና “ወ/ሮ ዙጢ” ለባለስሞቹ እስከሚገባኝ ድረስ “መጠሪያቸው” ሳይሆን ማጠሪያቸው ነው፡፡ (ማነህ ጎበዝ እንዲህ በየግሮሰሪው ሰርክ ለምትቀመቅመው ጠርሙስ ቢራ የምትመዥርጠውን ቀያይ ባውንድ ሳይ፤ ለልጅህ ስም ግን ያውም በነፃ ከባዶ ጠርሙስ ያነሰ ስም እንዴት ታወጣለህ?)፡፡
ሲጠሩትና ሲጠራ ሲሰሙት ምናልባትም የቴሌግራም እና ሞባይል አጠቃቀም ታሪፍን ታሳቢ ተደርጎ የወጣ የሚመስለኝ እና አቶ ምሳሌ ለልጃቸው ያወጡት “ለ” የሚባል ባለ አንድ ፊደል ስሞች፤ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ለከተሞች መጠሪያነት ሲያገለግሉ በእግረ መንገድ እንዴት ለማስጠንቀቂያ ማስገንዘቢያነት እንደሚውል ለማዬት “ዳንግላ” በአገውኛ “ሌባ የለም”፣ “ቡታጅራ” በኦሮምኛ ሽፍታ አለ እና አሁንም “ወልቂጤ” የርቀቱ አጋማሽ ከሚሉ ስያሜና ትርጓሜአቸው ጋር እነዚህ ይበቃሉ፡፡ (እዚህ ላይ ማነህ ጎበዝ ኑሮ መሮኛልና መሸፈቴ ነው እያልክ ታስወራ ነበር አሉ፤ ወንድሜ እኔ በፍላጎትህ ጣልቃ መግባት አልፈልግም፤ ነገር ግን ለአሰብከው አላማ ምናልባት “ቡታጅራ”ን ከመረጥህ አንተን ጠቁሞ ለማስያዝ አገሩ ብቻውን በቂ መሆኑን ጠቆም ላደርግህ እወዳለሁ)፡፡
ከስም አወጣጥ መሀከል ግርም የሚለው ደግሞ ችግር ቢፈጠር እንኳን ትልልቅ ሀገሮችና ፓርቲዎች ሳይቀር በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይተው በሚፈቱበት ሁኔታ እስኪ ለልጅ በላቸው እና ድፋባቸው የሚባሉ ስሞችን ማውጣት ለማን ሀርድ ለመስጠት ነው? (ጎበዝ ማናችሁ ወንድሞቼ እነ በላቸው ለእኔ እንደገባኝ ይሄ የስማችሁ ትርጉም እያደር መፈሪያችሁ ሳይሆን ማፈሪያችሁ እየሆነ ነውና እባካችሁ ከሀፍረት ለመውጣት በግዜ መላ ምቱ፡፡ አንተ ደመላሽስ ብትሆን ደግሞ የመቼው የሳይንስ ሰው ሆነህ ነው በፕሉምናሪ ቬን ተሰይመህ መማሪያ የሆንከው? “ደሜ” ለማንኛውም ለአንተ ብዬ ነው እንጂ እምቢ ካልክ ባዮሎጂን በአማርኛ ብዬሀለሁና አርፈህ ደምህን አመላልስ፡፡
አንዳንድ አካባቢ የተለያዩ ስሞች ለቅፅል መጥሪያነት ሲውሉም የሚያመጡትን የትርጉም መፋለስ በጥቂቱ ለማየት ደግሞ አዲስ አበባ ወይም ሌላ ቦታ አንድ ወጣት በከባድ ሚዛን ስድብነት የሚያውቀውን ውሻን ወደ ባሌ ሮቤ እና ጎባ ብቅ ብሎ የፍቅር መግለጫ የሆነውን የእኔ ውሻ መባል ቢያጋጥመው ነገሩ እስከሚገባው ድረስ ቢያንስ በቅሬታ ፊቱ ቅጭም ማለቱ አይቀርም (ውድ ባሌዎች በዚህች አጋጣሚ የሰው ልጅ ባለውለታ የሆነውን እንስሳ የፍቅር መግለጫ በማድረጋችሁ ወድጃችኋለሁ እናም ሁላችሁንም ቅቤ ካሳበደው  ጭኮ እና ቡና በወተታችሁ ጋር ይህንን ሚስተር ኮፊ አናን ሳይሰሙ ሰላም ብያችኋለሁ፤ የዲንሾን ቆሎ ሳልዘነጋ ማለት ነው)፡፡
በሀገራችን የስም አወጣጡ የኢኮኖሚ ግሽበትንና ምንዛሬን ከግምት እንደሚያስገባ ለመገንዘብ ደግሞ በልጅነታችን እነ ሺብሬና ሚሊዮን የሚባሉ ብዙ አብሮ አደጎች የነበሩኝ ሲሆን አሁን፣ አሁን እንዲህ የሚባሉ ስሞች ከቦክስ ኦፊስ ከወጡ ወዲህ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱን እና የብር ቅለቱን ተከትሎ ለልጆቻቸው “ቢሊዮን” እና “ትሪሊዮን” የሚባሉ መጠሪያዎችን የሰየሙ ወላጆች አላገጠሙኝም:: (በዚህ አጋጣሚ አብሮ አደጎቼ ሚሊዮንና ሺብሬ እባካችሁ ተገናኝታችሁ ተደራጁና አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ሁኑ)፡፡
እንግዲህ ለተረፈው ቀጠሮ ይዘን ለዛሬ ከመሰነባበታችን በፊት የሁላችሁንም ስም ተዋውቄ ለመጥራት እንደ ኤልያስ ተባባል ትእግስቱም፣ ጉልበቱም፣ የለኝምና የሚወዱትን ሰው፣ የምስጢር ወዳጅንና ሁነኛ ዘመድን በሽፍንፍን ለመጥራት እንደ ጎጃሞች እኔም “ሞረሽ” ብዬ ልሰናበት፡፡


Read 700 times