Saturday, 11 July 2020 00:00

የኢትዮጵያ ጠቢባን ለሕዝብ ትስስር ያበረከቱት አስተዋፅኦ

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

 ስለ ሕዝቦች ህላዌ ተግተው ከጻፉ የኢትዮጵያ ደራስያን መካከል የሁለት ባህሎች ውጤት አካል የሆነው፤በኦሮምኛ አፉን የፈታውና አማርኛንና ግእዝን በልጅነቱ ተምሮ ያቀላጠፈው ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን ፤ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ፤ ከሕንዳዊ አባቱና ከኢትዮጵያዊት ኦሮሞ እናቱ የተገኘው  ታላቁ ደራሲ፤ ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ የነበረው በዓሉ ግርማ፤ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ--- ለአብነት ያህል ይጠቀሳሉ፡፡
ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን  ሮባ፤ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ስለሆነው ሕዝብ ሕይወት፤ ታሪክ ባህልና ቋንቋ፤ ማንነት፤ የት መጤነት--- ላይ በመንተራስ ውበት በተመላበትና  ጥልቀት  ባለው ብእሩ በ“እሳት ወይ አበባ” እና በሌሎች የቴአትር ሥራዎቹ (ኦቴሎ፤ የከርሞ ሰው፤ የእሾህ አክሊል፤ ሀሁ በስድስት ወር፤ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት) ስለ ዓፄ ተዎድሮስ፤ ስለ አዋሽ ወንዝ፤ ስለ ዐድዋ --በገጠማቸው ግጥሞቹና በተቀኛቸው ቅኔዎቹ መልእክት በሕዝብ አእምሮ ውስጥ ለዘለዓለም ሲታሰብ ይኖራል፡፡ ሎሬት ጸጋየ በተለይ የገጣሚነቱ ዋጋ እጅግ ከፍ ብሎ በታየበትና በጎላበት በ”እሳት ወይ አበባ” ድርሰቱ (1966፤23) «ይድረስ ለወንድሜ ለቤጌምድር ወይጦ ባላገር፤ እምታውቀኝ አማላውቅህ  ማነህ” ብሎ የገጠመው ግጥም የኢትዮጵያን ኅብረ  ብሔር ሕዝብ ከምሥራቅ ዳር አገር  እስከ ምዕራብ፤ ከሰሜን ጫፍ  እስከ ደቡብ ኅዳገ ወሰን በስማቸው የሚያነሣሣና የተረሳው ማንነታቸውና ሥራቸው ጎልቶ እንዲወጣ፤ አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ፤ ከታሠሩበት የሐሳብ ሰንሰለት እንደፈቱ፤ከገቡበት የአርምሞ ዓለም እንዲወጡ፤ እንዲታወቁ የሚቀሰቅስ ሥራ ነው፡፡
ሎሬት ጸጋየ  የቋንቋ ውበትና ወኔ በታጠቀው ብዕሩ ከጠረፍ እስከ ከተማ በልዩ ልዩ ምክንያት ተራርቆ፤ተለያይቶ የሚኖረው ሕዝብ እንዲቀራረብ፤ባህል ለባህል፤ ቋንቋ ለቋንቋ እንዲግባባ፤ ወዝ ለወዝ እንዲላመድ፤ ትንፋሽ ለትንፋሽ እንዲዋዋጥና፤ ግንባር ለግንባር ተገናኝቶ እንዲነጋገር፤ እንዲተዋወቅ፤ ማንነቱ፤ ምንነቱ እንዲጎላ፤ የሥልጣኔ ተቋዳሽ እንዲሆን፤ ከመናናቅ ወደ መደናነቅ እንዲሸጋገር ሥጋ ለሥጋ እንዲወሐድ፤ በዘመኑ አጠራር ለብሌኑ፤ ለከረኑ፤ ለአኙዋኩ፤ ለገለቡ፤ ለአገውና ለሽናሻው፤ ለቅማንቱና ለፈላሻው፤ ተንቆና ተዋርዶ ለሚኖረው ለቆለኛውና ሸክላ ሠሪው፤ ለቦረኑ፤ ለሶማሌው፤ ለደናክሉ፤ ለአፋሩ፤ ለከምባታው፤ ለኩናማው፤ ለራያው መራራቅ መኳረፍ ይቅር፤ የሚገድበን ኬላ  ይሰበር ብሎ ጠንካራ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡
 ሎሬት ጸጋየ በ”እሳት ወይ አበባ” (51) ስለ ቦረን ሊበን ኦሮሞዎች ጀግንነትና ቀረርቶ፤ አውራሪስ ገድለው ስለሚጥሉት ግዳይ በማለፊያ ብዕሩ ግጥሙን ይደረድራልናል፡፡
ዳምበል አባ ገናሌ--
እኔ የመቅሰፍት እጁ
ከነጎልማሳ ልጁ
ተግ ሲል እንዳየሁት
በገዛ ደሙ አጠብኩት
ስመለስ ቀን ሳይነጋ
ብቻውን ካውሬ መንጋ
ጥንድ አውራሪስ አድፍጦ
ቢጋፈጠኝ አፍጥጦ
በከረዩ ሴት ኩራት
አልኖር ብዬ በጥቃት
ቤቴን በረቴን ትቼ
ሎጋ ጦሬን አንግቼ
በዳምበል ስም እንደማልኩ
ኮርማ አውራሪስ ተንተራስኩ፡፡
ሸንቃጣው ግዳይ ጣሌ
ዳምበል አባ ገናሌ!
ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን በ”እሳት ወይ አበባ” ግጥም መክፈቻው ከሰው ዘር በልቡ መቅረዝ ላይ የሚያበሩትን  የቤጌምድርን ወይጦ ከመዘከር ጀምሮ አበራ በነበርን፤ካሣ ተሰማን፤ ኢታፋ ቃላጋን፤ አሥመሮም ለገሠን፤ ጋማቹ ቃማሊቲን፤ ተፈራ ደግፌን፤ ፈረደ ዘሪሁንን፤ ጎሮምቲ ቱሉ ዳኛን፤ አቡነ ጴጥሮስን፤ ኤድዋርዶ ሞንድላኔን፤ አሳምነው ገብረ ወልድን፤ የኔታ አስረስ የኔሰውን፤ ክበበው አሻግሬን፤ ዘውዴ ሽዋሞልቶትን፤ ዓለማየሁ ቴዎድሮስን፤ ያወድሳል፡፡ የሸቀጥና የግርግር ዐምባ የሆነቺውን መርካቶን፤ እንዳ ሥላሴን፤ ዓድዋን፤ ቢሾፍቱን፤ አዲሳባን በተደጋጋሚ፤ ዋልዲያን፤ አምቦን፤ ፒያሳን፤ አዋሽን፤ ደብረብርሃንን፤ ተከዜን፤ ድሬዳዋን፤ ስድስት ኪሎን፤ ጂማን፤ ሐረርን፤ አዳማን፤ ያነሳል ያወሳል - በግጥሙ፡፡ በመስከረም ወር የሚፈካውን መስቀል አደባባይን፤ ማይጨውን፤ ኮልፌን፤ ጋርባ ጉራቻን፤ መቀሌን፤ ደሴን፤ ሎንዶንን፤ ዳሬ ሰላምን፤ ቤልግሬድን፤ ፓሪስን፤ ኒው ዮርክን፤ አሥመራን በቅን ልቦናው ሥሎና በጥበበኛ ብዕሩ ኩሎ ለሰው ልጅ፤ ለመልክዓ ምድራችንና ለዓለማችን ሁሉ ያለውን ፍቅርና አክብሮት  ያሳየናል፡፡ በተመሳሳይ በዓሉ ግርማ “”አድማስ ባሻገር” በተባለውና በተወደደው ድርሰቱ  ከአንድ የኦሮሞ ገጠር ቤተሰብ የተወለደችና ስሟን ሉሊት አሰኝታ አዲስ አበባ ውስጥ በውበቷ፤ በቁንጅናዋና በፍቅራ ሰውን ሁሉ ስታማልልና ጠይም ጣኦት እስክትባል ድረስ ስታንበረክክ ያስነብበናል “ሐዲስ” በተሰኘው ድርሰቱም ስለ ስለ ሱጴ ቦሮ ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ያስቃኘናል፡፡
በሐዲስ ዓለማየሁ “ወንጀለኛው ዳኛ” እንዲሁ ስለ ሱሉልታዋ ኩበት ለቃሚ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ስለሚገኙ የኪ ሕዝቦች  ማኅበራዊ እንቅስቃሴ፤ ስለ ቀኛዝማች ፍሪሳ ሕይወት በሰፊው ያስቃኙናል፡፡ ስለ ሀገራችን ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሥሉጥነትና አብሮነት  የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን ከሠሩ ደራሲዎቻችን ውስጥ ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ አንደኛው ተጠሪ ነው፡፡ ፍቅረ ማርቆስ በወርቃማ ብዕሩ እያሰሰ ወደ መድረክ ካመጣቸው የሀገራችን ሕዝቦች ውስጥ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩት ሐመሮች፤ ዘይሲዎች፤ ኪዎችና ኤልቦሬዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከሥራዎቹ ውስጥ “ኢቫን ጋዲ”፤ “የዘርሲዎች ፍቅር”፤ “አቻሜ”፤ “ከቡስካው በስተጀርባ” የሚሉት በምሳሌነት የሚታዩ ናቸው፡፡ እንደዚሁም በእንግሊዝኛ “Land of the Yellow Bull,” የሚል ልቦለድ ድርሰት የጻፈ ሲሆን ይኽም ሥራው ስለ ሐመር ኪዎና ኤልቦሬ ሕዝቦች ማኅበራዊና ተፈጥሯዊ ሕይወት የሚያትት ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በ2002 «ሕያው የጥበብ ጉዞ ወደ ቡስካው በስተጀርባ ድንግል ውበት አገር» በሚል መሪ ቃል ከ56 በላይ የሆኑ የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን፤ ተመራማሪዎችንና ጋዜጠኞችን ይዞ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ጥበባዊ ጉዞ ባደረገበት ወቅት “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች አምባሳደር” የሚል የክብር መጠሪያ የተሰጠው ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ፤ “ከቡስካው በስተጀርባ” በሚለው ድርሰቱ እንደነ ከሎ ሖራ፤ እንደነ ኸርለት፤ ጎይቲ አንተነህ በመሳሰሉ አዳዲስ ገጸ ባሕርያት የሐመሮችን ሕይወት፤ ፍቅር፤ ደግነት ከአውሮፓና ከመኻል ኢትዮጵያ ወደ አካባቢያቸው ለጥናትና ለሥራ ከሄዱ ሰዎች ጋር የድንግል ውበት ባለቤቶች የሆኑት ሐመሮች እንዴት ኅብርና አንድነት ፈጥረው እንደሚኖሩ ጥበብ በተሞላበት ብዕሩ አግዝፎ አሳይቶናል፡፡ “ኢቫንጋዲ” በተሰኘ ሥራውም ተወዳጅነትና ሳቢነት የተሞላበትን የሐመር ወጣቶች  የጨረቃ ምሽት ዳንስ ምንነት ከነ ሥነ ሥርዓቱ እንድንገነዘብ  ብርሃን ይፈነጥቅልናል፡፡
ደራሲ አንዷለም አባተ (ያፀደ ልጅ) በበኩሉ፤ ስለ መኤኒት ብሔረሰብ ባህልና ታሪክ፤ አብደልፈታሕ አብደላህ ስለ በርካታ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአስተዳደር ሕግና ባህል የሚያትቱና በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረቱ መጻሕፍትን ጽፎ አስነብቦናል፡፡ ደራሲ ሔኖክ ሥዩም ደግሞ ስለ ደቡብ ሕዝቦችና ስለ ጎንደር የሚያወሱ፤ የጉዞና የመንገድ በረከቱን እነሆ ብሎናል፡፡ “ወዮ ሐረማያ” የሚለው የአበባው መልአኩ ግጥምም የሀገራችን የተፈጥሮ ሀብት እየተመናመነ መሄዱንና ለሐረማያ ሐይቅም ሆነ ለሌሎች መስህቦቻችን  ጥበቃና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ያስረዳናል፡፡ እኔም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ  የኪነ ጥበብና ባህል ገጽ አዘጋጅ በነበርኩበት ጊዜ በየሳምንቱ ለማቀርበው ሥራ መረጃ ለማሰባሰብ በ1991 ዓ.ም ወደ ሰሜንና ደቡብ ኦሞ፤ ዐርባ ምንጭና  ጂንካ፤ ሐመርና  አካባቢዋ  ሄጄ በነበረበት ጊዜ “መንጊ” (የተረገመ) በሚል በጥርስ አበቃቀላቸው ተገልለው በሐመር ጫካ ውስጥ ስለሚጣሉት ሕጻናት ሕይወት የሚያትት “የጫካው ልጅ” የተሰኘ ልቦለድ  በኢትዮጵያ  ጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናት ወዳጆች ማኅበር አሳታሚነት  ለንባብ በቅቷል፡፡
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ረገድ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍል ስለሚኖረው ሕዝብ ደግነት፤ውበትና የፍቅር ሕይወት፤ስለ ሀገራችን መልክዓ ምድራዊ ማራኪነት ሙዚቃ ያቀነባበሩና በማራኪና በሚያማልል ድምጻቸው ያንጎራጎሩ ከየብሔረሰቡ የወጡ የኢትዮጵያ ዘፋኞች ብዙ ናቸው፡፡ ስለ ሀገራችን ውበትና መልክዓ ምድር ካቀነቀኑት ውስጥ ለአብነት  ድምጻዊው ኢዮኤል ዮሐንስ ይጠቀሳሉ፡፡
“በየቦታው ዞረን እኛ እንዳየናቸው፤
የኢትዮጵያ ግዛቶች የተዋቡ ናቸው--፡፡” እያለ ሀገሩን ሲያወድሳት
ሌላዋ ዘፋኝ
“ሀገሬ ኢትዮጵያ ተራራሽ አየሩ፤
ፏፏቴሽ ይወርዳል በየሸንተረሩ ልምላሜሽ ማማሩ”
እያለች ስለ አበቦቹ መዓዛ፤ ስለ ወንዞች፤ ተራሮችና ሜዳዎች ውበት አንጎራጉራለች፡፡ ሌላው ዘፋኝም (ምናልባት አያሌው መስፍን) ስለ ሐረር ውበትና የተፈጥሮ ሀብት  
“ልምላሜሽ ያምራል በጥበብ ፍሬ
ታምሪያለሽ ገና ሐረር ሀገሬ
ያታክልት ዓይነት የሞላብሽ
ውቢቱ ሐረር እንደምን ነሽ፡፡
ሐረር ተወልደን ሐረር አድገናል
መልካም ፍሬሽን ተመግበናል፡፡” እያለ ውዳሴውን ደርድሯል፡፡
አበበ ተሰማ በበኩሉ፤ የሽዋ ኦሮሞ ስለሆነቺው ወጣት ውበት “ሐሪ መሩ መሩ የሽዋየ ሐሪ መሩ መሩ---» እያለ በመዝፈን አድናቆቱን ሲገልጽ፤
ተሾመ አሰግድ እንዲሁ
“የሰላሌዋ ያባብላል ጎፈሬዋ
ሽንጥና ዳሌዋ ከወደኋላዋ”ን ዘፍኖልናል፡፡
ዓለማየሁ እሸቴ፤
“ኮቱማ ፍቅሬ ምንድን ነው ጥላቻ
ፍቅር የጋራ ነው አይደለም ለብቻ፡፡”
ጥላሁን ገሠሠ፤
“አሻሚ ያደማቴ---
ሰላማካ ያገኔ ሰላማካ
ሀርከፉኒያ እሜቴ ሰላማካ
እሽሩሩ ያገኔ እሽሩሩ--”
“የሸጊቱ ሱታ ሱታ ሱታ
ፍቅሬ ናደማሉታ” በሚለው የኦሮምኛ ጨዋታውና ሙዚቃው ሕዝብን ሲያስደስት ኖሯል፡፡
መልካሙ ተበጀ፤
“አዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁሽ
የሲዳሞ ቆንጆ እንዴት ነሽ”
በሚለው ሥራው የሲዳሞዋን ቆንጆ ውበትና ፍቅር አሳይቷል፡፡
አሊ ቢራ እንዲሁ (ከሔለን በርሔ ጋርም) ስለ ሐረር ኦሮሞ ቆነጃጅትና ስለ ሀገራችን ውብነት በርካታ ጨዋታዎችን አቅርቧል፡፡ ለአብነትም፡-
እሽሩሩ ሩ ያብርቱካንዮ
ዳማዋላላ ሀርኬፉያንጋላ፡፡
ማዲንጎ አፈወርቅና ብርሃኑ ተዘራ “ሰላም ያገር ሰው” ቴዎድሮስ ካሣሁን፤ ስለ ሐረር ወጣት፤ ስለ ኤርትራና ኢትዮጵያ “ዳህላክ ላይ ልሥራ ቤቴን”፤ በቅርቡ ያጣነው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ “ማሊ እንጅራ” (በአድዋ ጦርነት የኦሮሞ ጀግኖች ስለፈጸሙት ተጋድሎና በሌሎች ሥራዎቹ)፤ ያሬድ ነጉ ስለጉራጌና ጎጃም ጋብቻ፤ መስፍን አበበ “ሽዋ ላይ ባስጠይቅ--” የሚልና የመላ ኢትዮጵያን ቆነጃጅት ውበት የሚያደንቅ፤ ፀሐየ ዮሐንስ  ስለ ወላይታ ባህላዊ ዘፈንና ስለ ትግርኛ ጨዋታ፤ ነዋይ ደበበ ስለ ጂማና ጉራጌ ባህል፤ አስቴር አወቀ ስለጉራጌና ጎንድር ባህል፤ ሐመልማል አባተ እና ወጋየሁ ደግነቱ (ሐርኬ የጉማ) ስለ ሐረር ኦሮሞ አዚመውልናል፡፡
በሥነ ሥዕል ረገድ በርካታ ሠዓልያን በብሔረ ሰሞች ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን የሠሩ ባለሙያዎች በእጅጉ የበዙ ናቸው ለምሳሌ ሠዓሊ ለማ ጉያ አዘውትሮ ስለ ደናክል ልጃገረድና ስለ አጎጠጎጡ ጡቶቷ፤ ሠዓሊ አለቃ የማነ ብርሃን ተንበሌ ስለ አቆርዳት ግመል ነጂዎች፤ ሠዓሊ ሕዝቅያስ ተሰማ ስለ ጉራጌ ጭፈራ፤ ሠዓሊ አጥላባቸው ረዳ ስለዘላን ሕይወት፤ ሠዓሊ ግርማ አገኘሁ እንግዳ ስለ አደሬዋ፤ ሠዓሊት ማኅሌት ወርቁ ስለ ዐፋር ሰዎች፤ ሠዓሊ ታደለ ማመጫ ስለ የዐፋር ሰው፤ ሥለውልናል፡፡ ታየ ታደሰ (አንዳንድ ኢትዮጵያ ሠዓሊዎች አጭር ታሪክ 1983)፡፡ በፊልም ረገድ  “ጸማኮ”ን ጨምሮ  በብዙ ብሔረ ሰቦች ሕይወት ዙሪያ የተቃኙ በርካታ ሥራዎች ለዕይታ መቅረባቸው ይታወቃል፡፡


Read 709 times