Saturday, 11 July 2020 00:00

ማራኪ አንቀፆች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  እንባቆም፡- ጉዳት ወይም ችግር አግጦ በራሳችሁ ላይ ሲደርስ ይነዝራችኋል፤ የሌላ ሌላ ግን የገለባ ያህል አይከብዳችሁም…ያም ሆነ ይህ ጦርነት እጅግ አክሳሪና ውድ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ማጤን አለባችሁ… የቀደመ ታሪክ ማስታወስም ይበጃል፡፡
አባ ዘዮሐንስ፡- ለመሆኑ ለግብጽ አጀንዳ መንግሥታችን ምን መለሰ?
አዱኛው፡- በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር ቀዳሚ ጠጠር ወርዋሪ አይሆንም፤ ግብጽም ግድቦች አሏት፤ ጦር ስታወናጭፍ ለነሱ ምን ዋስትና ሰጥታ ነው? ሌላው ግብጾች ካላበዱ በስተቀር ወደ ጦርነት አይሄዱም ነው የተባለው… ውጤቱን ያውቁታላ!
በኃይሉ፡- ከባዱም ዓለም አቀፍ ህክምና ይቀርብላቸዋል፡፡
እንባቆም፡- አባይ የለም ግብጽ የለም የሚለውን ፈሊጥ ገልጠን ብናየው፣ ለማስፈራራትና የግብጽን ህዝብ በኢትዮጵያ ላይ ለማነሳሳት ብቻ ነው… ሌላው አስቂኝ ጩኽታቸው ግብጾች እውን ላንዲት ጠብታ ውሃ ከዓለም ላይ ይጠፋሉ? የግብጽን ያህል ውሃ ሳያገኙ የሚኖሩ ምድረ በዳነት የበዛባቸው ሀገሮች የሉም… አሉ /ጭብጨባ/
ደሌቦ፡- ከአባይ ላይ ጠብታ ውሃ አይቀነስም ይበሉ እንጂ እዚያው ሀገራቸው ውስጥ ከአስዋን ግድብ በትነት የሚጠፋ ውሃ መጠን በሚሊዮናት ኪዩቢክ ሜትር የሚለካ በየዓመቱ ይባክናል፤ ገልጠን ብናየው አባይን ደግሞ አድራቂዋ ሌላ ሳይሆን እራሷ ግብጽ ነች፡፡
እንባቆም፡- በሌላ በኩል፤ የህዳሴው ግደብ ከተሰራ በኋላ ወደ ግብጽ አልፎ የሚያጥለቀልቃትን ውሃ መጠንና ደለሉን በመቀነስ የጠራ ውሃ እንድታገኝ ለመከላከያው የምታወጣውንም ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ኪሳራ ይቀንስላታል፡፡
ደሌቦ፡- እናም ከኢትዮጵያ ያልተናነሰ ጥቅም ታገኛለች ማለት ነው እኮ… ሀቁ!
እንባቆም፡- (ፋታ) ውድ ተሰብሳቢዎች፤ ዳውድ እስካሁን ሲያወጋን የነበረው ፖለቲከኞቻቸው የሚያላዝኑትን የውሸት ጩኸት ነበር፡፡ የሱ ሙግትም የነሱ የመከነ ፖሊሲ ዜሮ ሳም ሜንታሊቲ ወይም አልቦ ድምር አስተሳሰብ ነጻብራቅ ነበር /ጭብጨባ/ እና ዳውድ ዋሽቼ ከሆነ አጋልጠኝ፡፡
ዳውድ፡- /ከሊፋ ጋር ተነጋግሮ ቀድሞ መልስ ይሰጣል/ ወንድሜ ሆይ እንዲሁም አባቶቻችን… ወደ ሃቁ እንምጣ፤ ሃቅ ያንቃል ይባላል /ፋታ/ እስካሁን በናንተ በኩል የተወረወረውና የኔም ልብ የሚያስበው  የግብጽ አዲሱ ትውልድ  በሆሆታና በጋጋታ… በኡኡታ ጠብ ያለሽ በዳቦ የሚነዳ አይደለንም /ጭብጨባ/ ከእንግዲህ ወደፊት የሚያራምደን ሳይንስና አመክንዮ፣ ነባራዊ እውነታ እንጂ የምናብ ከንቱ ፈጠራና ስጋት አይሰራም፤ከአዲሱ ትውልድ መፈጠሬ እድለኛ ነኝ /ፋታ/ ሌላው ነጥብ፣ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይቀነሳል ተብሎ የሚታሰበው የአባይ ውሃ መጠን እጅግ የሚገርም ነው፡፡ የአባይ ውሃ ጠቅላላ መጠኑ ከ80 ኪዩቢክ ሜትር በላይ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለህዳሴው ይቀነሳል የሚባለው ከ3-4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ነው፤ የጠብታ ያህል! ተመልከት እንግዲህ… እዚህ ግባ ለማይባልና ከቁጥር ለማትገባ መጠን… ለዚያውም ጥቅሙ የጋራ የሆነ ፕሮጀክት… ግብጽን ከቶም የሚያሰጋት ሊሆን አይችልም፣ ታዲያ ጉዳዩን ጠልቀን ሳንረዳ በርግገን ማስበርገግ ባልተገባ… አሁንም ሌላ ነጥብ የማነሳው ኢትዮጵያ በጣም በጣም ታጋሽ እናት ሀገር ነች /ጭብጨባ/ እኛ ብንሆን… የምሬን ነው የምናገረው ከስኩዊዝ ካናል ያልተናነሰ የአባይ ፈሰስ ወይም ቀረጥ እናስከፍላችሁ ነበር … በውነቱ የኔ ትውልድ ነቅቷል፤ ኋላ ቀር ፖሊሲ በሚያራምዱ አንድ አንድ ወግ አጥባቂ ብዥታም ባለስልጣናት ፈር የሳተ አመለካከት ብለን እሳት አንጭርም፤ አቃጥለን አንቃጠልም ! /ጭብጨባ/ ከእንግዲህ እኛ የአባይን ሸለቆ  ለልማት ማረስ እንጂ  በአንጡራነት የመያዝ እሳቤ እንደማያዛልቅ፣ ኢትዮጵያም በወንዟ  እንዳትጠቀም የሚያደርግ አንዳችም ምድራዊ ሀይል እንደሌለ በግልጽ የሚታይ ነው/ሞቅ ያለ ጭብጨባ/፡፡
ከሊፋ፡- እኔም የዳውድ ሃሳብ ደጋፊ ነኝ /ፋታ/ የኛ ትውልድ ለራሱ የሚኖር እንጂ ሙት ታሪክ  እየቆፈረ በጫጫታና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በልጓም የሚነዳ የጋሪ ፈረስ አንሆንም፤ እኛ እስካሁን ያቀረብንላችሁ  ክርክር የየግላችን ሀሳብ ወይም አቋም ሳይሆን የአንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ከንቱ ሙግት ነው፤ ማዕዳችን አንድ ነው፤ ላንዱ እሬት ላንዱ ማር አይደለም … ለምን ማሩን ወደ እሬት ለመለወጥ እንደምንተጋ አይገባኝም /ጭብጨባ/ ለማንኛውም የመንግስቶቻችን ውይይቱ ይቀጥላል፤ ለወደፊቱ ምን ላይ ሊደርስ እንደሚችል በንድፈ ሀሳብ ከወዲሁ አውቀነዋል፤ የግርጌ የራስጌ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ተብሎ ቅራኔ ማክረር ይቀራል፤ በአዲስ መንፈስና በአዲስ አመለካከት ተነሳስተንም ጠላት በዘመኑ መካከላችን ሰንቅሮ ያኖረውን ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ የቅራኔ ፈንጂ አምክነን፣ እንደ ጥንት አንጋፋነታችን የስልጣኔ እርካብ ላይ ተቆናጥጠን እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ አባይን በጋራ እያለማን፣ ትውልዱን በአንድ ቤተሰብነት መንፈስ ይዘን በስራና በፍቅር እየመራን መራመድ እንድንችል፣ ከእኛም ሆነ ከምሁሮቻችን ትጋት በጥብቅ ይጠበቅብናል /የጋለ ጭብጨባ/
ዳውድ፡- እኛም ግብጾች ከሚያስማማን ከውይይቱ መድረክ መሸሽ ወይ በራስ አለመተማመን ወይም ራስ ወዳድነት እንጂ ጥበብ አይሆንም /ጭብጨባ/ ስለዚህ ሀገሬ ግብጽ አወዛጋቢ ነጥብ ፈትታ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ሰምና ክር ሆና የመሪነት ሚናዋን ማጉላት ይጠበቅባታል የሚል የጸና ተስፋ አለኝ /ጭብጨባ/ ለዚህም በጋራ እንታገላለን፡፡
አባ ዘዮሐንስ፡- ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፤ አለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል እንዲሉ፡፡
ዳውድ፡- አዎን ከእንግዲህ ለአባይ አሉታዊ መፈክር ሳይሆን አዎንታዊ መፈክር እያሰማን፣ በተስፋ ወደፊት እንተማለን /ተሰብሳቢው እያጨበጨበ ከመቀመጫው ይነሳል/ መፈክሩን አብረን እንበል /ኖ ናይል ሳይሆን የስ ናይል እንበል -  አባይ ለግል ሳይሆን ለጋራ ይሆናል ! /ሆታና ጭብጨባ፤ መተቃቀፍ ይከተላል/
እንባቆም፡- ክቡራትና ክቡራን -ስብሰባች ንን ልንቋጭ ነው፤ መንፈስ እንደ አረቄ የሚያሞቁ ሀሳቦችን ሰምተናል፤ ያረጁ ያፈጁ ውሎች የሙዝየም እድል እንኳን አይሰጣቸውም፤ ይቃጠላሉ! /ሆታ/ በአሲሲው ካህን ፍራንሲስ አባባል ውይይቱን ብናጠናቅቅ ደስ ይለኛል፡- አምላኬ ማድረግ የምችለውን እንድፈጽመው ድፍረት ስጠኝ፤ የማልችለውን ደግሞ እንድቀበለው ትዕግስቱን ስጠኝ ይላል/ ሆታ/
አባ ዘዮሐንስ፡-  ልክ ነህ ልጄ፤ እሱ አንድዬ ልቦናችንን ወደ ቀና ጎዳና ይመልስልን /ሆታ፤ ክራርና መሰንቆ ያጅባል/
ጦቢያ፡- /ጦቢያ ያማጽናሉ/ ውይይቱ ቢጠናቀቅም ባህላዊ ቡና እየተዘጋጀ ስለሆነ እባካችሁን ለጥቂት ደቂቃ ባላችሁበት እየተጨዋወታችሁ ቆዩልን/ ከወንበራቸው ሄደው ይቀመጣሉ /ፋታ/
ሄንሪ፡- /ወደ እነ ዳውድ ጠጋ ብሎ ሹክ ይልና ይቆማል/ ክቡራትና ክቡራን፤ ቡናው እስኪመጣ ድረስ ለጥቂት ደቂቃ እንለያችኋለንና ፍቀዱልን… እንመለሳለን…/ይወጣሉ/ ሌሎች ጭውውታቸውን በቡድን በቡድን ይቀጥላሉ… ይጠጣሉ ይስቃሉ /መብራት ይጠፋል/
(ከግርማ እንቻለው የህዳሴ ግድብ እና "ፈርኦኑ ቀለበት" ተውኔት መጽሐፍ የተወሰደ፤ 2012)

Read 2639 times