Saturday, 18 July 2020 15:30

የልጅነት ጋብቻ---እ.ኤ.አ ከ2011-2020

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

    በአለም ላይ በየቀኑ 39,000 ልጆች ጋብቻ እንዲፈጽሙ ይደረጋሉ፡፡
በአለም ላይ ከ2011- 2020 ከ140 ሚሊዮን የሚበልጡ ሴት ልጆች ካለእድሜአቸው ጋብቻ እንዲፈጽሙ ይደረጋሉ፡፡
የልጅነት ጋብቻን በሚመለከት አለምአቀፍ ገጽታው ከ2011-2020 ድረስ ምን ሊመስል ይችላል ሲሉ March 2013 ላይ ግምቱን ያስነበቡት UNFPA/UNICEF/UN Women/WHO/World Vision/World YWCA/ በጋራ በመሆን ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው የልጅነት ጋብቻ ሲገመት በየአመቱ 14.2 ሚሊዮን ወይንም በየቀኑ 39,000 ልጆች ጋብቻ እንደሚፈጽሙ ያሳያል፡፡ ከዚህም በላይ ለገብቻ የበቁት 140 ሚሊዮን የሚሆኑት ልጆች እድሜአቸው ከ18 አመት በታች ነው ቢባል እንኩዋን 50 ሚሊዮን የሚሆኑት ከ15/አመታች እንደሚሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  
የልጅነት ጋብቻ በህጻነቱ ላይ የሚደርስ አካላዊ ጉዳት እና የሞራል ብሎም የመብት መጎዳትና መጣስ ሲሆን ይህንን አስከፊ ድርጊት ለመግታት በአለም አቀፍ ደረጃ የተወሰኑ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡  በእርግጥ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ያለው የወጣት ቁጥር መጨመር አሳሳቢ እንደሚሆን አይካድም፡፡
የልጅነት ጋብቻ የሴት ልጆች መብት መጣስ እና ልጃገረዶን ከትምህርታቸው ማስቀረት፤ለጤና እውክታ እንዲጋለጡ ማድረግ እና የወደፊት ሕይወታቸው እንዲጎዳ ማድረግ መሆኑን ጥናት አድራጊዎች ይመሰክራሉ፡፡
‹‹…ብዙ ወላጆች ሴት ልጆቻቸው ጥሩ ሕይወት እንዲገጥማቸው ቢመኙም እንኩዋን በልጅነታ ቸው የሚያገቡ ሴት ልጆች ግን ያላቸውን አቅምና ችሎታ በወደፊት ሕይወታቸው መጠቀም እንዳይችሉ የሚየደርጋቸው ጠንቅ እንደገጠማቸው የሚቆጠሩ ናቸው ብለዋል Babatunde Osotimehin, M.D, Executive Director, UNFPA.
የልጅነት ጋብቻ የገጠማቸው ሴቶች በትዳር ላይ እያሉ በትዳር ጉዋደኛቸው የሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት እና በኑሮ መጎሳቆል ትዳር መፈጸም በሚገባቸው እድሜ  ከተዳሩት ከፍ ያለ ነው፡፡
ልጅ በመውለድ ጊዜ የሚደርሱ ችግሮች እድሜአቸው ከ15-19 የሚደርሱ ማለትም በልጅነት ጋብቻ የፈጸሙትን ልጆች በዋነኛነት ለሞት ከሚዳርጉት መካከል ነው፡፡
ጋብቻን ማግባት በሚገባቸው እድሜ የሚፈጽሙ እና እርግዝናውንም የሚያዘገዩ ሴቶች ጤናማ ሆነው የመኖር እድል አላቸው::
በልጅነት ጋብቻ ያልፈጸሙ ሴቶች ትምህርታቸውን በሚገባ ተምረው የወደፊት ሕይወታቸውን በሚገባ ለመምራት የሚያስችላቸውን አቅም ገንብተው ጤናማ ቤተሰብን ለመምራት ይበቃሉ፡፡
ስለዚህም ከላይ የተገለጹትን በጎ ምኞቶች ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ መቆምና በጋራ መስራት ይጠበቅብናል፡፡
Flavia Bustreo, M.D. WHO
የልጅነት ጋብቻ ሲባል ከ18/አመት በታች የሉ ሕጻናትን ወንድና ሴትን ሳይለይ የሚመለከት ሲሆን በተግባር የሚታየው ግን በአብዛኛው በሴቶች ላይ መሆኑ እሙን ነው፡፡ የልጅት ጋብቻ አለምአቀፋዊ ነው ቢባልም በስፋት የሚታየው ግን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራትና በደቡብ እስያ ሀገራት ነው፡፡ በደቡብ እስያ ካሉት ሴት ልጆች ግማሽ የሚሆኑት፤ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ደግሞ ከ1/3ኛ በላይ የሚሆኑ ልጃገረዶች ከ18/አመት በታች እድሜ ላይ ሆነው የልጅነት ጋብቻ ሲፈጸምባቸው ይታያል፡፡   
ይህንን ድርጊ ለማስቆም በሚሰራው ስራ በመጠኑም ቢሆን ለውጥ የታየው በሁሉም ድርጊቱ በሚፈጸምባቸው ሀገራት በከተሞች ውስጥ ነው:: ኑሮአቸውን በከተማ ያደረጉ ወላጆች ልጆቻ ቸውን በማስተማር እና የተለያዩ ልጆቸውን የሚንከባከቡበት ስራ በመስራት እየተጠነቀቁላቸው ሲሆን  በገጠሩ ክፍል ለውጥ ለማምጣት ገና ትግሉ ገና መቀጠል አለበት፡፡
‹‹…ማንኛዋም ሴት ልጅነትዋን መነጠቅ የለባትም፡፡ ማንኛዋም ሴት እንድትማር እና ጤንነትዋ እንዲጠበቅ እንዲሁም የወደፊት እቅድዋ እንዲሟላላት ›› የሚል አለም አቀፍ መብት አላት:: ይሁን እንጂ ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴት ህጻናት በየአመቱ ካለእድሜአቸው ስለሚዳሩ መብ ታቸውን ተነፍገዋል፡፡ Michelle Bachelet, M.D   
የልጅነት ጋብቻ በአለምአቀፍ ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚተችበት እና ድርጊቱ የሚኮነንበት ምክንያት እንደሚከተለው ተዘርዝሮአል፡፡
ሴት ልጆች፤-
በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ አለማድረግ፤
ማንኛውንም የህይወት ልምድ እንዲቀስሙና እና የወደፊት ሕይወታቸውንም በሰከነ ሁኔታ መምራት የሚችሉበትን አቅም መፍጠር እንዳይችሉ ማድረግ፤
ከትዳር ጉዋደኞቻቸው ለሚደርስባቸው የወሲባዊ ጥቃት እና ለኤችአይቪ መጋለጥ ምክንያት በመሆኑ፤
የልጅነት ጋብቻ ከላይ የተገለጹትንና የመሳሰሉትን ችግሮች እንዲደርስባቸው የሚያደርግ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መወገድ እንዲችል የተቻለው ጥረት መደረግ አለበት፡፡
የልጅነት ጋብቻ ትዳር የሚመሰረተው ከማን እና ከምን አይነት ሰው ጋር መሆኑን ለመወሰን ወይንም ለመምረጥ በማይችሉበት እድሜ የሚፈጸም በመሆኑ ሴት ልቹን በቀሪው ሕይወታቸው እንዳዘኑና እንደተጎዱ እንዲቀጥሉ የሚያደርጋቸው ነው፡፡
ብዙ ሀገሮች የትዳር መመስረቻ እድሜን በህግ ደንግገው ተፈጻሚ እንዲሆን ውሳኔ አሳል ፈዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራት ሀሳቡን ተቀብለው በትክክል ማስፈጸም ቢችሉ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ የልጅነት ጋብቻ ሙሉ በሙሉ ይወገዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ግምት የተቀመጠው የዛሬ ሰባት አመት ገደማ ሲሆን እስከአሁን ድረስ ግን የታዩት ለውጦች እውነትም በ2030 የልጅነት ጋብቻ ያበቃል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም በህግ ተደግፎ የተሰናዳውን ስምምነት ድርጊቱ በሚፈጸምባቸው ሀገራት ህብረተሰቡ አክብሮ ተፈጻሚ ለማድ ረግ ክፍተቶች እየተስተዋሉ ስለሆነ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በባህልና በልማድ በመሸነፍ አዲስ አሰራርን ለመከተል የህብረተሰብ አባላት ሲቸገሩ ማየት የተለመደ ይመስላል፡፡  
የልጅነት ጋብቻ አካላቸው ልጅን አርግዘው ሊወልዱ በማይችሉበት ወቅት እርግዝና ስለሚገጥማቸው የስተዋልዶ ጤና ጉድለት እንዲያጋጥማቸው ምክንያት ይሆናል፡፡ ልጆች ቀናቸው ሳይደርስ አንዲወለዱ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ከመግጠማቸውም በላይ በሚወለዱበት ወቅትም በተራዘመ ምጥና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ለህልፈት የሚዳረጉበት እናቶቻቸውም ለፊስቱላ ሕመምና ሌሎችም የጤና እክሎች የሚጋለጡበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡እንደ ዩኒሴፍ ግምት ከሚሞቱት ውስጥ 50.000 የሚሆኑት በዝቅተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ ባሉ ሀገራት ነው፡፡ የሞተ ጽንስ መገላገል፤የተወለዱ ልጆች ሞት ከ50 ከመቶ በላይ የሚሆኑት እድሜአቸው ከ20 አመት በታች ከሆኑ እናቶች የሚወለዱ ናቸው፡፡   
በልጅነት የሚዳሩት ልጆች ልጆች በመሆናቸው ብቻ ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከያ እንዳይ ጠቀሙ ለማድረግ ጥያቄአቸውን ውድቅ የሚደረግበት ወይንም ደግሞ የትዳር ጉዋደኛቸውን ሳያስፈቅዱ መጠቀም የማይችሉበት አጋጣሚ በርካታ ነው:: ከዚህም በላይ ልጆቹ ስለያልተፈለገ እርግዝና መከላከያው ምንም እውቀት ላይኖራቸው ይችላል፡፡
ምንም እንኩዋን ወላጆች ልጆቻቸው አላስፈላጊ ለሆነ ትዳር ምስረታ ወይንም ጠለፋ እና መማገጥ የመሳሰሉ ነገሮች ሳይገጥሙዋቸው እውቅና ያለው ጋብቻ እንዲመሰርቱ ፍላጎት ቢኖራቸውም በተቃራኒው ደግሞ ልጆቹን እየጎዱዋቸው መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡ የልጅነት ጋብቻ እንዲገታም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በትኩረት እንዲሰሩ ይጠበቃል፡፡

Read 11662 times