Print this page
Saturday, 18 July 2020 15:06

ባሉ ሳይገኝ ሚዜ ታማርጣለች!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

   ደራሲ ከበደ ሚካኤል በታሪክና ምሳሌ ተረቶቻቸውና ግጥሞቻቸው ውስጥ የሚከተለው ወቅታዊና ዘላለማዊ ሆኖ ሲጠቀስ የኖረ ነው (Timely and timeless እንዲሉ)፡፡ ዛሬም ያንኑ ባህሪውን   ጠብቆ ጉልህ ሆኖ ይታያል፡-
አዝማሪና ውሃ ሙላት፣
አንድ ቀን አንድ ሰው፣
ሲሄድ በመንገድ፣
የወንዝ ውሀ  ሞልቶ፣
ደፍርሶ ሲወርድ
እዚያው እወንዙ ዳር፣
እያለ ጎርደድ
አንድ አዝማሪ አገኘ፣
ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ ፣
ድምጹን አሳምሮ፤
"ምንነው አቶ አዝማሪ፣
ምን ትሰራለህ…………"
ብሎ ቢጠይቀው፣
"ምን ሁን  ትላለህ ..
አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት፤
ሆዱን አራርቶልኝ
ቢያሻግረኝ ብዬ …"
"አሁን ገና ሞኝ ሆንክ
ምነዋ ሰውዬ!
ነገሩስ ባልከፋ፣
ውሃውን ማወደስ
ግን እንደዚ ፈጥኖ
በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ፣
ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን እያሽካካ፣
መገስገሱን ትቶ?!
እስቲ ተመልከተው፣
ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ፣
የሰማው ሲሄድ?!
ምክር፡- ተግሳጽም ለጠባይ፣
ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው፣
ካልተገኘ ሰሚ!
*   *   *
የሚሰማ ካልተገኘ ሲያወሩ ቢውሉ "ነገር ቢያበዙት በአህያ አይጫንም" እንደሚሆን ግለጽ ነው፡፡ ስለ ምንድን ነው የሚወራው? ማለት ብቻ ሳይሆን ለማን ነው የማወራው? ማለት ምንግዜም ተገቢ ነው" በሀገራችን "ያልሰማው መምጣቱ የሰማው መሄዱ" የተለመደ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ምንግዜም እንቅስቃሴ መኖሩን አመላካች ነው፡፡ ያልተገላበጠ ያራል የምንለው ያለ ነገር አይደለም፡፡ ጥበብ አስካለን ድረስ ጎርፉን ለማስቆምም  ይቻላል የሚለው ዕሳቤ፤ አንድም የጥበብን መኖር አስፈላጊነት፣ አንድም ደግሞ የጥበብ ሃይል የት ድረስ ሊያድግ እንደሚችል ያስገነዝበናል፡፡
ሃገራችን ክፉውንም ደጉንም፣ ሀገር ወዳዱንም ሀገር ጠሉንም እያስተናገደች እዚህ ደርሳለች፡፡ ዞሮ ዞሮ ከችግር ቋት አልወጣችም፡፡ የፖለቲካ ክስረት፣ የኢኮኖሚ ድቀት፣ ማህበራዊ ውዥንብር  ሁሌም ቀይዶ አንደያዘን ነው፡፡ ከሰራነው ያልሰራነው መብዛቱ መቼም፤ አገር ያወቀው ጸኃይ የሞቀው ጉዳይ ነው! የቤት ስራችን የበዛው ለዚህ ነው፡፡ የተዛባው ሲበዛ በትክክል የማቀድን ሁኔታ ያውከዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በፈንታው አፈጻፀሙን መላቅጡን ያሳጣዋል፡፡ ይህንን የመሰለ ምስቅልቅል ሂደት ውስጥ እያለን ኮሮና የመሰለ ተውሳክ፣ ሰላምን የሚያናጋ ነውጥ፣ ልክ የለሽ የስራ አጥነት መብዛት እያለ በኮሮና ሳቢያ የሚሰራውም ሰው አንዳይሰራ መገደዱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ ወዘተ--- በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ጣጣ የምበላው ሳጣ ልጄ ጥርስ አወጣ መሆኑን ለማየት 110 ሚሊዮን ህዝብ ባላት አገር አንፃር ማስላትና በችግሩ ማባዛት በቂ ነው፡፡
ከላይ ያነሳነው ችግር ላይ ሌብነት ስንጨምርበት "በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ" ከማለት በቀር የምስቅልቅሉን ውል ለማግኘት እንኳ እንቅልፍ የሚያሳጣ ነገር ነው፡፡ መንግስትና የግሉ ሴክተር አይናበቡም ይባላል እንጂ ዋናው አባዜ ያለው የየራስን ንባብ በቅጡ አለማንበብ ላይ ነው! ለዚህ ደግሞ "ለተገቢው ቦታ ተገቢ ሰው ማስቀመጥ" ትክክለኛ መርህ ነው! ያ ካልሆነ ዕቅዱ ሁሉ የግድግዳ ጌጥ ነው የሚሆነው! ማን ሊሰራው ይታቀዳል? እንኳንስ የኢኮኖሚ ዕቅዱማቀፊያ ነው የሚባለው የፖለቲካ ስርዓት የጠራ ዲሞክራሲም ያልተሟሸበት ነው፡፡ ይህን ያህል ዘመን ስለ ዲሞክራሲ ዳዴ ስለ አለመጎልበቱ፣ ህዝቡ መረዳት ስለማቃቱ ስናወጋ ለባህላችን፣ ለአስተሳሰባችን፣ ለአኗኗራችን አግባብ ያለው ዲሞክራሲ ሳይሆን የምዕራቡን ዓለም ዓይነት እያሰላሰልን ነው የኖርነው፡፡
በውጪው ቀመር የተለካው ስፌት ይጠበናል  ይሰፋናል? ሳንል አንድ ቀን ልብስ እንለብሳለን በሚል ተምኔታዊ ህልም ውስጥ ብዙ ባዝነናል፡፡ ለኛ የሚመጥነውን ልብስ የሚሸምን የሌላ አገር ባለሙያ ሳይሆን የኛው ሸማኔ ቢሆን ይመረጣል፡፡ በምዕራቡ ዓለም የተጠመቀ ወይን ጠጅ ቢያንስ እኛ ዘንድ ሲመጣ ጣዕሙ ሊቀየር እንደሚችል ማስተዋል ደግ ነው፡፡
ሌላው የወቅቱ ቁልፍ ጥያቄ፡- "የዘገየ ፍርድ ከሌለ አንድ ነው ነው፡፡" የሚባለው ነው፡፡ ለአንድ ሰሞን የምንጮሃቸው ጩኸቶች ሲውሉ ሲያድሩ እየቆዩ ይላዘዛሉ፡፡ የቡና ስብሃቱ መፋጀቱ መሆናቸው ይቀራል (decaffeinated ይሆናል እንደ እንግሊዞቹ አባባል!) ከነጭራሹ የሚረሱበትም ሁኔታ አለ፡፡ ይልቁንም ጉዳዮቹን ሁሉ በትኩስነታቸው መቋጨት ለአገርም ለህዝብም ለመንግስትም ይበጃል፡፡ ብረትን እንደጋለ ቀጥቅጠው (hit the iron while it is hot) ነው ጉዳዩ!
"ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ›› ዓይነት ሁኔታ ተለይቶ አያውቀም፡፡ በፈረንጅኛ አፍ ስንገልፀው፡- "They shout at most against the vices they themselves are guilty of" እንደሚባለው ነው፡፡ አንቺ ታመጪው አንቺው ታሮጪው እንደ ማለትም ነው፡፡
ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት፣ ሰላም፣ ሰብዓዊነት፣ ዲሞክራሲ መብት፣ ስነምግባራዊነት፣ ሙያዊነት፣ …..ከቃልነት አልፈው ወደ ተግባራዊነት ተሸጋግረው ልማትና ዕድገት የሚሆኑት፣ እጁን የታጠበና ልቡ የፀዳ ሰው ሲኖር ነው! የሁሉ ነገራችን ማሰሪያው ሰው ነው፡፡ አለበለዚያ "ባሉ ሳይገኝ ሚዜ ታማርጣለች" ይሆንብናል!

Read 13180 times
Administrator

Latest from Administrator