Monday, 20 July 2020 00:00

ቀታሪ ግጥም - (በአሰፋ ጉያ፤ ወፉ-ሰው)

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(1 Vote)

 “በግጥሞቼ እስቃለሁ - በልቤ ግን ግፍን እያስታወስኩ አዝናለሁ”
            
           ሂሳዊ አስተያየት
ግጥም  የሰውን ልጅ የህልውና ቅፈፍ ዳብዛ ያስሳል፡፡ በህሊናው ቅርጽ፤ በልቦናው መልክ እስኪቀርጽ ይባዝናል፡፡ ይህም ሀሰሳ ሥጋም ነፍስም ነውና አጠቃላዩንም ሆነ ተናጠላዊውን ህላዌ የመመዘን፣ የመፈተሽ ሂደትም መንገድም ነው፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ካንቴ ሜር፤ “በግጥሞቼ እስቃለሁ - በልቤ ግን ግፍን እያስታወስኩ አዝናለሁ” ማለታቸው፡፡ ይቀትራል፡፡ በርግጥ አባባሉ የባለቅኔውን፤ “ሰው…የተጋዘ አምላክ ነው” አገላለጽ ያስታውሰናል፡፡ በፈተና ውስጥ ሆኖ ህልሙን በቃላት ይቋጥራል፡፡ መንገድ ያስሳል፡፡ ያልታየውን ያያል፡፡ እዚህ ላይ በግጥም የመተንፈስ ተግባር ተተርጉሞ ሰውነት ይጸድቃል፡፡
[ቀታሪ* ስሩ ቀተረ ነው፡፡ ቀተረ* እኩል ለመሆን ተከታተለ* ተቀታተረ* ተመለካከተ* ተወዳደረ* ተተካከለ* ተመዛዘነ* ተፈካከረ* ተፈላለገ (አስ) ከባለ ቀትር አትቀታተር:: (ከሣቴ ብርሃ ተሠማ* የዐማርኛ መዝገበ ቃላት ገፅ ፫፻፹፬ *2008 ዓ.ም) ግጥም ምንጩ ህይወት ነውና (ቋንቋው (መንገዱ) አዕምሮን፣ ስሜቱ ልብንና መልዕክቱ ልቦናን ይቀትራል፡፡) አዕምሮን፣ ልቦናንና ልብን የቀተረ ከምናብ የሚፈለቀቅ የፀነነ የጥበብ ውጤት ነው፡፡ መቀተሩ ከልማድ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው፡፡ ፈጠራ ደግሞ  ልማድን መሻገር ይጠይቃል፡፡ ከልማድ ያልተሻገረ ግጥም ነፃ አያወጣም፡፡ አይታኘክም - የተመጠጠ ነውና፡፡]
                                            ***8
         ወፉ-ሰው
ሰው መሆኑን ጠልቶ
በነፋስ ተሞልቶ
ብረር ብረር አለው
ወፍ መሆን አማረው፡፡
ባየር ላይ መብረሩ
ፍሬ እየለቀሙ…የትም እያደሩ
ሲያሻ እየዘመሩ
የትም እየዞሩ
አሰኘው መኖሩ፡፡
ድንገት ትዝ ሲለው
ወፍ ሆኖ ሲያስበው
በጭልፊት መጠለፍ…
በወንጭፍ መነደፍ…መኖሩ ሲታየው
…ቢሆንም…
…ባይሆንም…
ሰው መሆን ተሻለው፡፡
(መጋቢ 1 ቀን 1982 ዓ.ም) (ከአሰፋ ጉያ፣የከንፈር ወዳጅ፣ 2008 ዓ.ም.፣ ገፅ 43)
በግጥሙ ሰው መሆን ምርጫም ግዴታም ሆኖ ተገልጧል፡፡ ምናባችን ውስጥ ወለል ያለ ቤት ይሰራል፤ የስሜትና የሀሳብ፡፡ ዞረን ዞረን ምርጫችን ሰውነት ይሆናል፡፡ ይኸውም፡-
….ቢሆንም…
… ባይሆንም…
ሰው መሆን ተሻለው፡፡
በሚል ተተርጉሟል፡፡ እዚህ ላይ “ጉዳዩ መሆን ወይም አለመሆን ነው” እንዲሉ በምርጫህ ህልምህን ትቋጥራለህ ወይም ትጥላለህ፡፡ ከፈቃድ ጋር ተዋደህ፣ተጋምደህ በጥልቅ ምልከታ እራስህንና አካባቢህን (ዙሪያህን) ከመዘንከው የተሻልክ መሆንህ ጎልቶ፣ነጥሮ ይታይሀል፡፡
እነኝህ ሰልስቱ ስንኞች “ሰውነትን” ማፅደቂያ፣ መትከያ ናቸው፡፡ ለሰው ስንቅ፣ ትጥቅ ያወርሳሉ፡፡ ያልተዛነፈ ምሰሶ ይተክላሉ፡፡
በስንኞቹ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ የገባው ነጠብጣብ ማለትም ሶስት ነጥብ ሰውነትን ተደግፈው የሚቆሙ የህልውና መገለጫዎችን ማሳያ፣ ወኪል ናቸው:: ይህም ማንነትህን በማሰስና ክህሎትን በመላበስ የሚገነባ ሰብዕ ወኪል ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ሀይነማን፤ “To be human is not a fact, but a task” ማለቱን መጥቀስ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
በሌላ ፅንፍ ነጠብጣብ /…ቢሆንም…፣…ባይሆንም…፣ሰው መሆን ተሻለው፡፡/ የሰውን ልጅ ባተሌነት፣ ስልቹነትና የኑሮን ባዘቶ ጥልፍልፍ ከነህመሙ ውጥንቅጥ ገፅታን ያመለክታል፡፡ ህልምህን ስትነጠቅ ምርጫ አልባ ስትሆን በነበርክበት ትቆማለህ፣ ፍለጋህን ትገታለህ፡፡ ያም ሆኖ ተፈጥሮ በረከቷን ትቸራለች፤ ህይወት (ህልውና) ይቀጥላል፡፡ ፍላጎትን መግደል በረከት ይሆናል፡፡ ይህ ጉዳይ በዳዊት ጸጋዬ፤ ግጥም ተሞሽሮ ቀርቧል፡፡ እነሆ፡-
ምዕራፍ ፳፰
ደስታን ስፈልግ ነው…
    ደስታዬ የራቀኝ፤
ፍቅርን ስሻ ነው…
    ፍቅር የጠፋብኝ፤
ሰላምን ሳስስ ነው…
    ሰላሜን ያጣሁት፤
ፍላጎቴን ስገድል…
    ሁሉን አገኘሁት፡፡
(ዳዊት ጸጋዬ፣--፣2012 ዓ.ም፣ ገፅ 32)
ለዚህ ይሆን ማህበረሰባችን “የምፈልገውን ሳይሆን የሚያስፈልገኝን ስጠኝ” የሚለው!! አጃኢብ ነው!...በርግጥ ጉዳቱ ተጠየቃዊ ነው፤ ያከራክራል፡፡ በግጥም መቅረቡ ግን እንድንቀበለው ያስገድዳል፤ የግጥም ሀይሉም ይህ ይመስለኛል፡፡
ሆኖም ይህን ወፈፌ ሰዋዊ ባህሪ በአመክንዮ የገራባቸው ስንኞ የሚከተሉት ናቸው፡፡
“ድንገት ትዝ ሲለው
ወፍ ሆኖ ሲያስበው
በጭልፊት መጠለፍ…
በወንጭፍ መነደፍ…መኖሩ ሲታየው”
በነዚህ ስንኞች ተራኪው ዳር ቆሞ የሰውን ልጅ ግስጋሴ ጠቅላላ ግብ የሚቀምርባቸውን መንገዶች መዝኖ ምክንያታዊነቱን የገለጠባቸው ናቸው:: የሰው ልጅ ውስንነቶችን ለመሻገርና “ፍፁም ነፃነትን” ለመቀዳጀት ካለው ምኞት በመነሳት በወፍ ተመስሏል፡፡ የህዋውን የተንጣለለ ዓለም ያለምንም ገደብ ለመቅዘፍ እንደ አንድ ምርጫ ቀርቦለታል፡፡ ሆኖም  ግን ውስንነቱ ሲገድበው ምኞቱ ይኮሰምናል:: በርግጥ ያለውን ፀጋ ትርጉም አስፍቶ፣ አውጥቶ አውርዶ፤ ማዕዘናቱን ፈትሾ “ሰውነትን” ያፀድቃል - ያልቃል፡፡ ሰው እንስሳ ነው፡፡ ከፍ ሲልም “መልዓክ” ነው፡፡ ሲልቅም ፈጣሪ ነውና ምርጫው ተገቢ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በሌላ መልኩ ሰው መሆን ስለነበረብን ሰው ሆነናል፤ ቀድሞውንም የተሻለ ምርጫ ቢኖረን ኖሮ ሰው ባልሆን ነበር- ያለ ይመስለኛል፡፡ ቀታሪ ነው፡፡ ሁሉም ነገር መሆን የቻለው መሆን ስላለበት ነው-- የሚለውን በአፅንኦት ይጠቁማል:: የሁሉም ምንጭ ሰው ሆኖ መገኘት ነውና -- ያጀግናል:: በመፅሐፍ ቅዱስ፤ “መመረጣችሁንና መጠራታችሁን ታፀኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ” መባሉን ማስታወሱ የግጥሙን መልከ ብዙነት ያፀናል፡፡ ለዚህም ይመስላል “ስነፅሁፍ አንድም ብዙም የሆነ ጥበብ ነው” የሚባለው፡፡  ከዚህም አንፃር ግጥም የልዕለ ተፈጥሮን ረድኤት መግለጫ ጥበብ ነው፡፡ ቀታሪነቱ የላቀን ጉዳይ በላቀ ቋንቋ ወይም መንገድ የሚያቀርብ መሆኑ ላይ ነው፡፡
ግጥሙ በመጀመሪያዎቹ ሁለት አንጓዎች በፅኑ መሰረት ላይ ቆሞ የሰውን ልጅ የነፃነት እሴቶች ፅኑነት በማሰስ አስረጅ ስንኞችን በማስከተል በስሜት ይገሰግሳል:: ሆኖም ጉዞው በምክንያት ተረትቶ ምኞት ይድበሰበሳል፡፡ ጥፋትን (ሞት እንበለው ይሆን) አምርሮ ይሸሻል፡፡ ነጻነትን በምናብ መዳፍ አፈፍ ለማድረግ መውተርተሩ ከንቱ ይሆናል፡፡
ግጥሙ ሰውን ወደ ሰውነት ለማላቅ የተሰናኘ ነው፤አንዳንዴ በግልፅ በአብዛኛው በስውር፡፡ ከስውር ገፅታው አንዱ የወቅቱን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ በዘይቤ ሰፍቶ ካነፀረ በኋላ ይቆዝማል፡፡ ሀሰሳ ነፃነት በመሆኑ ቁጭትን አዝሏል፡፡ የሰውን ልጅ ውስንነቶች አጉልቷል፡፡ በሌላ ፅንፍም ሰውነትን አልቋል፡፡ አፅድቋል፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ካንቴ ሜር፤ “በግጥሞቼ እስቃለሁ - በልቤ ግን ግፍን እያስታወስኩ አዝናለሁ” ማለታቸው፡፡
አሰነኛኘቱ የሰመረ ነው፡፡ አይጎረብጥም፡፡ በዘይቤ የተሞሸረ ነው፤ ወፉ-ሰው፡፡
ምፀት….ምፀት…ምፀት!!
(ማስታወሻነቱ ለሐይማኖት ጥላሁን ይሁንልኝ)
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይችላሉ፡፡


Read 1202 times