Saturday, 18 July 2020 16:37

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ይድረስ ለኛ

ይድረስ ለእኛ ለኔና ላንተ
ዘመን በትውልድ ክር ባንድ ስቦ ላቋጠረን
የዚያ ሰፈር ኤሊቶች፣ የዚህ ሰፈር ኤሊቶች እየተባባልን
በህዝብ ስም እየማልን፣ በወገን ስም እየማልን
አገር አቃጥለን ለምንሞቅ
በእናቶች ሃዘን ሰቆቃ፣ በአባቶች እንባ ለምንስቅ
ይድረስ ለእኛ ለኔና ላንተ
 ለነቃነው ለበቃነው
ክፉ ዘመን ክፉ ሥርአት፣ በጥፋት ላስተሳሰረን
በጥላቻ የተሰራ፣ በቂም በቀል የበቀለ ሴራና ሸፍጥ ለወረረን
ክህደት- ቅጥፈት- መሰሪነት፣ የህሊና አይናችንን ልባችንን ለሰወረን
ከሰው ተራ ወርደን ከፈጣሪ ተገዳድረን
ሃገር ሽቅብ የምትረጨው እንባ የማይገደን
ይድረስ ለእኛ ለኔና ላንተ
አክቲቪስት በሚባል ማዕረግና ካባ ተጠቅልለን
ከአገር በላይ … ከህግ በላይ…  ተቆልለን
ሰዎችን ከኑሮ  ነቅለን፣ ፍትህን ጫማችን ስር ጥለን
በአገር ላይ ፍቅርን መግደል ፤ ተስፋን መግደል፤ ደስታን መግደል፤ ሰላምን መግደል
እንደ ውሃ ጥም ለቀቀለን….ይመስለኛል ለኔና ላንተ
ድንቁርና፣ ዕብሪት፣ ትዕቢት፣ ክፋት ላስታጠቀን
ነገ ታሪክ በእውነት ችሎት በደም ቃል ለሚጠይቀን
ወንድምዬ፤ ምን መልስ አለህ ?--
(ከገጣሚና ጸሃፌ ተውኔት ጌትነት እንየው ;ይድረስ ለኛ; ዘለግ ያለ ግጥም የተቀነጨበ)

Read 2267 times