Print this page
Saturday, 25 July 2020 15:08

“እዛም ቤት እሳት አለ!” - (አለቃ ገብረሃና)

Written by 
Rate this item
(7 votes)


           በቀልደኝነታቸውና በዋዘኝነታቸው ስለሚታወቁት ስለ አለቃ ገብረሃና ብዙ ተወስቷል፡፡
አንዳንዴ እሳቸው ያላሉትም የእሳቸው ተደርጐ ይተረካል፡፡ ለማንኛውም የሳቸው ከተባሉት ጥቂቶቹን እንጥቀስ፡፡
አንድ ቀን አለቃ ወደ ገበያ ይሄዳሉ፤ አሉ፡፡
ገበያው ደርቷል፡፡ የአለቃን ተረበኛነት የሚያውቅና የሚወድ አንድ ተጨዋች ሰው ይመጣል፡፡
ሰውዬው እግሩ ገደድ ያለ ነው፡፡
አለቃን እንዳገኛቸው፤
“አለቃ እንደምን ዋሉ?” አላቸው፡፡
“ደህና ውለሃል ወዳጄ?” አሉ አለቃ፡፡
“ከየት እየመጡ ነው?”
“ሰው ሳስታርቅ ውዬ፣ የፍንጥር ምሣ በልተን ገና አሁን ተለያየን፡፡”
እግረ-ጠማማው ሰውዬ፣ አለቃ አፍ ላይ የተልባ ፍሬ ያያል፡፡ አለቃ ምሣ የበሉት በተልባ ወጥ መሆኑን በመገመት፤ ጥቂት ሊተርባቸው ፈልጐ፤
“ለመሆኑ ተልባ ስንት ስንት ዋለ፤ አለቃ?” አለ፡፡
አለቃም ወደ ሰውዬው እግር መልከት ብለው፤
“በጠማማ ጣሣ ሰባት ሰባት ነው” አሉት፡፡
*   *   *
አንድ ቀን ደግሞ፤ ጐጃም ውስጥ፣ አንድ ሰው ከወደ ሞጣ ሲመጣ አለቃ ያገኙታል፤ በእጁ በትር ይዟል፤
አለቃ - “እንደምን ዋልክ ወዳጄ?”
ሰውዬው - “ደህና እግዚሃር ይመስገን፡፡ ደህና ውለዋል አለቃ?”
አለቃ - “ደህና ነኝ፡፡ ከወዴት ትመጣለህ ወዳጄ?”
ሰውዬው - “ከምፃ” አላቸው…(“ጣ” የሚባለው “ፃ” አለው ማለት ነው)
አለቃ - “ምን ይዘሃል?”
ሰውዬው - “ድግፃ”…(ድግ “ጣ” የዛፍ ዓይነት ነው)
አለቃ - “በል መንገድ መትቶሃል፤ ምሣ እንብላ” አሉትና ተያይዘው ወደ አለቃ ቤት ሄዱ፡፡
ምሣ ቀርቦ እየበሉ ሳሉ፣ ሰውዬው ወጡ ጨው እንደሌለው ልብ ብሏል፡፡
ወደ አለቃ ቀና ብሎ፤
“ትንሽ ፀው ያስፈልጋል - ፀው አምጡ; አለ፡፡
ይሄኔ አለቃ፤
“አይ እንግዲህ! “ፀ”ን ምን ብንወዳት እወጥ ውስጥ አንጨምራትም?” አሉት፡፡
*   *   *
አንድ ቀን አለቃ ከሚስታቸው ከወይዘሮ ማዘንጊያ ጋር እየተጨዋወቱ ሳሉ፤ አንድ የጐረቤት ህፃን ልጅ ወደእነ አለቃ ቤት ይመጣል፡፡
ልጁ ረባሽ ነው፡፡
በአንፃሩ የእነ አለቃ ገ/ሃና ልጅ ደግሞ ወደ ጐረቤት ቤት ሄዷል፡፡
ረባሹ የጐረቤት ልጅ የወይዘሮ ማዘንጊያን ብርጭቆዎች ሲነካካ ሁለቱን ሰበረባቸው፡፡
ወይዘሮ ማዘንጊያ በጣም ተናደዱና፤
“አሁንስ ይሄን ልጅ ምን ባደርገው ይሻላል አለቃ! እጁን በእሳት ላቃጥለው እንዴ?” አሉ፡፡
አለቃ ገ/ሃናም፤
“ማዘንጊያ፣ እዛም ቤት እሳት አለኮ!” አሉ፡፡
*   *   *
ጥፋት ለማንም አይበጅም፡፡ ለጥፋት መቆም መጨራረስንና ውድመትን እንጂ የሚያመጣው ረብ - ያለው ነገር አይኖርም፡፡ ለረዥም ዘመን የኖረ ጐረቤትን ማጥቃትም ሆነ ማጥፋት ምላሹን መርሳትና የእርስ በርስ እልቂትን መደገስ ነው!
“የማ ቤት ጠፍቶ፣ የማ ሊለማ
የማ ቤት ጠፍቶ፣ የማ ሊበጅ
የአውሬ መፈንጫ፣ ይሆናል እንጅ”
የተባለው ለተራ ፉከራና ቀረርቶ እንዳልሆነ ትክክለኛ አዕምሮ ያለው ሚዛናዊ ሰው ልብ ይላል፡፡
ወትሮውንም ቢሆን፤
ለጥፋት የቆመ፤ ዐይኑ ያለጥፋት አያይም፡፡
የጐረቤቱ ዕድገትና ልማት አይጥመውም፡፡
“እኔ ዶሮ ሳረባ አይቶ፣ ጐረቤቴ ሸለ-ምጥማጥ ያረባል!” ይላል አበሻ፤ ምቀኛን ሲገልፀው፡፡
ልማትን ልፋት ለማድረግ፣ ለውጥን ነውጥ ለማድረግ መሻት ከንቱና እኩይ ተግባር መሆኑን ልብ ያለው፣ ልብ የሚለው፣ ማንም ጅል የማይስተው፣ ጉዳይ ነው፡፡
ሉዓላዊነቱንና ህልውናውን ቸል ብሎ ሲነካ ዝም የሚል፣
“ባለቤቱን ካልናቁ
አጥሩን አይነቀንቁ!” የሚለውን ምሣሌያዊ አነጋገር የማያውቅ ብቻ ነው!
አያሌ መንግሥታት ሁለት ዋና ነገሮችን ሲስቱ ለውድቀት ይዳረጋሉ፡- አንድም የዕብሪትና የንቀት፤ አንድም የድንቁርናና የአጓጉል ዕውቀት ሰለባ ሲሆኑ፡፡ የሁሉም ውጤት ድቀት ነው!
“ዐባይ ሞልቶ፣ ጣና ሞልቶ፣
ላጨኝ በደረቁ
          እራሴን ሳያመኝ፣
          ነደደኝ መናቁ!”…
(“መ” እና “ና” ይጠብቃል) የሚልን ህዝብ እሳቤ የማያውቅ የውጪ ኃይል ታሪክንም፣ ጂኦግራፊንም፣ ባህልንም የዘነጋ ነው፡፡
የውስጥን ችግር ለማስታገስ፣ ወደ ውጪ መተንፈስ የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት የፖለቲካ መላ ነው፡፡ ሆኖም የዘመነ - ብሉይ እንጂ የዘመነ - ሐዲስ ፖለቲካ አይሆንም፡፡ “አሮጌ ወይን በአዲስ ጋን” ነው፡፡ በሁሉም ረገድ ክፉና ደግ ያየች እንደኛ ያለች አገር፤ ከእነ ህዝቦቿ ህልውናዋን ለማስጠበቅ፣ ብልህነትን ከትዕግሥት፣ ዕውቀትን ከድፍረት አቅፋ የምትራመድ ታሪካዊ አገር ናትና፣ ዋና ማዕቀፏን ዲፕሎማሲያዊነቷን አድርጋ የምትጓዝ የጀግኖች ምድር ናት:: ባንድ ፊት ድህነትን፣ ባንድ ፊት ኮሮናን እየተዋጋች በጥኑ ልብ የምትቀጥል፤ አንድ አራሽ፣ አንድ ተኳሽ፣ አንድ ቀዳሽ ያሏት አገር ናትና ያሻችውን ሳትቀዳጅ፣ የጀመረችውን ዳር ሳታደርስ ከቶም ወደ ኋላ አትልም!

Read 14261 times
Administrator

Latest from Administrator