Saturday, 25 July 2020 15:59

የዘመ’ነ ይድናል

Written by  በእፁብድንቅ ስለሺ
Rate this item
(0 votes)

  የበይነ - መረብ ምጣኔ ሀብት ይዞታና አቅጣጫ
                     
            በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እንዳሁኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለም በአንድ የልብ ትርታ፣ በተመሳሳይ የፍርሃት ድባብና የጭንቅ ሲቃ እንዲሁም በጋራ የመድሃኒት ተስፋ፣ ስንቅ የያዘበት ወቅት ነበር ማለት ያስቸግራል። ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ትላልቅ ችግሮች፡- ጦርነት፣ ረሃብ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሁም መለስተኛ ቸነፈሮች አንድን አካባቢ ወይም ክፍለ ዓለም ለይተው ይጎዱ እንደሆን እንጂ፣ ባንድ ጊዜ በሁሉም አገር፣ ዜጎች ከሥራና ትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለው፣ እቤት የዋሉበት አጋጣሚ አልታየም፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የፍርሃት ድባብ ዓለምን አጠላባት። ደመና ሰንጥቀው አየር አቋርጠው ይበሩ የነበሩት ግዙፍ አየር መንገዶች አረፉ። የቅምጥልና የድሎት የባህር ላይ መዝናኛ መርከቦች፤ የደዌ መራቢያ የስጋት ቀጠና ሆኑ።የመስህብ ቦታዎች ጭር አሉ። ሰው እንደ ዥረት የሚፈስባቸዉ የዓለም ታላላቅ ከተማ አውራ ጎዳናዎች ኦና ሆኑ። ከመሬት ተስፈንጥሮ ጨረቃ ላይ ያረፈዉ የሰው ልጅ፤ ዓለመ ዓለሙን ለመረዳት መንኮራኩር አስወንጭፎና ሰው አምጥቆ እያሠሠ ያለው ዓለም፣ ለረቂቅ ተህዋስ ሰለባ ሆኖ እስካሁን እጁን እንደሰጠ ነዉ። ምናልባት የመድሃኒት ቀማሚዎች ድካም ፍሬ ካፈራ የክትባት፣ የማስታገሻ ከተቻለም የመፈወሻ መድኃኒት ይገኝ ይሆናል። እስከዚያ ድረስ ዓለም በአዲሱ ጉንፋን እንደ ገብስ ስትታመስና እንደ ደረቆት ስትቆላ መቀጠሏ ነው። ከአሥር አእላፋት (ሚሊዮን) ሰዎች በላይ በበሽታው መለከፋቸው በምርመራ ተረጋግጧል። ወደ አምስት መቶ ሺህ ሰዎችም ለሞት ተዳርገዋል። ይህ እንግዲህ በየቤቱ የሚያስለውን፣ በተዘጋ ቤት ውስጥ ብቻውን ሲያጣጥር የሚውል የሚያድረውን አይጨምርም። በጤና ሥርዓቱ የታየውን ብቻ እንጂ።
ታዲያ የዓለም ጤና ብቻ ሳይሆን፣ የምጣኔ ሀብት ሥርአትና የሰዎች ማህበራዊ መስተጋብር ሳንካ ገጥሞታል። ማምረቻ ቤቶች የንግድ ሰንሰለቱ በመቆራረጡ አንድም ግብአት በጊዜው አያገኙም፣ አንድም ምርታቸውን ለገበያ ለማውጣት ተቸግረዋል። በያዝነው የፈረንጆች ዓመት፣ የሸቀጥ ንግድ ከ13% እስከ 32% እንደሚያሽቆለቁል የዓለም ንግድ ድርጅት ትንበያ ያሳያል። የአቅርቦት ችግር አለ። በተለይ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት የተስፋፋዉ ሉላዊነት፤ “ቻይና ተመርቶ በሳምንት ቶሮንቶ” ሊባል በሚችል መልኩ፣ አምራችና ደንበኛ በተለያየ ቦታ መገኘታቸውና የአቅርቦት ሰንሰለት (ልዩ ልዩ ግብአቶች ከብዙ ቦታ የሚፈሱበት ቦይ) መበጣጠሱ ብዙ ኪሣራ አስከትሏል። የፍላጎትም ችግር አለ (የመጓጓዣ ዘርፉ፣የጉብኝት ዘርፉ፣ የነዳጅ ዘይት አምራቹ በእጅጉ ተጎድቷል)። ከ165 አገራት ውስጥ ወደ 1.5 ቢሊየን ተማሪዎች በወረርሽኙ ምክንያት ከትምህርት ቤት ርቀዋል። የተ.መ.ድ ሳይንስ ትምህርትና ባህል ድርጅት እንደዘገበው፤ ይህ ቁጥር 87% የሚሆነውን የዓለም ተማሪ ይሸፍናል። የተሻለ የበይነ መረብ አቅርቦትና ተጠቃሚ ባሉባቸው አገራት ከቤት ውስጥ ሆኖ ጥናትን ለመቀጠል ተችሏል። የእጅ ስልክ እና መቀምር (ኮምፒውተር) እንደ ልብ በማይገኝበት፣ የበይነ መረብ አገልግሎትም ባልተስፋፋበት፣ ትምህርት በእጅጉ ተስተጓጉሏል። በድሃና ሀብታም ቤተሰቦች (አገራት) መካከል ልጆች ወደፊት በዚህ ቀውስ ምክንያት የተለያየ እውቀት ስለሚኖራቸው፣ በሥራ ገበያው መበላለጥን ያስከትላል። ይህ ክፍተት ህይወታቸውን ሙሉ ዝቅተኛ ደመወዝና ያነሰ ልምድ እንዲኖራቸዉ ያደርጋቸዋል (አንድ ሰኔ የነቀለውን አሥር ሰኔ አይተክለውም እንደሚባለው)። ከዚህም ሌላ በወረርሽኙ የተነሳ ባደጉ አገራት የሥራ አጡ ቁጥር በብዙ እጥፍ ስላደገ መንግሥታት ድርጎ መስፈር ጀምረዋል። ወደ እኛ አገር ስንመጣ፤ ምንም እንኳ ወረርሽኙ ከሌላው ዓለም ዘግይቶ የገባ ቢሆንም ሰሞኑን የሚወጡት ዘገባዎች፤ የበለጠ የግለሰቦች ጥንቃቄ፣ የተሳለጠ የጤና ተቋማት ቅንጅትና የላቀ መንግሥታዊ አመራር የሚሹ ይመስላሉ።
በዚህ ጽሁፍ የምናተኩረው በኢትዮጵያ የበይነ መረብ ምጣኔ ሀብት ይዞታና ዕድሎች ላይ ነዉ። ምንም እንኳን አሁንም በአዲሱ የጉንፋን ወረርሽኝ ጥላ ስር የምንኖር ቢሆንም፣ እስካሁን ባሉት ተሞክሮዎች ገሃድ ከውጡ ጉዳዮች አንዱ ኢኮኖሚዎች ጠንካራ ሆነው እንዲዘልቁ፣ ማህበረሰቦች ይበልጥ አይበገሬ እንዲሆኑ፣ ወረርሽኙንም ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲዋጉ ለማድረግ የበይነ መረብ ምጣኔ ሀብት (Digital Economy) እጅግ ወሳኝ ሆኖ ተገኝቷል። የበይነ መረብ ምጣኔ ሀብት በዚህ ጽሑፍ፤ ማንኛዉም የስልክና ከበይነ መረብ ጋር ተያያዥ የሆኑ የመረጃ- መገናኛ ስልቶችን በመጠቀም የሚካሄድ የገንዘብ ዝውውር፣ ምርትና አገልግሎት፣ ማስታወቂያ እንዲሁም ግብይት ሊሆን ይችላል። የበይነ መረብ ምጣኔ ሀብት፤ ለግላዊ ጥቅም፣ ለንግድና ለሕዝብ አገልግሎት ጉዳዮች፣ አዳዲስ የመገናኛና የመረጃ አዉታሮችን ጥቅም ላይ ማዋል ነዉ። ይህም በኤሌክትሮኒክስ ንግድ አማካይነት የንግድ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ማስተላለፍን ያመለክታል።
የበይነ መረብ ምጣኔ ሀብት እውን የሚሆነው የመገናኛ መሠረተ ልማትና መተግበሪያዎች፣ አውታረ መረቦች ተሟልተው ሲገኙ ነው። የዘመኑ የተግባረ ዕድ ውጤቶችን ከረቂቅ መተግበሪያዎች ጋር በማቀናጀት የሚከወን ነው። የበይነ መረብ ምጣኔ ሀብት መምጣት ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ፣ ምርትና አገልግሎትን በመጨመር፣ የስራ ዕድልን በማስፋትና የንግድ ሥራ ውጤታማነትና ተወዳዳሪነትን በመጨመር ማህበረሰባዊ ኑሮን ለማሻሻል ተችሏል። ዛሬ በዓለም ላይ ቁንጮ የሚባሉ ድርጅቶች (ማይክሮሶፍት፣ አፕል፣ አማዞን፣ ፌስቡክ ወዘተ) ምርታቸውም ሆነ አገልግሎታቸው በይነ መረብ እና በበይነ መረብ ለበይነ መረብ ነው። የወደፊቱ ዓለም በስልኮቻችን ውስጥ ነው። ኢትዮጵያም ምጣኔ ሀብቷን አዘምና፣ በህግና ሥርዓት ወደ በይነ መረባዊ ምጣኔ ሀብት ቀልጠፍ ብላ ካልገባች፣ ሀብት አይገባላትም። በዘመናዊ ዓለም ተወዳድራ ለማሸነፍ የምጣኔ ሀብት ሥርአቷን አሃዛዊ ማድረግ አለባት። ዜጎቿም በተድላ መኖር ይችሉ ዘንድ ከሰፊዉና በፍጥነት እየተለዋወጠ ከሚገኘው የዓለም ክፍል መቀላቀልና ዕድል መሻማት ይኖርባቸዋል። ሌላዉ ዓለም በብርሃን ፍጥነት እየተፈተለከ እኛ በኤሊ ጀርባ የምንፈናጠጥ ከሆነ ግን በጉስቁልና ተወልደን፣ በድህነት አድገን በረሀብ እንሞታለን።
እስካሁን ባለን ተሞክሮ በጣት የሚቆጠሩ ድርጅቶች ብቻ በይነ መረባዊ ምርትና አገልግሎት ይሰጣሉ። እነዚህ ጅማሮዎች በገንዘባዊ ክፍለ ምጣኔ ሀብት፣ በመጓጓዣ፣ እንዲሁም በመዝናኛው ዘርፍ ናቸው። ይህ ሙከራ በዓይነት በዝቶ፣ በጥራት ልቆ እናየዉ ዘንድ የፖሊሲ ድጋፍ ይሻል። አሁን ባለው ወረርሽኝ ሰበብ በኢትዮጵያ ውስጥ ከድህረ ምረቃ ተማሪዎች በስተቀር ሌላው ሁሉ ትምህርቱ ተስተጓጉሏል። በቅርቡ የተጀመረዉ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን በትሥሥር ገጾች የማስተማሪያ ጽሁፎችን ማሰራጨት የሚያበረታታ ቢሆንም፣ ተማሪዎች በየገጠሩ ያለ በቂ ስልክና መቀምር የሚገኙ በመሆናቸዉ፣ የተሟላ የርቀት ትምህርት ለማካሄድ የማይቻል አድርጎታል፡፡ ሙከራው  ጥሩ ቢሆንም፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦትና የየዘመ’ኑ ስልኮች ወይም የግል መቀምሮች እንደ ልብ የማይገኙ በመሆናቸዉ  ብዙ ርቀት አያስኬድም።
በኢትዮጵያ በቅርቡ የተከናወኑ ሦስት ክስተቶች፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በበይነ መረብ ውስጥ ለመማገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ ብዬ አስባለሁ። አንደኛዉ፤ የግል ድርጅቶች በመገናኛና መረጃ አቅርቦት አገልግሎት ላይ እየተጋበዙ መሆኑ  ነዉ። አገልግሎቱን በማስፋት፣ ውድድር በማጦፍ፣ ጥራቱንም ከፍ በማድረግ የመረጃና ግንኙነት ዘርፉን ማራመድ ይቻላል ብዬ አስባለሁ። የቴሌ መስፋፋትና መጠንከር ለብዙ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች እርሾ ስለሆነ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ህዝባዊ ተቋማት፤ በትምህርት፣ በምርትና በንግድ የተሻለ ተግባር እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል። ረዥም ጊዜ የሚወስዱ አሰራሮች በደቂቃ ውስጥ ይከናወናሉ፡፡ መረጃ በገፍ እንደ ልብ ይፈሳል። ውሳኔዎች በነዚህ መረጃዎች ላይ ተመስርተው በቅልጥፍና ይተላለፋሉ። ስለዚህ ጊዜ በመቆጠብ፣ ቁስ ባለማባከን፣ እንዲሁም የቦታ ርቀት ሳንካን በማስወገድ ማለፊያ ሥራ ያከናውናል ማለት ነው። መዘመን ከብዙ ችግር ይታደጋል።
ሁለተኛው ተያያዥ ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በንግድ ባንኮች ጥሬ ገንዘብ በማውጣት ላይ የጣለው ገደብ ነው። ላይ ላዩን ሲያዩት፤;ምጣኔ ሀብታችን በበሽታ ሰበብ ተቀዛቅዞ፣ ሳል የገንዘብ ፍሰትን መቀነሱ ይበልጥ አያባባብስም ወይ?” የሚል ጥያቄ ያጭራል። እውነት ነው፣ በተባበረዉ የአሜሪካ ግዛቶች፣ በጃፓን እንዲሁም  በአዉሮጳ በብዙ ትሪሊዮን ዶላር የሚቆጠር የማነቃቂያ ገንዘብ ወደ ገበያ ተነዝቷል። ለሥራ አጦች በድጎማ፣ ገቢ ለቀነሰባቸው ድርጅቶች ከወለድ ነጻ (ዝቅተኛ ወለድ) ብድር፣ እንዲሁም እንደ ቦይንግ ላሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ከፍ ያለ ድጋፍ ሲደረግላቸዉ እናያለን። ይሄ ሁሉ ቢደረግም ካሽ ከባንኮች ቁጥጥር ወጥቶ ትራስ ዉስጥ የሚደበቅ ሳይሆን በየባንክች ሳንዱቅ ሆኖ ካንዱ የሂሳብ ባለቤት ወደ ሊላው እየተዘዋወረ ንግድን ያሳልጣል እንጂ ባንኮችን በጥሬ ገንዘብ በማራቆት የገንዘብ ሥርዓቱን ማናጋት ላይ አይደርስም።
 ታዲያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣዉን መመሪያም ጠጋ ብለን ስንፈትሸው፤ በቀን የሁለት መቶ ሺ ብር ገደብ መጣሉ፣ ከባንኮች እይታ ዉጭ ያለ ሥራ የሚቀመጥን የወረቀት ገንዘብ ይገድባል:: ይህ ዜና ሲወጣ በአደገኛ ወረርሽኝ ወረርሽኝ ኢኮኖሚ ውስጥ የገንዘብ ፍሰት መገደብን ተገቢነት እጠይቅ ነበር። ነገር ግን ዝቅተኛ ገቢ ላላቸዉ በቀን 200,000 ብር  ያን ያህል አሉታዊ ተጽዕኖ አይኖረውም። ለመካከለኛና ለትላልቅ ንግዶች ደግሞ ጥንቱንም በሲ.ፒ.ኦ፣ በቼክና በሌላም፤ ከጥሬ ገንዘብ ውጭ በሆኑ ዘዴዎች ክፍያ የሚፈጽሙ በመሆናቸዉ አዲሱ መመሪያ ይበልጥ ከጥሬ ገንዘብ ያፋታቸዋል እንጂ የንግድ ሥራቸዉን አያስተጓጉልም እላለሁ፡፡ ይህም በሙዳዬ ንዋይ ዉስጥ የሚከናወነዉን የገንዘብ ዝውውር ያሳልጣል። ይህ ባይሆን ግን ብዙ ጥሬ ገንዘብ በየጆንያዉ ተጠቅጥቆ፣በየሳጥኑ ታጭቆ፣ በትራስና ፍራሽ ሥርም ተደብቆ  ለአገር የሚሰጠዉን ጥቅም ያባክናል። ለምን ቢሉ? አንድ ሰዉ መቶ ብር ባንክ ዉስጥ በቆጠበ ጊዜም፣ ባንኩ ለሌላ ያበድራል፣ የተበደረዉ ደግሞ ለስራ ያውለዋል። እንዲህ እንዲህ እያለ--ትራስ ዉስጥ ቢቀመጥ ምንም የማይፈይደዉ ብር የብዙ ሰዎችን ህይወት ለመለወጥ ይችላል። የተደበቀ ገንዘብ መሐን ነዉ። የብሔራዊ ባንክ ሌላ ተያያዥነት ያለው ጠቀሜታ ደግም ሰዎችን በወረቀት ገንዘብ ንክኪ ለበሽታ እንዳይጋለጡ የሚያግዝ መሆኑ ነዉ (የወረቀት ገንዘብን መጠቀም ከቀነሱ)። ብሔራዊ ባንክ የወረቀት ገንዘብ ከባንክ የማዉጣትን ወሰን በተመለከተ ያለው አዲስ ደንብ ግብይትን፣ የባንኮችንና የንግድ ስራን ወደ በይነ መረባዊ ለማዛወርም ተፅእኖ ያደርጋል። በዚህ  ወቅት የዲጂታል ግብይት ንክክኪን ስለሚቀንስ የበሽታ ተህዋስያን ከሰዉ ወደ ሰዉ እንዳይዛመቱ ይረዳል። የበይነ መረብ ምጣኔ ሀብት ይበልጥ እየዳበረ ሲሄድ ደግሞ  ሙስናን ለመቆጣጠር፣ የገንዘብ ንጥቂያንም ለመቀነስ ይረዳል። ታዲያ ዘመናዊ መንታፊዎች በበይነ መረብ ላይም ስላሉ የተጠናከረ የሳይበር ቁጥጥር ያስፈልጋል።
ሦስተኛው በኢትዮጵያ ለበይነ መረብ መፋፋት ሊረዳ የሚችለዉ ጉዳይ አዲስ የወጣውና በህዝብ እንደራሴዎች የጸደቀዉ የኤሌክትሮኒክ ግብይት አዋጅ ነዉ። ይህ የምስራች ነው! የጨዋታውን ህጎች በመግለጽና የዲጂታል ክፍያ ሥራን በመምራት፣ የንግድ ሥራዎችንና የህዝብ አገልግሎቶችን ወደ አዲሱ ኢኮኖሚ ለመቀየር እንደ ትልቅ ግብአት ሆኖ ያገለግላል፡፡ የዲጂታል ኢኮኖሚ ደንብና መመሪያ ይፈልጋል። አቅጣጫና እገዛም ይሻል። ስለሆነም የዚህ አዋጅ መዉጣት ንግድን በማሳለጥ ምጣኔ ህብቱን ከማገዙም ባለፈ፣ ህገ ውጥ የገንዘብ ዝዉዉርን ይቀንሳል። የግብር ማጭበርበርን ያስቆማል። ሙስናን ይቀንሳል። አነስተኛ የንጥቂያ ወንጀሎችንም ያስወግዳል፡፡
በአንጻሩ ማለፊያ ቁጥሮች ሰብረዉ በመግባት የበይነ መረብ መዝባሪዎች ጉዳት ሊያደርሱ ስለሚችሉ የተጠናከረ የሳይበር ደህንነት ያሻል። የወደፊቱ ዓለም በይነመረብ ውስጥ ነው። እራሱን ወደዚህ አዲስ ደማቅ ዓለም ውስጥ ለማስገባት የሚያመነታ ቢኖር፣ ካለፈው አካላዊ ዓለም ጋር ተጣብቆ ይቀራል። በይነ መረባዊ መረጃዎች፤ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ለማምረት ዋና ግብአት እየሆኑ ሲመጡ የዘመነዉ አትራፊ፣ የተንቀራፈፈዉ ከሳሪ መሆናቸው የማይቀር ነዉ። ይህ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዝግመተ-ለውጥ ተፈጥሯዊ መንገድ ነው። ግለሰቦች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ አገራት  በዕውቀት ዳብረዉ፤ በአሠራር ተሻሽለዉ ወደ በይነ መረቡ ዓለም መግባት እየመጣ ካለዉ ዓለማዊ የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ሞገድ ንዉጽዉጽታ ይታደጋቸዋል። ይህም በትምህርት ሥርአት፣ በፖሊሲ ለዉጥ፣ እንዲሁም በማህበራዊ ንቃት ማሳደግና በተሰላ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ሊከወን ይችላል፡፡
ዘጋጁ፡-ጸሀፊዉን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል::


Read 2629 times