Saturday, 25 July 2020 16:10

ሰረገላ ሀሳብ

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(1 Vote)

    የምሽት ከዋክብትን የማሳደድ  ልማድ የተጠናወታቸው ሁለት ጥንዶች ዛሬም ከተንጣለለው የመኖሪያ ጊቢ ውስጥ እየተዘዋወሩ አስሬ  ቢያንጋጥጡም ሰማዩ እንደተዳፈነ ነው፡፡ ሁሌም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይከራከራሉ፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ በሰከነ መልኩ ሀሳብ ይለዋወጣሉ:: በተለይም ሐይማኖት ቅብጥብጥ ባህሪዋ ሰከን የሚለው በዚህ ወቅት በመሆኑ ግሩም የሆነ የመንፈስ ስምረት ይፈጥራሉ፡፡
አለማየሁ የከዋክብቱ መሰወር ሁሉም ነገር እንደተጠበቀው እንዳልሆነ አምኖ ስለ ተፈጥሮ ተቃርኖ ያብሰለስላል፡፡ ድንገት “እኔ የምለው? ሀይሚ!...” አለና አይኖቹን ወደ ሰማይ ሰቀላቸው፡፡
ትከሻዋን ሰበቅ ዳሌዋን ነቅነቅ አድርጋ፤ “ወዬ!... የኔ ፍቅር!” አለችው፤ በስስት እየተመለከተችው፡፡
“ህይወትን በምን ትተረጉሚያታለሽ?” አለ ወደ ውስጡ እየተመለከተ…  “አየሽ አንዳንዴ ታሳሳኛለች…” ከማለቱ ታቋርጠውና፤
“እየውልህ ውዴ፤ ከምኔው እንደለኮስኳት ባላውቅም ህይወት ሲጋራ ናት፤ ታማኝ አገልጋይ፡፡ ስትስባት የምትሳብ፡፡ ስትምጋት የምትማግ፡፡ ብቻ ከአንተ የሚጠበቀው መለኮስና እንዳትጠፋ ደጋግመህ መምጠጥ ብቻ ነው፡፡ ምጠጣት!... ምን አስፈራህ፤ መግምጋት፡፡” በማለት በስርዓት ወደተከረከሙ ጽዶች ዘወር አለች፡፡
አለማየሁ “ለነገሩ ቁሮ የበዛበት ተግዳሮቷ አሰልቺ ቢሆንም የምትወሰነው በልኳ ነው፤ ጥቅጥቅ ጨለማ  ጭላንጭሏ ያማልላል፡፡ እናም ኑሮ ብርሃንን ማሳደድ ይሆንብኛል:: የተጋለጠ ፍለጋ፡፡ ምናልባት በላብህ እደር ተቃርኖ ይሆን?------- እላለሁ” አለና አንገቱን ሰበረ፡፡
ሃይማኖት “እየውልህ፤ በራስህ ስልት ከቃኘኸት በስፍሩ ልክ ትከፍልሃለች፡፡ ይሄኔ የእሴትን አስፈላጊነት ትረዳለህ፤ በእርግጥ የጠራ ምልከታ ብርቱ ከሆነ የመተግበር ጥማት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ይሄ የነገሮችን መሆን ወይም አለመሆን ይወስናል:: ምርጫም፣ ግዴታም ነው፡፡ አለማለም አይቻልም…
ምትሃት ይሉት ነገር ህሊናህን ቢወጥርህ አትስጋ፡፡ የትኛውም ህልም እስኪጠራ ጥንውቱ ልክ የለውም፡፡ ደርዝ ሲይዝ ከእ ነአካቴው ትዝ ላይልህ ይችላል:: …. ልክ ሲያድግም፤ ሲቆረጥም ስሜት አልባ እንደሆነ ጥፍር፡፡ ቢያንስ ከቀን ቀን እድገቱን እንታዘባለን እንጂ ሲለጠጥ፣ ሲመዘዝ እድገቱን መቆጣጠርም ሆነ ሂደቱን በእያንዳንዱ ቅጽበት ማጣጣም አንችልም፡፡ ብዙ ነገሮች የአንተ ቢመስሉህም ታጣቸዋለህ፡፡ ያም ሆኖ ህይወት የተፈጥሮ ረድኤቷን አትነፍግህም፡፡ ይብዛም ይነስ ግድ የላትም፤ ግን እኮ የበረከቷ ምንጭ  ለህልውናዋ አስፈላጊ ስለሆነ እንጂ ለአንተ አስባ ላይሆን ይችላል፡፡ ማለትም የተፈጥሮ መገለባበጥ (እንቅስቃሴ፤ ኡደር) በራሱ ህልውናችን ላይ ሚናውን ይጫወታል:: የነገሮቻችን መለዋወጥ (የፊት፣ የቁመት፣ የቁመና እና የጸጉር እንዲሁም የሰውነት ቅርጽ…) በጠቅላላው በተፈጥሮ መገለባበጥ የሚፈጠር እንጂ ለእያንዳንዳችን የተለየ የለውጥ ሕግ ስለተቀመጠ የሚፈጠር አይደለም፡፡ የጠቅላላ ተፈጥሮ መለወጥ በእኛ ውስጥ ይተገበራል፡፡”… ጣቶቿን አንቃቃቻቸው፡፡
“ልክ ብለሻል የከዋክብቱ መሰወር ለጨለማው ብርታት እንደሆነው ማለትሽ መሰለኝ… ምናልባትም የነገሮች የጋራ ጉዳይ የሕልውና ምንጭ ሆኖ ይሆን…” እያለ ጺሞቹን አሸት አሸት ያደርጋል፡፡
“ህልምም እንዲሁ ነው፡፡ የአንተ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ታየዋለህ ወይስ ያይሃል?... ማነው መሪ?... ህልምህ ወይስ ህሊናህ?...ያው ህልም ከሌለ ህሊና ምንድን ነው?... ህሊናስ ከሌለ ህልም ቦታው የት ነው?... ህይወት የህልም ውጤት እንጂ የህሊና ቋት አይደለችም፡፡ ቃልም እኮ ህልም ነው፤ አበባ፡፡ ጥሩ ህሊና ሲያገኝ ይፈካል፡፡ እና የፈካ ነገር ሁሉ የጥሩ ህልም ውጤት አይመስልህም? ልክ ውብ ፍጥረትን ውብ ተፈጥሮ እንደሚፈጥረው ሁሉ፡፡ አይመልስላትም፡፡
ነገር ግን ጽሞናው እየማረካት ይበልጥ ሀሳቧ ላይ አተኮረች፡፡ አዘውትራ እንደምታደርገው አንዳች እውነት ማሰሱን ቀጠለች፡፡ የምሽቱን አይረሴነት ለመመዝገብ ልቦናዋን ከፈተች፡፡
አካባቢዋን እየቃኘች “በእርግጥ ማህበረሰብ በምድረ በዳ ላይ ሕይወት ለምልማ፣ ለጥ ባለ ቃጠሎ አሸዋ ላይ ውብ አበባ ፍክታ የማሳየት ነባር ልማድ ቢኖረውም፣ ለተፈጥሮ ግን እንዲህ ያለው ጨዋታ ሕጓ አይደለም፡፡ ማህበረሰብ የተፈጥሮን ንፍገት እና ጭካኔ የሚያክምበት የሕልውናው መታገጊያ  ሆኖ ይታየኛል፤ ስንቅ፡፡ ወፉ ሰው እራሱን የነጠለበት ተረክ አይመስልህም? ነው እንጂ! ነው (የእሱን መልስ አልጠበቀችም)፡፡ ታዲያ ይህ ጉዳይ ሰውን እልህ ውስጥ ከቶታል፤ የተቆጣጠረችውን ተፈጥሮ ሃይሏን ለመንጠቅ ይኳትናል፡፡ ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ብዙ ርቀት አስጉዞታል፡፡ ልክ ተፈጥሮን ስትገለባበጥ ሰውን እንደምትቆጣጠረው ሁሉ ሰውም መገለባበጥ ሲጀምር ተፈጥሮ እየገላለጠ ነው፤ እየለዋወጣት፡፡”  ወደ ውስጧ ዘልቃ የሀሳብ ቋጠሮ ይዛ ብቅ በማለቷ እየተገረመች፣ ፈገግ እያለችም ዝምታውን እንዲሰብር በአይኖቿ አጫወተችው፡፡ እሱም ቢሆን የነገሮች ስርዓታዊነት በግብታዊነት እንዳልመጣ ተገንዝቧል፡፡  
ያሰላሰለው ሀሳብ ድንገት ሲተራመስ ተሰማው፡፡ ጥቂት ካማጠ በኋላ “በእርግጥ ዓለማት ሁሉ የጥሩ ህልም ውጤቶች  ናቸው፤ የህልሙ ባለቤት ማንም ይሁን ማንም፡፡ በፍጥረት ደረጃ ሁሉም ፍጡር ጥሩም መጥፎም አይደለም፡፡ ይህን ጉዳይ ጉዳዬ ብሎ የሚብሰለሰለው ሰው ብቻ ነው፤ የምግባር ጣጣ ሳይሆን ይቀራል? ቋንቋን ከመልመዱ ጋር አብሮት ወደ ህሊናው የዘለቀ የማህበረሰብ ሕግ ይመስለኛል፡፡ እንጂ እማ ተፈጥሮ ለዚህ ጉዳይ ግድ ያላት አይመስልም:: ለነገሩ ተፈጥሮ ሚዛን የምታስጠብቀው በተቃርኖ ነው፡፡ የሰው ልጅም የዚህ ሰለባ አንዱ አካል ነው፡፡ በርካታ ሰዋዊ እሴቶቹን የገነባው በተቃርኖ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ፍርዱም ሚዛኑም ተቃርኖ ነው፡፡” በማለት አከለበት፡፡
“በእርግጥ አንዳንድ ጉዳይ አለ፡፡ ሲርቁት የሚከተል፤ ሲከተሉት የሚርቅ፡፡ ልክ እንደ ጥላ------ ያለ፡፡ ከዛም ከዚህም ያልሆነ፡፡ ሰውም እንደዛ ይመስለኛል፡፡ ተነጥሏልም፤ ተዋህዷልም፡፡ አንድም፣ ሁለትም ነው:: እንዲህ አይነት ጉዳዮች ላይ ማተኮር የተፈጥሮን የማዕከላዊ ነጥብ ለመገንዘብ የሚረዳ ይመስለኛል፡፡ አሁንነት ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ነገ እና ትናንት፣ ላይ እና ታች፣ ግራ እና ቀኝ እንዲሁም ፊት እና ኋላ  የአሁንነት ተቀጽላዎች ናቸው፤ ያለ ዛሬ (አሁን) ህልው የማይሆኑ…” ትንታ ንግግሯን  ገታው፡፡ በሀሳቧ ተማርኳል… ጊዜን በመዳፏ ስትጨብጠው በአይነ ህሊናው ተመለከተ:: አደነቃት፡፡ እጆቹን ከቆዳ ጃኬቱ ኪስ ከተታቸው፡፡ ደጋግሞ መላ አካሏን በአድናቆት ተመለከተው፡፡ ውስጧን ዘልቆ አጣጣመው፡፡ “ውብ ናት!” አለ፤ በልቡ፡፡
እንዲህ እየተናበቡ የሚሰማቸውን ከተጫወቱ በኋላ ጥቂት እርምጃዎች ወደ ኋላ ገስግሰው ወደ ቤት ገቡ፡፡ የቋጠሩትን ይፈቱ ይሆን?.... ወይስ የወጠኑትን ሀሳብ ይፈታትሉ?....
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1202 times