Saturday, 25 July 2020 16:16

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)


             ‹‹ዘንዶው ከዋሻው ብቅ ባለ ጊዜ የትንሽቱ ከተማ ሕዝቦች ከተራራው  ተሰበሰቡ›› ይላል፤ አንድ የግሪክ አፈ-ታሪክ፡፡ ራሳቸውን ከውስጣቸው በመረጡ ካህናቶቻቸው በኩልም፡-“ግብራችንን ተቀበል” ብለው ምስኪኗን ቆንጆ ለዘንዶው አሳልፈው ሰጡት፤ ሳይጠየቁ፡፡ በዓመቱ ሲመጣ ደግሞ ሌላ ወጣት ገበሩለት:: …በቀጣይም እንዲሁ::… ዘመናት አለፉ፡፡ ወጣቶቹ መንምነው የንጉሡ ልጅ ብቻ ቀረች:: ዘንዶው ሲመጣ የሚሰጡት ባለመኖሩ ህዝቡ በፍርሃት ተንቀጠቀጠ፡፡… አልቀረም፤ መጣ፡፡
‹‹የምንገብረው የለንም›› አሉት፡፡
‹‹የንጉሡን ልጅ ስጡኝ›› አላቸው - ወደ ቤተ መንግስቱ ተጠግቶ፡፡ ንጉሡ አቻ የሌለው ተዋጊ ነበረና አንገት፣ አንገታቸውን መቶ አባረራቸው፡፡ ጎራዴውን እንደ ጨበጠም ወደ ተራራው ወጣ፡፡
 ‹‹እኔ ሳልሞት ልጄን አትበላትም›› እያለ ወደ ዘንዶው ቀረበ፡፡ ነገር ግን ከዘንዶው  ዓይን በፈለቀ ጨረር ጎራዴው ቀለጠበትና ባዶ እጁን ከፊቱ ቆመ፡፡
‹‹ጥሩ ጦረኛ ነህ፤ ግን ጥሩ ንጉስ አይደለህም›› አለው ዘንዶው፡፡
‹‹እንዴት?››
‹‹ንጉስ ማለት ጥሩ አባት ነው፤ ጥሩ አባት ልጆቹን አያበላልጥም፡፡ ህዝቦችህ የመጀመሪያዋን ልጅ ሲገብሩ “አይሆንም” ማለት ነበረብህ” …ንጉሡ አንገቱን ዝቅ አደረገ፤ በፀፀት::
ዘንዶውም በመቀጠል…
“ያ ዘንዶ የኔ አገልጋይ ነበር፤ ህዝቦችህ ጉቦ አስለመዱት፣ እየተመላለሰም ዋጣቸው፡፡… በርግጥ  ልጆቹ አልሞቱም” ሲል ተናገረ፡፡
የተደናገረው ንጉሥም “እ?…ያ ዘንዶ ሌላ ነበርን?...ልጆቹስ እንደምን ሊተርፉ ቻሉ?” ሲል ጠየቀው፡፡
“ነገርኩ’ህኮ እሱ ሞቷል። ሁሌም ልጅ ከዋጠ በኋላ ያንቀላፋ ስለነበር፣ አፖሎ ሆዱ ውስጥ እየገባ ያወጣቸዋል፡፡
“አፖሎ ማነው?”
“የኔ ልጅ… የብርሃን፣ የጥበብና የፍትህ አምላክ!”
“አንተስ?”
ማንነቱን ነገረው፡፡ መጨረሻ ላይ እንመለስበታለን፡፡
*   *   *
የጥንታዊ ፐርሺያ ሃይማኖት የነበረው ዞሮአስተረዝም (Zoroasterian religion)  ቅዱስ መጽሐፍ “The Avesta” እግዜር መጀመሪያ ያነጋገረው አዳምን ነው፣ እሱም በፍጥረታት ሁሉ ላይ ያዝዝ ዘንድ ስልጣን ሰጠው” ይላል፡፡ አቬስታ እኛ “አዳም” የምንለውን “Fair Yima” በማለት ሲጠራው፣ ፈጣሪውን ደግሞ “Ahura Mazda” ይለዋል፡፡
በጥንታዊት ቻይና ሚቲዎሎጂ ደግሞ ምድርና ሰማይ ከመፈጠራቸው በፊት ዕንቁላል የሆነ “rehaos” እንደነበረ ይተረካል:: የመጀመሪያው ሰው ፓንኩ (P’an-ku)ም ከቅዠቱ (Chaos) አስኳል እንደተፈለፈለ የሚገልጥ ጥንታዊ ጽሑፍ መገኘቱን የኦሬንታል ጥበብ ፕሮፌሰር የሆኑት አንቶኒ ክርስቲ በጥናታቸው ይገልፃሉ፡፡ ፓንኩ በተወለደበት ቅፅበት የእንቁላሉ ቅርፊት መሬትን ሲሆን፣ ነጩ ፈሳሽ ደግሞ ወደ ሰማይነት ተቀየረ፡፡
የተፈጠሩት ሰማይና ምድር በጣም የተጠጋጉ ስለነበሩ፣ የፓንኩ ቁመት አጭር ሆነ፡፡ ነገር ግን ክፍተቱ ለአስራ ስምንት ሺ ዓመታት ያህል በየቀኑ በአስር ጫማ እየጨመረ ከፍ፣ ከፍ አለ:: የፓንኩም ቁመት ያን ያህል ጨምሮ ግዙፍ ፍጡር ሆኖ ነበር:: ፓንኩ ሲሞት ሰውነቱ ተበትኖ ወደተለያዩ የተፈጥሮ ኤለመንቶች መቀየሩንም ትረካው ያስረዳል፡፡
በሳውዝ አሜሪካ የሚኖሩት የኢንካ ጐሳዎች ትውፊትም፣ ከፓንኩ ጋር የሚመሳሰል እንግዳ ፍጡር በምድርና በሰማይ መሃል እንደነበር ይናገራል፡፡ ይኸውም ፍጡር ለእያንዳንዱ ምድራዊ ብሔር መነጋገሪያ ቋንቋ፣ ለወንዶችና ለሴቶች በነፍስ ወከፍ ነፍስና የማንነት መለያ (Being and soul) ከሰጣቸው በኋላ በተለያየ ቦታ እንዲኖሩ እንዳደረጋቸው የትውፊቱ ቅጅ እንደሚያስረዳ፣ ፕሮፌሰር ክርስቶባል ደሞሊና በደቡቡ አሜሪካ ሚቲዎሎጂ ጥናት ላይ አስፍረዋል፡፡ ግብፃውያን፣ ቲቤታውያን፣ ፔሩቪያን፣ ሜክሲኮአውያንና ሌሎችም ተመሳሳይ ተረቶች አሏቸው፡፡
“መጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም ስጋ ሆነ” በማለት እግዜር፣ እግዜርን እንደፈጠረ የሚገልፀው የኛ መጽሐፍም፤ ከሌሎች ትርክቶች ጋር የሚቀራረብባቸው ምዕራፎች አሉት፡፡ ዞሮ ዞሮ አብዛኞቹ ጥናታዊ ተረቶች፤ መጀመሪያ የሰው ልጆች አባት አንድ መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን፤ ማጠቃለያው ሰው በራሱ ስህተት (ፓንዶራም ሳትረሳ) የራሱ ጠላት ለመሆን መብቃቱን ለማረጋገጥ የሚሞክር ነው፡፡
ወዳጄ፡- “ሁሉም ስህተትን ሰርተዋልና ይቅር በላቸው” ተብሎ እንደተፃፈው የማይሳሳት ማንም የለም፡፡ ስህተት ሲደጋገም ግን ስህተት መሆኑ ቀርቶ ጥፋት ይሆናል፡፡ ጥፋቱን የማይቀበልና ለመታረም ያልተዘጋጀ ደግሞ ለሌላ ጥፋት ከመነሳሳት አይቆጠብም፡፡
ወዳጄ፡- የአገራችን ፖለቲካም እንደዛ እየሆነ ነው፡፡ በመንግስት ኃላፊነትና በፀጥታ ማስከበር ላይ የተሰማሩ ሰዎች፣ ከወንጀለኞች ጋር በማበር፣ በንፁሀን ዜጐችና በንብረት ላይ የሚያደርሱት ጥፋት ጨርሶ ከለየላቸው የሀገር ጠላቶች የከፋ መሆኑን ታዝበናል፡፡ የውስጥ አርበኞች ከውጭ ጠላቶች ይብሳሉ:: በተለያዩ ሽፋኖች ቢንቀሳቀሱም እውነተኛ ተልዕኳቸው ግን ለውጥ አደናቃፊነት ከሆነው “የቀበሮ ባህታውያን” ህዝባችን ሊጠነቀቅ ይገባል:: የቀበሮ ባህታውያንን ካነሳን አይቀር፣ ድሮ የጣሊያኑ ማፊያና በጊዜው የነበረው መንግስት በተካረሩበት ጊዜ የሆነና የሰማሁት ነገር ነበር፡፡
ሰውየው ሃጢአቱን ሊናዘዝ ቤተ መቅደስ ሄዶ ከሳጥኑ (Confession box) ውስጥ እንደገባ፤
“ተናዘዝ፣” ተባለ፡፡
“አንድ ፖሊስ ገድያለሁ”
“ይቅር ይበልህ ልጄ” ብለው አሰናበቱት፤ አባ፡፡
ከሳምንት በኋላ መጣና…
“ሁለት ገድያለሁ” አላቸው፡፡ ኑዛዜውን ተቀብለውት ተመለሰ፡፡
 ለሶስተኛ ጊዜ ሲመጣ…
“ስንት?” በሚል ጥያቄ ተቀበሉት፡፡
“ሚስቴን እንደደበደብኩ ለመናዘዝ ነው” አለ፡፡
“ይቅር ይበልህ” ብለውት ተመለሰ፡፡
 እንደገና ሌላ ጊዜ ሲመጣ፡-
“ስንት?” ብለው ጠየቁት፤ እንደ በፊቱ፡፡
“መቶ ሺ ሊሬ” አላቸው፣ የሰረቀውን ገንዘብ::
“ስንት ገደልክ ነው የምልህ?” አባ ጠየቁት፡፡  
“እኔ’ኮ ስቀልድ እንጂ ሰው ገድዬ አላውቅም” አላቸው፡፡
“እሰይ!” እንደ ማለት ተበሳጩ፡፡
“ስራ ፈት!” ሰድበውት ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ አባ ራሳቸው በሽፋን የሚኖሩ ማፊያ ነበሩና!
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ንጉሡ ዘንዶውን “አንተ ማነህ?” ብሎ ሲጠይቀው፣ ሰማየ ሰማያትን በሞላ ብርሃን ውስጥ ሆኖ ፊቱን አሳየው፡፡ …ሻማሽ ነበር፤ ከልጁ ከአፖሎ በፊት የመጀመሪያው የፀሐይ አምላክ፡፡ ወዲያውም ከዘንዶው ሆድ የወጡትን ልጆችና ጐራዴውን መልሶለት በብርሃኑ ውስጥ ተሰወረ።
“We have enough religion to make us hate, but not enough to make us love one another” ይለናል፤ታላቁ ዮናታን ስዊፍት፡፡
ሠላም!!


Read 1277 times