Monday, 27 July 2020 00:00

“በቃህ!” በይው አያቴ… “ኢንጋ!” በይው አኮዬ… “ይአኸለከ!” በይው አደይዬ

Written by  ገዛኸኝ ፀ. ጸጋው (ዶ/ር)
Rate this item
(2 votes)

“ብሔርሽ” ማን እንደሆነ፣ በአንቀጽ በይኖብሽ ሲነሳ፣
“እንዴት ዝም አልሺው አያቴ? እኩይ ርዕዮቱን ሲኮሳ፤
ሥልጣን ብቻ እያለመ፣ እኔንም፣ አንቺንም ሲረሳ!
የእሱ “ብሔር” ሆዱ ነው አኮዬ? ብቻ ለከርሱ አይጣ፣
ጎሰኝነትን ያቀለመበት፣ መንታ ምላሱ እስኪ ገረጣ፣
ተፈጥሮን ከተመክሮ ቀላቅሎ፣
ዕውነትን ከሀሰት አዳቅሎ፣
ታሪክሽን ባዲስ አብቅሎ፣
“ሀገር” ማለትን ችላ አስብሎ… ሥልጣን ላይ ከወጣ፣
አደይዬ፣ በእውነት ስልሽ፣ ታሪክሽ ሁሉ ቅጥ አጣ!  
እርሱ ምን ቸግሮት እቴቴ፣ ሕዝቡ ሁሉ ትርፍ ካመጣ፣
በየቋንቋው ነው የሚያሰልፈው፤ ሊያወጣብሽ ባቢሎን ዕጣ፡፡
እናም አባቴን አንድ በይው! ላንቺም እንግዴ ልጅ አይሁንብሽ፣
ለምን ስለ አባቱ አትነግሪውም፤ የእናቴን ወገን ከሚያንቋሽሽ!?
ድንገት ከሰማሽ አደይዬ፣ ተግሳጽሽ ነው ምሱ
የነፍሱን ጥሪ የሚበጃት፣
ሀገራችንን ሸቅጦባት፣ በእሳት ምላሱ ከሚፈጃት፣
የልጁን ጥያቄ ከሚያዳፍን፣ ነገዬን በቂሙ ከሚፈርጃት፣
እባክሽ አኮዬ ለምኚልኝ! ቃሉን ከቃልሽ ያወዳጃት፡፡
“ብሔር” ማለት “ሀገር” ነው በይው፤ ሀቅንም
ከሀገረ ቃልሽ ይዋጃት፡፡
አየሽ ውዷ አያቴ፣ ሰማሽ አኮዬዋ፣ ገባሽ ወይ የኔ አደይ …
ከልዩነት የወጣን ውበት፣ የሚዋጁበት ቋንቋሽ ሳይለይ፣
“ልዩነት ውበት ነው” እያሉ፣ ሲያቅራሩብሽ ዝም አትበይ::        
ልዩነትን ውበት ብቻ አ’ርገው፣ ሠርክ ሲለፍፉ ጠርጥሪ!
“ብሔርሽ…” ማለቱን ሞግተሽ፣ ከሰሜን ደቡብ ጫፍ… ቁጠሪ!
መሽቶ እስኪነጋም ሩቅ ነው… እውነትን ለማወቅ ስ’ጥሪ፡፡
አባቴ እንዳሻው ሲተርክ፣ እኔም እንዳሻኝ እያፈስኩ
የጎሳ ወሬ አንቀርቅቤ፣
ውኃ ከሚጠብስ ዘረኛ ጋር፣ ታሪክ ከሚደልዝ መሠሪ ጋር
“የበሬዬ ወለደን” ቅቤ፣
ተማሪዎቼን እያነካካሁ፣ ሰውን ሁሉ እያቃባሁ
ዕውነትን እንዳያውቁ አቅቤ፣
ይኸው ከሰው ተራ አስወጣኝ! ይኼ ዋሾ ልጅሽ…
ሠርክ ባንቺ እየማለ፣
በሥልጣን ልክፍት ታውሮ፣ “ብሔር!” ብሎ “ብር” እያለ…፣
የወል ቋንቋችንን ቀብሮ፣ አንድነታችን ጎደለ፡፡
እናም አደይ በርሱ ኃጢያት፣ ትውልድሽ ሁሉ ከሚያፍር፣
በቀበረው ፈንጅ ሳይጠፋ፣ የአብሮነትሽን ሕያው ድምር፣
“‹ብሔሬ…› ማለቱን ተወውና፣ ‹እኔ ማን ነኝ …?› ብለህ ጀምር፣
ቅድሚያ ራስህን ዕወቅ ልጄ! የአባትህን ማንነት መርምር!”
ከወል ቋንቋችን ጎሳ አትፍጠር፤ ልዩነትን ብቻ አትዘምር፡፡
የሰው ደም ሁሉ አንድ ነው፤ ቀይነቱ ተመሳጥሯል፣
ልዩነታችን እንዲያምር!”
እያልሽ ምከሪው አያቴ፣ ምህላሽ ነው ነፍሱን ‘ሚበጃት፣
ሀገርሽን በቀበረው ፈንጅ፣ በቋያ እሳቱ ከሚያስፈጃት፣
ትውልድ ከሚታዘበዉ፣ እኔ ልጁም ከማፍር
ጦቢያንም በቁርሾው ከሚያጃጃት፣
እባክሽ አኮዬ ተማለጂኝ፣ አባቴን በጡትሽ አስክኚው
ቀልቡንም ከቀልብሽ አወዳጃት፡፡
አየሽ ልጅሽን አደይዬ፣ እኔን ምን እንዳለኝ አልሰማሽም!?
“ብዙ በቀቀኖች ለማራባት፣ የጭቆና ተረክ ብቻ አይበቃም፣
ታዋቂ ብሔርተኛ ተባል! ነገርህ በጀምላው እንዲቃም …
ዋልታ ረጋጥ ካልሆንክማ፤ ባዶ ትረካህ አያነቃቃም፡፡
‹የብሔር ትዩብ›ም ከፍተህ፣ የቂም ቱልቱላህን አናፋ!
ጸጉርህን ጋሜና ቁንጮ፣ ወይ ተሠራ ወይ ቆብ ድፋ …
ግማሽ ጎፈሬም ከሆነብህ፣ ‹ልዩነት ውበት ነው፣› በል አትዘን፣
በመላጣም ሊያዩህ ካሉ፣ ከመላጨት አትቦዝን …
እንደ ምንም ‹ጎጥ መሪ› ከሆንክ፣ ከዚያ በኋላማ ምን አትለው?
ያሻህን ወሽክት፣ ማን ጠይቆህ? ሰውን ሁሉ “እግዝኦ!” አስብለው፡፡
ዕውነቴን እኮ ነው የኔ ምትክ…!
ሥራ ፈጣሪ መሆን ካቃተህ፣ ወሬ ፈጥረህ
ዝናህን  ያውሱት፣
ወጣትነት ለምን ሊሆንህ… ባይሆን ‹ጀብድህን›
አይርሱት፡፡
የፈለገ ሙያ ቢኖረው፣ ዩኒቨርሲቲዉ አንተን ካልዋጀ!
‹በክልልህ› ውስጥ መከፈቱ፣ ቀየህ ላይ መሆኑ ምኑን በጀ!?
ይልቅ እንዳያሳጣህ፣ ‹ፈሪነትህን› እያወጀ …
‹በብሔሬ የተነሳ፣ ዩኒቨርስቲው አገደኝ› ብለህ፣
ግጭት መፍጠር ትችላለህ…
ሰውን በቁሙ ታነዳለህ፤ አንተም ታዋቂ ትሆናለህ!
ከዚያ መንበሩ ትነጥቅ ዘንድ፣ መንግሥት መድከሙን ታውጃለህ…
ብቻ ‹አክቲቪስታቸው› ሁን፤ የብሔራቸው ካርድ ካለህ!…”
እያለ እየሰበከ፣ ጥላቻውን እያጣባኝ
        ነገዬን ከሚያበላሸው፣
ቦተሊከኛው ልጅሽ፣ ቂም አውራሹ አባቴ
        ዘመኔን ከሚያቆሽሸው፣
“ይአኸለከ!” በይው አደይዬ! ጽንፈኛ’ኮ ልበ’ውር ነው …
ማስተዋልሽን አውርሺው፡፡
ኮስተር በይበት አኮዬዋ፣ አንቺ እኮ ነሽ የኛ ግርማ!
ኢትዮጵያሽን የገዘተብሸ፣ ይኼ የጥፋት መሲህማ…!?
ያባትሽን ዘመን የተረተልሽ፣ ጥራዝ ነጠቁ ልጅሽማ!
የልጁን ርዕይ ሊያስጨነግፍ፣ አባቱን ወቃሹ አባቴማ፣
የኔን ዘመን በጉልበት ወርሶ፣ ዛሬም በሴራዉ ሊያዳማ…
ዘመዶችሽን ሁሉ ጠርቶ፣
አብሮ አደጎቹንም ገርቶ፣
ስለጎሳሽ በደል አውርቶ፣
የጠባውን ጡት ረስቶ፤ “ጡት መቆረጥሽን” ተርቶ፣
የኮረዶችን ጡት አጫርቶ፣ ከልጆቹ ጡት ተዳርቶ፣
ስሜታቸው ውስጥ ገብቶ፣
የታሪክ ቁርሾውን አጣብቶ… የጥላቻን ፍሬ እየዘራ
ከትላንት ማትረፉን ሲያሰላ፣
አርቆ ማሰብ ተስኖት፣ በጥፋት አዙሪት አክብቦን
ነጋችንን ትቢያ ሊያስበላ፣
ይኸው ሰደድ እሳቱን፣ ግድብሽ ላይ አዳፈነው
የግፍ ጽዋው እስኪሞላ፡፡
አደይዬ ቁርጡን ስሚ! አንዱን ጉድማ ልንገርሽ?
ስለ አፈ ጮሌዉ አባቴ፣ ስለ ሴራ ጠማቂው ልጅሽ!
ትሰሚኛለሽ አደይዬ? ቁማርተኛው አባቴማ…
“ሆድ አምላኩ” ልጅሽማ፣
ዕውነትና ዕውቀት ግድ ሳይሉት፣ የሀሰት ተረክ
ሠርክ እያሶራ፣
ጥላቶችሽ ጋር ዛሬም አብሯል፣ ለህልውናሽ
ቅንጣት ሳይራራ!
የናቱን ገመና ተራች! ይኼ ደም ሸቃጭ፣ የሴራ አውራ፡፡
እንደ ኢያሪኮ በጩኸቱ፣ ሀገርሽን ሊያፍረስ የማይተኛ፣
አባቴ ማለት እርሱ ነው፤ “ዲሞክራቱ” ብሔርተኛ፡፡
አንቺም፣ ድንቁርናውን ገዝተሸ፣ የልቡን ዕውነት ሳታስሺው፣  
እንዴት? የአያትሽን ቃል ገድፎ፣ ብሔርሽን ሲነግርሽ አመንሺው!?
እንዴት በጎሳ አጥር ከልሎ፣ ደንበር ሲያበጅልሽ ዝም አልሺው?
ከ “እንቁላሉ ሳትቀጭዉ…” በኅብረ መምሽ ላይ ስላስሮጥሺው፣
ስሁት ርዕዮቱን ሠይጥኖበት፣ ይኸው ሕልውናሽን አስፈተንሺው፡፡
“ብሔርሽ” ያለሽም ለዚህ ነው፤ የድውይ ዜጎች መገኛ፣
ጽንፈኝነቱን ያጀለበት፣ ሀገርሽን ያመማት መጋኛ!
ይሄኮ ነው ወካያችን፣ የጎሳችን ማደራጃ
የአውርቶ አደር መጠፍጠፊያ፣
የቀለም ጠል መፈልፈያ፣ የጎጠኞች መጠፋፍያ፣
የደናቁርት መቀፍቀፊያ፣
ይኼ እኮ ነው የሴራዉ ውል፣ የትውልዱ መቀጠፊያ!
“ኢንጋ!” በይው አኮዬ፣ አባቴን መልሽልኝ፣ ሠርክ እያነባሽ
አትፈውሺው፣
ጡትሽን አሽተሸ እርገሚው! በልብሽ መድማት ውቀሺው!
የጡት እናቱ መሆንሽን፣ “ከሌሎቹም” መዋለድሽን
በጠባው ጡትሽ አስታውሺው፡፡
የጉድፍቻ ልጅነቱን፣ የጦቢያ ውኅድ ማንነቱን
መንገሩንም እንዳትረሺው!
“በቃህ!” በይው አደይዬ! ቀልቡን አሳርፈሽ
የሴራ ድግምቱን አርክሺው!
የምስርን የተንኮል ዶሴ፣ የጫካዉን ውል ፍቺለትና፣
ልቡናውን መልሺው፡፡
ዘረኝነትን እየሻተ፣ ዘመኔን ሁሉ እንዳይመርዝ
ከመካን እሳቤው ፈውሺው…
     “በቃህ!” በይው፡፡

Read 747 times