Saturday, 01 August 2020 11:36

ዕዳ ከሜዳ!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ አዝማሪ፣ በአንድ ገጠር ውስጥ ከሚስቱ ጋር ይኖር ነበር:: ሚስቱ ህልም ባየች ቁጥር ጠዋት ሲነሱ፤ “ዛሬ ምን ህልም አየሁ መሰለህ?” ትለዋለች፡፡
አዝማሪ - “ምን ህልም አየሽ?”
ሚስት - “በጣም ትልቅ አውሎ - ንፋስ አየሩን ሲያናውጠው፤ ከሥር ደግሞ መሬቱ ጐርፍ በጐርፍ ተጥለቅልቆ፣ ህዝብ መጠጊያ አጥቶ፤ ሲራወጥ አየሁ፤ እኔ አገሩን ጥዬ ጠፋሁ”
አዝማሪው - "መምሩን እንጥራና ይፍቱልን፣ ይሄ ከባድ ህልም ይመስላል፡፡”
ይልና ከጐረቤት መምሩን ይጠራል፡፡ መምሩ ይመጣሉ፡፡ ሚስትየው ህልሟን ትነግራቸዋለች:: እንደ ሁልጊዜው ትንሽ ይፀልዩና የህልም ፍቺያቸውን ይጀምራሉ፡፡
መምሩ - “ይሄ መልካም ነው፡፡ አውሎ ነፋሱ ረሀብ ነው፤ ስለዚህ ምግብ አጠራቅሙ:: ጐርፉ በሠፈሩ ላይ ጦርነት ሊመጣ ነው ማለት ነው፡፡ በመጨረሻ መጥፋትሽ ግን ትልቅ መልዕክት አለው፡፡ በተቃራኒው ነው የሚፈታው፡፡ ከቤት አትውጪ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ አንቺም ባልሺም ከቤት አትውጡ፡፡ እንዳትነቃነቁ ዕዳ ከሜዳ ነው የሚመጣው” ብለው ይሄዳሉ፡፡
አዝማሪው ወደ ጫካ ሄዶ ክራር መጫወት አምሮታል፡፡
 ሚስትየውም - “ተው አትውጣ፤ መምሩ ዕዳ ከሜዳ” ነው የሚመጣው ብለዋል’ኮ” ትለዋለች::
አዝማሪው ግን አንዴ ልቡ ተነስቷልና ክራሩን ይዞ ወደ ጫካ ይሄዳል፡፡ ጫካ ውስጥ አንድ ትልቅ ዛፍ ያገኝና፤ ከሥሩ ይቀመጥና ግንዱን ተደግፎ ክራሩን ይጫወታል፡፡ ከጀርባው ብዙ የበሬ ሥጋ በሰሌን ላይ ተዝረክርኮ ይታያል፡፡ እሱ ሥጋ መኖሩን አላየም፡፡
በመካከል የሰዎች ሁካታ ድምጽ ይሰማል፡፡ ወዲያው ድምፃቸውን የሰማቸው ሰዎች ይመጣሉ::
“ይሄ ነው ሌላው ደሞ፤ የጥጋቡ ጥጋብ በሬያችንን ሰርቆ፣ አርዶ፣ በልቶ የተረፈውን ይሄው ከጀርባው አስቀምጦ፣ እሱ ክራሩን ይከረክራል”
ብለው አስነስተው እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ይቀጠቅጡታል፡፡ ለካ በሬያቸውን የሰረቁት ሌቦች ጫካ አምጥተው፤ አርደው በልተው፣ የተረፋቸውን ትተው ሄደው ኖሯል::
አዝማሪው እንዳይሆን ሆኖ ደማምቶ፣ ቆሳስሎ ቤት ሲሄድ፤ ሚስቱ ደንግጣ፤ “ምን ሆነህ ነው?” ብላ ጠየቀችው፡፡ አዝማሪውም የሆነውን ሁሉ ነገራት፡፡
ሚስቲቱም፤ “ይሄውልህ፤ መምሩ ህልሜን በትክክል ነው የፈቱት፤ “ዕዳ ከሜዳ ነው የሚመጣው፤ ከቤት አትውጡ” ብለውን አልነበረም” አለችው፤ ይባላል፡፡
*   *   *
የሰው ነገር መስማትና ቢያንስ ልክ ነው፤ ልክ አይደለም ብሎ መጠራጠር መልካም ነው:: አንዳንድ ሰዎች፣ አንዳንድ ነገር ከመከሰቱ በፊት ይታያቸዋል”፡፡ ስለሆነም ያስጠነቅቃሉ:: በዕውኑ ዓለም ከመሆኑ በፊት ምልክት የሚሰጥና በምክንና በውጤት ስሌት ሊደረስበት የማይችል ጉዳይ ያጋጥማል፡፡ እህ ብሎ ማዳመጥ ከብዙ መዘዝ ያድናል:: ከብዙ ጣጣ ያድናል፡፡ ፈረንጆች “Coming events cast their shadow” ይላሉ፡፡ ነገ የሚመጣው ነገር ዛሬ አስቀድሞ ጥላውን ይጥላል እንደ ማለት ነው፡፡ መጠንቀቅ መልካም ነው ማለት ነው፡፡ አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ጨምሪበት እንደተባለው ነው፤ ከፊሉ እየተራጠረው ከፊሉ ተሸጧል ሲለው ከፊሉ ከናካቴው አይሆንም ሲለው የከፋው ሰው ቢኖርም ባይኖርም የግድቡ ሙሌት ተጀምሯል፡፡ ተስፋ ሰጪ ነው መጨረሻው ይናፍቃል:: ወጣም ወረደም ለሀገራችን ኢኮኖሚ አከርካሪ አጥንት በመሆኑ ዕድገትን ማመላከቱ ግልጽ ነው:: ትዕግስት፣ ጥበብ፣ ታታሪነትና ጥንቃቄ አሁንም ወሳኝ ነው
የሀገራችን የኢኮኖሚ ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ሥራ አጥነቱ እንዳገጠጠ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ ነው፡፡ አቅርቦትና ፍላጐት ርቀታቸው የትየለሌ ነው፡፡ የወጣቱ ትግል እየጨለመ መሄድ ብቻ በመሆኑ፤
“ደሞም ማወቅ ማለት…
ከውጪ ያለውን፣ ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ"
የሚለው መልዕክት፤ ገና አልሰረፀበትም፡፡ በሰዓቱ ችግርን መረዳት ግማሽ መንገድ እንደተጓዝን ይቆጠራል፡፡ ከዚያ በሰዓቱ ማቀድ በሰዓቱ መፈፀምና በሰዓቱ ውጤቱን መገምገም::
አበው ሲመርቁ፤
“ትምርትህን ይግለጥልህ” ብለው ነው፡፡ ከዚያም “መጨረሻውን ያሳምርልህ” ብለው ነው የሚደመድሙት፡፡ ጅምርህ እንዳማረው፣ ፍፃሜውም የተባረከ ይሁንልህ እንደ ማለት ነው፡፡ ትምህርታችንን ይገልጥልን ዘንድ ችግሩ እንዲገባን፣ እጥረቱ እንዲሰማን ያስፈልጋል:: ያ ደግሞ እንዲገባን እጥረቱ እንዲሰማን ያስፈልጋል፡፡ ያ ደግሞ እንዲሰርጽብን ከልብ አገርን መውደድና ከልብ ለህዝብ መቆርቆርን ይጠይቃል፡፡ መካያውም፤ “ምን ተባብለን ነበር? የት ደርሰናል?” ማለት የአባት ነው፡፡ አንድ የፍቅር የምንለው ነገር ግን ለሀገር ጉዳይ ሊያገለግለን የሚችል ግጥም አለ፤
“ተማምለን ነበር እንዳናቀላፋ
ተኝተሽ ተገኘሽ መተማመን ጠፋ”
የዘፈን ግጥም ይሁን እንጂ ህይወትንና አገርን አሻግረን ልናይ የምንችልበት ነው:: መማማል፤ ማቀድ ነው፡፡ አደራ መባባል ነው፡፡ ማንቀላፋት፣ መስነፍ ነው፡፡ አለመሥራት ነው፡፡ መተኛት ኋላ መቅረት ነው፤ ዳተኛ መሆን ነው፡፡ ቃልን አለማክበር ካለ፣ መተማመን ይጠፋል፤ ዕምነት ይጐድላል፡፡ ዕምነት ማጉደል ከሙስናም ጋር ይያያዛል፤ "ዕምነት ሲታመም፣ ሺ ወረቀት መፈራረም" ይላል፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን:: አካባቢን አለማስተዋል፣ ግራ ቀኙን አለማየት፤ ዙሪያ  መለስ አስተሳሰብ አለማዳበር፤ ዕዳ ከሜዳ መኖሩን እንድንዘነጋ ያደርገናል፡፡ ሜዳው ላይ ሌብነት እንዳለ አለማየት፣ ንብረታችን እንደሚሠረቅ አመላካች ነው፡፡ ሜዳው ላይ ብዙ ኢ-ፍትሐዊ ነገር እንደሚፈፀም አለማስተዋል፣ ህጋዊ መንገድን ልብ እንዳንል ያደርገናል፡፡ ሜዳው ላይ ኮሮና እንደሚጠብቀን መዘንጋት፣ ዕዳው የህይወትን ዋጋ የመክፈል ያህል ይሆንብናል፡፡ ካለማስተዋል፣ ካለመጠንቀቅና ከቸልተኝነት የሚመነጩ፣ ለአገርም ለህዝብም የማይበጁ አያሌ ዕዳ - ከሜዳዎች እንዳሉብን አውቀን፣ ለነገ እንብቃ!!   

Read 13989 times