Saturday, 01 August 2020 13:03

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የሚስቱን ግትርነት የታዘበው ጐልማሳው ሙሴ ሃኔቡ አድማው የምሳ ግብዣውንም ሆነ ሴንት-ቶማስን መጐብነትን እንደሚያደናቅፍ ሊነግራት አስቦ ከንቱ ልፋት ሲሆንበት ተወው፡፡
“ያዘጋጀውን ምግብ ለምን እንጥለዋለን? ደግሞም እነዚያን ሰዎች ለመጋበዝ መፈለጌን ታውቃለህ፡፡ ጋብቻው ቢፈፀም ደግሞ ከማንም በላይ ጥቅሙ ላንተው ነው:: ግብዣው የግድ ነውና፡ አትሞግተኝ” አለችው፡፡
የተጋለጠ ትከሻዋንና ከፊል እርቃን ደረቷን ተመለከተ፡፡ የጐልማሳው ባል ፊት ኮስታራ ቢሆንም የውስጣዊ የልቡን ፍርሃት ሸፍኖለታል፡፡
የእመቤት ሃኔቡ ሰውነት የአዋቂ ገላ ቢሆንም ዛሬም ስሜት የመቀስቀስ አቅሙን አላጣም፡፡ የስንዴ ማሳ ወርቃማ ቀለም ያለው ለስላሳ ቆዳዋን ሲመለከት ተወርውሮ ሊከመርባትና በጡቶቶ መካከል ፊቱን ሊቀብር ተመኘ፡፡ የተቀባችው ሽቶ እንዲሁም የመኝታ ቤቷ ጠረን የአማላይ ሴት መገለጫ ናቸው፡፡ የደም ስሩን የወጠረውን ስሜት ተቆጣጥሮ ምኞቱን ተወዉ፡፡ ለአስር አመታት ጥንዶቹ መኝታ ለይተዋል፡፡
“እሺ፤ እንዳቀድሽው ይቀጥላል” ብሏት ወጣ፡፡
ሙሴ-ሃኔቡ የተወለደው አርዲነስ ግዛት ውስጥ ቢሆንም የህፃንነት ዘመኑ አስቸጋሪ በመሆኑ ወላጆቹ በመሞታቸው ፖሪስ የህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ለመኖር ተገደደ:: የማዕድን ሙያ ማሰልጠኛ በመግባት በሃያ አራት አመት እድሜው ኢንጂነር በመሆን ሴንት -ባርቤ ማዕድን ማውጫን ተቀላቀለ:: ቅርንጫፍ ኢንጂነር በመሆን ፖስ-ዴ-ካላስ መኖር ጀመረ፡፡
ፖስ-ዴ-ካላስ ሳለ ነበር ከባለፀጋው የክር ፋብሪካ ባለቤት ልጅ ጋር ትዳር የመሰረተው፡፡ እመቤት ሃኔቡን ካገባ በኋላ ጥንዶቹ ለአስራ አምስት ዓመታት በዚያው ገጠራማ ግዛት ኖሩ፡፡ አመታቱ ለሁለቱ ተመሳሳይና እጅግ በጣም አሰልቺ ነበሩ:: መሰላቻቸቱን ለአፍታ የሚያስቀርላቸው አጋጣሚ አልነበረም፤ ልጅም አልወለዱም፡፡
የተቀናጣ ህይወት በመመኘት ያደገችው እመቤት ሃኔቡ የባሏን ስራም ሆነ ዝቅተኛ ደሞዝ በግልፅ መናቅ ጀመረች፡፡ የሁለቱ አለመጣጣም ቀጠለ፡፡ በመካከላቸውም የስጋ ፍላጎት መጋራት አልነበረም፡፡ የሚስቱ አካላዊ ቅርፅ ፍትወት ቀስቃሽ ነው፡፡ ገላዋን በጣም ቢወድላትም ቅሉ ተለያይተው ነበር የሚተኙት፡፡ ይህ ደግሞ ዘወትር ልቡን ያደማዋል፡፡ እመቤት ሃኔቡ በግልፅ የምትጎበኘው ውሽማ እንዳላት እያወቀ ባልየው አልተቃወማትም፡፡ የተሻለ መቀራረብ ለመፍጠር በመመኘት ፖሪስ የቢሮ ስራ አግኝቶ ይዟት ሄደ፡፡ ፖሪስ የሁለቱን መለያየት ይፋ ያደረገ ገጠመኝ ተፈጠረ፡፡ እመቤቲቱ በፖሪስ ህይወቷ ከባላገር ሴትነት ወደ ዘመናዊ ፋሽን ተከታይነት ተቀየረች፡፡ ለአስር አመታት በፖሪስ ከኖሩ በኋላ ሙሴ-ሃኔቡ በህይወታቸው ተሰላቸና ፍቺ ፈፀሙ፤ ከፍቺው በኋላ ሚስቱ በሃዘን መጎዳቷን አይቶ የሞንሱ ማዕድን ኩባንያ ሃላፊ የመሆን እድል ሲያገኝ ይዟት ለመሄድ ወሰነ፡፡
ባልና ሚስቱ የሞንሱ ቆይታቸው ስድስት ወር እንዳለፈው ወደ ቀድሞው መሰላቸት ተመለሱ፡፡ እመቤት ሃኔቡ ለወራት ራሷን ነጥላ ከረመች፡፡ ከመንፈቅ በኋላ ለግዜ ማሳለፊያ ያሰበችውን የቤት ማስዋብ ስራ ተያያዘችው፡፡ የቤቱ ውበት እስከ ሊል ከተማ ድረስ ተደነቀላት፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን በድጋሚ ሰለቻት፡፡
ባለቤቷ ላይ መነጫነጭ ቀጠለች፡፡ ለአርባ ሺህ ፍራንክ ደሞዝ ብሎ የእርሷን ህይወት እንዳባከነ መናገር ሁሉ ጀመረች፡፡ ባሏ እንደ እኩዮቹ ትልቅ ህልም የለሽ መሆኑ አበሳጫት፡፡ የማዕድን ኩባንያ አክሲዮን ድርሻ እንዲኖረው አለመፈለጉ የባሰ ያነጫንጫት ቀጠለ፡፡
ሙሴ ሃኔቡ ምላሽ ያጣ ስሜቱን ለመሸሽ ራሱን በስራ ውስጥ መደበቅ ቀጥሏል:: እድሜው ሲጨምር የሥጋ አምሮቱ ከፍተኛ ሆነበት ፡፡ ሚስቱ የእርሱ ያለመሆኗ ደግሞ የበለጠ አሰቃየው፡፡ እርሱ በስሩ ሊያደርጋትና የጥማቱ ተገዥ አድርጎ ሊቆጣጠራት ቢሻም ሚስቱ በአንፃሩ ራሷን ለሌላ ወንድ አሳልፋ መስጠቷን ቀጠለች፡፡
ዘወትር ማለዳ ከአልጋው ሲወርድ የሚያስበው ነገር የሚስቱን ስሜት አንበርክኮ ማሸነፍ ነው፡፡ ሆኖም በቀዝቃዛ አይኖቿ ስትመከከተውና የልቧን እንቢተኝነት ስታሳየው እጇን መንካት አቆመ፡፡ ለስድስት ወራት ባል ስጋዊ ደስታ በማጣት ተሰቃየ፡፡ እመቤት ሃኔቡም ቤቱን አስውባ ስትጨርስ ወደቀድሞው አሰልቺ ህይወቷ ተመለሰች፡፡ ሞት የተሻለ አማራጭ መሆኑ ተሰማት፡፡

Read 2837 times