Saturday, 01 August 2020 13:09

በኮቪድ-19 የተሽመደመደው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   - ባለፉት 4 ወራት በኮሮና ሳቢያ ከ1.ቢ ዶላር በላይ ገቢ አጥተናል
          - በቱሪዝም መስራት የሚገባንን ያልሰራነው በገንዘብ እጦት ነው
          - የኢትዮጵያ ቱሪዝም የ10 ዓመት ዕቅድ ምን አዲስ ነገር ይዟል ?

           በኮቪድ-19 ተጽዕኖ ሳቢያ ከተሽመደመዱ የሥራ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በቀዳሚነት ይጠቀሳል:: ባለፉት አራት ወራት ብቻ አገሪቱ ከዘርፉ ከ1ቢ. ዶላር በላይ ገቢ አጥታለች ይላሉ፤ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ፡፡ ከቱሪዝም ጋር ተያይዞ፣ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የቱሪስት መዳረሻዎችና ሌሎችም በወረርሽኙ ሳቢያ ጉዳት ደርሶባቸዋል:: በሌላ በኩል፤ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ፣ አዳዲስ የቱሪዝም ገበያዎችንና ፕሮጀክቶችን ለመፈተሽና ለመቃኘት ኮቪድ-19 መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም አቶ ስለሺ ያስረዳሉ:: የ10 ዓመቱ መሪ እቅድ ተነድፎ ይፋ የተደረገውም ባለፉት 4 ወራት ኮቪድ በፈጠረው ፋታ ነው ተብሏል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፤ ኮቪድ-19 በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያስከተላቸውን ጉዳቶች፣ የማገገምያ ስትራቴጂዎች፣ እንዲሁም የ10 ዓመቱ  መሪ ዕቅድ ያካተታቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ ላቀረበችላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል:: እነሆ፡-


                በዓለም ላይ ኮቪድ 19 መከሰቱን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፉ ክፉኛ መጐዳቱ ይታወቃል:: እስቲ ወረርሽኙ በአገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያስከተለውን ጉዳት በዝርዝር ይንገሩን?
እንግዲህ የቱሪዝም ሴክተሩ በተለይ በመዳረሻ ቦታዎች የሚገኙ አስጐብኚዎች፣ የመኪና አከራዮች፣ በመስህብ ቦታዎች ላይ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች፣ ባለቤቶች… ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል:: ከዚህ በተጨማሪ ብሄራዊ ፓርኮች፣ ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ አቢያተ መንግስታት፣ የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ እምነት ጥለው ይሰሩ የነበሩ የተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት በተለይ ሆቴሎች፣ አስጐብኚ ድርጅቶች፣ የስጦታ እቃ መደብሮች፣ ባህላዊ ምግብና መጠጥ ቤቶች እንዲሁምና ተያያዥ የንግድ ድርጅቶች በአሁኑ ሰዓት ተዘግተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በቢዝነስ ተቋማቱ ውስጥ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩት ሁሉ ስራ ፈተው ተቀምጠዋል፡፡
መንግስትም ቢሆን እነዚህ የቢዝነስ ተቋማት በመስራታቸውና ግብር በመክፈላቸው፣ ከተቀጣሪዎቹም ጭምር ያገኘው የነበረውን ገቢ አጥቷል፡፡ ለምሳሌ መንግስት ለእነዚህ ሁሉ የንግድ ድርጅቶች የታክስ እፎይታ ሲሰጥ፤ መሰብሰብ የነበረበትን ግብር እያጣ ነው ማለት ነው፡፡ በተጨማሪ ኢምፖርት ኤክስፖርቱን (ትሬድ ባላንስ የምንለውን)  ስንመለከት፣ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምንልካቸውን እቃዎች (ቡና፣ አበባ፣ የቆዳ ውጤቶችና ሌሎችም) መጥቀስ እንችላለን፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ አንዱ የዶላር አመንጪና አምጪ ዘርፍ ቱሪዝም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሌላው ዘርፍ የዓለም ገበያ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ አለ፡፡  ሌሎች አገሮች የሚያገኙት፣ እኛ የምናወጣው የውጭ ምንዛሪ አለ:: ማሽነሪዎችን፣ መኪናና ሌሎችንም ለመግዛት ማለቴ ነው፡፡ ይህንን ትሬድ ባላንስ ከሚመሩት አንዱም ቱሪዝም ነው - ዶላር አምጪ ነውና፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ መገደብ የትሬድ ባላንስ መናጋትን ያመጣል፡፡ ከውጭ ምንዛሬ እጦት ባሻገር፣ በአጠቃላይ የቱሪዝም ዘርፉ መንግስትንም ሆነ፣ የግሉን ዘርፍ እንዲሁም ታች መዳረሻው አካባቢ የሚገኙ ግለሰቦችንም ህይወት የሚነካ ነው፡፡
ባለፉት 4 ወራት በዘርፉ የደረሰውን ጉዳት በቁጥር መግለጽ ይቻላል?
የደረሰውን ጉዳት በቁጥር ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከቱሪዝሙ ዘርፍ በየዓመቱ የሚገኘውን ገቢ እናውቀዋለን:: በዓመት ውስጥ እናገኛለን ተብሎ የሚታሰበው ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ (ከመጋቢት እስከ ሰኔ) ከገቢው 1/3ኛውን ወይም በትንሹ ከ1 ቢ ዶላር በላይ አጥተናል:: ኮቪድ 19 ባይከሰት ኖሮ ከላይ የተገለፀውን የገቢ መጠን እናገኝ ነበር፡፡ ይህ የሆነው ከመጋቢት ጀምሮ እስከ ሰኔ ድረስ ሊመጡ አቅደው የነበሩ ጐብኚዎች ጉዟቸውን ሙሉ በሙሉ በመሰረዛቸው ሳቢያ ሲሆን ለሆቴሎች፣ ለቱር ኦፕሬተሮች፣ ለአየር ትኬትም ሆነ ለቱሪዝም መዳረሻዎች ክፍያ አልተፈፀመም፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ከ1 ቢ. ዶላር በላይ ገቢ አጥታለች፡፡
እንቅስቃሴዎች ቢገደቡም፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን እንደነበር ይታወቃል፡፡ እስኪ ስለ ስራዎቹ ይንገሩን?
ገና ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከመግባቱና ከቻይና ተቀስቅሶ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን እየገታው መሆኑን ስንሰማ፣ የክልል መንግስታትንና በርካታ ባለድርሻ አካላትን ካፒታል ሆቴል ሰብስበን፣ ኮቪድ ወደ አገራችን የመግባት እድሉ ከፍተኛ ስለሆነ እዚህ አገር ለጉብኝት የመጡ ቱሪስቶች መገለልና እንግልት እንዳይደርስባቸው በሚል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሰራን:: ምክንያቱም በወቅቱ ብዙ ቱሪስቶች አገራችን ውስጥ ነበሩ፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ፤ ቅድመ ዝግጁነት ነው፡፡ ይሄ ማለት ኮቪድ አገራችን በሚገባበት ጊዜ፣ ክልሎች ምን መስራት አለባቸው? ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል? መንግስትስ ምን ማድረግ አለበት? በሚለው ላይ በዝርዝር ተነጋግረናል፡፡ ከእነዚህም አንዱ፡-  ከዚህ በፊት ልንሰራቸው ሲገባ ያልሰራናቸው ነገሮች ካሉ ወቅቱን ተጠቅመን መስራት አለብን የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ፡- ቅርስ ጥገና ላይ ትኩረት እናድርግ የሚል ነው:: ብሄራዊ ፓርኮችም ላይ የአስጐብኚዎች ስልጠና እንዲሰጥ፣ ባለድርሻ አካላትና አስጐብኚዎች በተለይም ሆቴሎች የንፅህናና የጥራት ደረጃ ስርዓት እንዲዘረጉ የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ይህን ሁሉ ያደረግነው ገና ኢትዮጵያ ውስጥ ኮቪድ ገብቶ እንቅስቃሴ ከመገደቡ በፊት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ኮቪድ ገባ፡፡ ወረርሽኙ ደግሞ የመስፋፋት እድሉ ሰፊ ስለሆነና የውጭውንም የአገር ውስጡንም የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሊገታ ስለሚችል፣ ከባህልና ቱሪዝም ጋር በመነጋገር የማገገምያ ስትራቴጂ (Recovery Strategy) ቀረጽን፡፡
የማገገምያ ስትራቴጂው ለምንና ለማን ነው የተዘጋጀው…?
ይህ የማገገሚያ ስትራቴጂ ሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች አሉት፡፡ ስትራቴጂው ከአለም ቱሪዝም ድርጅት (WTO) ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ነው የተቀረፀው፡፡ የመጀመሪያው ምሰሶ (ፒላር)፡- “ምጣኔ ሀብታዊ” ነው፡፡ ኮቪድ 19 ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገባ፣ ሊያስከትል ከሚችላቸው ችግሮች አንዱ ፋይናንስን ማዳከም ስለሆነ ምን እናድርግ የሚለውን ተመካክረን፣ የፋይናንስ ችግር የደረሰባቸውን ሆቴሎች፣ አስጐብኚ ድርጅቶችና እስከ ታች መዳረሻ ያሉትን ተጐጂዎች በፋይናንስ የመደገፍ ሃሳብ አፈለቅን፡፡ ሁለተኛው ምሰሶ (ፒላር)፡- “ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን” ነው፡፡ በማርኬቲንግና ፕሮሞሽን በኩል በርካታ ስራዎች መሰራት ነበረብን፡፡ የንግድ ትርኢቶች፣ ኤግዚቢሽኖችና ትልልቅ መድረኮች በወረርሽኙ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተሰርዘውብናል፡፡ ክፍያ የፈፀምንባቸውም ጭምር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጊዜ በማገገሚያ ስትራቴጂው ውስጥ ኦንላይንና የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ መጀመር አለብን በሚል የዲጂታል አጠቃቀማችንን ማሻሻል እንዳለብን አቀድን፡፡ ሦስተኛው ምሰሶ (ፒላር)፡- “የአቅም ግንባታ ስልጠና” ነው:: ስልጠናዎችን በማመቻቸት የአቅም ግንባታ ስራ መሰራት ነው፡፡ እስካሁን አንደኛና ሁለተኛውን ምሰሶ ሰርተናል ብዬ አምናለሁ:: ለምሳሌ ኢኮኖሚያዊ ምሰሶውን በተመለከተ እስካሁን ለዋና ዋና ሆቴሎችና አስጐብኚ ድርጅቶች ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር፣ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ ሆቴሎችና አስጐብኚዎች ከግልና የመንግስት ባንኮች ገንዘብ የሚበደሩበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡
ቱሪዝም ኢትዮጵያና  የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ያደረጉት የ10 ዓመት መሪ እቅድ ዋና ግቡ ምንድን ነው?
እንደሚታወቀው ከዚህ በፊት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እና የሚባሉ ነበሩ:: በተመሳሳይ፤ መንግስት ከለውጡ በኋላ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በኢኮኖሚ ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች፣ በ10 ዓመት ውስጥ መድረስ የሚፈለጉበት ቦታ አለ:: እዚያ ቦታ ለመድረስ ተቋማት ወይም ዘርፎች በ10 ዓመት ውስጥ ሰርተው ውጤታማ የሚሆኑባቸውን ጉዳዮች በአንድ ላይ አቀናጅተውና አቅደው ማቅረብ አለባቸው የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ያንን መሰረት በማድረግ፣ የቱሪዝም ዘርፍ (ቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የቱሪዝም ዘርፉ፡- አስጐብኚ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች ወዘተ...)  እቅድ ነው ያዘጋጀነው፡፡ የቱሪዝም ዘርፍ እቅዱ በርካታ ግቦች ቢኖሩትም፣ ዋና ዋና የሚባሉትን ልግለፅልሽ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው፤ የቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ነው፡፡ የቱሪዝም ዘርፍ በባህሪው እንደሚታወቀው፤ በመንግስት ብቻ የሚሰራ አይደለም፤ በተለይ ደግሞ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት:: ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ አገር ናት፡፡ በዚህ ላይ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ይኖሩባታል:: በርካታ ባህላዊ ትውፊቶችና ታሪካዊ ቦታዎች አሉን፡፡ እኒህን ሁሉ መንግስት ላልማ ቢል አይችልም፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ሆቴል ልገንባ፣ አስጐብኚ ድርጅት ላቋቁም፣ ራሴ ላስጐብኝ፣ የቱሪስት መረጃ ማዕከል ልከፈት፣ መንገድ ልስራ፣ ላስተዋውቅ ወዘተ… ቢል ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም:: ስለዚህ በእነዚህ የቱሪዝም አካባቢዎች ላይ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ ተይዟል:: ሁለተኛው፤ በቱሪዝም ዘርፍ የተለያዩ አገልግሎቶች አሉ፡፡ እነዚህን የአገልግሎት አሰጣጦችን በቴክኖሎጂ ማዘመን ነው፡፡ አሁን በተለይ በቱሪዝም ዘርፉ ቴክኖሎጂ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ትራንስፖርቱንም ብትወስጂ፣ አገልግሎት ሰጪ ሆቴሎችንም ብታይ፣ የጉብኝትን ሁኔታም ለማሳደግ ብሎም ለማላቅ በቴክኖሎጂ መደገፍ አለበት በሚል የቴክኖሎጂ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
ሶስተኛው ጉዳይ፤ የአገር ውስጥ የጉብኝት ባህልን ማሳደግ ነው፡፡ የአገር ውስጥ የጉብኝት ባህልን በማሳደግ ረገድ ሁሉም ቁጭት አለው፡፡ ሌሎች አገራት በቱሪዝም ያደጉበት አንዱ ምስጢር፤ ለአገር ውስጥ ቱሪዝም ቅድምያ በመስጠታቸው ነው፡፡ ዜጐች አገራቸው ውስጥ በሚገባ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ፣ የሚያርፉባቸውን ቦታዎች በማመቻቸትና የሚፈልጓቸውን ነገሮች በማደራጀት ሌሎች አገራት፣ የአገር ውስጥ ቱሪዝማቸውን አሳድገዋል:: በነገራችን ላይ ለአገር ውስጥ ብለሽ የሰራሻቸው ነገሮች ለውጭም ይሆናሉ:: ለውጪ አስጐብኚ ድርጅቶች ከቀረጥ ነፃ እንደሚሰጣቸው፣ ማበረታቻዎችን ሁሉ አሟልተን፣ የአገር ውስጥ አስጐብኚዎችን አልፈጠርናቸውም፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ አስጐብኚ ድርጅቶች አገር ውስጥ ብቻ ማስጐብኘት እንዲችሉ ትኩረት የሚሰጥ ነው የሚሆነው፡፡ አራተኛው፤ የመዳረሻና የመስህብ ልማት ማጐልበት ነው፡፡ ይሄኛው ጉዳይ በዋናነት ቱሪዝም ኢትዮጵያን የሚመለከት ሲሆን፤ መዳረሻዎች እንዲለሙ በርካታ ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲያድግ ያለመ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ጣና ወይም ጐርጐራ አሊያም ሀዋሳ ሀይቅ የመሳሰሉት ቦታዎች ላይ ተንሳፋፊ ሆቴሎች መስራት ብንፈልግ፤ ተራራ ላይ ወይም መሃል ከተማ ሎጆችና ሪዞርቶች መገንባት ብንፈልግ… እንዴት ነው መልማት ያለበት የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ የመዳረሻ ልማት ስትራቴጂ የለንም፡፡ ይኼ በስትራቴጂክ እቅዱ ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የመዳረሻ ሀብት ቢኖርም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ “Resource Mapping” የምንለው ነው:: ሌላው መዳረሻዎችን ማስተዳደር ደግሞ አንዱ ውስብስብ ነገር ነው - በእኛ አገር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባለቤት ናት፣ ዩኔስኮ ባለቤት ነው፣ ክልሉ ባለቤት ነው፣ ማህበረሰቡም ባለቤት ነው፡፡ የመዳረሻዎች የባለቤትነት ጉዳይ ውስብስብ ስለሆነ የልማት ስራ ለመስራት እንቅፋት ነው፡፡ መዳረሻን ለማልማት በቅድምያ መሰራት ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡
አምስተኛ፤ ግብይትና ፕሮሞሽን የምንለው ነው፡፡ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ፣ በኦን ላይንም ሆነ በኦፍ ላይን ማስተዋወቅ አለብን፡፡ በዚህ ዙሪያ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ የምንሰራቸው ስራዎች ምን መሆን አለባቸው? በዓለም አቀፍ ትልልቅ የንግድ ትርኢቶች ላይ መስራት ያለብን ስራዎች ምንድን ናቸው? በምናስተዋውቅበት ጊዜ ይዘን መሄድ ያለብን ፕሮዳክት ምን ቢሆን ይሻላል? የሚሉትን የሚመለከት ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ በደንብ አደራጅተን፣ ስትራቴጂክ ሆነን እንድንሰራበት በ10 ዓመቱ እቅድ ውስጥ ተካትቷል፡፡ ሌላው  በግብይትና ፕሮሞሽን፣ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በስፋት መጠቀም ነው:: ለምሳሌ ከዚህ በፊት እንደ CNN እና BBC ያሉ የሚዲያ አውታሮችን ደፍረን አናውቅም:: በተመሳሳይ ዩሮ ኒውስንም ተጠቅመን አናውቅም፡፡ በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ በእነዚህ ሚዲያዎች ተጠቅመን ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ አንዱ ዓላማችን ነው፡፡ አዳዲስ ገበያዎች ላይ መግባትና የቀጠና ቱሪዝም መመስረትም በእቅዱ ተቀምጧል፡፡
የቀጠና ቱሪዝም ምን ማለት ነው?
የቀጠና ቱሪዝም የምንለው ለምሳሌ ኬኒያ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ቱሪስት፣ ከታንዛኒያናና ኡጋንዳ ታገኛለች፡፡ እኛ ከአፍሪካ አገራት ምንም አናገኝም፡፡ ስለዚህ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ወይም የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሪጅን ቱሪዝም ብለን ፓኬጅ ቀርፀናል፡፡ ለምሳሌ ታንዛኒያን የሚጐበኝ ቱሪስት፤ አሩሻ ተራራን ወጥቶ ብዙ ፈተናዎችን አይቶ፣ ጭቃ ተለውሶ፣ መጨረሻ ላይ መዝናናትና መዋኘት ሲፈልግ ዛንዚባር ይሄዳል፡፡ ይሄን ሁሉ የሚያደርገው እዚያው ታንዛኒያ ውስጥ ነው፡፡ እኛም በርካታ ተራሮች አሉን፡፡ እነ ዳሸንን… አድዋን… ጐብኝቶ፣ ባህር ቢፈልግ ኤርትራ ሊሄድ ይችላል፡፡ እንደዚህ አይነት ቀጠናዊ ፓኬጆችን ቀርፀን ለመስራት በእቅዱ ውስጥ አካተናል፡፡ ይህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ፓኬጅ ማዘጋጀት አለብን ብለን የቀጠና ቱሪዝምን በእቅዱ ውስጥ አስገብተናል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ዋና ዋና ነገሮች የመሪ እቅዱ አንኳር አንኳር ጉዳዮች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል፤ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከባህልና ቱሪዝም ጋር በመተባበር፣ በሁሉም ክልሎች የቱሪዝም መረጃ ማዕከል እንከፍታለን፡ በዓለም አገራት የቱሪዝም አምባሳደሮችን እንሾማለን፡፡ በዋና ዋና ገበያዎች ላይ የቱሪዝም አምባሳደሮችን ለመሾም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን ጨርሰናል:: ሌላው በጣም አስፈላጊው ጉዳይ፣  ሌሎች አገራት በውጭ አገር ገበያ አላቸው፡፡ ኬኒያ  ቱሪዝሟን በአለም ገበያ ለማስተዋወቅ በተለያዩ አገራት 17 ቢሮዎች አሏት፡፡ ለምሳሌ ለንደን ስትሄጂ፣ “ማጂካል ኬኒያ” የሚባል ትልቅ የኬኒያን ቱሪዝም የሚያስተዋውቅ ቦታ አለ፡፡  ኢትዮጵያም እንደ አገር በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የቱሪዝም አምባሳደሮችን ትጠቀማለች፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን የጨረስነው ሁለት ነገር ነው:: አንደኛ፤ በመላው ዓለም ያሉ 66 የቆንፅላ ፅ/ቤቶችን መጠቀም፡፡ ሁለተኛ፤ የቱሪዝም አምባሳደሮችን መሾም ሲሆን ሶስተኛው በዋና ዋና ገበያዎች ላይ የቱሪዝም ቢሮዎች መክፈት ነው፡፡ “Land of Origin” (ምድረ ቀደምት) የሚሉ ቢሮዎችን እንከፍታለን፡፡
ሌላው የቱሪዝም ፈንድ እናቋቁማለን:: ምክንያቱም ይህንን ሁሉ ስንሰራ ገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ እስከ ዛሬ ብዙ ነገር መሰራት ሲገባው ያልተሰራበት ሌላ ምስጢር የለውም፤ ገንዘብ ስለሌለን ነው፡፡ የኬኒያ አመታዊ የቱሪዝም ፈንድ 1 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ 40 ወይም 50 ሚሊዮን ብር ተበጅቶላቸው አይደለም ህንፃ ተከራይተው የሚሰሩት፡፡ ትሬድ ፌሮች ሲዘጋጁ የሚሰሩት ስራ ያስደነግጥሻል፡፡ ይሄ የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ የእኛም የቱሪዝም ፈንድ ይህን አቅም እንዲያመጣ እንፈልጋለን፡፡ ከ10 ዓመት በኋላ 7 ሚሊዮን ቱሪስት ነው ወደ አገራችን እንደሚገባ የሚጠበቀው፡፡ ይህንን ለማሳካት መንግስት ፍላጐት ብቻ ሳይሆን ቁርጠኝነትም ማሳየት አለበት፡፡ ለቱሪዝም የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶታል፤ ይሄ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ ገንዘብ መበጀት፣ በተቀናጀ መልኩ ሴክተሩን መደገፍ አለበት:: በቱሪዝም ላይ ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚመጡ ሰዎች ሲኖሩ የሚፈልጉት መሬት ከሆነ በአግባቡ መስጠት፣ በቂ መስተንግዶ ማድረግ ይገባል:: እኛ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ሲኖር 3ሺህ አልጋ ከተማ ውስጥ ማቅረብ አቅቶን፣ ቢሾፍቱና ናዝሬት እስከ ማሳደር ደርሰናል:: የቱሪስቱን ቁጥር ለመጨመር መሰረተ ልማቱን ማሟላት ዋነኛው ጉዳይ መሆን አለበት፡፡

Read 2341 times